Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአንድ ምርጫ ተቀባይነትና ዴሞክራሲያዊ ጥራት ከምርጫው በፊት ዜጎች እየተጠቀሙበት ባለው ነፃነት ላይ ይመረኮዛል››

ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ፣ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት

ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ሄሴቦን የሕገ መንግሥት ኤክስፐርት ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ በምርጫ ሕግ፣ በሚዲያ ሕግና በሕገ መንግሥት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ ዶ/ር ጌድዮን የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፣ የማስተርስና የሦስተኛ ዲግሪ (ዶክትሬት) ትምህርታቸውን የተከታተሉት ሀንጋሪ በሚገኘው ሴንትራል ዩሮፒያን ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ በቅርቡ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበርና በኢትዮጵያ ወጣት የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በጋራ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ ላይ ባተኮረው የፓናል ውይይት የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ ላይ ንፅፅራዊ ጥናት አቅርበው ነበር፡፡ ሰለሞን ጐሹ ባቀረቡት ጥናት፣ ባሳተሟቸው ሥራዎችና በግላዊ ምልከታቸው ዙርያና ከምርጫ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ ዶ/ር ጌድዮንን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ባቀረቡት ጥናት ላይ አንድ ምርጫ ተቀባይነት እንዲኖረው ከሚያስፈልጉ ዝቅተኛ መሥፈርቶች መካከል ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የመደራጀት መብቶች ተጠቃሽ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ የእነዚህን መብቶች ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ጌድዮን፡- የእነዚህ መብቶች አፈጻጸም ብዙ የሚቀረው ነገር አለ፡፡ ብዙ መሻሻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ኢትዮጵያ ያላት አፈጻጸም ብዙ ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ የታሰሩትና የተሰደዱት ጋዜጠኞች ብዛት ሲታይ የዚህ መብት አፈጻጸም ተሟልቷል ለማለት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ምልከታ ደግሞ እንደ ኢኮኖሚስት፣ ፍሪደም ሐውስና ሞ ኢብራሒም ባሉ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው የዴሞክራሲ ጠቋሚዎችም ድጋፍ የተቸረው ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ በኢትዮጵያ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ተፈጻሚ እየሆኑ እንዳልሆነ ይጠቁማሉ፡፡     

ሪፖርተር፡- ከ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ ቀደም ብሎ ምርጫን የተመለከቱ የሕገ መንግሥቱና ሌሎች ዝርዝር ሕጎች አንቀጾች አግባብነት ባላቸው ባለድርሻ አካላት ጥያቄ ቀርቦባቸዋል፡፡ በተለይ በተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. የተካተተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ቁጥርና መረጣ የሚደነግገው አንቀጽ አፈጻጸም አወዛጋቢ ሆኖ ነበር፡፡ ሕጉ በአንድ የምርጫ ክልል የዕጩዎች ቁጥር ከ12 እንደማይበልጥ ይደነግጋል፡፡ ከ12 በላይ ዕጩዎች ከተመዘገቡ 12ቱን ለመለየት ዕጣ ተግባራዊ እንደሚሆንም ያመለክታል፡፡ ዕጣ አወጣጡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ቅድሚያ መስጠቱ ችግር ያለበትና ኢ ሕገ መንግሥታዊ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ ዋነኛ ምክንያትዎ ምንድነው?

ዶ/ር ጌድዮን፡- በአንድ የምርጫ ክልል ለመወዳደር ከ12 ዕጩዎች በላይ ፍላጎት ካሳዩ በቀደሙት ምርጫዎች የተሻለ እንቅስቃሴና አፈጻጸም ላሳዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ሕጉ ይደነግጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በዕጣ ይለያሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ያልሞላ ከሆነ የግል ተወዳዳሪዎች በዕጣው እንዲካተቱ ይደረጋል፡፡ የተረፈ ቦታ ከሌለ የግል ተወዳዳሪዎች ዕጣው ውስጥ አይካተቱም፡፡ ለዚህ ገደብ አሳማኝ የፖሊሲ ምክንያት አለ፡፡ የግለሰቦች በምርጫው ሒደት የመሳተፍ፣ ዕጩ ሆኖ የመቅረብና የመወዳደር መብት ላይ ገደብ የሚያደርግ ድንጋጌ ነው፡፡ በዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብት ላይ ገደብ የምናደርግ ከሆነ መጠየቅ ያለብን መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የፖሊሲ መነሻው ምንድነው? ይኼ ገደብ የሚያሳካው ጥቅም ምንድነው? በፖሊሲ መነሻውና በገደቡ መካከል ምክንያታዊ ግንኙነት አለ ወይ? ገደቡ ከሚያስገኘው ጥቅም ጋር ተመጣጣኝ ነው ወይ? የመሳሰሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ገደብ ስለተደረገ ብቻ ኢ ሕገ መንግሥታዊ ነው ልንል አንችልም፡፡ የዕጩዎችን ቁጥር በ12 መገደብ ተቀባይነት ያለው የሕዝብ ጥቅምን የሚያሳካ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የዕጩዎች ቁጥር ላይ ገደብ ካልተደረገ የምርጫ ሒደቱን ለማስተዳደር ያስቸግራል፡፡ መራጩም ቢሆን የዕጩዎች ቁጥር ከ12 በላይ ከሆነ ለመምረጥ ይቸገራል፡፡

ትልቁ ጥያቄ እነዚህ 12 ዕጩዎች እንዴት መምረጥና የተቀሩትን ማግለል ይቻላል የሚለው ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕግ ፓርቲዎች ባለፉት ምርጫዎች ለነበራቸው አፈጻጸም ትኩረት ይሰጣል፡፡ በተወሰነ መልኩ ውሳኔው በዕድልም ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆኑትን አካላት የሚያገል ነው፡፡ ይኼ ምክንያታዊ አሠራር አይመስለኝም፡፡ በገደቡ ምክንያትና ገደቡ በሚፈጸምበት መንገድ መካከል ምክንያታዊ ግንኙነት የለም፡፡ በሕዝብ ተቀባይነት ያለው አዲስ ፓርቲ ቢመሠረት በዚህ አሠራር ተጎጂ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ባለው አሠራር የዚህ ፓርቲ ዕጩዎች ለምርጫ ላይቀርቡ ይችላል፡፡ ባለፉት ምርጫዎች ተሳትፎ ስለማያውቅ ወደ ምርጫው ለመግባት ያለው ብቸኛ አማራጭ ዕድል መሆኑ አሠራሩን የዘፈቀደ ያደርገዋል፡፡

በዚያ የምርጫ ክልል ውስጥ ያለውን የሕዝብ ድጋፍ ለመለካት ምክንያታዊ መንገድ መከተል ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግለሰብ ዕጩዎች በአካባቢው ባላቸው ድጋፍ መሠረት ለምርጫ እንዲቀርቡ ማድረግ ከተቻለ የዘፈቀደ አሠራሩን መቀየር ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአካባቢው ያላቸውን ድጋፍ ለማረጋገጥ የድጋፍ ፊርማ እንዲያቀርቡ ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ አሁን ያለው አሠራር በግለሰብ ዕጩዎች ላይ ያልተመጣጠነ ጫና የሚያሳድር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይኼ ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የለውም፡፡        

ሪፖርተር፡- በሥራዎችዎ ላይ ፍርድ ቤቶች በቀረቡላቸው ጉዳዮች እንዲሁም በራሳቸው ፍላጎት የፖለቲካ ፓርቲዎችን መብቶች ከማስከበር አኳያ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተጫወቱ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ይኼን ለማለት ያስቻለዎት ምንድነው?

ዶ/ር ጌድዮን፡- በመሠረቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታዎቻቸውንና ቅሬታዎቻቸውን ወደ ፍርድ ቤቶች ለመውሰድ በጣም ቸልተኛ ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ገዥው ፓርቲና መንግሥት በመብታችን ላይ ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ መስማት ግን የተለመደ ነው፡፡ በፍርድ ቤቶች ተዓማኒነትና ገለልተኝነት ላይ በጣም የወረደ ዕምነት ነው ያላቸው፡፡ ስለዚህ ባለፉት ዓመታት በጣም በጥቂት ጉዳዮች ላይ ነው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ ፍርድ ቤቶች የቀረቡት፡፡ በዚህ ምክንያት በሁኔታው ላይ ጥናት የሚያደርግ አካል ስለ ፍርድ ቤቶቹ አሠራር፣ ስለሚከተሉት መንገድ፣ ተፈጻሚ ስለሚያደርጉት ሥነ ሕግና ፍልስፍና ለመወሰን በበቂ ሁኔታ መረጃ አያገኝም፡፡ አልፎ አልፎም ዓቃቤ ሕግ በምርጫ ሒደቱ ላይ ግለሰቦች መለስተኛ የሕግ ጥሰት ሲፈጽሙ ጉዳያቸውን ለፍርድ ቤት ያቀርባል፡፡ ይሁንና በጣም ትልቅና አወዛጋቢ የሆኑ ከምርጫ ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤቶች ሲቀርቡ አይታዩም፡፡ ፍርድ ቤቶች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ነፃና ገለልተኛ ሆነው ቢወስኑ ተመራጭ ነው፡፡ ይህን ሚና እንዲጫወቱ በትክክል ነፃና ገለልተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ነፃና ገለልተኛ መስለው መታየታቸው በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፍርድ ቤቶች ገለልተኛ አይደሉም ብለው የሚያምኑ በመሆኑና ይኼን ዕምነት የያዙ በመሆናቸው፣ በዴሞክራሲ ውስጥ ፍርድ ቤቶች ሊኖራቸው በሚገባው መጠን ያህል በኢትዮጵያ ሚናቸውን እየተጫወቱ አይገኙም፡፡  

ሪፖርተር፡- ፍርድ ቤቶች ከምርጫ ጋር በተገናኙ በተለይ ለሁለት የመሰንጠቅ ውስጣዊ ልዩነትን አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጉዳዮች የሰጧቸው ውሳኔዎች አወዛጋቢ ናቸው፡፡ በቅርቡ የተሰጠውን የአንድነት ፓርቲ ውሳኔ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች ላይ ጥያቄዎች የሚነሱት ለምንድነው?

ዶ/ር ጌድዮን፡-  በአንድ ፓርቲ ጥላ ሥር የነበሩና ወደ ግጭት ውስጥ ገብተው እርስ በርስ ሲወቃቀሱና አንዳቸው ሌላቸውን ጥፋተኛ የሚያደርጉ የከረሩ ምልልሶችን ሲያደርጉ የነበሩ ሁለት አካላት መወዛገባቸው ተፈጥሮዓዊ ነው፡፡ የትኛውም ወገን ቢያሸንፍ ሌላኛው ቅሬታ ማቅረቡ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይሁንና እነዚህ የፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ለአንዱ ወገን ዕውቅና በመስጠት ሌላኛውን ተሸናፊ ካደረጉ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሲዳከሙ ይታያሉ፡፡ በሕዝቡ ዘንድ ከፓርቲው ጋር ተያይዘው የሚታወቁ የፖለቲካ መሪዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪዎች ሆነው የሚታወቁ ግለሰቦች በአብዛኛው በክርክሩ ከተሸነፈው ወገን ነው የሚገኙት፡፡ ይኼ ውዝግቡን የሚያፋፍም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ተንታኞች እነዚህ የፍርድ ቤት ክርክሮች የሚጀምሩትና በመጨረሻም አሸናፊ ሆነው የሚወጡት በገዥው ፓርቲ የሚላኩ ጥቂት ሰርጎ ገቦች እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ እርስዎ ይህን አመለካከት ይጋራሉ?

ዶ/ር ጌድዮን፡- በእነዚህ የፍርድ ቤቶች ክርክሮች የተረቱ ብዙ ሰዎች ስለሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች ግንዛቤው አለኝ፡፡ የበርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዋቂ መሪዎች ገዥው ፓርቲ ሰርጎ ገቦችን በመላክ ፓርቲውን እንደሰነጠቀ ይከሳሉ፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከፍርድ ቤቶች ጋር በመተባበር ፓርቲዎቹ በሰርጎ ገቦች እጅ እንዲወድቁ ያደርጋል ተብሎ ይወነጀላል፡፡ በተለያዩ ግለሰቦች በተለያዩ ጊዜዎች የሚቀርብ ክስ በመሆኑ በቀላሉ አልሰርዘውም፡፡ ነገር ግን እነዚህን ጉዳዮች በተገቢ መንገድ በማጥናት የጉዳዩን አነሳስ፣ የፍርድ ቤቶችን ምክንያት፣ የተጠቀሙትን መለኪያ በጥልቀት በማየት ነው ቁርጥ ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚቻለው፡፡ አሁን እነዚህን ጉዳዮች በጥልቀት ስላላጠናሁ የውሳኔዎቹ ጥንካሬና ድክመት ላይ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ፡፡ ይሁንና የእነዚህ ክሶች አለመቋረጥና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች በፍርድ ቤቶች ላይ ያላቸው አመኔታ በጣም ደካማ መሆን ሊያሳስበን ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቶች በትክክል ገለልተኛ ቢሆኑም፣ በአንዳንድ ተከራካሪዎች ገለልተኛ እንዳልሆኑ መታሰቡ ትልቅ ችግር ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የፍርድ ቤቶች ውሳኔ አወዛጋቢ እንዲሆን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስተዳደራዊ ውሳኔ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያደርግ ያምናሉ፡፡ በዚህ ይስማማሉ?

ዶ/ር ጌድዮን፡- የፍርድ ቤቶች ሥራ በአብዛኛው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን አስተዳደራዊ ውሳኔ መከለስ ነው፡፡ ከምርጫ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ከባዶ አይጀምሩም፡፡ የክርክሮቹ ፍሬ ነገሮች የሚመሠረቱት በቦርዱ ውሳኔ ላይ ነው፡፡ በተወሰነ ሁኔታ ምርጫ ቦርድ ላሰፈራቸው የፍሬ ነገር ግኝቶች ፍርድ ቤቶች ክብር አላቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲውና ምርጫ ቦርድ ጥሩ ግንኙነት ካላቸው ይኼ በፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ የራሱ ተፅዕኖ አለው፡፡ ስለዚህ የምርጫ ቦርዱ አስተዳደራዊ ውሳኔ፣ አቋምና አመለካከት በፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው፡፡  

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ካሉባቸው መሠረታዊ ችግሮች አንዱ የገንዘብ እጥረት ነው፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ የወጡት የምርጫ ሕጎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ምንጫቸውን ሪፖርት እንዲያደርጉ መደንገጋቸው ይኼን ችግር እንዳባባሰው ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥር ከሰደደው የሚስጥር ባህል አንፃር ስማቸውን ሳይገልጹ ለፓርቲዎች መርዳት መከልከሉን ብዙዎቹ ፓርቲዎች ተቃውመዋል፡፡ መሰል ድንጋጌዎች በሌሎች አገሮች የተለመዱ ናቸው?

ዶ/ር ጌድዮን፡- መሰል ድንጋጌዎች በሁሉም ዴሞክራሲየዊ አገሮች ማለት ይቻላል ያሉ፣ መደበኛ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማስተዳደርና ተጠያቂ ለማድረግ ተግባራዊ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይኼ የኢትዮጵያ ሕግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው አሠራር ያፈነገጠ አይደለም፡፡ በመሠረቱ ሕጉ እንደ ችግር ሊታይም አይገባም፡፡ ይሁንና ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህልና ዓውድ አንፃር ችግሩን መረዳት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ የምትሠራው ማንኛውም ሥራ በአንድም ይሁን በሌላ በኩል ከመንግሥት ጋር ያገናኝሃል፡፡ ስለዚህ ሥራህ በመንግሥት መልካም ፈቃድና በጎ አመለካከት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ በሆነ መንገድ የገዥው ፓርቲ አባላትን ከነካህ ወይም ከተጋጨህ ለምሳሌ ለሌሎች ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የገንዘብ  ዕርዳታ ካደረግክ፣ ገዥው ፓርቲ ቀጣዩን ምርጫ ሲያሸንፍ አሉታዊ ተፅዕኖና የበቀል ዕርምጃ ይደርስብኛል ብለህ ትፈራለህ፡፡ ስለዚህ በፍርኃት በተሞላው የፖለቲካ ባህላችን ሕጉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከደጋፊዎችና ከተለያዩ አካላት የሚያገኙት ገንዘብ እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የሚዲያ ተቋማት የፖለቲካ ፓርቲዎችን በፍትሐዊነት ማገልገል ያለባቸው በመደበኛነት እንደሆነ ሕገ መንግሥቱ ያመለክታል፡፡ ይሁንና ዝርዝር ሕጎች ይህን ነፃነት ለምርጫ ጊዜ የገደቡት ይመስላል፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ጌድዮን፡- ከሕገ መንግሥቱ የሚነበበው ዕይታ እነዚህ የሚዲያ ተቋማት ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራሽ መሆን ያለባቸው ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ዝርዝር ሕጎች በምርጫ ጊዜ ስላለው አጠቃቀም ዝርዝር ሁኔታዎችን እንዳስቀመጡ መተርጎም ይቻላል፡፡ ይኼ ከሕገ መንግሥቱ መንፈስ ጋር ላይጋጭ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እነዚህ የሚዲያ ተቋማት መጠቀም ያለባቸው በምርጫ ጊዜ ብቻ እንደሆነና በሌሎች ጊዜያት መጠቀም እንደማይችሉ የሚጠቁም ነገርም ሕጎቹ ላይ ይታያል፡፡ ይኼ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ ችግር ያለበት አረዳድ ነው፡፡ በተግባር የሚፈጸመው ይህ ከሆነ የሚዲያ ተቋማቱ የመንግሥትን ፖሊሲና መመርያ ከሚፈጽሙ የመንግሥት ኤጀንሲዎች የተለዩ አይደሉም ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁት ሰዎች ሐሳብ እነዚህ የሚዲያ ተቋማት ሕዝቡን እንዲያገለግሉ እንጂ፣ የመንግሥት ዓላማ ማስፈጸሚያዎች ብቻ እንዲሆኑ አይደለም፡፡ ይሁንና ካለፈው ምርጫ በኋላ በእነዚህ የሚዲያ ተቋማት አሠራር ላይ አዎንታዊ ለውጦችም ታይተዋል፡፡ በተለያዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮችና ፖሊሲዎች ላይ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመጋበዝ ማከራከራቸው ሊበረታታ ይገባል፡፡ ይኼ በተቋማዊ አሠራር ሊታገዝ ይገባል፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫዎች፣ እንቅስቃሴዎችና አመለካከቶች በቋሚነትና በፍትሐዊነት ሊስተናገዱ ይገባል፡፡ ዴሞክራሲን በምርጫ ወቅት መገደብ ተገቢ አይሆንም፡፡   

ሪፖርተር፡- በአንዱ የምርምር ሥራዎት ላይ ገዥው ፓርቲ የመንግሥት ሥልጣኑን በመጠቀም የሚዲያ ተቋማቱን፣ የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን፣ ምርጫ ቦርድንና የደኅንነት ተቋማትን ያላግባብ እንደሚጠቀም ተከራክረዋል፡፡ በሌሎችም አገሮች ሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ከሌሎቹ የተሻለ ተጠቃሚ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የተለየ የሚያደርጉት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ጌድዮን፡- መንግሥት በምርጫ ተወዳዳሪ አይደለም፡፡ ፓርቲዎች ሲወዳደሩ የመንግሥት ሠራተኞችና ቢሮዎች፣ የደኅንነት መሥሪያ ቤትና የጦር ኃይሉ ገለልተኛ መሆን አለባቸው፡፡ የሕዝብ ሀብት ሌሎች ፓርቲዎችን በማግለል የአንድ ፓርቲን አቋም ለማስፋፋት ጥቅም ላይ ሊውል አይገባም፡፡ በኢትዮጵያ እነዚህን መሠረታዊ መርሆዎች የጣሱ አሠራሮችን እናያለን፡፡ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በመንግሥት ደመወዝ ቢከፈላቸውም የፓርቲ ሥራ ብቻ የሚሠሩበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ የፓርቲ ሠራተኞች ከመንግሥት ጥቅማ ጥቅም፣ ደመወዝ፣ መኪኖችና የመሳሰሉትን ያገኛሉ፡፡ ይኼ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ረጅም የፓርቲ ሥልጠናዎች ወጪያቸው በመንግሥት የሚሸፈን ሲሆን፣ መንግሥት ይባስ ብሎ ተሳታፊዎችን ያለፈቃዳቸው ተገደው እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡ በእነዚህ ሥልጠናዎች የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራንና ሌሎችም አካላት እንዲሳተፉ ይገደዳሉ፡፡ እነዚህ ዓይነት ሥልጣንን ያላግባብ የመጠቀም መገለጫዎች አሉ፡፡ እነዚህ አዝማሚያዎች ከቀጠሉ የኢትዮጵያ ምርጫዎች በፓርቲ ‹‹ሀ›› እና በፓርቲ ‹‹ለ›› መካከል መካሄዳቸው ቀርቶ፣ ጉልበት ባለውና የሕዝብ ሀብትን በያዘው መንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚካሄዱ ይሆናሉ፡፡ ምርጫው ፍትሐዊ የሆነ ውድድር የሚካሄድበት መሆኑ ይቀራል፡፡   

ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶች ላይ የሚዲያ ተቋማት ማረሚያ እንድናደርግ መጠየቃቸው ቅድመ ምርመራ ነው ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ቅሬታቸውን እንዴት አዩት?

ዶ/ር ጌድዮን፡- በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ዝርዝር ሕጎች ቅድመ ምርመራ በግልጽ የተከለከለ ነው፡፡ ስለዚህ በእኔ ዕምነት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክት ይዘትን በማየት ፖለቲካ ፖርቲዎቹ ማሻሻያ እንዲያደርጉ መጠየቅ ቅድመ ምርመራ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ የሚዲያ ተቋማቱ ሥራም አይደለም፡፡ ሕገወጥ የሆነና ሕጋዊ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ከሆነ የመክሰስ ሥልጣን የዓቃቤ ሕገ ነው፡፡ ነገር ግን በቅድመ ምርመራ ተግባር ራሳቸው የሚዲያ ተቋማቱ መሳተፋቸው ሕግ መንግሥቱን የሚጥስ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ አንፃር ቅድመ ምርመራ ትልቁ ፈተና ነው፡፡ መደረግም ካለበት እጀግ በተለዩ ሁኔታዎች ውስጥ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ሁሉንም የምርጫ ቅስቀሳ መልዕክቶች የሚዲያ ተቋማቱ ማስተላለፍ አለባቸው እያልኩ አይደለም፡፡ ለምሳሌ መልዕክቱ ብጥብጥና አመፅን የሚጠራ ከሆነ፣ ሕገወጥና የወንጀል ድርጊቶችን የሚያበረታታና መሰል ሥጋቶችን የሚፈጥር ከሆነ የሚዲያ ተቋማቱ ያለማስተላለፍ መብት አላቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ላይ ግን ጣልቃ መግባት የለባቸውም፡፡

ሪፖርተር፡-  የኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት የሚተቸው ለምንድነው? በዓለም ላይ ያሉት አማራጭ የምርጫ ሥርዓቶችን የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ጌድዮን፡- በአጠቃላይ በዓለም ላይ ሁለት ዋነኛ የምርጫ ሥርዓቶችና ሌሎች በሁለቱ መካከል የሚገኙ የምርጫ ሥርዓቶች አሉ፡፡ አንዱ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ የምርጫ ሥርዓት ፓርቲዎቹ በምርጫው ባገኙት ድምፅ ልክ ከሞላ ጎደል የፓርላማ ወንበር ያገኛሉ፡፡ ከአጠቃላይ መራጮች 20 በመቶ የሚሆኑት ድምፃቸውን ከሰጡህ 20 በመቶ የሚሆነውን የፓርላማ ወንበር አሸነፍክ ማለት ነው፡፡ ፍትሐዊና ተመጣጣኝ ነው ተብሎ ይወሰዳል፡፡ በሌላ በኩል የዚህ የምርጫ ሥርዓት ጉዳት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ማበረታታቱ ነው፡፡ ከምርጫ በፊት ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች እንዲሁም ሕዝቡ አመለካከቱንና ፍላጎቱን በማቻቻል በአንድነት እንዲሠሩ የሚሰጠው ማበረታቻ የለም፡፡ ይኼን የምርጫ ሥርዓት በሚከተሉ እንደ እስራኤል ባሉ አገሮች አንድ ፓርቲ የበላይነት አይኖረውም፡፡ ፓርላማው በተለያዩ ፓርቲዎች የሚሞላ ሲሆን፣ ጥምር መንግሥት ለመፍጠር ረዥም ድርድሮችን ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ ጥምር መንግሥቱ ያልተረጋጋ ሲሆን፣ ትንንሽ ፓርቲዎች በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ከመጠን ያለፈ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡

ሁለተኛው የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ሲሆን፣ ዋነኛ ምሳሌ እንግሊዝ ናት፡፡ ኢትዮጵያም ይኼንን ነው የምትከተለው፡፡ በዚህ የምርጫ ሥርዓት አገሪቱ በተለያዩ የምርጫ ክልሎች የምትከፋፈል ሲሆን፣ በዚያ ክልል ከተሰጡ ድምፆች ከፍተኛውን ድምፅ ያገኘ ዕጩ ወይም ፓርቲ አሸናፊ ይሆናል፡፡ በአሸናፊውና በተሸናፊው ዕጩ መካከል ያለው ልዩነት ሦስት ወይም 100 ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼ የምርጫ ሥርዓት ላይ ጥያቄ የሚያነሱና በኢትዮጵያም ተፈጻሚ መሆኑን የሚቃወሙ አካላት የሚያነሱት ችግር፣ ይኼ የምርጫ ሥርዓት ለአሸናፊው ሁሉንም ነገር የሚሰጥ በመሆኑ ነው፡፡ ምንም እንኳን አሸናፊው ዕጩ በጥቂት ድምፆች ልዩነት ቢያሸንፍም፣ በምርጫ ክልሉ ያሉትን የአብዛኛዎቹን መራጮች ድጋፍ ባያገኝም ብቸኛው የክልሉ ተወካይ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ጠቅላላ ምርጫ ኢሕአዴግ ከፓርላማው ወንበር ውስጥ ከ99 በመቶ በላይ የሚሆነውን አሸንፏል፡፡ ነገር ግን 99 በመቶ የሚሆነውን የመራጩን ሕዝብ ድጋፍ አላገኝም፡፡

ይኼ የምርጫ ሥርዓት ሁለት ጥንካሬዎች አሉት፡፡ አንዱ የተረጋጋ መንግሥት ለመፍጠር ማስቻሉ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከተፈጥሮው በመነሳት ሥርዓቱን ያጠኑ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ከአፈጻጸሙ እንደ ደመደሙት፣ ሥርዓቱ ሁለት ወይም ሦስት ዋነኛ ፓርቲዎችን የሚፈጥር ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ለትንሽ ፓርቲ ድምፅ መስጠት ድምፅ ማባከን እንደሆነ መራጮች እየተማሩ ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ የሆነ ልዩነት የሌለውን ጠንካራ ፓርቲ እየመረጡ ይመጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ በምርጫ 97 ሦስት ትልልቅ ፓርቲዎች ተፈጥረው ነበር፡፡ ምንም እንኳን 75 የተመዘገቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ቢነገርም፣ ሥርዓቱ ቢጠናከርና አሳታፊ ቢሆን የተለያዩ ፓርቲዎች አንድ እየሆኑ በመጨረሻ ሁለት ወይም ሦስት ጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡ ምሁራንና ፖለቲከኞች ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት የምርጫ ሥርዓት ላይ ስምምነት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ እኔ ግን አሁን በሥራ ላይ ያለው ሥርዓት ተመራጭ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ ያለውን ብዝኃነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓቱን ተመራጭ ያደርጋሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተሻሽሎ ይህን ሥርዓት እንዲያካትም ይጠይቃሉ፡፡ የእርስዎ አመለካከት ግን ከዚህ የተለየው ለምንድነው?

ዶ/ር ጌድዮን፡- በሥራ ላይ ያለው ሥርዓት የተረጋጋ መንግሥት ለመፍጠርና ፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማጠናከር ይረዳናል፡፡ በብሔር በጣም የተከፋፈልን ማኅበረሰቦች እንደመሆናችን ይበልጥ ልዩነት ከሚፈጥር ይልቅ፣ አንድነትን የሚያበረታታው የምርጫ ሥርዓት ይሻለናል፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በተከፋፈሉ ማኅበረሰቦች ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ ሊኖር የሚገባውን አሠራር በተመለከተ ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ አንዱ ልዩነቶችን ለማስተናገድ የተመቸ ሥርዓትን ሲጠይቅ ሌላው ደግሞ ልዩነቶች ተባብሰው ወደ አንድነት የሚመጡት መንገድ ያመቻቻል፡፡ አንድነት ላይ የሚያተኩረው አመለካከት ለብሔር ማንነት ትኩረት የማይሰጥ ሲሆን፣ አንድ የጋራ ሲቪክ ማንነት መፍጠር ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ልዩነት ስለማቻቻል ትኩረት የማይሰጥ ሲሆን አንድ የጋራ ሲቪክ ማንነት መፍጠር ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ልዩነትን ስለማቻቻል ትኩረት የሚያደርገው አመለካከት ግን የብሔር ግንኙነትን ማስወገድ ስለማይቻልና ስለማያስፈልግ ማቻቻልና ማስተናገድ ስለሚቻልበት መንገድ ትኩረት ይሰጣል፡፡ አረን ሊፓርት የተባሉ ታዋቂ የፖለቲካ ምሁር በዋንኝነት የሚያቀነቅኑት ኮንሶንሺየሽናሊዝም (የስምምነት ዴሞክራሲ) አስተሳሰብ ለተከፋፈሉ ማኅበረሰቦች የምርጫ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥት ሥራ ጭምር በተመጣጣኝ ውክልና መደረግ አለበት ብሎ ያስቀምጣል፡፡

በሌላ በኩል ዶናልድ ሆሮዊትዝና ተከታዮቻውን ይኼን አምርረው ይቃወማሉ፡፡ እነሱ የሚከራከሩት የብሔር ማንነት ተቋማዊ ከሆነና በተመጣጣኝ ውልክና ሁሉም ነገር የሚወክለን ከሆነ፣ ልዩነቱ ሳይጠብና ሳይለወጥ ባለበት ይቆያል በማለት ነው፡፡ በእኔ ዕምነት ለተመጣጣኝ ውክልና ቦታ የሚሰጡ የተለያዩ አሠራሮች በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ እነዚህን ብዝኃነቶች የሚይዘው ብቸኛ አሠራር አሁን እየተጠቀምንበት ያለው የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡ የተመጣጣኝ ውክልና አሠራርን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ተግባራዊ ካደረግን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተለየ አይሆንም፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕግ ብሔርን መሠረት ያደረጉትን ፓርቲዎች ጭምር ከምርጫ በፊት ጥምረት እንዲፈጥሩ የሚያበረታታ ነው፡፡ ነገር ግን የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ዛሬ ተግባራዊ ብናደርግ የተለያዩ የማይጣጣሙ ፍላጎቶች ያሏቸው ፓርቲዎች ፓርላማ እንዲገቡ እናደርጋለን፡፡ ይኼ ደግሞ ለአገሪቱ መረጋጋት አይበጅም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅድመ ምርጫ 2007 አዝማሚያዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩ ምርጫዎች ጋር ሲነፃፀሩ ምን ይመስላሉ?

ዶ/ር ጌድዮን፡- ስለቅድመ ምርጫ 2007 ስናነሳ ያለፉትን ጥቂት ወራት ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን አዝማሚያ ማየት ይመረጣል፡፡ የአንድ ምርጫ ሞገስ፣ ተቀባይነትና ዴሞክራሲያዊ ጥራት ከምርጫው በፊት ዜጎች እየተጠቀሙበት ባለው ነፃነት ላይ ይመረኮዛል፡፡ የምርጫውን ጥራት አንድ ጤነኛ ሕፃንን ከመውለድ ጋር ማነፃፀር ይቻላል፡፡ እናትየዋ ለመውለድ የሄደችበት ሆስፒታል ጥራትና ያገኘችው የአገልግለት ዓይነት የሕፃኑን ጤንነት አይወስንም፡፡ እናትየዋ ከምጡ ጊዜ በፊት የሚጠጡ ከነበረ፣ የንፁህ የመጠጥ ውኃና የምግብ አቅርቦት ያልነበራቸው ከሆነ፣ በቀን ለ18 ሰዓታት ይሠሩ ከነበረ፣ የሕክምና አገልግሎት አያገኙ ከነበረ በምጥ ጊዜ ያገኙት ምርጥ ሆስፒታልና ዶክተር የሕፃኑን ጤንነት አይቀይሩትም፡፡

በተመሳሳይ የምርጫው ሒደት ጤናማ እንዲሆን ከምርጫው ዕለት በፊት የነበሩት ከባቢ ሁኔታዎችና ዓይነቶች ወሳኝ ናቸው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት የነበረው አጠቃላይ ከባቢ ሁኔታ በፍርኃት የተሞላ ነበር፡፡ ምን ያህል ሕዝባዊ ሠልፎች እንደተደረጉ መቁጠር ይቻላል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ሕዝባዊ  ሠልፎችን ማድረግ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበርም ታይቷል፡፡ ምን ያህል የሆቴል ባለቤቶች መሰብሰቢያ አዳራሻቸውን ለፖለቲካ ስብሰባ ለማከራየት ፈቃደኛ ነበሩ? ምን ያህል ዜጎች የሚደግፉትን ፓርቲ በገንዘብ ረድተዋል? ወይም አባል ሆነዋል? ባለፉት አሥር ዓመታት ያለው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ነፃነት ከዚያ በፊት ከነበሩት አሥር ዓመታት ጋር ሲነፃፀር እየቀነሰ ነው የመጣው፡፡ በአጠቃላይ የሚዲያ፣ የሲቪል ማኅበራትና የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሠራር በፍርኃት የተከበበ ነው፡፡ ይኼ በምርጫው ጥራት ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ የዚህኛው ምርጫ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ይኼን ከባቢ ሁኔታ ማሻሻልና ዜጎች በነፃነት የሚሰማቸውን ሐሳብ እንዲገልጹ የሚያደርግ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት አለብን፡፡ አሁን  ከዚህ እውነት በብዙ ርቀት ላይ ነው የምንገኘው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...