በሒሩት ደበበ
ስለሙስናም ሆነ የመልካም አስተዳደር እጦት ወይም ፀረ ዴሞክራሲያዊነት መነጋገር ጤናማነት ነው፡፡ለአገር ግንባታም ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር ስለልማትና ሰላም ከመወያየትም በላይ ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ባይገባኝም የመንግሥት የትኩረት ከፍታ ነጥብ ግን አልሆነም፡፡ በቅርቡ በዚሁ ጋዜጣ ላይ አንድ ጸሐፊ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ አስተዳደር የሙስና ገጽታዎች ላይ ያነሷቸውን አንዳንድ የመወያያ ነጥቦች ጠቃቅሰው ያቀረቡትን ጽሑፍ ተመልክቸዋለሁ፡፡
በእውነቱ ጸሐፊው አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት መልካም ጥረቶችና የአገሪቱን ጅምር ተስፋዎች ዕውቅና መስጠታቸው ተገቢ ነው፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ሆይ!›› እያሉ ከልብ ያቀረቧቸውን ምክረ ሐሳቦችም ቢሆን የምጋራቸው ናቸው፡፡ ሁላችንም በቅንነት በአገራችን ጉዳይ ላይ ያገባኛል ብለን ከተነሳን ሥጋት ቅሬታችንንም ሆነ ጥርጣሬያችንን መተንፈስና ‹‹የሰሚ ያለህ!›› ማለት ያለብን እንደዚህ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ሙስና ደግሞ የሁላችንንም ጓዳ የሚበረብርና ‹‹ተደብቆ ቢፈጸምም ሕዝቡ የሚያውቀው›› ስለሆነ አጀንዳ ሊሆን ግድ ነው፡፡
በእኔ በኩል ለዛሬ ማንሳት የፈለግኩት የሙስና ትግሉን ይበልጥ ለማቀጣጠል ሕዝብና መንግሥት ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ስለምላቸው ነጥቦች ነው፡፡ በዚሁ መሠረት የሌሎች አገሮችንም የፀረ ሙስና አካሄድ ለመጠቃቀስ ተሞክሯል፡፡
ዘራፊዎችን መቅጣትና ማጋለጥ
በዓለም የተለያዩ አገሮች የፀረ ሙስና ትግሉ አንድ ዓይነት ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በአንዳንዱ አካባቢ ጠንከር ያለ ሲሆን በሌላው ላላ ይላል፡፡ በአገራችን ዕድገቱም ሆነ ሙስናው ይበልጥ እየታየ የመጣው አሁን እንደመሆኑ መጠን፣ ባለፉት 12 ዓመታት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቋቁሞ ትግል በመደረግ ላይ ነው፡፡
እስካሁን በአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና መከላከያ ሚኒስትር ደረጃ በደረሱ ሰዎች ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ የከተማ ከንቲባዎች፣ የክልል ቢሮ ኃላፊዎችና እንዲሁም የዞንና የወረዳ ሥራ አመራሮች ላይ የቅጣት ዕርምጃ ሲወሰድ ታይቷል፡፡ ከመንግሥት መዋቅሩ ውጪም እንደ ባንክና ኢንሹራንስ ባሉ ዘርፎች፣ ባለሀብቶች የፀጥታና የፖሊስ አባላት ደረጃ የሙስና ወንጀል ፈጽመው ወንጀሉ በመረጋገጡ እንዲቀጡ መደረጋቸው ታይቷል፡፡ የፌዴራሉም ሆነ የክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽኖች አሁንም የተለያዩ ጉዳዮችን በመመርመር አስፈላጊውን ሕጋዊ ዕርምጃ ለማስወሰድ እንደሚንቀሳቀሱም ይታያል፡፡
በዚህ ረገድ የሚታየው ክፍተት አንደኛው የፍርድ መዘግየት ነው፡፡ ሕዝብ ‹‹እገሌ ሌባ ነው፣ ይህን ሁሉ ሀብት ከየት አመጣው? ከጀርባው እገሌና እነእገሌ አሉ፤›› ብሎ በተጨባጭ መረጃ ይናገራል፡፡ የተከማቸው ሀብትም የሕዝብ ገንዘብ መሆኑን በተለያዩ ማረጋገጫዎች ለማሳየት ይታትራል፡፡ ምናልባት ከመኖር ዋስትና አኳያ ደፍሮ ነገሩን አደባባይ ለማውጣት ቢቸገርም በኮንትሮባንድ ማጭበርበር፣ በወጪና ገቢ ምርት ቅሸባ፣ በታክስ ማጭበርበርም ሆነ በመሬት ሽያጭ ውስጥ እየተሳተፈ ያለው ሙሰኛ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በዚያው ልክ በተቆርቋሪነት ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ጥቆማና መረጃ ለመስጠት የሚሞክሩም አሉ፡፡ ግን ክሱ ከመታየቱ ባሻገር ምርመራውም የውኃ ሽታ ሲሆን ይስተዋላል፡፡
በጥልቅ ምርመራ ከሚጋለጡ የሙስና ወንጀሎች ባሻገር በሕግ ውሳኔ ያገኙትን የሙስና ድርጊቶች ለሕዝብ ይፋ በማድረግ በኩል የመንግሥት መዘግየት ያለ ይመስላል፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሙስና የሥርዓቱ አደጋ መሆኑን በግልጽ የሚናገር ቢሆንም፣ በውስጡም ሆነ በውጭ ያለውን ሙሰኛ ከሥሩ ለመመንጠር እየተቸገረ ይመስላል፡፡ እነ ቻይና በልማታዊ መንግሥት ባህሪያቸው በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር የሚገመት የሕዝብ ሀብት በመዝረፍ የሚሸሸጉ ባለሥልጣናት እንዳሏቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህን ግለሰቦች ግን በምንም ተዓምር ከኮሙዩኒስት ፓርቲው ዓላማ በላይ ወይም ከሕዝብ ጥቅም አጥፊነት ነጥለው አያይዋቸውም፡፡ ባለፉት ወራት እንኳን እንደታየው ከፓርቲው ቁልፍ መሪዎችና መሥራቾች አንስቶ እስከ አገሪቱ ቱባ ቱጃሮች ድረስ፣ የዕድሜ ልክ እስርና ስቅላት የሚደርስ የሙስና ወንጀል ፍርድ ሰጥታለች፡፡ ይህንንም ቻይናውያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም እንዲያውቀው ሆኗል፡፡ ከቻይና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ባህሪና የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ክፍተት አኳያ ግድያው እንኳን ቢቀር አሳማኝና የማያዳግም ዕርምጃ በእኛም አገር ሊሰፋ የግድ ነው፡፡
ወርቅን በጥፍጥፍ ብረት ለውጦ፣ ከደሃ ሕዝብ ጉሮሮ ላይ የተሰበሰበን ገንዘብ በዓለም አቀፍ ግዥ መዝብሮ፣ ከብዙኃኑ ጥቅም እየነጠቀ መሬት በመቸብቸቡ መቶ ሚሊዮኖችን ሰብስቦ በየዘመዱ ስም የቀበረን ወንጀለኛ ‹‹በአመክሮ›› ሰበብ በጥቂት ዓመታት ከእስር መልቀቅ ‹‹እነ እገሌ ምን ሆኑ?›› ማለትን ያስከትላል፡፡ በሌላ በኩል በአንዳንድ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች የሙስና ወንጀልና መጠርጠር ላይ የሚወሰደው ‹‹ፖለቲካዊ›› ዕርምጃም መታየት ያለበት ነው፡፡
አማራ ክልል የሰረቀ አዲስ አበባ፣ አዲስ አበባ የዘረፈ ኦሮሚያ ወይም ትግራይ የሚመደብበት አካሄድ አለ፡፡ በፍርድ ቤት ተከሶ፣ በመገናኛ ብዙኃን ድርጊቱ ተገልጾ ስሙ ከጠፋና ወንጀሉን ሕዝብ ካወቀው በኋላ ቅጣትና እስር ሲጠብቅ ከኃላፊነቱ ተነሳ፣ የእገሌ አማካሪ ሆነ ወይም እዚህ ክልል ተመደበ የሚለው ዜና ሕዝብን ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ወንጀሉ በሕዝብ ጥቅም ላይ የተፈጸመ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ በመረጃና ማስረጃ ካልተረጋገጠ እንኳን እውነታው ለሕዝብ ተገልጾ ግለሰቡ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፡፡ ጥፋቱም ዝቅተኛ ከሆነ ሳይሸፋፈን ለሕዝብ ሊገለጽ ይገባዋል፡፡
የተነጠቀን የሕዝብ ሀብት ማስመለስ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃን ጠቅሶ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባቀረበው ጽሑፍ ዓለማችን በሙስና ከ2.6 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ታጣለች፡፡ ለደሃው የኅብረተሰብ ክፍል መዋል ከሚገባው ሀብት ውስጥም በዓመት አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በጉቦ መልክ ይባክናል፡፡ በእርግጥ ይህ ሀብት ከአኅጉር አኅጉር የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ በአፍሪካ ከ148 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲመዘበር፣ በአውሮፓ ደግሞ 120 ሚሊዮን ፓውንድ ይመዘበራል፡፡
በአገራችንም በየዓመቱ በሙስና የሚበላውና የሚባክነው ገንዘብ በጥልቅ ጥናት ባይረጋገጥም፣ ካለን ኢኮኖሚና ከሕዝቡ ድህነት አንፃር ከፍተኛ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሕዝቡን በማሳተፍ በሙስና ላይ መራራ ትግል ከማድረግ ባሻገር የተመዘበረን ሀብት ተጠናክሮ ማስመለስ ግድ ይለዋል፡፡
እንደ ኮሚሽኑ የቅርብ መረጃ በያዝነው ዓመት ብቻ ከሙስና ወንጀሎች ወደ መንግሥት የተመለሱ ሀብቶችን ይፋ አድርጓል፡፡ አንደኛው በኅዳር 2000 ዓ.ም. ብሔራዊ ባንክን በማጭበርበር ወርቅን በጥፍጥፍ ብረት የለወጡ ወንጀለኞች ሀብት ነው፡፡ ወንጀለኞቹ በ2004 ዓ.ም. 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና 180 ሺሕ ብር የሚደርስ ቅጣት ከማግኘታቸው ባሻገር፣ ከወራት በፊት በተለያዩ ባንኮች የሚገኝ ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ፣ 81,422 ግራም ወርቅ፣ የተለያዩ ድርጅቶችና የመኪና ዕቃ መለዋወጫ በሐራጅ ተሽጠው ገንዘቡ በወንጀል ድርጊቱ ለተጎዳው ብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ በጥቅሉ በዚህ ዓመት 78 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ፣ 26,044 ካሬ ሜትር መሬት፣ ሦስት ተሽከርካሪዎች፣ አራት ቪላ፣ ባለፎቅ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች ከሙሰኞች እጅ ወደ መንግሥት ገቢ ተደርገዋል፡፡፡
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት 1993 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. አጋማሽ በ13 ዓመታት ውስጥ በሙስና ተዘርፎ ተመላሽ የተደረገውንም ይፋ አድርጓል፡፡ 704,409 ካሬ ሜትር የከተማ መሬት (በዝቅተኛው የሊዝ ዋጋ ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ)፣ ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ፣ 34 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው ተሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎች፣ 15 ቪላዎችና ሕንፃዎች፣ ከዘጠኝ የሚበልጡ የንግድ ድርጅቶችና ሌሎችም ይገኙበታል ሲል ያብራራል፡፡
በአገሪቱ ከከፍተኛ ሙስና ይልቅ አነስተኛ ሙስና (Petty Corruption) ሰፊ ሽፋን እንዳለው ይነገራል፡፡ ብዙዎቹ በአነስተኛ የመንግሥት ደመወዝ የሚተዳደሩ ሰዎች ይኼንን ከየት አመጡ? ተብሎ ቢጠየቅ፣ ‹‹ከዚህ›› ሊባሉ የማይችሉ ሰዎች የናጠጠ ሀብታም አኗኗር የጀመሩት ያለጥርጥር በሙስናና በሕዝብ ሀብት ነው፡፡ የሕገወጥ ደላሎች፣ ጉዳይ ገዳዮችና የባንክ ውስጥ ዘራፊዎች ሀብት ሁሉ በላብ ብቻ የተገኘ ነው? ለማለት ያዳግታል፡፡ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት የሥራ ኃላፊነትና በዕርዳታ ተቀባይ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩም ሙስናን የሀብት ማፍሪያ አድርገው ታይተዋል፡፡ ከገቢዎችና ጉምሩክ አሠራር ጋር በተያያዘ የታክስ ማጭበርበርና የጉምሩክ አሻጥር ያከበራቸው እንዳሉም በግልጽ ይታወቃል፡፡ የእነዚህን የወንጀል ተጠርጣሪዎች ሀብት ብድግ ብሎ መውረስ ሊታሰብ አይገባም፡፡ መሆንም የለበትም፡፡
ነገር ግን ማንም ይሁን ማን የሕዝብ ሀብት ዘርፎ እየተንደላቀቀ መኖር እንደማይችል እንዲያውቅ መደረግ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የባለሥልጣናትና የተሿሚዎች የሀብት ምዝገባ ሥርዓቱና የንግድና ኢንቨስትመንት ጤናማ ገቢ ማረጋገጫ አሠራሩን በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ በሙስና የተመዘበረን ሀብት የማስመለሱ ሥራ በሌላውም አገር ቢሆን ከፍተኛ ፈተና ያለበት ነው፡፡ ለምሳሌ በዓለማችን በሙስና ምክንያት የሚባክነውን ሀብት ያህል ተመጣጣኝ ሀብት ማስመለስ እምብዛም ውጤቱ ጎልቶ የሚታይ እንዳልሆነ ‹‹Organization for Economic Cooperation Development›› የተሰኘው ድርጅት አረጋግጧል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 በወጣው መረጃ በሁለት ዓመት ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከተዘረፈባቸው አገሮች ሊመለስ የቻለው 174 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው ብሏል፡፡
ለዚህ ችግር እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ ከሙስና ወንጀሉ ውስብስብነትና ልዩ ባህሪ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ሙስና የሚፈጸመው ዕውቀት፣ ሥልጣንና ገንዘብ ባላቸው ሰዎች በመሆኑ ድርጊቱን ሲያድበሰብሰው ይታያል፡፡ ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ሙስናን ተሸክሞና እያባበሉ መሄድ ስለማይቻል፣ አስፈጻሚውም ሆነ ሕግ ተርጓሚው ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ በሙሰኞች ስም ተይዘው በፍርድ ቤት ውሳኔ መዘግየት ምክንያት በየቦታው በጅምር የቀሩ ሕንፃዎች፣ ታጥረው የተያዙ ቦታዎች፣ ለብልሽት የተጋለጡ ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ሁሉ ፈጣን መፍትሔ ማግኘት አለባቸው፡፡
የድርጊቱን ፀያፍነት በተግባር ማሳየት
የሙስና ዋነኛ ሠሪውም ሆነ ተከላካዩ መንግሥታዊ መዋቅሩ ነው፡፡ የእኛ አገር ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አንፃር ሲነፃፀር የከፋ ሙስና የሚፈጸምባት አይደለችም፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም በአንፃራዊነት የተሻለ የዲሲፕሊንና የዕርምት አካሄድ እንዳለው ማረጋገጥ የሚቻለው የውጭ ባለሀብቶች፣ የዕርዳታ ድርጅቶችና የአንዳንድ አገሮችን አምባሳደሮችን አስተያየት መስማት ሲቻል ነው፡፡ ያም ሆኖ የሙስናን አስከፊነት አምርሮ የሚታገልና ጠንካራ አብዮተኛ መሪና ተከታዮች ገና ማስፈለጉ ላይ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ከላይኛው ፖሊሲ አውጪ አካል እስከ ታችኛው የሕዝብ አገልግሎት ሰጪው ድረስ ሙስናን በተግባር መፀየፍ፣ ሕዝብ ሲጠቀም እጠቀማለሁ ማለትና ተገልጋይን ማስቀደም ይገባል፡፡ በድህነት ውስጥ የኖርን ሕዝቦች እንደ መሆናችን መጠን በአገልግሎት አሰጣጥም ሆነ በምርት አቅርቦት ፍላጎትን ሊያሟላ የሚችል ሀብትና አሠራር ላይኖር ይችላል፡፡ ይህ እውነታ እየታወቀና በጊዜ ሒደት መፈታቱ እንደማይቀር እየታመነ፣ ዜጎች መብታቸውን በገንዘብ እንዲገዙ ማስገደድና ማባበል አደገኛ አካሄድ ነው፡፡
ይህን ችግር በኤሌክትሪክ ኃይል፣ በመጠጥ ውኃ፣ በስኳርና በዘይት አቅራቢዎች እያየን ነው፡፡ ከተገልጋዩ ብዛት አንፃር ‹‹ቅድሚያ›› በመስጠት ስም ንግድ ፈቃድ ለማውጣትና ለማደስ፣ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት፣ የተሽከርካሪ ቦሎና ዓመታዊ ግብር ዓይነቶቹ መንግሥታዊ አገልግሎቶችም ጉቦ የሚጠየቅባቸው ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ግብር ለማስተመን፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሽን ለማስገጠም ወይም የትኛውንም የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት መብትንም ብቻ ሳይሆን ግዴታንም በገንዘብ መግዛት መታየቱ፣ የሙስናን መበርታትና የተሿሚዎችን ችላ ባይነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
አንዳንዶች ከሰው በልጠው ለመታየት በመስገብገብ ሕገወጥ የመሬት ካርታና የተጭበረበረ የይዞታ ማረጋገጫን በሙስና እንዲሠራ ጥፋትን ያስተምራሉ፡፡ የፋብሪካ ምርትን ቀድሞ ለማግኘት፣ የባንክ ብድርን በፍጥነት ለማስጨረስ ሕጋዊ በሚመስል ጉቦ (በኮሚሽን የተጀቦነ ማጭበርበር) ፍትሐዊውን አካሄድ ያደፈርሳሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ በተተመነ ኮሚሽን በመግዛትና በመሸጥ ችግር የሚፈጥሩ አሉ፡፡ ለእነዚህና በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶች መባባስ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ደግሞ ደላሎችና ሕገወጥ ‹‹ጉዳይ ገዳዮች›› ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ ‹ጉዳይ ገዳይ› የሚባሉት አንዳንድ የሙስና አቀባባዮች ቀደም ሲል ስለመሥሪያ ቤቱ በቂ መረጃ ያላቸው ውሳኔና ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ ኃላፊዎችን የያዙ (የሚያውቁ) ናቸው፡፡ ሕጋዊውንም ሆነ ሕገወጡን አሠራር በጥልቀት ለይተው፣ ማምለጫ አበጅተው የሙስና ወንጀሉ እዲወሳሰብም ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነት ወገኖች ‹‹ትራንዚተር››ን በመሰሉ ከሕጋዊነት ይልቅ ኢሕጋዊነት የሚቀናቸው የሥራ መስኮችም ይሰማራሉ፡፡
በአጠቃላይ የሙስናን ሕገወጥነት ተገንዝቦ አገርንና ሕዝብ እንዳይበተን የማድረግ ኃላፊነት በዋናነት የመንግሥት ነው፡፡ በመቀጠልም ሕዝቡ ‹‹ሲሾም ያልበላን …›› ትቶ መብቱን ለማስከበር መታገል አለበት፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማትና መገናኛ ብዙኃን ሥነ ምግባርና ሞራል ያለው ትውልድ እንዲቀረፅ፣ ሌብነት፣ ሙስናና ምዝበራ እንዲወገድ አልመው ሊሠሩ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ፖለቲከኞች (ሁሉም) ምሁራን፣ ተመራማሪዎችም ፊት ለፊት ወጥተው የሚታገሉ መሆን አለባቸው፡፡ የሙስናን ወንጀል በጋራ ለመታገል ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብቻ ሳይሆን፣ በዋና ዋና የትግል ሥልቶች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል መባሉም ለዚሁ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊዋን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡