ወ/ሮ ኬሊ ሰይፉ ዮሐንስ የተወለዱት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆንም፣ የተማሩትና ብዙ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በአሜሪካና በስዊዘርላንድ ነው፡፡ ባለቤታቸው ዲፕሎማት ስለነበሩም፣ እሳቸው ተዘዋውረው በሠሩባቸው በርካታ አገሮች አብረው በመጓዝ ከውጭው ዓለም ጋር በሚገባ ተዋውቀዋል፡፡ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ውስጥ ፍሪደም ፎር ሀንገር (Freedom For Hunger) በሚባል ፕሮጄክት ውስጥ ዳይሬክተር ሆነው ከመሥራታቸውም በተጨማሪ፣ የአፍሪካ ኅብረት ሲመሠረት አማካሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ወ/ሮ ኬሊ በደቡብ አፍሪካ ሥልጣን ከኔልሰን ማንዴላ ወደ ታቦ ምቤኪ ሲሸጋገር የምርጫ ታዛቢ በመሆን ሠርተዋል፡፡ በዚምባብዌ፣ በዛንዚባርና በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች በተደረጉ አገር አቀፍ ምርጫዎች ላይ በታዛቢነት ተሳትፈዋል፡፡ ከ25 ዓመታት በላይ በውጭው ዓለም ኖረው የደርግ መንግሥት ሊወድቅ ሁለት ዓመታት ብቻ ሲቀሩት ወደ አገራቸው የተመለሱት ወ/ሮ ኬሊ፣ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንደሚሳተፉና በአገር ውስጥም የራሳቸውን የተለያዩ ሥራዎች እንደሚሠሩ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን አምስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ ወ/ሮ ኬሊ ስላላቸው የዓለም አቀፍ የታዛቢነት ልምድና በአጠቃላይ ስለምርጫ ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አምስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ የቀሩዋት ቀናት ብቻ ናቸው፡፡ ከመራጮች ምዝገባ እስከ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ድረስ የነበረው ጊዜ ተጠናቆ የሚቀረው የሕዝቡ ድምፅ መስጠትና የታዛቢዎች ሥራ ነው፡፡ እርስዎ በተለይ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተደረጉ ምርጫዎችን የታዘቡ ወይም በታዛቢነት የሠሩ እንደመሆንዎ፣ በአፍሪካ ምርጫዎች ላይ ተሞክሮዎ ምን ይመስላል?
ወ/ሮ ኬሊ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ የታዘብኩት ምርጫ የደቡብ አፍሪካን ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ለቀው ታቦ ምቤኪ ሥልጣን የያዙበትን ምርጫ ታዝቤያለሁ፡፡ በተለይ ሁሉም አፍሪካውያን ልንከተለው የሚገባና ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተደረገበት ነበር፡፡ እኔም የዚያ ታሪካዊ ምርጫ ታዛቢ በመሆኔ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ከካርተር ሴንተር፣ ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከአፍሪካ ኅብረትና ከተለያዩ ቦታ ለመታዘብ ከመጡና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካላቸው ታዛቢ ቡድኖች ውስጥ መገኘቴም ልዩ ደስታ ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ታዛቢ ሆነህ ስትሠራ፣ ነገሮች ትክክል ይሄዳሉ ወይ? ምርጫው በትክክል ከመድልዎና ከማጭበርበር የፀዳ ነው? ሕዝቡስ ድምፁን የሚሰጠው በነፃነት ነው? የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሕግንና ሥነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ ተዘጋጅተዋል? በተለይ ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚወዳደሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳያሸንፉ የሚደረግ ጫና አለ? በምርጫው ቦታ ከውስጥና ከውጭ የሚታይ ጫና አለ? ወዘተ የመሳሰሉትን ከማንም ወገን ሳይሆን በትክክለኛውና የታዛቢዎችን ሥነ ምግባር ደንብ ወይም መመርያ ባከበረ መልኩ ታዝቦ ሳይጨምሩ፣ ሳይቀንሱና ሳያጋንኑ የታዘቡትን ለሚመለከተው (ላሰማራህ አካል) በዝርዝር ማቅረብ (ሪፖርት) ማድረግ ነው፡፡ ከደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ በታንዛኒያ፣ በዚምባቡዌና በሴራሊዮን የተደረጉ ምርጫዎችንም ታዝቤያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ታዛቢ እንዲሆኑ የመረጠዎት ወይም የሚልክዎ ማነው?
ወ/ሮ ኬሊ፡- ብዙ ጊዜ የሄድኩት በአፍሪካ ኅብረት በኩል ነው፡፡ የመጀመሪያውን ማለትም የደቡብ አፍሪካን ምርጫ በጥሩ ሁኔታ በመታዘቤና ሪፖርት በማድረጌ፣ ጥሩ ልምድ እንዳለኝ ስለታወቀ እየተመረጥኩ እንድታዘብ ተደርጌያለሁ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ በወቅቱ ብዙ ሴቶች ስላልነበሩ፣ እኔ ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት ተመራጭ ለመሆን በቅቻለሁ፡፡ አፍሪካን ለማገልገል ፍላጎት ስላለኝ ሁሌም ስመረጥ ደስተኛ ነበርኩ፡፡
ሪፖርተር፡- የምርጫ ታዛቢ ማለት ለእርስዎ ምን ማለት ነው?
ወ/ሮ ኬሊ፡- በምርጫ ላይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ገዥ ወይም አስተዳዳሪ ፓርቲ አለ፡፡ እነዚህንና ሌሎች የተለያዩ አካሎች ወደ አንድ ሜዳ ማለት ወደ ምርጫ መጥተው የሚያደርጉት እኔ አሸንፍ፣ እኔ አሸንፍ ውድድር በትክክል መካሄዱን ማየት፣ መመልከትና ለማንኛውም ወገን ሳያዳሉ እውነትን መመስከርን እኔ ታዛቢነት እለዋለሁ፡፡ አግባብ ያለው ውድድር፣ ትክክለኛ እንቅስቃሴና ከምንም ነገር የፀዳ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ታማኝ ሆኖ፣ በአንድ የምርጫ ውድድር ላይ የሚሰማራ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው አካል ጥሩ ታዛቢ ነው ማለት እችላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የአፍሪካ ምርጫዎችን ለየት የሚያደርጋቸው ምንድነው?
ወ/ሮ ኬሊ፡- ምርጫ ከባድ ቢሆንም፣ አፍሪካውያን እየተማሩና ዴሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነ እየገባቸው መጥቷል፡፡ የመቻቻል፣ አብሮ የመሥራት፣ የራስን ጉዳይ በራስ የማየት ነገር እንዳለ ለማየት ችያለሁ፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት የሌለ ነገር አሁን እየታየ የመጣ የኔነት ስሜት እየዳበረ መምጣቱን የተማርኩበትና ልምድ ያገኘሁበት ነገር ነው፡፡ አፍሪካ አሁን ወደ ዴሞክራሲ መንገድ ገብታለች፡፡ ይኼ በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ የግድ በሁሉም ነገር መስማማት ባይቻልም፣ በሚስማሙበት ነገር ላይ እየሠሩ ልዩነቶችን ማጥበብ ይቻላል፡፡ በዚህ ደግሞ አፍሪካውያን በራሳቸው በአፍሪካውያን ሲዳኙና ውጤት ሲያገኙ ማየት በጣም ያስደስታል፡፡
ሪፖርተር፡- ታዛቢ በነበሩባቸው ምርጫዎች ላይ ያጋጠሙ ችግሮች ነበሩ?
ወ/ሮ ኬሊ፡- ችግር የለም አይባልም፡፡ በሁሉም ቦታ ችግር ይኖራል፡፡ ችግሩ አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛ ችግር ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ትክክል አይሆንም፡፡ አንደኛው ትዕግሥት አጥቶ የማይሆን ነገር ሊያደርግ ይችላል፡፡ አለመግባባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ምንም ይሁን ምንም ምርጫ ማድረጋቸው ግን አይቀርም፡፡
ሪፖርተር፡- በተጨባጭ በምርጫ ዕለት ያጋጠመና በተለይ ኢትዮጵያ ልትማርበት ይገባል የሚሉት ወይም ያዩት ችግር አለ?
ወ/ሮ ኬሊ፡- ችግር አለ፡፡ በዚህ አገር ይኼ ተደርጓል ብሎ ስለችግር ማውራት ለማንም አይጠቅምም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ተወዳዳሪ አካሎች የአንድ አገር ዜጎችና ለአንድ ዓይነት ሕዝብ ለማገልገል እስከሆነ ድረስ፣ ሁሉን ነገር በፍቅር ማድረግ አለባቸው፡፡ ሕዝብ መሠልጠን አለበት፡፡ ነፃና አግባብነት ያለው ምርጫ መደረግ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ምርጫ የሚታዘቡት በአገር ውስጥ የተመረጡና ከአፍሪካ ኅብረት የሚመደቡ ናቸው፡፡ የሌሎች አገሮች ታዛቢዎች አልተፈቀደላቸውም፡፡ እርስዎ አግባብ ነው ይላሉ?
ወ/ሮ ኬሊ፡- እኔ የምመኘው አፍሪካውያን ለአፍሪካውያን ታዛቢ እንዲሆኑ ነው፡፡ የራሳችንን ችግር ራሳችን መፍታት አለብን፡፡ የሌሎች አገሮች ታዛቢዎች ማምጣት የለብንም፡፡ የእኛው የአፍሪካ ታዛቢዎች ለአፍሪካ በቂ ናቸው፡፡ ለምን ቢባል እኛ አፍሪካውያን ወደ ሌሎች አገሮች እንሄዳለን እንዴ? ታዛቢ እንሆናለን? አንሆንም፡፡ ስለዚህ የእኔ ምኞት አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን መፍታት ያለባቸው በአፍሪካውያን እንዲሆን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ እየተጀመረ በመሆኑ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ይተገበራል፡፡
ሪፖርተር፡- ታዛቢ መመረጥ ያለበት እንዴት ነው?
ወ/ሮ ኬሊ፡- ታዛቢን ለመምረጥ ግለሰቡን/ግለሰቧን በደንብ ማወቅ የግድ ይላል፡፡ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የገቡት መሆን አለበት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተቆርቋሪ የሆነ መሆን አለበት፡፡ ስለምርጫና የምርጫ ሕጎች ዕውቀት ያለውና ሀቀኛ መሆኑ በደንብ የተጠና ሰው መሆን አለበት፡፡ አፍሪካ ውስጥ ብዙ ምሁራን አሉ፡፡ አርቀው የሚያስቡ አሉ፡፡ የአፍሪካን በሽታ የሚያውቀው አፍሪካዊው ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ምሁራን ተመርጠው ሊታዘቡ ይችላሉ፡፡ መዳኘትም ስለሚችሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. አምስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ታደርጋለች፡፡ ካለፉት አራት ምርጫዎች መካከል እርስዎ ታዛቢ የሆኑበት አለ?
ወ/ሮ ኬሊ፡- እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ በአገሬ ምርጫ ላይ መታዘብ አልችልም፡፡ አንድ ዜጋ በአገሩ ውስጥ ምርጫ ሲደረግ የምርጫ ታዛቢ መሆን አለበት የሚል ዕምነት የለኝም፡፡ እኔ ለአገሬ ሁሉን መልካም ነገር እመኛለሁ፡፡ ታዛቢ ሆኜ ግን አላውቅም፡፡ በአንዳንድ አገሮች ግን ያደርጋሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የታዛቢዎች ሥነ ምግባር ሕግ አለ፡፡ አንድ ታዛቢ አንድን ምርጫ ሊታዘብ ሲመደብ ከማንኛውም ተፎካካሪ ወገን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ በ1997 ዓ.ም. በተደረገው አገራዊ ምርጫ ላይ በታዛቢነት የተገኙ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የሚታሙበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
ወ/ሮ ኬሊ፡- አንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ ነገሮች አሉ፡፡ አንድ ዓለም አቀፍ ታዛቢ አድልዎ መፍጠር የለበትም፡፡ ወገናዊ መሆን የለበትም፡፡ ከሁሉም የነፃ መሆን አለበት፡፡ ሕጉን ተከትሎ መሥራት እንጂ፣ ለአንዱ ወገን አድልቶ ሌላውን ለመጉዳት መሥራት የለበትም፡፡ አግባብ ያለው ሥራ ይሠራል ተብሎና እምነት ተጥሎበት ስለተመረጠ፣ ዕምነቱን ጠብቆ መሥራት አለበት፡፡ ከዚህ በፊት በአንዳንድ አገሮች ላይ የተፈጸሙ ችግሮች አሉ፡፡ የማዳላት ነገር ታይቷል፡፡ ይኼ ግን የምርጫ ሕጉ ፈጽሞ የሚከለክለው ተግባር ነው፡፡ መሆንም የለበትም፡፡ ከሁሉ ነገር ለመፅዳት ሲባል ነው አንድ ታዛቢ በአገሩ ላይ ለሚካሄድ ምርጫ ታዛቢ የማይሆነው፡፡ ትልቅ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ የአገርና የዜጎች ጉዳይ ስለሆነ፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ከ1987 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ አራት ምርጫዎች ሲካሄዱ እርስዎም እዚሁ ነበሩ፡፡ ዓለም አቀፍ ታዛቢ እንደመሆንዎ መጠን በአገርዎ ስለተካሄዱት ምርጫዎች ጥሩና ጥሩ ያልሆኑ ሒደቶችን ሰምተዋል፣ አይተዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ምን ታዘቡ? እንዴት ይገመግሟቸዋል?
ወ/ሮ ኬሊ፡- እኔ እንደ ታዛቢ አብሬ አልተቀመጥኩም፡፡ ከምሰማው ተነስቼ ዳኝነት መስጠት አልችልም፡፡ እኔ ዓለም አቀፍ ታዛቢ ነኛ! የምመኘው ግን ታዛቢዎች አግባብነት ያላቸው ትክክለኛ ታዛቢዎች እንዲሆኑ ነው፡፡ ስላለፉት ምርጫዎች ምንም ማለት የምችለው ነገር የለም፡፡
ሪፖርተር፡- በ1997 ዓ.ም. የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢ ቡድንን መርተው የመጡት ሚስ አና ጎሜዝ፣ ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ምርጫው በተፅዕኖ የተተበተበና ትክክለኛ ያልሆነ መሆኑን በመግለጽ የኢትዮጵያን መንግሥት አውግዘዋል፡፡ መንግሥትም የራሱን አፀፋ መልስ ሰጥቷል፡፡ እርስዎ እንዴት ተመለከቱት?
ወ/ሮ ኬሊ፡- ታዛቢ ሲኮን ሕጉን ጠብቆና አክብሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት የአፍሪካን ጉዳይ በአፍሪካ ማየትና መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ሌላ ጣልቃ ገብነት አያስፈልግም፡፡ በአጠቃላይ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን መፈታት አለበት፡፡ የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- በአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከአፍሪካ ኅብረት ታዛቢዎች በስተቀር ሌሎች ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች አይኖሩም፡፡ በእርስዎ አስተያየት መንግሥት የወሰደው አቋም ትክክል ነው ማለት ነው?
ወ/ሮ ኬሊ፡- ‹‹የአገሩን በሬ በአገሩ…›› እንደሚባለው አፍሪካ የአፍሪካን ችግር ይፍታ፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም የተቋቋመው ለዚሁ ነው፡፡ እኔ ከድሮም ጀምሮ አፍሪካ ለአፍሪካ ከሚሉት ውስጥ ነኝ፡፡ የድንበርም ሆነ ሌሎች ችግሮች ቢፈጠሩ በአፍሪካውያን ይፈቱ፡፡ መንግሥት ትክክል ነው ወይም አይደለም ሳይሆን የኔ እምነት አፍሪካ ለአፍሪካ የሚል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ በ2002 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ 99.6 በመቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበሮችን ተቆጣጥሮ ነበር፡፡ በምርጫ ውድድር እንደዚህ ዓይነት ውጤት መገኘቱ ምርጫውን አግባብነት ያለው፣ ፍትሐዊና ተዓማኒነት ያለው ነው ሊያስብል ይችላል?
ወ/ሮ ኬሊ፡- እኔ በወቅቱ ታዛቢ አልነበርኩም፡፡ ይኼንን መናገር የሚችለው በወቅቱ የታዘበና የሠራ ሰው ነው፡፡ እዚህ ላይ ምንም አስተያየት መስጠት አልችልም፡፡
ሪፖርተር፡- አምስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለሚታዘቡ ምን ይመክሯቸዋል?
ወ/ሮ ኬሊ፡- እኔ እንደ ኢትዮጵያዊ አገሬን እወዳለሁ፡፡ ሕዝቤን እወዳለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ፡፡ ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት ነው፡፡ በመሆኑም ታዛቢዎች እውነተኛ ሆነው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ እመክራለሁ፡፡ ትክክል የሆነውን ነገር መሥራት አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ አፍሪካውያን ለምርጫ ሥርዓት መብቃታችን ተመስገን የሚያሰኝ ነው፡፡ ትልቅ ዕድገትም ነው፡፡ ስለዚህ በመቻቻል፣ በመተማመን፣ በመደጋገፍና ዕውነተኛ ምርጫ በማድረግ ተጋግዞ አገርን ማሳደግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡ በመሆኑም ታዛቢዎች ብቻ ሳይሆኑ ተወዳዳሪዎችም በአግባቡና በሥርዓቱ ሕጉን ጠብቀው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ መቃወም ብቻ ሳይሆን፣ መተባበር በሚገባን ነገር ላይ መተባበር አለብን፡፡ በልዩነቶች ላይ መቃወም ተገቢ ቢሆንም፣ ሥርዓትና ሕግን በተከተለ መንገድ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ግን ከደቡብ አፍሪካ በተለይ ከኔልሰን ማንዴላ ወደ ታቦ ምቤኪ ሥልጣን በተላለፈበት ወቅት የተደረገውን ምርጫ አካሄድ መከተል አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያም ምርጫ ሕግን የተከተለና ሰላማዊ እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡ እንደሚሆንም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ምርጫ በሕዝብ የተመረጡ ኢትዮጵያውያን ይታዘባሉ፡፡ እርስዎ ደግሞ ዓለም አቀፍ ታዛቢ ኢትዮጵያዊት ነዎት፡፡ ለምን የአገርዎን ምርጫ አይታዘቡም?
ወ/ሮ ኬሊ፡- አገሬማ አገሬ ነው፡፡ ሁሉን ነገር አያለሁ እመለከታለሁ፡፡ እንደ ታዛቢ ግን የአገር ተወላጅ ሆኜ አልታዘብም፡፡ በፊት እንደዚህ አይደረግም ነበር፡፡ አሁን ግን አላውቅም፡፡ ያንተው ጉዳይ ስለሆነና አንተም ከሚመርጡትና ከሚመረጡትም ወገን ስለሆንክ ልታዳላ ትችላለህ፡፡ ግን እንደ ዓለም አቀፍ ታዛቢ የአገሩ ተወላጅ በአገሩ ጉዳይ ላይ ታዛቢ መሆን አይችልም፡፡ እውነተኛና ሀቀኛ የሆነ ሰው ከተገኘ ግን ቢታዘብ ምንም ችግር የለውም፡፡ በራስ ጉዳይ ላይ ግን ታዛቢ ባይኮን ይመረጣል፡፡ ኢትዮጵያ ቆንጆ አገር ነች፡፡ ብዙ ነገር አለን፡፡ ሀብቷን ጠብቀን፣ የእኔነት ተሰምቶን፣ አገራችንን በሰላም፣ በፍቅርና በመቻቻል እያለማን ዓለምን ማስደነቅ አለብን፡፡