Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት ገዳቢ መሣሪያ መግጠም አስገዳጅ ሊሆን ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተሽከርካሪዎችን ፍጥነት የሚገድቡ መሣሪያዎችን በእያንዳንዱ ተሽከርካሪ ላይ ለመግጠም እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውና ለዚህም የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያን በተሽከርካሪዎች ላይ የመግጠም አስፈላጊነትን ባለሥልጣኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲመክር ቆይቷል፡፡ በአገሪቱ የሚታየውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ያስችላል የተባለውን ይህንን የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እያንዳንዱ ተሽከርካሪ እንዲገጠም ለማድረግም ራሱን የቻለ መመርያ እየተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ እየተዘጋጀ ነው የተባለውም መመርያ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ተሽከርካሪዎቻቸው ላይ ፍጥነት ገዳቢ መሣሪያን መግጠም የሚያስገድዳቸው ጭምር ነው፡፡

እስካሁን ባለው አሠራር የፍጥነት ገዳቢና የጂፒኤስ መሣሪያን የግድ የሚያስገጥሙት የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ወደፊት ግን ሁሉንም ተሽከርካሪዎች እንዲያስገጥሙ የሚያስገድድ ሕግ እየተረቀቀ ነው፡፡ ይህ ሕግ ሥራ ላይ እስኪውል ድረስ ግን የተሽከርካሪ ባለንብረቶች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያዎቹን በፍቃደኝነት እንዲገጥሙ የማግባባት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቤልነህ አግደው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተለይ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችና የጭነት ተሽከርካሪዎች መሣሪያውን እንዲገጥሙ ግፊት እየተደረገ ነው፡፡

እንደ ባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ገለጻ፣ በሌሎች አገሮች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ መግጠም እንደ ግዴታ የሚሠራበት ነው፡፡ በኢትዮጵያም ይህንን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፣ መሣሪያውን በማስመጣት ለገበያ የሚያቀርቡና ለሚገጥሙ ኩባንያዎችም ጥሪ ተደርጓል፡፡

በዕቅዱ መሠረት የፍጥነት መቆጣጠሪያውንና ጂፒኤሱን አጣምረው እንዲገጥሙ የሚገደዱት የነዳጅ ማመላለሻና የጭነት ተሽከርካሪዎች ይሆናሉ፡፡ ከዚያም ሌላ የሕዝብ ማመላለሻዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡ በተለይ የፍጥነት መቆጣጠሪያውን ሁሉም ተሽከርካሪዎች እንዲገጥሙ ከማድረጉ ጐን ለጐን ወደፊት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያው ተገጥሞላቸው እንዲገቡ የማድረግ አሠራር እንዲኖር መታቀዱን ከአቶ አቤልነህ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የትራፊክ አደጋዎች በአብዛኛው እየደረሱ ያሉት ከፍጥነት ጋር በተያያዘ በመሆኑ፣ ፍጥነት ገዳቢ መሣሪያው እዚያው ተሽከርካሪዎቹ ከሚመጡበት አገር ተገጥሞ መምጣቱ የግድ ይሆናል፡፡ ወደፊት ወደዚህ ዓይነት አሠራር መግባቱ አይቀሬ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የፍጥነት ገዳቢ መሣሪያ በመግጠም እየሠሩ ያሉት ጥቂት ተቋማት ብቻ እንደሆኑም አቶ አቤልነህ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ኤምባሲዎችና የነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች የሚጠቀሙባቸው ተሽከርካሪዎች ፍጥነት መገደቢያ የተገጠመላቸው መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ጂፒኤስና የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሣሪያውን በኩባንያ ወይም በማኅበራት ደረጃ በተቋቋሙ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጩ ተቋማት መጠቀም እንዲጀምሩ ማድረጉ ለኩባንያዎቹም ጥቅም መሆኑ ተገልጿል፡፡  

ፍጥነት ገዳቢ መሣሪያው አደጋን ከመከላከል ውጪ ንብረትን በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል፡፡ አንድ አሽከርካሪ ከተፈቀደለት የፍጥነት ገደብ በላይ ለማሽከርከር ሲሞክር መሣሪያው ማስጠንቀቂያ በመስጠት ነዳጁ እንዲቋረጥ በማድረግ መኪናው እንዲቆም ያደርጋል፡፡

በፍጥነት ማሽከርከር በዓለም አቀፍ ደረጃ ገዳይ ከሚባሉ ምክንያቶች መካከል እንደ አንዱ የሚታይ ሲሆን፣ ይህንንም የዓለም ጤና ድርጅት ማረጋገጫ እንደሰጠበት አቶ አቤልነህ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያም ከሚደርሱት የትራፊክ አደጋዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ከፍጥነት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው፣ ፍጥነት ገዳቢ መሣሪያዎችን መግጠም አስገዳጅ ከሆነ የትራፊክ አደጋን በመቀነሱ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ከዚህ ቀደም መሣሪያውን ገጥመው እየሠሩ ካሉ አንዳንድ ተቋማት የተገኘው መረጃ፣ መሣሪያው አደጋን ለመቀነስ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

እንደ አቶ አቤልነህ ገለጻ መሣሪያውን የማስገጠሙን ሥራ በአንዴ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ ማስተግበር ስለማይችል፣ በተመረጡ ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ በቀጣይነት ግን ሁሉም ተሽከርካሪዎች መሣሪያውን እንዲገጥሙ ይደረጋል፡፡ የፍጥነት ወሰኑም እንደተሽከርካሪው ዓይነት ይለያል ተብሏል፡፡

ይህንን መሣሪያ እንዲገጠም ለማበረታታት ከተደረጉት ውይይቶች በኋላ ባለሀብቶች ፍጥነት ገዳቢ መሣሪያውን አስመጥተው ለገበያ እንዲያቀርቡና የመግጠም ሥራውን እንዲሠሩ ጥሪ መደረጉን ያስታወሱት አቶ አቤልነህ፣ እስካሁን አንድ ኩባንንያ ቀርቦ አገልግሎቱን ለመስጠት ፍቃድ ወስዷል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱን ለማቀላጠፍም ሌሎች አቅራቢዎችና አገልግሎት ሰጪዎች እንዲበራከቱና አገልግሎቱም በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ደረጃ እንዲሰጥ የሚፈለግ በመሆኑ፣ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ጉዳዩን ሊመለከቱት ይገባል ተብሏል፡፡  

የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያውን አንድ ተሽከርካሪ ላይ ለመግጠም እስከ 25 ሺሕ ብር ይፈጃል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከዚህ ባነሰ ዋጋ ሊቀርብ የሚችል መሆኑን የሚጠቁሙም አሉ፡፡ ለፍጥነት መገደቢያው ሊወጣ የሚችለው 30 ሺሕ ብር ቢሆን እንኳን ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንፃር ውድ የሚባል እንዳልሆነ ይገመታል፡፡ አቶ አቤልነህም ዋጋው ውድ አይደለም ይላሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚገዙ ተሽከርካሪዎች ከፍጥነት ጋር በተያያዘ የሚደርስባቸውን አደጋ በዚህ ወጪ መቀነስ ከተቻለ ለባለንብረቱም ጥቅም መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

ከፍጥነት ገዳቢ መሣሪያው ጐን ለጐን ጂፒኤስ እንዲገጥሙ ይገደዳሉ ተብለው የሚጠበቁት የጭነትና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ የጂፒኤሱ መገጠም እያንዳንዱ ባለንብረት ተሽከርካሪው የት እንዳለ ለማረጋገጥ የሚያስችለው ነው፡፡

ጂፒኤሱ ተጨማሪ አገልግሎት እንዲሰጥ ከተፈለገም አነስተኛ በሆነ ወጪ የሚገዙ መሣሪያዎች ተገጥመውለት አንድ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ምን ያህል ሰው እንደጫነ፣ ተሳፋሪዎችን የት የት ቦታ እንዳወረደና እንዳሳፈረ በሞባይልና በኮምፒውተር መቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

አሁን ባለው ገበያ ጂፒኤስ አንድ ተሽከርካሪ ላይ ለመግጠም እስከ 10 ሺሕ ብር ሊፈጅ ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ከ580 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ የትራንስፖርት ባለሥልጣን ይገልጻል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች