በበሪሁን ተሻለ
ኢትዮጵያ ረዥም የነፃነት ታሪክ ያላት አገር ናት፡፡ በዓለም ጥንታዊነት ካላቸው ጥቂት አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በአገሪቷ የረዥም ዘመን ማለትም የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ የተጻፈ ሕገ መንግሥት ባለቤት የሆነቸው ገና ከ84 ዓመት ወዲህ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እምነትና ከ59 ዓመት በፊት 25ኛው ዓመት የዘውድ በዓል ኢዮቤልዩ በተከበረበት በጥቅምት 23 ቀን 1948 ዓ.ም. በፓርላሜንት በተናገሩት የዙፋን ቃል መሠረት፣ “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዘመናዊ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት የሚያሰኘው አስተዳደር የተመሠረተው የዛሬ [84 ዓመት] ይጠቅማል ብለን ያደራጀነውን ሕገ መንግሥት በሰጠን ጊዜ ነው፡፡”
እስከ 1966 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ያገለገለውና የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሥልጣን ሲይዝ የታገደው፣ የ1948 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሁለተኛው የተጻፈ ሕገ መንግሥት “የተሰጠው” እና የፀናው ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ 25ተኛውን የዘውድ በዓላቸውን ባከበሩበት ወቅትና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ “በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ውስጥ ያልተደረገውን በፈቃዳችን ለተወደደው ሕዝባችን ሕገ መንግሥት ከሰጠነው ይኸው ዛሬ 24 ዓመት ሆነ፤” ያሉትም ያን ጊዜ ነው፡፡
ምርጫ የተጀመረውም በዚሁ የ1948 ዓ.ም. የተሻሻለው ሕገ መንግሥት መሠረት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከፀናበት ከጥቅምት 24 ቀን 1948 ዓ.ም. ጀምሮ ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በምርጫው ሕግ መሠረት የሕግ መምርያ ምክር ቤት አባላት መጀመሪያው ምርጫ ይፈጸማል በተባለው መሠረት፣ በአገሪቷ የሦስት ሺሕ ዘመን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ምርጫ በ1949 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ተደረገ፡፡ የ18 ሚሊዮን ሕዝብ አገሯ ኢትዮጵያ የወቅቱ የመራጭ ሕዝብ ቁጥሯ አምስት ሚሊዮን ይሆናል ተብሎ የተገመተ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 3,015,260 ድምፅ ሰጪዎች ከ491 ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል 210 እንደራሴዎችን መርጠዋል፡፡
በ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥትና በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን አምስተኛውና የመጨረሻው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ የተካሄደው በ1965 ዓ.ም. ነበር፡፡ በ1965 ዓ.ም. በአምስተኛው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ የተመረጡት 220 እንደራሴዎች መደበኛውን ሥራቸውን የጀመሩት፣ በ1966 ዓ.ም. የቀድሞው ፓርላሜንት መደበኛ የጉባዔ ወራት ከሚጀመርበት ከጥቅምት 23 ቀን 1966 ዓ.ም. ጀምሮ ቢሆንም፣ የእነሱም ዕጣ ፋንታ ሆነ የአገሪቷ የምርጫና የዴሞክራሲ ነገር ከወታደራዊው መንግሥት ሥልጣን መያዝ፣ ከሕገ መንግሥቱ መታገድና ከፓርላሜንቱ መበተን ጋር አብሮ አበቃ፡፡
የ1965 ዓ.ም. አምስተኛ የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ አሁን እንደገና ከአንድ ጀምረን የቆጠርነውና አምስት ያልነው ምርጫ ባህል እንደ አዲስ እስከ ተጀመረበት እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ድረስ፣ የኋሊት ዞር ብለው የሚያስታውሱት የመጨረሻው የአገር ምርጫ ነበር፡፡
በ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የተካሄዱት ምርጫዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ያስመዘግቡት የነበረው፣ በተለይ የምርጫ ተቋማትንና ታህታይ መዋቅራትን የተመለከተ ለውጥ የሚያስቆጭም የሚያስደምም ገጽታ ነበረበት፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የምርጫ ዓመት በመጣ ቁጥር ለመራጭነት ተመዝገቡ አልልም፣ የመራጮች ቋሚ መዝገብ ይኖረኛል ብላ የወሰነችው ከ1961 ዓ.ም. የምርጫ ዓመት ጀምሮ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት በመራጭነት መመዝገብ ቋሚ ሆነ፡፡ አንዴ የተመዘገበ ሰው እንደገና ለመመዝገብ ሳይገደድ ወደፊት በሚደረጉት ምርጫዎች ሁሉ ድምፅ እንዲሰጥ ለተመዝጋቢው ሰው መብት የሚሰጥ አሠራር ዘረጋች፡፡ ጉዞው በዚያ አጭር ጊዜ ውስጥም ይህን የመሰለ የማይናቅ ዕርምጃ ያስመዘገበ ነበር፡፡
ደርግ ምርጫ ብሎ የተጫወተባቸው፣ ለ17 ዓመት የኖርንባቸውንና እንዴት እንደሚወጠወጡ አሳምረን የምናውቃቸውን፣ ገና ከርቀት በጠረን ብቻ የምንለያቸውን የምርጫ ቴአትሮች የሚመረቱበትን ገጠመኝ አልፈንና ተራምደን፣ ወደ 1983 ዓ.ም. ስንገባ ቅድሚያ የምናገኘው የሽግግር ወቅት ቻርተሩን ነው፡፡
ቻርተሩ “ኢትዮጵያን ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲገዛ የቆየው የወታደራዊ አምባገነን መንግሥት መገርሰስ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና መንግሥቱን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደ አዲስ ለመገንባት የሚችልበትን ዕድል የከፈተ ታሪካዊ ወቅት ነው፤” ነው ብሎ ይጀምራል፡፡ የሽግግር ወቅት ፕሮግራም ይዘረጋል፡፡ የሽግግሩን ፕሮግራም መሠረታዊ ግቦችም ሕገ መንግሥት አርቅቆ/አስረቅቆ የሚያፀድቅ ሕገ መንግሥታዊ ጉባዔ መጥራት፣ በፀደቀው ሕገ መንግሥት መሠረት ምርጫ ማካሄድና መንግሥት መመሥረት፣ ለዚህም ሁሉ ስኬት መሠረታዊና መነሻ የዴሞክራሲ ሁኔታዎችን በሥፍራና በቦታቸው ማደላደል ሆነ፡፡
ሕገ መንግሥቱም በብዛትና በስፋት ዋስትና ስላለው ዴሞክራሲ ይናገራል፡፡ “ሕገ መንግሥቱ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል” በማለት ገና ከአንቀጽ አንድ በኢትዮጵያ መንግሥት ስያሜ ይጀምራል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝመር የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ራሱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት ማንፀባረቅ አለበት ይላል፡፡ የሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ መርሆዎች የሚዘረዝረው ምዕራፍ ከሁሉም አስቀድሞና ግንባር ቀደም አድርጎ የሚደነግገው የሕዝብ ሉዓላዊነትን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችን ይወስናል፡፡ ሕገ መንግሥቱም የእነሱ የሉዓላዊነታቸው መግለጫ ነው፡፡ ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ነው ይላል፡፡ የምርጫ መብትንም ይደነግጋል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል በምርጫ የሚቋቋመው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን፣ ተጠሪነቱም ለአገሪቱ ሕዝብ እንደሆነ ይጠቁማል፡፡ እንዲህ እያልን አገራችንንና መንግሥቷን በአገርና በዓለም አቀፍ ሕግና ወግ መሠረት እያደራጀንና እያበጀን መንገዱን ተያይዘነዋል አልን፡፡
በዚህ መካከል ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከገዥው ፓርቲ በተለይና በዋነኛነት ከሕወሓት መከፋፈል፣ ከሁለተኛው የ1992 ዓ.ም. አገራዊ ምርጫ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የፖሊሲና የስትራቴጂ ሰነዶች በሰፊው ተሰራጩ፣ መወያያም ሆኑ፡፡ በእነዚህ የፖሊሲ ሰነዶች ላይ የተመሠረተ ነው የተባለውና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሳስ 9 ቀን ያፀደቀው “የኢትዮጵያ ራዕይ” ጥር 1996 ዓ.ም. ይፋ ሆነ፡፡
በፌዴራል መንግሥት በልዩ ልዩ ሰነዶች በሰፊው የቀረበና የተብራራ እንደሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስረግጦ የሚመሰክርለት “ከ20 እስከ 30 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ የት መድረስ እንደሚገባት” በአጭሩ የሚገልጸው ምክር ቤቱ ታኅሳስ 9 ቀን 1996 ዓ.ም. ያፀደቀው የኢትዮጵያ ራዕይ፡-
በሕዝብ ተሳትፎና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት፣ ማኅበራዊ ፍትሕ የነገሠባት፣ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ያላት ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ራዕይ ይህ መሆኑን በሰርኩላር/በደብዳቤ “ያወጀው” እና ይህም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያፀደቀው ውሳኔ መሆኑን የሚገልጸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የጥር 1966 ዓ.ም. ደብዳቤ ያፀደቀውን ራዕይ በተወሰነ ደረጃ ይዘረዝራል ወይም ያብራራል፡፡
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ራዕይ በፖለቲካው መስክ፣
1ኛ) የዴሞክራሲ ባህል አብቦ የዴሞክራሲያዊ አመራር ተቋማት ተጠናክረው በሕዝብ ተሳትፎ ላይ የተመሠረተው ዴሞክራሲያችን በሕዝቡ ውስጥ ሥር የሰደደና ጠንካራ መሠረት ያለው ሥርዓት ይሆናል፡፡
2ኛ) በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለው ሕዝባዊ አንድነት የራስን ዕድል በራስ በመወሰን መብት መከበርና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ ተመሥርቶ በፀና ሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ መሠረት ላይ የተገነባ አንድነት ይሆናል፡፡
3ኛ) በሃይማኖቶች መካከል እኩልነት የተረጋገጠበት የሕዝቡ ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር ባህል ዳብሮ የማይናወጥበት ደረጃ ላይ የደረሰባት አገር ትሆናለች፡፡
4ኛ) በወንዶችና በሴቶች መካከል እኩልነት የሰፈነባት፣ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰባት አገር ትሆናለች ማለት ነው ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ራዕይ በኢኮኖሚውም መስክ በማኅበራዊና በባህላዊ ዕድገቷ ምን ማለት እንደሆነም በአጭሩ ተብራርቷል፡፡ እናም “በሕዝብ ተሳትፎና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና መልካም አስተዳደር የሰፈነባት … ኢትዮጵያን እውን ማድረግ” (በፖለቲካው መስክ) የኢትዮጵያ ራዕይ ነው፡፡
ይህን ራዕይ ያለምነው በ1996 ዓ.ም. ነው፡፡ ምርጫ 97 ዋዜማ ላይ ሆነን ነው፡፡ አሁን ደግሞ ግንቦት 2007 ላይ እንገናኛለን፡፡ እንዲያውም ምርጫ 2007 ውስጥ ከዚያም በላይ በድምፅ መስጫው ዕለት ላይ ነን፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ ይህን ጽሑፌን ካስተናገደልኝ፣ ጋዜጣው ጋዜጣ ሆኖ በዕለተ ቀኑ ከወጣ ጋዜጣው በዛሬው ዕትሙ በመራጮች የድምፅ አሰጣጥ ባህርይ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ከሚችሉ ይዘቶች እንዲቆጠቡ በሕግ ይገደዳል፡፡ በዚህ ምክንያት ለዘወትር ከምንለውና ከሚፈቅድልን “ክፉና ደግ” እንቆጠባለን፡፡
ዛሬ የድምፅ ሰጪው ቀን ነው፡፡ የመራጭነት ምዝገባ ካርዱን የያዘው መራጭ ቀን ነው፡፡ ስታትስቲክሱ ከ36.8 ሚሊዮን በላይ ይሆናል የሚለው ይህ የመራጭነት ምዝገባ ካርድ የያዘው ሕዝብ አነሰም በዛም አረረም መረረም እስካሁን የሰማውን ሰምቷል፡፡ እስከ ሐሙስ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. አመሻሽ ድረስ ሁለመናው ጆሮ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ አሁን የእሱ የማሰቢያና የማሰላሰያ ጊዜ ነው፡፡ ለምን ቢሉ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመምረጥ መብቱን ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ወይም እንቅፋት እንዳያደርግበት የማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው ሚዲያዎችም ጭምር በመሆናቸው ነው፡፡
ከዚህ የበለጠም ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ኢትዮጵያ ያወጀችው የምርጫ ሥነ ምግባር መሠረታዊ የመርህ ድንጋጌ በመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ሥርዓት የሚመረጥ መንግሥት ሕጋዊነት (ተቀባይነት) ወይም (ሌጀትማሲ) ከሚመሠረትባቸው ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ፣ መራጮች በነፃነት ያለምንም ጣልቃ ገብነት፣ ያለፍርኃት፣ ያለተፅዕኖ፣ ያለጫና ወይም ከመደለያና ከጉቦ ነፃ ሆነው ድምፅ መስጠት ሲችሉ ነው፡፡
ሕገ መንግሥቱ ምርጫዎች ሁሉ አቀፍ በእኩልነት ላይ የተመሠረተና በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልጽበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት ይላል፡፡ የምርጫ ሕጉም ይህንኑ ይደነግጋል፡፡ የድምፅ መስጫ ክፍል የሚዘጋጀው፣ የድምፅ መስጫ ክፍሉም ከማንም ዕይታ የሚሰወረው በሚስጥር ድምፅ የመስጠት መብት የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ትክል ባህሪይ በመሆኑ ነው፡፡
ብዙዎች ሰው የሚፈራው ነገር ከሌለ ‘ሚስጥር ሚስጥር’ ለምን ይላል ብለው አደባባይ ላይ የሚያቀርቡትን ክርክር፣ በየአዳራሹ በየስብሰባው አጋጣሚ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ዕቁቦች፣ ዕድሮችም፣ “ማኅበራት”፣ ቻምበሮች፣ ፌዴሬሽኖች ዩኒየኖች ውስጥ እጅህን አውጥተህ በግልጽ በአደባባይ ድምፅ የማትሰጥበት ምክንያት ምንድነው ብለው፣ የአሠራር ግልጽነት አርበኝነታቸውን ሲያውጁ መስማት የተለመደ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥቶች በመላው ዓለምና እነሱን መሠረት አድርገው የሚወጡ ሕጎች፣ በሚስጢር ድምፅ የመስጠት መብትን በእንደዚህ ያለ ብርቱ ጥንካሬና ፅኑ አቋም የሚከላከሉት ለዚህ መሠረት የሆነ መነሻ ስላለ ነው፡፡ በዓለማችን፣ በአኅጉራችን እንዲሁም በአገራችን በርካታና ስውር ማስፈራሪያዎች ስላሉ ነው፡፡
ኅብረተሰቡን በእንጀራ ገመድና በሌላ ቅጣት ማስፈራራት በሚቻልበት ባህል ውስጥ፣ የሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ መብት መከበር ወሳኝ ነው፡፡ የመራጮች በነፃነት ያለምንም ጣልቃ ገብነት፣ ያለፍርኃት፣ ያለኃፍረት ያለተፅዕኖና ያለ ጫና ድምፅ መስጠት መቻል የመምረጥ መብት ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ራዕይ ‹‹በሕዝብ ተሳትፎና በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት… ያላት ኢትዮጵያ ዕውን ማድረግ ነው፤›› ይላል፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ በነፃነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ አገራችን ውስጥ የምርጫ ድምፅና ድጋፍ ገና አልተግባቡም፡፡ ሌላ አመለካከት እንዳይወሰድብኝ ደግሞ እንዲህ ነው እንዳይሉኝ፣ ችግር እንዳይገጥመኝ፣ በእንጀራ ገመድህ መጣንብህ እንዳይሉኝ፣ እህል ውኃዬን እዳይቆርጡብኝ ተብሎ ምርጫ መውጣትና ያልወደዱትን መምረጥ አሁንም አለ፡፡ እንዲህ ያለ ምርጫ ሁሉንም ያታልላል፡፡ እንዲህ ያለ ምርጫ ለሕዝብ ድጋፍ ምስክር ተደርጎ ሲቀርብ ደግሞ ለአገር ጉዳት ያመጣል፡፡
ዛሬ ይህ ፓርቲ ከዚያ ፓርቲ ብለን ቲፎዞነት ውስጥ የምንገባበት ቀን አይደለም፡፡ ዛሬም ሆነ ነገ ማሸነፍ ያለበት ዴሞክራሲ ነው፡፡ ዴሞክራሲ እንዲያሸንፍ የጨዋታው ሕጎች በሁሉም ተጫዋቾች በሁሉም አጫዋች ኃይሎች ዘንድ መከበር አለባቸው፡፡ የምርጫው ዴሞክራሲያዊነት እንዳይጓደል ማንም በጨዋታው ውስጥ አፍራለሁ እንዳይልና ሰበብ እንዳያገኝ፣ የሙሉ ጊዜ ሥራቸው አድርገው መሥራት አለባቸው፡፡
ዛሬም ሆነ ነገ ወይም በዚህ ሳምንት ውስጥ አሸናፈውን የመግለጽ ሥልጣን ያለው ምርጫ አስፈጻሚው የሥልጣን አካል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች አፍ፣ አመልና ሚዲያ መፆም አለበት፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይህንን ሕግ ማስከበሩን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ መላው ኢትዮጵያ ይህ መሆኑን እየታዘበ ነው፡፡ ሌላው ቢቀርና ቢያንስ ቢያንስ ከ36.8 ሚሊዮን በላይ የመራጭነት ምዝገባ ካርድ የወሰደ ሕዝብ የየገዛ ራሱና የየአካባቢው የነፍስ ወከፍ ምስክር ነው፡፡ ይህን ያህል ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ መረጠ ማለትም እያንዳንዱ ሰው የኢትዮጵያ ምርጫ ነቃሽ ነው ማለት ነው፡፡ እናም ሕዝቡ ከላይ በሰማይ ከታች በምድርም፣ በውስጥም በውጭም ሲያየውና ሲታዘበው የሚውለው ምርጫ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡