Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‘ሾፒንግ ላይ ነን’

ሰላም! ሰላም! መለካከፍ በየት አሳብሮ እንደሚደርስብን አናውቅ አይደል? እናም እኔና ማንጠግቦሽ ገሃዳዊው ተውኔት አልበቃን ብሎ በቴሌቪዥን ተውኔት ምርጫ ተለካክፈን ይኼው ተኳርፈናል። የ‘ዲሹ’ ሲያልቅባት ወደ አገር ቤቱ፣ የአገር ቤቱ ‘ይቀጥላል’ ብሎ ሲጨርስ ወደ ቅርብ ሩቆቹ ቻናል እየቀያየረች ወሬ መስማት አልቻልኩም። ነገሩ ሲጀምር እኔ ምን ያልኩ ይመስላችኋል? ‹‹አንቺ ሴትዮ የፊልምና የድራማ ዘር በሙሉ በማካለል ‘ካስት’ ትደረጊያለሽ ያለሽ ማን ነው?›› አላልኩም?! አበደች! ለካ እንደ ፖል ቴርጋት አንድ ጊዜ እንደ ምንም ፊቴን በ‘ስክሪን’ ካስመታሁ ከዚያ ‘ቢዝነሱ’ ተውልን ብለው ከሚያስቡ፣ ከኪነ ጥበብ ለ‘ቻፓ’ እና ለዝና ከሚሽቀዳደሙ ቀሽሞች ተርታ የመደብኳት መስሏት ነው። ዘንድሮ በመሰለኝ አይደል የምንነዳው? አያድርስ እኮ ነው እናንተ።

 እናም አንዲህ ከተባባልን ወዲያ እኔ ሳሎን ተቀምጬ አላውቅም እላችኋለሁ። ‘ሕዝብ በሕዝብ ላይ’ የተባለው ትንቢት በእኔ ቤት በኩል ሲያልፍ ‘ፊልም በፊልም ላይ’ ተብሎ የተቀየረ እስኪመስለኝ ድረስ ቤቴ ሲኒማ ቤት ሆኗል። አያችሁ እኔ ደግሞ ይኼውላችሁ ብልጥ መሆን አለብኝ። ጊዜው የምርጫ ነው። ከምርጫው በላይ ደግሞ መንግሥታችን ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እያለ በተለይ የሰላሟን ነገር አለቅጥ አራግቧታል ተብሎ ይታማል። ወዲያ ወዲህ ስል የተባለ እየሰማሁ እንዴት ይሆናል ብዬ ሌሎች ተከታታይ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ አዘል መልዕክቶችን በጆሮዬ ለመስማት ፈልጌ ነበር። ዳሩ ‘ሪሞት ኮንትሮሎ’ እጄ አልገባ አለ። ለካ የሥልጣን ጥማት የሚጀምረው ከቤት ነው አልኩላችሁ። የማንጠግቦሽ ፊልምና ተከታታይ ድራማዎች አላልቅ አለ። ምርጫዋም እንደ አገር አቀፉ ምርጫ ከርሞ ከራርሞ የሚመጣ አልሆነም። ሁሉም ነፍሷ ነው። የሚጣል የላትም። ‘ታዲያ ምን ተሻለህ?’ አትሉኝም? ምን ይሻለኛል ይብስብኛል እንጂ። ከመሸ ደጅ እወጣና ህዋ እንደናፈቀ ሰማየ ሰማያት እንደሚመኝ ባህታዊ እዚያ ጥቁር ስጋጃ ላይ ሿ ብትን ያሉ ከዋክብት ስቆጥር አመሻለሁ። ኮከብ ቆጥሬ ስገባ እቤቴ ማንጠግቦሽ ሆዬ በ‘ዲቪዲ’ ማጫወቻ ፊልም ከፍታ ታያለች፡፡ ምርጫችንና ‘ላይካችን’ እንደ አሻራችን የማይገናኝ ነን ሰዎች ስንባል!

ታዲያ እንዲህ ማንጠግቦሽን ሳብጠለጥል እኔ የሲኒማ ጥበብ የማይገባኝ ሞኝ እንዳልመስላችሁ። የሐምሌ ዝናብ በቆዳችን ቀዳዳ ሾልኮ መሬት የሚያደርስ እስኪመስል በላብ ተጨማልቀን፣ ተፋፍገን በ‘ቦሊውድ ትራጀዲ’ እንባ ስንራጭ፣ ‘እፍፍ . . . ’ ያልነው የአፍንጫችን ጭቃ እስከዛሬ አልደረቀም። (የእኔንም ይጨምራል) ጀምስ ቦንድ ያለ ደጋፊ አንዳች የሚያህል ግንብ ዘለለ ብለን እንዳሁኑ ግንብ በግንብ ላይ፣ ሕንፃ በሕንፃ ላይ ሳይደረደር ከጎረቤት ጎረቤት አጥር ዘለናል። (እዚያ መሀል ነበርኩ) ‹‹እነዚህን ውሪዎች ምን እናድርጋቸው? ወልደናቸው እንደ ባላንጣ ድንበር አጋፉን እኮ?›› ተብሎ ቡና ተፈልቶብናል። ‘ሲሪየስ!’ የኖረ አይማልለትም። የነበረን ማርዳት ፋይዳ የለውም። ያንጋለልናቸው አጠናዎች ምስክር ነበሩ። አልነበሩም? ዛሬ በሲሚንቶ ብሎኬት እያጣበቅን ልማት አጣድፎን መንደር በ‘ግሬደር’፣ ታሪክ በ‘ዶዘር’ መዳመጥ ሆነ እንጂ ሥራችን፣ አልፎ አልፎ ወላቃ ጥርስ የሚመስሉ አጥሮች ካጋጠማችሁ፣ በቃ እነሱ የእኛ ‘ሆሊውዶች’ ነበሩ።

ዛሬ ግን በግሌ በትራንስፖርት እጦት ተሠልፌ ስተክዝ ‘ሥነ ጽሑፍ ቀጭጮ፣ የአጭርና የረጅም ልብ ወለድ ድርሰቶች ኅትመት ተቀዛቅዞ፣ ልይስ ብል ምን ዓይነት ፊልም ላይ ነው?’ እያልኩ ቢያምረኝም በየሲኒማ በር ለመሠለፍ እለግማለሁ። (‘ኦፒኒየን’ ይከበር እ? ይህ የእኔ ‘ኦፒኒየን’ ነው። በእንግሊዝኛ ‘ቴረር’ ለቀቀብን ብላችሁ ደግሞ በእንግሊዝኛ እንዳትከሱኝ ደግሞ አደራ) ከትምህርት ቤቴ የሰንደቅ ዓላማ መዝሙር ሠልፍ በላይ ግን ብርክ እስኪይዘኝ አምባሳደር ሲኒማ ተሠልፌ አውቃለሁ። መቼም አገሩ ብቻም አይደል። ሕይወትም ሠልፍ በመሆኑ መሠለፍ ዕጣ ሆኖብን ለዳቦም ለፊልም ሠልፍ ስንይዝ ኖርን። እናስ? ያኔ በሃምሳ ሳንቲም ሦስት ተከታታይ የክትክት ፊልም ዓይተን ስንወጣ፣ ቀኑ ይመሽልን ነበር። ታዲያ ሲኒማ ቀን እንዳልገፋልህ እንዴት ዛሬ አንገሸገሸህ አትሉኝም? እንዲያ ነው ጨዋታ!

 በሲኒማ ጥበብ ‘ፊልም’ ‘ሲፈለም’ ከጥብቅ ሴራዎች ይልቅ በ‘ልቅ’ ሴራዎች (ማለትም የማይመስሉ በገሃዱ ዓለም ብዙም ሲከሰቱ የማይታዩ ታማኝነት በብዙ የሚጎላቸው) ውስብስብ ታሪኮች ይሠራሉ። ዓይተንም አጃኢብ እንዲህ ብሎ ነገር አለ ተባብለን እናውቃለን። እንደ ዛሬ እንግዳ የሚሆንብን ነገር ሳይጠፋ ‘ፋራ’ እያለን (እስኪ ፋርነቱ የናፈቀው? አለሁ እኔ አይዟችሁ፣ እጅ ካላያችሁ እጅ አታወጡ ጥሎባችሁ) ሕግና መንግሥት የሌለበት ወና ከተማ በሚመስል መቼት የተደራጀም ያልተደራጀም ማፊያ የንፁኃን ዜጎችን ሕይወት ሲያከስም በስክሪን ብቻ ነበር የተመለከትነው። ዛሬስ ብትሉኝ ‘ፊልም’ የሚያስንቁ ውንብድናዎች አጠገባችን ተገኙ እላችኋለሁ። በሕዝብ ስም፣ በሃይማኖት ስም፣ በግል ስም ንግዱ ደራ። የገነት ሕግ ‹‹የሰው ገንዘብ ብቻ ብሉ የላባችሁን ፍሬ ግን እንዳትቀምሱ›› ተብሎ የተገለበጠ መሰለ። መሰለም አይደለም ሲሆን አየን። አላያችሁም? አዳኝ ፍለጋ፣ የንፁኃን ጠበቃ፣ ጀብደኛ ‘ሂሮ’ አክተር ፍለጋ ዓይናችን ቃበዘ። ግን ሳስበው ሰብስበው ያጣን ይመስለኛል። ሙሰኛ እያሰደደን፣ ጉቦ መስጠት አገር እያስለቀቀን ተሰብስበን ያወገዝነው ማንን ነው? ታዲያ እንዲህ ዘመን ለ‘ትራጀዲ’ ተውኔት መልምሎት ለኑሮ ደፋ ቀና የሚል ተዋናይ ምን ሰዓት ኖሮት፣ እንዴትስ አዕምሮው ዘለል ብሎ ለሲኒማ ወንበር ቲኬት ይቆርጣል? ይገባችኋል መሰለኝ የማወራው? ብራቮ!

 የሆነው ሆኖ ግን አያችሁ? ሕይወት በምርጫ የተሞላች ናት። በ‘ሳይንስ ፊክሽን ፊልም’ ዓለም አበደች። ሥጋ ለባሽ ከሥጋ ለባሽ ጋር (ትናንት የፊልም አጻጻፍ ዘውግ ብቻ በመሰለን ልቅ ሴራ) መናቆር ሲሰለቸው፣ በብረት ለበሶች ፍልሚያ አጨብጭቦ እንዲወጣ ምርጫ ተሰጠው። ‹‹ፈረንጆች ብልጥ ናቸው አየህ። ዛሬ የምናየውን ሲኒማ ደግሞ ነገ ደንበኛ ኑሮአችን የሚያደርጉትና (መሆኑ አይቀርም ባይ ነኝ እመነኝ) ደግሞ ሌላ የሚሳዩን አያጡም፤›› የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። ምን ልላችሁ ነው በአጭሩ? ኑሮ ራሱ ፊልም ስለሆነብኝ በሁለት ስክሪን ዓይኔ እንዳይደክምና ልቤ እንዳይዝል፣ በማንጠግቦሽ ‘ሪሞት’ ከመመራት ከምርጫዎቿ ራሴን አግልዬ ኮከብ ብቆጥር መረጥኩ። መቼም ከዚህ በላይ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የለም! ሰሞኑን ታዲያ ‘ሬስቶራንት’ ገብቼ ከተመገብኩ ዘመን እንደሌለኝ ድንገት ትዝ አለኝ። የድንገት ትዝታና ትንታ አልወድም ብያችኋለሁ? እንጃ። ብቻ ትዝታዬን ለሰው አላወራሁም። ‹‹እኔ ከቤቴ ውጪ ከበላሁ ዘመን የለኝም’ ስል ‘እኔ መቼ ቤት አለኝና?’ የሚለኝ ሰው ትንሽ እንዳልሆነ አውቃለሁ። ታዲያስ! ወዲያው ወደ ባሻዬ ልጅ ደወልኩ። ‹‹ዛሬ እስኪ ምሳ ልጋብዝህ?›› ስለው እንደጥጃ እየቦረቀ መጣ። እውነቱን ነዋ። እንኳን አፍቅሮ ማዕድ እንቋደስ የሚል ተቀይሞ ጥፊ የሚያልስ ሰውም እኮ ጠፍቷል። የማንጠላና የማንወድ ሆነን ደርቀናል እኮ ጎበዝ፡፡ የምሬን እኮ ነው!

ብቻ ተያይዘን አንድ ምግብ ቤት ገባን። አስተናጋጁ ቀልጠፍ ብሎ መጣና መዝገብ የሚያህል ‘ሜኑ’ ሲያስታቅፈን የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ይኼስ ብርድ ሲመጣም ብትለብሰው ይሆናል፤›› እያለ ይቀልዳል። ከአስተናጋጁ ጋር እያፌዘ፣ ‹‹ማኅበራዊ አምጣልን፤›› ይላል። እሱ ሲያዝ እኔ በዚያ ምን በሚያህል ‘ሜኑ’ ተደብቄ ዋጋውን አያለሁ። ‹‹በተሰቀለው በዚህማ ለወር የሚበቃ ሽንኩርትና ቲማቲም አልገዛም?›› ስል አስተናጋጁ፣ ‹‹ማኅበራዊ ጨርሰናል፤›› ይላል። ነፍሴ ወደ ሥፍራዋ መለስ ከማለቷ፣ ‹‹እሺ ቅቅል፤›› ይላል የባሻዬ ልጅ መልሶ። ዋጋውን ሳይ እሱም አንጀቴን ሊቀቅለው ደረሰ። ተሳቅቄ ሞትኩ። ‘ወይ ኑሮ!’ አልኩ። እውን ጊዜ ነው የሚሮጠው ኑሮ? ‘የቀበጡ ለት’ እያልኩ በውስጤ ‘የሚቀጥለው የባሻዬ ልጅ የምግብ ምርጫ ምን ሊሆን ይችላል?’ — ስገምት — ‹‹ታዲያ ምንድነው ያላችሁ? ዳቦና ሻይ ልንበላ አልመጣን?›› ብሎ ደነፋ። አስተናጋጁ ግራ ገብቶት፣ ‹‹ትኩስ ነገር የለም። መብራት ጠፍቷል፤›› ብሎ አረፈው። ይኼን ጊዜ ሁለታችንም እኩል፣ ‹‹ለምን ቁርጥ አንቆርጥም?›› ተባባልን። በሞላላቸው ሥጋ አፍቃሪያን ማኅበር ያልሞላላቸው ዓይኖች በአምሮት እየጠቀሱን እስክንዘረር ዳቢትና ሻኛ በሐሞት አጠቀስን። ሒሳብ ስከፍል ያለሰቀቀን መዥረጥ አድርጌ ማውጣቴን ያየው የባሻዬ ልጅ ‹‹ለወደድከው፣ ላጠገበህ፣ ላመንከው፣ አምሮት ሐሳብህን ለሚያሳካልህ የምትከፍለው ዋጋ ሲቆረቁር አይቼ አላውቅም፤›› ቢለኝ አባባሉ አምታታኝ። እስኪ ድገሙት የሚያምታታ ነገር የለውም?

እንሰነባበት እስኪ። የባሻዬ ልጅ ቁንጣን ያዘኝ ብሎ ዕረፍት ስላማረው ተለያየን። መጥገብ አያምርብን መራብ አያምርብን፣ ችግር እኮ ነው። በመንገድ እየተጓዝኩ ድንገት የምወደው ግራጫ ቀለም የተነከረ ጃኬት በዓይኔ ገባ። መለካት ከጀለኝ። ከሆነኝ መልበስ አማረኝ። ‹‹ምን አባቱ ሺሕ ዓመት አይኖር›› ስል ባሻዬ ትዝ አሉኝ። ‹‹ይህቺ ሺሕ ዓመት አይኖር ይሏት አባባል የተሸከምነውን የኑሮ ሸክም መሬት አውርዳ እየፈጠፈጠች ዘና ባታደርገን ኖሮ የስምንተኛው ሺሕ ድብርት ጨርሶን ነበር፤›› ሲሉ መጡብኝ። ፈገግ እያልኩ ወደ ልብስ መሸጫው ሱቅ ስገባ ሻጩ ከሁለት ፈረንጆች ጋር ገበያ ይዟል። በሩቅ ያየሁትን ጃኬት በቅርብ እየዳበስኩ እስኪያናግረኝ እጠብቃለሁ። ፈረንጆቹ በተሰባበረ አማርኛ ዋጋ እንዲቀንስላቸው ይከራከራሉ። እሱ በተሰባበረ እንግሊዝኛ (ሲናገረው ራሱ ስፔሊንግ እየገደፈ . . . ምናለበት እስኪ ቢቀርበት?) ዋጋ እንደማይቀንስ ያብራራል። ይሰቃያል ብል ይቀላል። ሳይገዙት ትተውት ሄዱ። አደራዳሪ የልዑካን ቡድን መላክ እስኪቀረው ተከትሎ ሲለምናቸው ቆየና ወደእኔ ሲመለስ፣ ‹‹ይቅርታ! የአገር ገጽታ ግንባታ ላይ ስለነበርኩ ነው፤›› አለኝ። የእሱ ዓይነቱ በየአቅጣጫው ስለበዛብኝ እውነቱን መስሎኝ የአገር ገጽታ ግንባታ በመንተባተብና በመወለካከፍ ሆነ ብዬ ራሴን ልስት ነበር። ለምን እዋሻለሁ?!

ይሁን ብዬ ምርጫዬን ሳሳየው ደግሞ ‘ለካሃው? ወደድከው?’ ሳይል፣ ‹‹ሌላም አለ። ይኼውልህ ይኼንን አይተኸዋል?›› ብሎ ጎርጉሮ ሸሚዝ አወጣ። ‹‹የፈለግኩት ጃኬት ነው። ከጃኬትነቱ በላይ ቀለሙን እወደዋለሁ። ዋጋ ንገረኝ፤›› ስለው፣ ‹‹ዋጋው አያጣላንም። ሌሎች ልብሶችም እኮ ስላሉ ነው። እ . . . ይኼውልህ እዚ-ጋ አሪፍ አሪፍ ጂንስ ሱሪዎች አሉ። ታይላንድና ጣሊያን…›› እያለ አደከመኝ። ‹‹ኧረ ስለጉልበትህ አምላክ። ለምን የጃኬቱን ዋጋ አትጠራም?›› ኮስተር ብዬ ስለው፣ ‹‹‘ሚስድ ኮሉ’ 1000 ብር ነው። ዋናውን የጥሪ ማዕከል 20 ብር ስትቀንስ ታገኘዋለህ። ከዚያ ውጪ ‘ኔትወርክ’ አይሠራም፤›› ብሎኝ አረፈው። አነጋገሩ ቢያበሽቀኝም ጃኬቱ ቀልቤን ስለሳበውና ስለወደድኩት አውጥቼ ከፈልኩ። ስወጣ ግን አልኩት፣ ‹‹ሌላ ጊዜ ግን በሰው ምርጫ እጅህን አታስገባ!›› አይደል እንዴ የሚባለው እንደዚህ ያለው? ‘ሾፒንግ ላይ ሆነን አትበጥብጡን ማለት እኮ የአባት ነው፡፡ አይደል እንዴ?’ መልካም ሰንበት!         

           

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት