– የዘገየው የጅማ-ቦንጋ መንገድን አስረከበ
ከአዲስ-አዳማ ቀጥሎ ሁለተኛው የፍጥነት መንገድ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ከሚሸፍነው 202.45 ኪሎ ሜትር መንገድ ውስጥ የመጀመርያውን ክፍል ሥራ ኪንግናም ለተባለው የደቡብ ኮርያ ኮንትራክተር ለመስጠት የኮንትራት ውል ሊፈረም መሆኑ ተነገረ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ኪንግናም ከመቂ እስከ ዝዋይ ያለውን 37 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ብቸኛ ተጫራች ሆኖ የቀረበ ሲሆን፣ ጨረታው ከተከፈተ በኋላ ያቀረበው ዋጋ ላይ ድርድር ሲደረግ መቆየቱ ታውቋል፡፡
አሁን ግን ባቀረበው ዋጋ ላይ የተደረገው ድርድር ተጠናቆ ስምምነት ላይ በመደረሱ ሥራውን መረከብ የሚያስችለውን የኮንትራት ውል በቅርቡ ይፈራረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች የዚህ መንገድ ሥራ ለኪንግናም የሚሰጥ መሆኑን ቢገልጹም፣ መንገዱን ለመገንባት ስምምነት ላይ የተደረሰበትን ዋጋ ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል፡፡ የመቂ-ዝዋይ መንገድ ለመገንባት ከሚያስፈልገው ወጪ ውስጥ የደቡብ ኮርያ መንግሥት 100 ሚሊዮን ዶላር ለማበደር መፍቀዱ ይታወሳል፡፡
የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል ተብሎ ሲገመት፣ ከደቡብ ኮርያ መንግሥት በተጨማሪ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና የቻይና ኤግዚም ባንክ ይሰጡታል ተብሎ በሚጠበቅ ብድር የሚገነባ ነው፡፡ ፕሮጀክቱም በአራት ቦታ ተከፋፍሎ የሚሠራ ሲሆን፣ ግንባታውም በሁለት ምዕራፍ የሚካሄድ ነው፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ የሞጆ-መቂና የመቂ-ዝዋይ መንገዶች ይካተታሉ፡፡ የሞጆ-መቂ መንገድ 56.8 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ሲኖረው፣ ይህን መንገድ ፋይናንስ የሚያደርገው የአፍሪካ ልማት ባንክ ነው፡፡ ባንኩ ለዚህ የመንገድ ግንባታ 126 ሚሊዮን ዶላር ለማበደር ተስማምቷል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ የዝዋይ-አርሲ ነገሌና የአርሲ ነገሌ-ሐዋሳ መንገዶች ይካተታሉ፡፡ የዝዋይ-አርሲ ነገሌ መንገድ 57.1 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ሲኖረው፣ ይህን የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ፋይናንስ የሚያደርገው የዓለም ባንክ ነው፡፡ ቀሪውን የአርሲ ነገሌ-ሐዋሳ 51.68 ኪሎ ሜትር መንገድ ፋይናንስ የሚያደርገው ደግሞ የቻይና ኤግዚም ባንክ ነው፡፡ ለሁለቱ የመንገድ ግንባታ ክፍሎች የዓለም ባንክና የቻይና ኤግዚም ባንክ ብድሩን ለመስጠት የተስማሙ ቢሆንም፣ እስካሁን ግን ብድሩን ለመልቀቅ የሚያስችል ስምምነት አልፈረሙም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኪንግናም ገንብቶ ያጠናቀቀውን የጅማ-ቦንጋ መንገድ ማክሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2007 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡ 110 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ይህንን መንገድ ለመገንባት ከ860 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ገልጿል፡፡ ለመንገዱ ከዋለው ጠቅላላ ወጪ ውስጥ የአፍሪካ ልማት ባንክ 70 በመቶ፣ ቀሪውን 30 በመቶ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ሸፍኗል፡፡
የጅማ-ቦንጋ መንገድ በ2001 ዓ.ም. ሲጀመር በአራት ዓመት ይጠናቀቃል ቢባልም፣ ይህ ፕሮጀክት ግን በኮንትራት ውሉ መሠረት ሊጠናቀቅ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ግንባታው ሊዘገይ የቻለው ለግንባታው አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎች በተደጋጋሚ በማጋጠማቸውና ለረዥም ጊዜ ግንባታውን የሚያስተጓጉል ዝናብ በመከሰቱ ነው፡፡ ኮንትራክተሩ ይህንኑ በማሳወቁና ማስረከቢያ ጊዜው እንዲራዘምለት ጠይቆ ተፈቅዶለት እንዲሠራ መደረጉን የባለሥልጣኑ መረጃ ያስረዳል፡፡ በፌዴራል ደረጃ ግንባታ ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከመጠናቀቂያ ጊዜያቸው በላይ በመውሰድና በመዘግየት ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ የጅማ-ቦንጋ መንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡
ኪንግናም ኮንስትራክሽን በኢትዮጵያ ውስጥ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከ16 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ በዚህ የቆይታ ጊዜው የአዘዞ-መተማ፣ የሐረር-ቁልቢ፣ የአምቦ-ጌዲዮና ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለት ፕሮጀክቶች ላይ እየሠራ ሲሆን ቀሪዎቹን አስረክቧል፡፡