በባንክ ከሚፈጸሙ ግብይቶች መካከል በውክልና የሚስተናገዱት ቁጥራቸውበርካታ ነው፡፡ በየዕለቱ ወደ ባንክ የሚመጡ ደንበኞች ገንዘብ ለማውጣት፣ ብድር ለመውሰድ፣ ውል ለመዋዋል፣ ወዘተ በአካል መጥተው የሚስተናገዱትን ያህል በውክልናም መስተናገዳቸው የተለመደ ነው፡፡ የባንኮቹ ደንበኞች የሆኑ ነጋዴዎች የንግድ ሥራቸውን እንዳይሻማባቸው፣ በአካልም ንግዳቸው ካለበት አገር ውጭ ሲሆኑ፣ ወይም በሌላ ምክንያት ግብይታቸውን በውክልና ማስቀጠልን ይመርጣሉ፡፡
ቀደም ሲል የውክልና ጉዳይ ልክ እንደተራ የደብዳቤ ልውውጥና ግብይት ያን ያህል ውስብስብ አልነበረም፡፡ አሁን አሁን ግን በሰነድ የሚያታልሉ፣ በማጭበርበር የተካኑና በወንጀል ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች አውቀውና አቅደው ደንበኞችንም ሆነ ባንኮችን ጉዳት ላይ መጣላቸው ተለምዷል፡፡ በዚህ ሳቢያ በርካታ ባንኮች ውክልና ሲቀርብላቸው ሰነዱን ወደ መዘገበው አካል በመላክ ትክክለኛ ስለመሆኑ ካረጋገጡ በኋላ ነው ደንበኞቻቸውን የሚያስተናግዱት፡፡ ለምሳሌ መቀሌ በሚገኝ ባንክ ሒሳቡን ለማንቀሳቀስ የፈለገ አዲስ አበባ የሚገኝ የባንክ ደንበኛ፣ ለወኪሉ ውክልና ቢልክለት ወዲያው አይስተናገድም፡፡ ባንኩ ውክልናው ከወጣበትና አዲስ አበባ ከሚገኘው መዝጋቢ አካል ዘንድ በመላክ ካረጋገጠ በኋላ ነው ወኪሉ ገንዘብ እንዲያወጣ የሚፈቅድለት፡፡ ይህ ሒደት ቢያንስ አንድ ሳምንት የሚፈጅ በመሆኑ የሒሳቡ ባለቤት ገንዘቡ ያለበት ቅርንጫፍ ድረስ በመሄድ ራሱ ቢያንቀሳቅሰው ይመርጣል፡፡ ይህ አሠራር በሁሉም ባንኮች ባይሆንም በአብዛኛዎቹ እየተተገበረ ያለና ከሕግ ውጭ የሆነ አሠራር ነው፡፡ ይህን አሠራር ለመተግበር የሚያስገድዱት የሕጉን ይዘትና አስተምህሮውን የሚያውቁት ነገረ ፈጆች መሆናቸው ደግሞ ግርምትን ይፈጥራል፡፡
የውክልና የቅቡልነት መሥፈርቶች መሟላታቸውን (ችሎታ ባለው ሰው መሰጠቱን፣ ውክልና ሰጪው በፈቃድ መስጠቱን፣ በትክክለኛ ፎርም መስጠቱን ማረጋገጥና መመዝገብ) የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሐፈት ቤት ወይም የክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊነት ነው፡፡ ባንኮቹ ሰነዱ ሲቀርብላቸው ሰነድ ከጽሕፈት ቤቱ መውጣቱን በውክልናው ላይ ማኅተም መኖሩን፣ መፈረሙን ከመመልከት በቀር ማህተሙ ወይም ፊርማው ትክክለኛ ስለመሆኑ በምርመራ እንዲያረጋግጡ ሕግ ግዴታ አይጥልባቸውም፡፡
የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 334/1995 በአንቀጽ 27 ‹‹በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የተረጋገጠ ሰነድ በውስጡ ስለሚገኘው ይዘት ሙሉ እምነት የሚጣልበት በቂ ማስረጃ ነው፡፡ የተረጋገጠ ሰነድ መቃወም የሚቻለው ፍርድ ቤት በበቂ ምክንያት ሲፈቅድ ብቻ ነው፤›› በማለት ይህንን ሐቅ በአጽንኦት ደንግጓል፡፡ ባንኮቹ የሚከተሉት አሠራር ግን የውክልና ዓላማን ዋጋ ያሳጣል፡፡ ባንኮች ይህን አሠራር መተግበራቸውን ከቀጠሉ ግብይቶች በፍጥነት አይከናወኑም፤ ባንኮች ግብይት የማሳለጫ ቦታ መሆናቸው ይቀርና ሰነድ መርማሪ ይሆናሉ፡፡ ደንበኞችም በባንኮች ላይ ያላቸው መተማመን በሒደት ይቀንሳል፡፡ የውክልና ዋና ዓላማው በአካል ተገኝቶ ግብይት መፈጸም ያልቻለን ወካይ፣ በተወካዩ አማካይነት ግብይት እንዲያከናውን ማስቻል ነው፡፡ ይህ ከሆነ ውክልና የወካዩን ችግር ያቃልላል፤ የንግድ ልውውጥንም ያፋጥናል፡፡ ዳግም የውክልና ሰነድ ወደ መዝጋቢ አካል መላክ ግን ሰዎች በውክልና እንዳይገበያዩ የመከልከል ውጤት አለው፡፡ ባንኮቹ ወደ መዝጋቢው አካል እየተላኩ እንዲያረጋግጡ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤትም የተቀበለውና የወደደው አሠራር መሆኑን በጽሕፈት ቤቱ መረጃ መረብ ከተዘረዘሩት ተግባራት መረዳት ይቻላል፡፡ አንዱ የጽሕፈት ቤቱ ተግባር ‹‹ስለተረጋገጡና ስለተመዘገቡ ሰነዶች ሥልጣን ባለው አካል ሲጠየቅ ማስረጃ መስጠት›› በሚል ሥልጣኑ ተለጥጦ ቀድሞ የሠራውን የማረጋገጥ ሥራ፣ በየዕለቱ ሁለት ሦስት ጊዜ በድጋሚ ለማረጋገጥ ተገዷል፡፡
የባንኮቹ ሥጋት ግልጽ ነው፡፡ የውክልና ሰነዶች በተጭበረበሩ መጠን ባንኩ ጉዳት ላይ ይወድቃል ወይም ተደጋጋሚ የማጭበርበር ድርጊቶች በተፈጸሙ ቁጥር ደንበኞች ባንክ ላይ ያላቸው መተማመን ይጠፋል ከሚል ምክንያት በመነሳት ነው፡፡ ሥጋትን ለመቀነስ ወይም ለማስወገድ ባንኮቹ በኅብረት የወሰዱት አቋም ስለመኖሩ ጸሐፊው መረጃ የለውም፡፡ ይሁን እንጂ ውክልና የማረጋገጥ ሕጉን ያልተከተለ አሠራር በሁሉም ባንኮች የሚተገበር ባይሆንም ባንኮቹ በጋራ ሊያስቡበት የሚገባ ችግር ነው፡፡
አሠራሩን የሚከተሉ ባንኮች ከውክልና ሰነድ ባለፈ ማንኛውንም ለባንክ የሚቀርብ ሰነድ ከወጣበት የመንግሥት ተቋም ካላረጋገጡ እንደማያርፉ ከጅምራቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ አሠራር በሌሎች ሰነዶች (የፍርድ ቤት ውሳኔ፣ የጋብቻ ማስረጃ፣ መታወቂያ፣ የመኪና ባለቤትነት ደብተር፣ የባለአክሲዮን ሰርቲፊኬት፣ የንግድ ፈቃድ፣ የግብር ከፋይነት የምስክር ወረቀት፣ ወዘተ) መፈጸም ከጀመረ ግብይትን በጥርጣሬ እንዲሞላ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ለምሳሌ በፍርድ ቤት መብቱ ተረጋግጦለት የመጣ ደንበኛን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ትክክለኛ ስለመሆኑ ሳናረጋግጥ መብትህን ልንፈጽምልህ (ገንዘብ ልንከፍልህ) አንችልም ሊባል ነው፡፡ የዚህ አሠራር መጨረሻው እኛ ካላረጋገጥን ማንኛውም የመንግሥት አካል የሰጠውን ሰነድ አንቀበልም በማለት የተቋማቱን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ፣ ሥልጣንና ተግባራቸውን የሚገዳደር አካሄድ ማምራት ነው፡፡
ሕግ የሚያቅፈውን አሠራር የማይከተሉ ባንኮች ተግባራዊ የሚያደርጉት መፍትሔም ችግሩን ለዘለቄታው የሚቀርፈው አይመስልም፡፡ አንዳንዶች የተወካዩን ፎቶ በመቀበልና የውክልና ማስረጃውን ከወካዩ የቁጠባ ሒሳብ ጋር በማያያዝ ደንበኞች እንዲስተናገዱ ያደርጋሉ፡፡ ከቁጠባ ሒሳብ ውጭ ያሉ የባንክ ግብይቶችን በተመለከተ ጥቅም ላይ ባያውሉትም ባንኩን ከመጭበርበር ይታደጋል በማለት መፍትሔውን በወጥነት ይጠቀማሉ፡፡ ሆኖም መፍትሔው ረጅም መንገድ አያስኬድም፡፡ ሲጀመር ወካዩና ተወካዩ በአካል መጥተው፣ ተወካዩ ፎቶውን ሰጥቶ መስተናገዱ ተጨማሪ ግዴታ ከሌለው የሰነዱ ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ወካዩንም አንድ ጊዜ የወከልከው ተወካይ ለዘለዓለሙ እንዲያንቀሳቅስ ፍቀድለት ብሎ የማስገደድ ያህል ነው፡፡
ወካይና ተወካይ በመመሳጠር ለሚፈጽሙት የተጭበረበረ ሰነድ መከላከያ የመሆን አቅሙም አናሳ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአንድ ግብይት ከአንድ የበለጡ ተወካዮችን የመወከል ሥልጣኑ በሕግ ዕውቅና ስላለው የአንዱን ተወካይ ፎቶ መለጠፉ የወካዩን ነፃነት መጋፋት ነው፡፡ ሁለተኛ ተወካይ ሒሳብ ለማንቀሳቀስ ሲመጣ ‹‹ፎቶህ ስላልተለጠፈ አናስተናግድም፤›› የሚል ዘዬ ሊመጣ ነው፡፡ ካልሆነም እንደ ፎቶ ቤት መስተዋት የባንኩን የሰነድ ቋት ፎቶ እየለጠፉ ማጨናነቅ ነው፡፡
ለዚህ ነው ባንኮችን ከውክልና መጭበርበር ሥጋት የሚታደግ፣ ሕጉንም የማይጥስ፣ ደንበኞችንም የማያንገላታ መፍትሔ መፈለግ አማራጭ የማይኖረው፡፡ መፍትሔ እንዲጠቁሙ የተለያዩ ባንኮችን የሕግ አማካሪዎችና ሌሎች ተያያዥ ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በመጠየቅ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ መፍትሔ ለመጠቆም ጸሐፊው አሰበ፡፡ እናም የተወሰኑትን በችግሩ ላይ ጠይቆ ችግሩን በዘላቂነት ይፈታል ያሉትን ሐሳብ ተቀብሏል፡፡
የሕግ ባለሙያዎቹ ሕጉ የውክልናን ትርጉም፣ ውጤትና የተወካይንና የወካይን መብትና ግዴታ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ሕጉን መለወጥ፣ ማሻሻል፣ ከሕጉ መቀነስ ወይም መጨመር ለጉዳዩ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሕጉን በትክክል በመተርጐም ረገድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለባንኮቹ ጠቃሚና የማጭበርበር ድርጊት በውክልና ማስረጃ ላይ በተፈጸመ ጊዜ መከላከያ የሚሆንላቸውን ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ሰበር ችሎቱ በመ/ቁ 20890 ሐምሌ 10 ቀን 1999 ዓ.ም. በሰጠው ገዥ ፍርድ፣ ባንኮቹ ውክልናው የመጣው ከመዝጋቢ አካል መሆኑን ከማረጋገጥ በቀር ጠበቅ ያለ ምርመራ ማከናወን አይጠበቅባቸውም፡፡ ይህን የሰበር ፍርድ መነሻ በማድረግ አንዳንድ የሕግ ምሁራን ባንኮች የማይወጡበት አሠራር ውስጥ ከመግባት የውክልናው ገጽ ምልከታን (Apparently) በማስተዋል ቢያስተናግዱ የሚደርስባቸውን ችግር መቀነስ እንደሚችሉ ያሰምሩበታል፡፡
ያነጋገርኳቸው ባለሙያዎች የሚስማሙበት ዓብይ መፍትሔ ግን፣ ባንኮቹ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ጋር በመወያየት የሚያመጡት የሥርዓት ለውጥ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ የአንድ የግል ባንክ የሕግ አማካሪ እንደሚሉት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የውክልና ሰነዶችን ምዝገባ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ (E- Registration) እንዲፈጸም በማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረጃውን እንዲያገኙ ማድረግ የተሻለ መፍትሔ ነው፡፡ የሕግ ባለሙያው ይህ አሠራር ለጽሕፈት ቤቱ አዲስ ሊሆን እንደማይችል ሲያስረዱም ጽሕፈት ቤቱ ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደሮች ጋር ያለውን ግንኙነት በመጥቀስ ያብራራሉ፡፡ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የቤት ሽያጭ ውል ደንበኞቹ ሲዋዋሉ የሚያቀርቡትን ካርታ ትክክለኛነት እንዲሁም ዕዳና ዕገዳ መኖሩን ከክፍለ ከተማ ጋር በተገናኘው የኤሌክትሮኒክስ መረጃ ግንኙነት አማካይነት ያጣራሉ፡፡ ተመሳሳይ አሠራር ባንኮች እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት መሠረት ቼክን ከማረጋገጥ ጋር የተገበሩት የጋራ የኤሌክትሮኒክ የቼክ ማጣሪያ ዘዴ እንዳላቸው ሌላ የሕግ ባለሙያ ለጸሐፊው ገልጸውለታል፡፡ ቀደም ሲል ባንኮች አንድ ቼክ ትክክለኛ ስለመሆኑ በተላላኪያቸው እያዞሩ ከእያንዳንዱ ባንክ ያጣሩ የነበሩትን አሰልቺና ጊዜ የሚወስድ አሠራር በማስቀረት፣ በጋራ በፈጠሩት ሥርዓት ቼኩ እንደቀረበ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡ ተመሳሳይ ሥርዓት በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤትና በባንኮች መካከል ቢፈጠር ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል ብዙኃኑ የባንክ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ አንዳንድ ባንኮች የሚጠቀሙበት ውክልናን ለመዝጋቢው አካል በመላክ የማረጋገጥ ሥርዓት ባንኩን ከመጭበርበር ፈጽሞ ሊያድነው እንደማይችልም አንዱ የሕግ ባለሙያ ተሞክሯቸውን አጫውተውኛል፡፡
ግለሰቡ በፎርጅድ መታወቂያ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ውክልና በማውጣት ከባንኩ የሌላ ግለሰብን ገንዘብ ለማውጣት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ባንኩ መልሶ ሰነዱ ከወጣበት ክፍል አረጋግጦ ተወካዩን ቢያስተናግደውም የባንኩን መጭበርበር አላስቀረለትም፡፡ ምክንያቱም ለውክልና መነሻ የሆነው መታወቂያ መጭበርበሩ ባንኩ ያከናወነውን ዳግም ማጣሪያ ውጤት አልባ አድርጐበታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ባንኮቹ አሁን የሚከተሉት ወደ መዝጋቢ አካል በመላክ የማረጋገጥ አሠራር የደንበኛውን ጥቅም ሙሉ በሙሉ ላያስጠብቀው ይችላል፡፡ ከዚያ ይልቅ ደንበኛው የሰጠውን ሰነድ ባንኩ ገጹን በአግባቡ ተመልክቶ ቢጭበረበር እንኳ ኃላፊ ወይም ተጠያቂ የማይሆንበትን ውክልና እንደ ፖሊስ በመመርመር አሰልቺ ሥርዓት እንዲያልፍ፣ ጊዜውን እንዲያቃጥልና በገንዘቡ እንዳይጠቀም ማድረግ የከፋው ጉዳት እንደሆነ አንዳንዶቹ ይገልጻሉ፡፡
ሥርዓቱን መለወጡ የባንኮቹን የጋራና የነቃ ተሳትፎ የሚፈልግ መሆኑን የሚያምኑት አንድ የሕግ አማካሪ፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የውክልና መስጫውን ወረቀት ፎርማት (heading) ቅርጽና ይዘት ወጥ ቢያደርገው ችግሩን ሊቀርፈው እንደሚችል ያስባሉ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ተመሳሳይ ዓይነት ወረቀት ከተጠቀመ ከጽሕፈት ቤት የመጣውን ሰነድ ለመለየት ያስችላል፡፡ ማኅተሙና የባለሥልጣኑ ፊርማ እንደተጠበቀ ሆኖ ወረቀቱም ጽሕፈት ቤቱን ገላጭ ከሆነ እንደማንኛውም የመንግሥት ተቋም የውክልና ሰነድ ወጥ የሆነ ቅርጽ (Standard) ስለሚኖረው ችግሩ ይቀረፋል፡፡
ባንኮቹ በአሠራር ያመጡትን ችግር ሊያሻሽሉት የሚችሉት በዋናነት ራሳቸው ናቸው፡፡ የባንክ ሠራተኞች ባንኮች የውክልና ሥልጣንን በማረጋገጥ ረገድ ያለባቸውን ግዴታ የሚያውቁ አይመስሉም፡፡ አንዳንድ ባንኮች ውክልና ማጣራትን የነገረፈጅ የሥራ መዘርዝር ውስጥ አካተውት ይፈጽሙታል፡፡ ነገረፈጆቹም ተቀብለውታል፡፡ ነገረፈጆቻቸው በሕግ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የፍርድ ቤት ሙግት ላይ አድምተው ከመሥራት ይልቅ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ውክልና እንዲያጣሩ መቅጠር ሙያውን ዝቅ ማድረግ፣ የተማረ የሰው ኃይልንም ማባከን ነው፡፡
ከላይ በጽሑፉ እንደተመለከተው፣ ባንኮች የውክልናውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የጽሕፈት ቤቱን ማኅተምና ፊርማ በመመልከት፣ የውክልናውን ገጽ በማየት ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ ከዚህ የዘለለ ምርመራ ማከናወን ግዴታቸው አይደለም፤ ሕጉም አይፈቅድላቸውም፡፡
ስለዚህ በተግባር ውክልናን ወደ መዝጋቢ አካላት መላክ፣ በፖሊስ ፎረንሲክ ማስመርመር፣ ስልክ መደወል፣ ወዘተ ስህተት መሆኑን መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ለመለወጥ ባንክ ውስጥ የተቀመጡ የሕግ ባለሙያዎች መነሳሳቱን ካልወሰዱ ሌላ ባለሙያ በቀዳሚነት የሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ተሳታፊ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የሕግ ባለሙያዎቹ ሕጉን የተከተለ ዝርዝር መመርያ ማስተላለፍ፣ ሥልጠና መስጠት፣ ከዚያም አልፎ አስተያየት ሲጠየቁ በድፍረት ሕጉ የሚለውን ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የመጭበርበሩ ሥጋት ከፍተኛና በየዕለቱ የሚከሰት ከሆነ ደግሞ ከላይ የተጠቆሙትን መፍትሔዎች መጠቀም ተገቢ ነው፡፡ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ጋር በመነጋገር በመረጃ መረብ ለማረጋገጥ የሚቻልበትን አሠራር ማዘጋጀትና መተግበር ይገባል፡፡ ካልተቻለም ደንበኛው ሳያውቅ በተለይ ብዙ ገንዘብ ለሚያወጡ ተወካዮች፣ በስልክ ከጽሕፈት ቤቱ ለማረጋገጥ መሞከር፣ የማጣሪያ ጥያቄዎችን ማቅረብ አማራጭ ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ፈጣን አሠራር በአንድ በኩል የውክልና ንግድን በፍጥነት የማሳለጥ ዓላማ አያደናቅፍም፤ በሌላ በኩልም ባንኮች በሕጉ ከሚጠበቅባቸው ግዴታ በተጨማሪ ተገቢ ጥንቃቄ በማድረጋቸው የሚያድርባቸውን ሥጋት ያርቃል፡፡ ይህ አማራጭ የምዝገባ ሥርዓታችን ደካማ በሆነባት አገራችን ውስጥ ለተወሰኑ ጊዜያት ሊጠቅም ይችላል፡፡
ባንኮቹ ከሕጉ ዓላማ ውጭ ውክልና የመጣበት አካባቢ ድረስ ዳግም በመመለስ ጊዜ ማባከንና ደንበኞች ላይ ጉዳት በማድረስ የሚቀጥሉ ከሆነ ግን፣ ባንኮቹን ራሳቸውን ተጠያቂ ከማድረግ ውጪ ሥጋቱን የሚከላከል አይሆንም፡፡ በዚህ ድርጊታቸው ባንኮች በውል ወይም ከውል ውጭ ኃላፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ደንበኛው ገንዘቡን በጊዜው ባለማውጣቱ ምክንያት ለደረሰበት ጉዳት ባንኮቹ የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ ከውል ውጭ ኃላፊነት ሕግ መሪ ደንብ ‹‹ማንም ሰው ከራሱ ጥፋት የተነሳ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ካደረሰ ላደረሰው ጉዳት ኪሳራ መክፈል አለበት፤›› ሲል የደነገገውን መዘንጋት ሞኝነት ነው፡፡ በባንኮቹ ተገቢ ያልሆነ አሠራር በአካል ካለበት መጥቶ ገንዘቡን አሟጥጦ ከመውሰድ ባለፈ ባንኩ ላይ ክስ መሥርቶ የሚያስፈርድበት ሁኔታ መኖሩን ማወቅ አይከፋም፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡