Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርስለፓርላማው በሐቀኝነት ይዘገብ

ስለፓርላማው በሐቀኝነት ይዘገብ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተግባሩን የሚፈጽመው በሕገ መንግሥቱ፣ በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ማሻሻያዎችና ደንቡን ተከትለው በወጡ መመርያዎች መሠረት ነው፡፡ ምክር ቤቱና አባላቱ እነዚህን የሕግ መሠረቶች ተላልፎ የሚፈጽመው አንዳችም ተግባር የለም፡፡

ሪፖርተር ግን በቅጽ 20 ቁጥር 1568 የግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትሙ የምክር ቤት አባላት ወደ ምርጫ ክልላቸው በመሄዳቸው ፓርላማው ለሁለት ሳምንት መደበኛ ስብሰባውን ሳያካሂድ ቀርቷል በማለት በዜና አምዱ ገጽ 3 ላይ በማውጣት፣ ምክር ቤቱ ከተቀመጠው አሠራር ውጪ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ አንድምታ ያለው ዘገባ አስነብቧል፡፡ ይህ እንዳልሆነ ለመግለጽ ለሪፖርተር አንባቢያን ይህ አጭር ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

ሚያዝያ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ምክር ቤቱ 27ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል፡፡ እንደ ሪፖርተር አባባል ከሆነ የተቋረጡት የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባዎች ለሁለት ሳምንታት ማለትም የሚያዝያ 27 እና 29 እንዲሁም የግንቦት 4 እና 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ስብሰባዎች ናቸው፡፡

- Advertisement -

ሚያዝያ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. የሕዝብ በዓል በመሆኑ መደበኛው ስብሰባ አልነበረም፤ መካሄድ ሲኖርበት የቀረው መደበኛ ስብሰባ የሚያዝያ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ስብሰባ ብቻ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ሥራዎች በእጁ ሲኖሩ መደበኛ ስብሰባውን በጠዋት ብቻ ከማድረግ አልፎ በሰዓት ክፍለ ጊዜዎች ይቀጥልበታል፡፡ በዚህ የማይሸፈን ሥራ ሲያጋጥም ልዩ ስብሰባ በማድረግ ተግባሩን ይፈጽማል፡፡ አጀንዳዎች ከሌሉት ደግሞ መደበኛ የስብሰባ ቀናት ያለስብሰባ ያልፋሉ፡፡ የአሁኑ ሁኔታም ከዚህ በፊት ከነበሩት የተለየ አይደለም፡፡ ከምርጫ ቅስቀሳ ጋር አያይዞ የተለየ ሥዕል ለመፍጠርና ሕዝቡን ለማደናገር የተሳሳተ መረጃ ስለመደበኛ ስብሰባዎች አለመካሄድ በማስመልከት ያወጣው ዘገባ ትክክለኛ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ምክር ቤቱ 28ኛ መደበኛ ስብሰባውን በማካሄድ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን የ2007 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አድምጧል፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ሪፖርተር በሁለቱ ሳምንታት መደበኛ ስብሰባዎች እንዳልተካሄደ አድርጐ ለአንባቢያን ያቀረበው ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው በሐቀኝነት ስለፓርላማው ይዘገብ የምንለው፡፡

የተከበሩ አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ በአርሲ ዞን ኢተያ ምርጫ ክልል መገኘታቸውና ስብሰባውን ለማካሄድ አንዳንድ አስቸጋሪ ምክንያቶች በመኖራቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የተከበሩ አፈ ጉባዔ ለፓርላማ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ወደ ተለያዩ አገሮች ሲሄዱ ያልተቋረጠ መደበኛ ስብሰባ፣ ዓይንና አፍንጫ ለሆነው ኢተያ አካባቢ በመሄዳቸው መደበኛ ስብሰባ ተቋርጧል ማለት አሳማኝ ምክንያት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፡፡ መደበኛ ስብሰባ ለማካሄድ ምንም አስቸጋሪ ሁኔታ አልተፈጠረም፡፡

መንግሥት መሠረተ ልማት ላይ አተኩሮ በመሥራቱ ለቀጣዩ ጊዜ ዕቅድ ዝግጅት ግብዓት የሚሆን መረጃ ከተወከሉበት የምርጫ ክልል እንዲያመጡ ለሥራ የተፈለጉ የምክር ቤት አባላት በፍጥነት ወደ ምርጫ ክልላቸው በመድረስ የሚፈለግባቸውን ተልዕኮ ከምክር ቤቱ ሥራ ጋር ጐን ለጐን ያከናወኑ በመሆኑ፣ ስብሰባውን ለማካሄድ የሚከለክል ምንም አስቸጋሪ ነገር አልነበረም፡፡

ስለሆነም እውነታውም ሆነ የተቀመጡት ምክንያቶች ከሐቅ የራቁ መሆናቸውን እየገለጽን ለወደፊቱም ቢሆን ለአገሪቱ የጋራ ጥቅም ሲባል በእውነትና በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረተ ዘገባና ትንታኔ ለማቅረብ ሞክሩ ምክራችን ነው፡፡

(የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት)

* * *

የሆስፒታሉን መክሰር በማስረጃ እንወቀው

የምጽፈው እንቆቆልሽ ስለሆነብኝ አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ባህር ዳሩ አፍላጋት ሆስፒታል አክሲዮን ማኅበር ለመታከም ሔጄ በነበረበት ወቅት ከስሮ ተዘጋ መባሉን ስሰማ ማመን አቃተኝ፡፡ ምርጥ ምርጥ ስፔሻሊስት ሐኪሞች የነበሩበት ሆስፒታል አትራፊነቱ ቀርቶ በዜሮ እንኳ ቢንቀሳቀስ በጭራሽ ከስሮ ተዘጋ መባሉ ሊያሳምነኝ አልቻለም፡፡ አክሲዮን ከነበራቸው ግለሰቦች አንዱ ረብጣ ገንዘብ ሲመዙና ሲያበድሩ እያየሁ፣ እየሰማሁ እንዴት ሆኖ ሊዘጋ ቻለ? በእርግጠኝነት ከስሮ ስለመዘጋቱ ተቆርቋሪ ነኝ ከሚሉ አካላት ወይም ከቦርድ አባላት ወይም ሲያስተዳድሩት ከነበሩ ውሳኔ ሰጪዎች ስለመክሰሩና የመዘጋቱ መንስዔ ምን እንደሆነ ሕዝብ እንዲያውቀው ቢያደርጉ ጥሩ ነው፡፡ ለምን ቢባል ከገንቢና ከዓለምሳጋ ሆስፒታል ቀጥሎ የሚታይ ስለሆነና በዋጋ ደረጃም ምርጥ ሆስፒታል እንደነበር ስለማውቅ ነው፡፡

ስለዚህ እውነታውን ሕዝብ ቢያወቀው ጥሩ ነው፡፡ በኮሚቴ ስም የተሰገሰኑ ተወካዮች ለኪሳራ ዳርገውት ከሆነም ሕግ ፊት መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በኪሳራ ተዘጋ የሚለው ሊያሳምነኝ ባለመቻሉ የሚመለከታቸውን ክፍሎች ተጠይቀው፣ ሒሳቡም በገለልተኛ ኦዲተሮች ታይቶ ከሆነም ውጤቱ በይፋ ይታወቅ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡

(ወ/ሮ አቦዘን ወልደ ኪዳን፣ ከባህር ዳር)

  •  

የቀረበው ዘገባ ከእኔ አስተያየት ጋር ተዛብቷል

በሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የሪፖርተር ረቡዕ ዕትም፣ በገጽ 3 ላይ ‹‹የአዲስ አበባ ካቢኔ በመሬት ጉዳይ ውሳኔ ባለመስጠቱ ኢንቨስተሮች መቸገራቸውን ገለጹ›› በሚለው ርዕስ ሥር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሐሰን አብዱ ለሪፖርተር ገልጸዋል በሚል፡-

  1. ‹‹የአስተዳደሩ ካቢኔ በየሳምንቱ ቢሰበሰብም የከተማው አስተዳደር በሌሎች ጉዳዮች በመጠመዱ በመሬት ጉዳይ ላይ ውሳኔ እያሳለፈ እንዳልሆነ፤›› ተብሎ የተገለጸው እኔ በጉዳዩ ላይ ከሰጠሁት አስተያየት ፍፁም የተለየና የከተማ አስተዳደሩ ከግማሽ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ በኋላ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የመሬት ዝግጅትም ሆነ የፕሮጀክት ሐሳብ ግምገማና የውሳኔ ሐሳብ ለካቢኔ የማቅረብ ሥራ መሻሻሉንና የከተማው አስተዳደር ካቢኔም በየሳምንቱ ከሚካያሂደው መደበኛ የስብሰባ ቀን በተጨማሪ፣ የመሬት ጉዳይ እያየና ውሳኔ እየሰጠ መሆኑን፤ ሆኖም ከሚቀርበው የአልሚዎች ጥያቄ መብዛት ጋር ተያይዞ ከቀረቡ የፕሮጀክት ሐሳብና ጥናቶች መካከል ውሳኔ ያላገኙና በቀጣይ እንዲታዩ የተያዙ መኖራቸውን የገለጽኩ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በመሬት ጉዳይ ላይ ውሳኔ እየሰጠ እንዳልሆነ ተጠቅሶ የተዘገበው፣ በእኔ የተገለጸ አለመሆኑና እውነታውም ከዚህ የተለየ በመሆኑ ዘገባው እንዲታረም እንዲደረግ እጠይቃለሁ፡፡
  2. ‹‹የመንግሥትን ሐሳብ በመቀበል ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመግባት የመጡት ባለሀብቶች በመሬት አቅርቦት ችግር እየተጉላሉ መሆኑ አግባብ አለመሆኑን አቶ ሐሰን ገልጸው …›› ተብሎ የተዘገበው ከላይ በገለጽኩት ሐሳብ መሠረት የመሬት አቅርቦትና ማስተላለፍ ሥራችን መሻሻል እንደሚገባው ታምኖበት በመሬት ተቋማትም ሆነ በካቢኔ ደረጃ አፈጻጸሙ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጬ እያለ፣ ከዚህ ጋር የሚጋጭ ይዘት ያለው ሐሳብ የተዘገበው እኔ የሰጠሁትን አስተያየት የማይወክልና ተዛብቶ የተዘገበ በመሆኑ፣ የጋዜጣው አንባቢዎች የተዛባ ግንዛቤ እንዳይዙ ሁለቱም ሐሳቦች ታርመው ለጋዜጣው አንባቢያን የሚደርስበት ሁኔታ እንዲመቻች እጠይቃለሁ፡፡

(ሐሰን አብዱ በሽር፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...