Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉአጋር ወይስ ባላጋራ?

አጋር ወይስ ባላጋራ?

ቀን:

በሳምሶን ሰ. (ዶ/ር)

መልካም አስተዳደር የስኬታማ አገር መሠረትም መለኪያም ነው፡፡ መልካም አስተዳደር አገሪቱ የሰውና የተፈጥሮ ሀብቷን በሙላት እንድትጠቀም ይረዳል፡፡ ከሌሎች አገሮች  በዕውቀት የተመሠረተ ጥምረት እንድትመሠርት ያግዛል፡፡ እንዲሁም በዜጎቿና በሌሎች ለሥራና ለኑሮ ተመራጭ ያደርጋታል፡፡ በተቃራኒው የመልካም አስተዳደር እጦት ለጥቂት ‶የዘመኑ ሰዎች″ የተለጠጠ ዕድገት፣ ለብዙኃኑ መጨናነቅና ስደት፣ ለብዙ የሀብት (የሰውና የገንዘብ) ብክነት፣ አለመረጋጋትና ጥላቻንም ያፋፋል፡፡

መልካም አስተዳደር የሚሠራ አመራርና የሚሠሩ ሰዎች ውጤት ነው፡፡ መልካም አስተዳዳሪዎች (የሚሠሩ ሰዎች) ደግሞ በዋነኝነት ሦስት መሥፈርቶችን እንዲያሟሉ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህም በሦስት ‶C″ ይሰየማሉ፡፡

- Advertisement -
 1. ብቃት (Competence) ሲሆን ይህም ለደረጃው በሚመጥን ትምህርትና ልምድ የተገኘን የአስተዳደር ዕውቀት ወይም ክህሎት ያሳያል፡፡
 2. ባህሪ (Character) ሲሆን ይህም ኃላፊነቱ የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር ያመለክታል፡፡ የሕዝብ መሪ እንደ አገሪቱ እምነትና ባህል ምሳሌያዊ ሥነ ምግባር ይጠበቅበታል፡፡ ከጎላ ነቀፌታም ራሱን ሊያነፃ ይገባል፡፡
 3. የሥራ ተነሳሽነት (Courage) ሲሆን መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያለውን/ያላትን የመንፈስ ጥንካሬ ወይም መነሳሳት እንዲሁም ዋጋ የመክፈል (የመስዋዕትነት) ዝግጁነትን የሚያመለክት ነው፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የቀበሌና ወረዳ ምርጫ ለመምረጥ መልካም አስተዳደርን እንደሚናፍቅ ዜጋ ወደ ምርጫ ጣቢያው አመራሁ፡፡ በሙያዬ የሕክምና ተመራማሪ ብሆንም ስለተለጠፉት ዕጩዎች ከላይ በተጠቀሱት መሥፈርቶች መጠነኛ የዳሰሳ ጥናት አደረግሁ፡፡ ዕጩዎቹ ከአቅም በታች እንደሆኑም በመገንዘብ ከትውልድ ተጠያቂነት ለመዳን እያዘንኩ ሳልመርጥ ተመልሻለሁ፡፡ በጊዜው ራሴን እንዲህ ስል ሞገትኩት፡፡ ለምን ለምርጫ አልወዳደርም? ይህ ጥያቄ ነበር የአገራችንን የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አሠራር፣ የፖለቲካ መሪዎችንም ብቃት (ባህሪ) ተነሳሽነት እንድቃኝ ያነሳሳኝ፡፡ ፈረንጆች ያለዕውቀት ተናግረው ሰውን እንዳያስቀይሙ ሲፈሩ ከወዲሁ ‶አለማወቄን ይቅር በሉኝ″ (Forgive My Ignorance) እንደሚሉት፣ እኔም የመስኩ ባለሙያ ባለመሆኔ የሚከተሉት ጥያቄዎቼ ያለዕውቀትና የልጅነት ከመሰላችሁ ይቅርታ ከወዲሁ በቀብድ እጠይቃለሁ፡፡ ቢሆንም ሳትፈርዱብኝ እንደ ልጅ አስረዱኝ፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲ የሚለው ስያሜ ለምን አስፈለገ? ዓላማቸውስ ምንድን ነው? ባልንጀራ ናቸው ባለጋራ?

‶ተቃዋሚ″ (Opposition) የሚለው ስያሜ ዓለም አቀፍ መጠሪያ መሆኑን ባውቅም፣ የፈጣሪ ቃል አይደለምና ለፍተሻና ተሃድሶ ወይም ለውጥ ማቃረቡ ክፋት አይመስለኝም፡፡ ስያሜው በራሱ ተቃራኒ፣ ተፃራሪ፣ አፍራሽ፣ እንቅፋትና ባለጋራ የሚል አሉታዊ እንድምታ አለው፡፡ ይህን ሳስብ በመጽሐፍ ቅዱስ በ1ኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 5 ቁጥር 8 ለሰይጣን የተሰጠውን ‶ባላጋራ″ የሚል መጠሪያ ያስታውሰኛል፡፡ ይህም ሰይጣን ሊሰርቅ፣ ሊያርድና ሊያጠፋ እንጂ ለሌላ ገንቢ ዓላማ እንዳልመጣ በማሳየት እርሱን የመቃወም እንጂ፣ የጋራ የመቻቻልም ሆነ የትብብር አጀንዳ ሊኖረን እንደማይገባ የሚያመላክት ነው፡፡ በገዢና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለ ግንኙነት ቅኝቱ ወደዚያ እያመራ ይሆን?

ሰሞኑን በአገራችን የመገናኛ ብዙኃን በሚተላለፈው የፖለቲካ ፓርቲዎች ‶የፉክክር″ መድረክ የታዘብኩት ግንኙነታቸው ከትብብር ይልቅ ፉክክርን ያማከለ፣ ከመከባበር ይልቅ መናናቅ ያጠላበት፣ መነጽሮቻቸው የሌላውን ድካም የሚያጎሉና ውድቀትን የሚሹ፣ ስለራሳቸው ድካምና ስለሌሎች ብርታት ትንፍሽ የማይሉ፣ እንደማይጠቅም ባለመድኃኒትና በከንቱ ለባጭ የተቆጣጠሩበት፣ ድካምን ለሚመለከታቸው ከመግለጥ ይልቅ ለሕዝብ የማጋለጥ ወይም የማንጓጠጥ ዝንባሌ፣ ከአገር ዕድገት ይልቅ የወንበር ወይም የሥልጣን ጥማት ድል ነስቶ የወጣበት፣ ዱላ ቀረሽ ስድድብና መናናቅን የተማርንበትና ከመልዕክታቸው ይዘት በተጨማሪ የሚናገሩበት መንፈስ (የፊት መኮማተርና የደም ሥር መገታተር) የጥላቻቸውን ጥልቀት የሚያሳይበት እንደነበረ አይተናል፡፡

የ12 ዓመት ልጄ በመገረም ‶ፖለቲካ ማለት ስድድብ ነው ወይ?″ ሲል ቢጠይቀኝ፣ ተጨማሪ ስድብና ንቀት እንዳይማርብኝ ከክፍሉ አስወጥቼዋለሁ፡፡ በማግሥቱም የአመራር ጥላቻ እንዳያድርበት ሠግቼ  የፓለቲካ ፓርቲዎችን ውይይት እንዴት አገኘኸው? ብለው፣ ‶ሁሉም ከእኔ በቀር ሌሎቹ አይረቡም ነበር የሚሉት፤″ ሲል የጉዳቱን ጥልቀት አሳየኝ፡፡ ይህን አደገኛ አካሄድ እንደ ‶ጎጂ ዘመናዊ ድርጊት″ እናውግዘው፣ ካልሆነም የመናናቁን መድረክ ‶ከ18 ዓመት በታች የተከለከለ″ ስንል እንገድበው፡፡

እስቲ ቅኝቱን ከኮረጅናቸው የምዕራብ አገሮች በአንዱ የተከታተልኩትን ታሪክ ላውጋችሁ፡፡ የዛሬ ሰባት ዓመት አካባቢ በእንግሊዝ አገር በቶኒ ብሌር የሚመራውና አገሪቱን የሚመራው ሌበር ፓርቲ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርንና የአሸባሪዎችን እንቅስቃሴ ይቆጣጠራል የተባለለትን አዲስ የመታወቂያ ካርድ ይፋ አደረገ፡፡ ይህን በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆት የተቸረውን ፈጠራ የአገሪቱ የኮንሰርቫቲቭ (ተቃዋሚ) ፓርቲ መሪ ማይክል ሆዋርድ በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው መልካምነቱን አፀኑ፡፡ ከመግለጫቸው በኋላ ግን (የገዥውን ፓርቲ ሥራ በመደገፋቸው) ከፍተኛ ተቃውሞ ከፓርቲያቸው አመራርና ደጋፊዎቻቸው ገጠማቸው፡፡ በሁኔታው ግራ የተጋቡት የተቃዋሚ ፓርቲው መሪ ዳግም በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው እንዲህ ሲሉ ሙግታቸውን ቀጠሉ፡፡ ‶ስሜ ተቃዋሚ ፓርቲ ስለሆነ የገዥውን ፓርቲ መልካሙንም ሥራ ጨምሬ መቃወም አለብኝ ወይ?″ ከዓመት በኋላ በተደረገው የእንግሊዝ ምርጫ የእኚህ በሳል ሰው አቋም ፓርቲያቸው መንበረ ሥልጣኑን እንዲረከብ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ጥላቻ ተላላፊ ነውና አለቆቹ በመገናኛ ብዙኃን ሲሰዳደቡ ያየ የመንደር ካድሬ ቡጢ ቢጨባበጥ ምን ያስደንቃል?  በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት አንዱ ሌላውን እንደ ባንዳ በመቁጠር አከርካሪውን ለመስበር የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ተጨማሪ የቤት ሥራ፡፡ ታዲያ እንደ አዋጭ የፖለቲካ ሥርዓት ያስተናገድነው የገዢ ተቃዋሚ ቅኝት ለአገራችን አበጀ ወይስ አፋጀ? እንደኔ እንደኔ  በዴሞክራሲና በመናገር ነፃነት መልካም እሴቶች ተቀላቅሎ ያደገ አረም ነውና በጊዜ እንንቀለው፡፡ ጥምር መንግሥት ለመመሥረት የሚረዳ ብስለትን እንኳን ቢያጡ ምነው በተወሰነ ደረጃ በጥምረት መሥራትና መቀባበል ተሳናቸው?

ከባህላችን፣ ከታሪካችን፣ ከእምነታችንና ከዘመናዊነታችንም አኳያ ለብዙ ዓለም ተምሳሌት የሚሆን የአስተዳደር ቅኝት ብንከተልስ?

 1. ተቃዋሚ ፓርቲ ከሚለው ይልቅ ድጋፍ ሰጪ (አጋር) ፓርቲ ተብለው ቢሰየሙ፣
 2. ስለሌላው ፓርቲ የምንሰጠው አስተያየት ቢያንስ ሲሶው አዎንታዊ/ብርታት ቢሆን፣
 3. አስተያየትን፣ አቋምንና ግለሰብን በመለየት አስተያየትን ወይም አቋምን ልንቃወም ብንችልም ግለሰቦችን ግን የመውደድና የማክበር ዝንባሌ ቢኖረን፣
 4. የፓለቲካ መሪዎች (በገዥውም ሆነ ተቃዋሚ) ተቀባይነት ባላቸው የብቃት መመዘኛዎች ፈቃድ ቢሰጣቸውና የዕድሜ ገደብ ቢኖራቸው፣
 5. የትኛውንም የፓለቲካ ፓርቲ ሳይወግኑ በመሥሪያ ቤትና በአካባቢ እንዲሁም በሌሎች የአመራር መድረኮች አገራቸውን በአስተዳደር ለማገልገል ለሚወዱ በቂ ዕድል ቢመቻች፣
 6. የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ ወይም ተለዋጭ ሐሳብ በበቂ መረጃ የተደገፈ ብቻ ቢሆን፣ በበቂ ማስረጃ ወይም በሳይንሳዊ ጥናት ያልተደገፈ ነቀፌታ በስም ማጥፋት ወንጀል ቢያስጠይቅ፣
 7. ሌሎችን እያጥላሉ ራስን እንደ ብቸኛ የሰላምና የልማት መንገድ ማቅረብ እንደ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ቢፈረጅ፣ ይህ በንግድ ማስታወቂያ ሕግ እንኳን አይፈቀድም፣
 8. ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጠቃሚ ግብዓቶችና ጠባቂ ባልንጀሮች እንደሆኑ በመረዳት ቢያጠናክራቸውና በበቂ ቢያሳትፋቸው፣ ተቃዋሚዎችም በሕዝብ እንደተመረጠ የጊዜው ባለአደራ ተገቢ አክብሮትን በመቸር አጋርነታቸውን ለገዥው ፓርቲ በቃልና በሥራ ቢገልጡ፣
 9. በአጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱ ስድብና ውሸት ለማንችልና እምነትና ብስለታችን ይህን ለማይፈቅድልን ጋባዥ ቢሆን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...