Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ394 ሺሕ ኩንታል በላይ ስኳር ለማጓጓዝ የትራንስፖርት ችግር የለም ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቀድሞ ስያሜው የጅምላ ንግድ አስመጪና አከፋፋይ ድርጅት ወይም ጅንአድ ይባል የነበረው መንግሥታዊ ተቋም፣ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት፣ ለኢንዱስትሪዎች ፍጆታ የሚውሉ ግብዓቶችንና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን የማከፋፈል ሥራዎችን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ግብዓት አቅራቢው አዲሱ ተቋም በሚያዝያ ወር አውጥቶት የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ጨረታ ግን አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ ይኸውም በጂቡቲ ወደብ የተከማቹ ዕቃዎችን ለማንሳት በአገር ውስጥ ያሉት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በሙሉ ወደ ጂቡቲ ቢመደቡ እንኳ በሚፈለገው ጊዜ ውስጥ ጭነቶችን ለማሳት አይችሉም የሚል ሥጋት ነበር፡፡ ይህ ሥጋት እያለ ግን የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት 394,053 ኩንታል ስኳር ለማጓጓዝ ጨረታ ማውጣቱ ውጥረት ፈጥሮ ነበር፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ የአገሪቱ ብሔራዊ ሎጂስቲክስ ፖሊሲ ይፋ በተደረገበት ወቅት ከሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበሩት የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ናቸው፡፡ አቶ መኮንን፣ በጂቡቲ ተከማችተው የሚገኙ ዕቃዎች በዘመቻ እንዲነሱ እንደሚደረግና የአገር ውስጥ የትራንስፖርት ድርጅቶች እንዲያነሱት እንደሚደረግ ገልጸው ነበር፡፡ በመሆኑም ተሽከርካሪዎች ወደ ጂቡቲ መሰማራታቸው ግድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በግዳጅ ጭምር መሰማራታቸውም ይታወቃል፡፡

ከዚህ ባሻገር የስኳር ኮርፖሬሽን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚያስፈልገውን አራት መቶ ሺሕ ኩንታል የሚጠጋ ስኳር ከሦስት ፋብሪካዎችና ከአዲስ አበባ ኮርፖሬሽን መጋዘኖች ለማንሳት በሚያዝያ ወር መጀመርያ አካባቢ ጨረታ አውጥቷል፡፡ ‹‹በተቻለ መጠን ሁሉንም ማስተናገድ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ነው ዋነው ትኩረት፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ ግን አንገብጋቢ ለሆኑት ቅድሚያ በመስጠት በተቀናጀ መልኩ የሚሠራ ኮሚቴ አለ፤›› ያሉት አቶ መኮንን፣ ክረምት ከመግባቱ በፊት መሰራጨት ላለበት ማዳበሪያ፣ ለሕዝብ በወቅቱ መዳረስ ለሚገባቸው ስኳርም ሆነ ሌሎች ሸቀጦች እንደ አስፈላጊነቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራበት ሥርዓት ተዘርግቷል ይላሉ፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ገመዳ አለሜ በበኩላቸው፣ የጂቡቲ ጭነትን በማይነካ መልኩ ስኳር ወደ ማከፋፈያ ቅርንጫፎች እንዲጓጓዝ እየተደረገ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይኸውም አነስተኛ የጭነት አቅም ያላቸውን መኪኖች በመጠቀም ስኳሩ በመጓጓዝ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከሚያዝያ 15 እስከ ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ውስጥ 400 ሺሕ ኩንታል ስኳር ከወንጂ፣ ከመተሐራ፣ ከፊንጫና ከአዲስ አበባ ኮርፖሬሽን መጋዘኖች እንደሚጓጓዝ ይጠበቅ ነበር፡፡ በእስካሁኑ ሒደት እስካለፈው ሳምንት 40 ከመቶው ስኳር መጓጓዙን አቶ ገመዳ አስታውቀዋል፡፡

ወደተመረጡ 30 የማከፋፈያ ቅርንጫፎች እየተጓጓዘ የሚገኘው ስኳር በአንዳንድ ቅርንጫፎች ላይ መዘግየት እንደሚታይበት የገለጹት አቶ ገመዳ፣ ይህም ሆኖ በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ውስጥ ስኳሩ ወደ ማከፋፋያ ቅርንጫፎች እንደሚጓጓዝ አስታውቀዋል፡፡

በ32ኛው ዙር ሥርጭት መሠረት ከሚሰራጨው ስኳር ውስጥ ከወንጂ ስኳር 116,850 ኩንታል ወደ ዘጠኝ ማከፋፈያ ቅርንጫፎች ይጓጓዛል ተብሏል፡፡ ከመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ወደ ሰባት ቅርንጫፍ ማከፋፈያዎች የሚጓጓዘው መጠን 115,994 ኩንታል መሆኑም ታውቋል፡፡ ለ11 ቅርንጫፎች ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ የሚከፋፈለው የስኳር መጠን 124,090 ኩንታል ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ኮርፖሬሽን መጋዘኖች 37,119 ኩንታል ለሦስት ቅርንጫፎች እንደሚሰራጭ ይፋ ተደርጓል፡፡

በአገሪቱ አምስት ሚሊዮን ቶን ስኳር በዓመት በማምረት የመንግሥት የ15 ዓመታት ዕቅድ መሆኑን፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ ግን 623,000 ቶን ጥሬ ስኳር እንዲሁም 623,000 ቶን ነጭ ስኳር በድምሩ አንድ ሚሊዮን 246 ሺሕ ቶን ስኳር ተመርቶ ለውጭ ገበያ እንደሚቀርብ ሁሉ ይጠበቅ ነበር፡፡ ጣና በለስ፣ ኦሞ ኩራ አንድና ሁለት፣ ኦሞ ኩራዝ ሦስት፣ አራት፣ አምስትና ስድስት ፋብሪካዎች እያንዳንዳቸው 278 ሺሕ ቶን ስኳር የሚያመርቱንና እንዲሁም ወልቃይትን ጨምሮ የሚጠበቀው ምርት ከስኳርም በላይ ኢታሎን እንደነበር በ42 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል በ2003 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው የስኳር ኮርፖሬሽን ዕቅድ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የስኳር አቅርቦት እጥረት በመከሰቱ ከውጭ ሲገባ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል በቅርቡ ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት፣ የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅትን ከተካ በኋላ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በተለይ ከአምስት ወራት በፊት በ137 ሚሊዮን ብር 35 ሺሕ ኩንታል ጥጥ ከህንድ በማስመጣት ለ11 ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ማከፋፈሉ ይታወሳል፡፡ ድርብ ኃላፊነቶች በተወካዮች ምክር ቤት ተሰጥቶት ጥሬ ዕቃዎችን በአንድ በኩል ለአምራች ፋብሪካዎች እያቀረበ በሌላ በኩል መሠረታዊ ሸቀጦችን የሚያሠራቸው የኢትዮጵያ የኢንAnchorዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት በየወሩ ሰባት ሺሕ ኩንታል ስኳርና ስድስት ሺሕ ጄሪካን ዘይት ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እየተረከበ በማሰራጨት ላይ ሲሆን፣ አለ በጅምላ ተጠናክሮ መሥራት ሲጀምር የስኳርና የዘይት ሥርጭቱን ኃለፊነት እንደሚረከብ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች