ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን በግንባታው ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ዘልቋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት 80 የደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች መካከል አንዱ ነው፡፡
ኩባንያው ባለፈው ሐሙስ የወቅታዊ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ የኩባንያውን ወቅታዊ እንቅስቃሴን ለመግለጽና በቅርቡ ያገኘውን ዓለም አቀፍ ሽልማት በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ላይ፣ የአገሪቱን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ሥጋትና ተስፋ የሚያሳይ ገለጻ ተደርጓል፡፡
የኩባንያውን አዲስ አወቃቀርና የአገሪቱን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እየተፈታተነው ይገኛል በተባለው ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ዙሪያም የኮንስትራክሽን ኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከህዳሴው ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ሜጋ ፕሮጀክት ነው በሚባለውና በተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን እየተሠራ ስላለው የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ወቅታዊ የግንባታ ደረጃ የሚያሳይ ገለጻም የመግለጫው አካል ነበር፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫውን የተክለብርሃን አምባዬ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፉ አምባዬ፣ የምሕንድስናና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂነር ሀብታሙ መንግሥቴና የሰው ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌቴ ዳኙ በጋራ ሰጥተዋል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ከተነሱ አንኳር አንኳር ነጥቦች ውስጥ የተወሰኑት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
የኩባንያው የሥራ ሒደት ለውጥና ተወዳዳሪነት
ተክለብርሃን አምባዬ በዕለቱ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ትኩረት የሰጠበት ነጥብ ተወዳዳሪ ኩባንያ ለመፍጠር እያደረገ ያለውን አዲስ አደረጃጀት ይመለከታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ዓለም አቀፋዊ ውድድርና የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሳደግ የግድ ለውጥ በማስፈለጉ ኩባንያው አዲስ የኩባንያ አወቃቀር ለውጥ ውስጥ ስለመግባቱ የሥራ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ በተለይ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሰይፉ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የኮንስትራክሽን ዘርፉም ከሚገመተው በላይ እያደገ በመምጣቱ ይህንን የሚመጥን አወቃቀር ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል፡፡
በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራትና ከውጭ የሚገቡ ኮንትራክተሮችን ለመወዳደር የእስከዛሬው አካሄድ ስለማያዋጣ፣ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አዲስ አደረጃጀት በማስጠናት ወደ ትግበራ ተገብቷል ተብሏል፡፡
ይህ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን የጀመረው የለውጥ ሒደት ሌሎቹ አገር በቀል ኮንትራክተሮችን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑ የተሰጠው ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ አሁን ያለው የአገር በቀል ኮንትራክተሮች አቅምና አሠራር ሲፈተሽ በምንም መመዘኛ ከውጭዎቹ ጋር ሊመጣጠን የማይችል በመሆኑ፣ ይህንን ክፍተት ለማጥበብ ሥር ነቀል ለውጡ ጊዜ የማይሰጠው በመሆኑ የተወሰደ ዕርምጃ ስለመሆኑም ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፉ አለ የሚባለውን ክፍተት በተለይም የአገር በቀል ተቋራጮች ተወዳዳሪ ሆነው ለመዝለቅና የውጭ ኮንትራክተሮች እንዳይገቡ አዋጅና ሕግ እንዲወጣ መጠየቅ እንደማይቻል የገለጹት አቶ ሰይፉ፣ ኮንትራክተሮች ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይችሉም ይናገራሉ፡፡
ተክለብርሃን አምባዬም ይህንን ለመተግበር የሚያስችለውን ጥናት አጥንቷል፡፡ አዲሱ መዋቅር ተወዳዳሪ የሆነ ኩባንያ ለመፍጠር የሚያስችል ከዚህ በፊት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የነበሩ ግድፈቶችን የሚያስቀር ነው ተብሎለታል፡፡ በዚህም መሠረት አዲስ የሠራተኛ ምደባ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ ምደባውም ብቃት ያለው የኮንስትራክሽን ተቋም በመፍጠርና ብቁ አስፈጻሚዎችን በማሠልጠን አዲስ የሥራ ምደባ ውስጥ ገብቷል፡፡
በእስካሁኑ ሥራም በከፍተኛ ደረጃ ያሉ የሥራ ኃላፊዎችን ምደባ አጠናቅቆ ወደታች እየወረደ መሆኑንም አቶ ሰይፉ ገልጸዋል፡፡ በአዲሱ ተቋማዊ አደረጃጀት እያንዳንዱ ሠራተኛ ለተመደበበት ቦታ ብቁ እንዲሆን ተጨማሪ ሥልጠና ተሰጥቶት የሚመደብ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ለዚህም በራሱን ማሠልጠኛ ተቋም እየተጠቀመ ነው ተብሏል፡፡ ይህ አደረጃጀት ለኩባንያውም ሆነ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዕድገት የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎም ታስቧል፡፡ ሌሎቹም አገር በቀል ኮንትራክተሮች ቢከተሉት የሚመረጥ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰይፉ፣ ኮንትራክተሮች ሥር ነቀል ለውጥ ካላደረጉ እየተመሙ ያሉት የውጭ ኩባንያዎች ከሥራ ውጭ ያደርጉናል በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ዓለም አቀፋዊውን ውድድር ማሸነፍ የሚቻለው በግል ወይም በአንድ ተቋም ብቃት ብቻ ባለመሆኑና ከዘርፉ ዕድገት ውጭ አንድ ተቋራጭ ብቻውን ያድጋል የሚል አሠራር ስለሌለ ዕድገቱ የጋራ መሆን አለበትም ብለዋል፡፡ ስለዚህ ዘርፉ በጥቅል ካልተቀየረ የትም መድረስ ስለማይችል ሥራ ተቋራጮች ራሳቸውን ለማብቃት ከሚያደርጉት ጥረት በላይ መንግሥትም ሊያግዛቸው ይገባል ተብሏል፡፡
ብቁ ተቋራጭ ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ደግሞ ሌላኛው መንገድ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ሁለት የሥራ ተቋራጮች ማኅበራት ክንዋኔ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ እንደ አቶ ሰይፉ ገለጻም፣ እነዚህ ሁለት ማኅበራት (የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኅበርና የኢትዮጵያ የደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ማኅበር) በተናጠልና በጋራ ሆነው አሉ የሚባሉትን ችግርች በመፍታት መንግሥትንም በአጋርነት በመያዝ መሥራት ከተቻለ ለውጥ ሊመጣ የሚችልበት ዕድል ይኖራል፡፡ ካልሆነ ግን ዘርፉ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል አቶ ሰይፉ ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
የአገር በቀል ኮንትራክተሮች የጋራ እንቅስቃሴ ወሳኝ በመሆኑም ከዚህ በኋላ ኮንትራክተሮች በተናጠል የሚያደርጉት ጉዞ አደጋ እንዳለው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በተናጠል የሚደረገው እንቅስቃሴ የዓመታት ልምድ ያላቸውና ተደራጅተው እየመጡ ያሉትን የውጭ ኮንትራክተሮች ማሸነፍ አያስችልም ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገር በቀል ኮንትራክተሮች ላይ ያለውን የአቅም ውስንነትና የአደረጃጀት ችግር ለመቅረፍ ኩባንያቸው የተለያዩ መፍትሔዎች ተግባራዊ ለማድረግ ግን ኃላፊነት ወስዶ በመንቀሳቀስ ላይ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ይህንንም በደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ማኅበር በኩል ለማስፈጸም እየጣረ ነው ተብሏል፡፡ የአገሪቱን ተቋራጮች የራሳቸው ግብ ኖሯቸው እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል ደግሞ የኮንስትራክሽን ስትራቴጂክ ፕላን በማዘጋጀት ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ኮንትራክተሮችን ተወዳዳሪ የሚያደርግ ጭምር ነው የተባለውን ስትራቴጂክ ፕላን እንዲያዘጋጅ ከኧርነስት ኤንድ ያንግ ከተባለው ዓለም አቀፍ ኩባንያ ጋር ስምምነት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ በሚዘጋጀው ፕላን መሠረት ከተሠራ ለውጥ ይመጣል የሚል ተስፋ አላቸው፡፡
ያዩ ‹‹ያልተወራለት›› ትልቁ ፕሮጀክት
ያዩ የማዳበሪያ ማምረቻ ፕሮጀክት መንግሥት ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ነዋይ የሚፈስበት ፕሮጀክት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ ይገመታል፡፡
አቶ ሰይፉ እንደገለጹትም፣ የያዩ ፕሮጀክት መንግሥት ለመገንባት ካቀዳቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀስ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ በ54 ሺሕ ሔክታር ቦታ ላይ የሚገነባ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል በኢሊባቡር ያዩ አካባቢ በመገንባት ላይ ያለውን ይህን ፕሮጀክት በባለቤትነት የሚያስገነባው የኢትዮጵያ ኬሚካል ኮርፖሬሽን ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ግንባታ ሥራውን ለመሥራት ኃላፊነት የተሰጠው ደግሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ደግሞ የሲቪል ሥራውን ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተረክቦ እየሠራ ይገኛል፡፡ የኮንትራት ውሉ እንደሚያመለክተውም ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን የሲቪል ሥራውን ለመሥራት የተዋዋለበት ዋጋ 920 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ እየተሠራ ያለው ግንባታ በተለያዩ ጊዜያት ተቋርጦ የተጀመረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ያለችግር እየተጓዘ መሆኑን አቶ ሰይፉ ይናገራሉ፡፡
እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች በአገር በቀል ኮንትራክተሮች መገንባት መጀመራቸው ተስፋ ሰጪ ነው የሚሉት አቶ ሰይፉ፣ መጀመሪያ ግን የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ የኮንስትራክሽን ሥራውን ለማሠራት ታቅዶ የነበረው በውጭ ኮንትራክተሮች እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ሥራው በአገር በቀል ኮንትራክተሮች መሠራት አለበት የሚል ውሳኔ በመወሰኑ፣ ለአሥር አገር በቀል ኮንትራክተሮች ሥራውን እንዲሠሩ ዕድል ቢሰጥም ዘጠኙ ሥራው አስቸጋሪ ነው ብለው በመውጣታቸው፣ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ሥራውን ሊረከበው ችሏል፡፡
በድፍረት የተገባበት ሥራ አልጋ በአልጋ ባይሆንላቸውም በመሃከል ላይ ያጋጠማቸውን ፈተና በመወጣት በአሁኑ ወቅት ከጠቅላላ የሲቪል ሥራው ውስጥ 50 በመቶ ሊያጠናቅቅ መቻሉን አመልክተዋል፡፡ ሰኔ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይም የሲቪል ሥራው 65 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ተገምቷል፡፡ ይህ ፕሮጀክት እንደሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ትኩረት አልተሰጠውም የሚሉት የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች፣ ፕሮጀክቱ ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ ለማመላከት የተለያዩ ምሳሌዎችን አቅርበዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከ4,200 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን የያዘ መሆኑ አንዱ ምሳሌ ነበር፡፡ በየወሩ ለዚህ ፕሮጀክት ለሚሠሩ ሠራተኞች ብቻ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉ፣ የያዩ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገው የአርማታ ብረት ብቻ ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ኪሎ ግራም የሚደርስ መሆኑና ከ400 ሺሕ ኩንታል በላይ ሲሚንቶ ሊፈጅ የሚችል ግንባታ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የሲቪል ሥራው 92 የሚደርሱ የሕንፃ ግንባታዎችን የሚያካትት መሆኑ ፕሮጀክቱ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ ያመላክታል ይላሉ፡፡ ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ከማዳበሪያ ምርቱ ባሻገር ተያያዥ ሥራዎችን ያካተተ ነው፡፡ ፋብሪካው የከሰል ድንጋይ የሚያመርት በመሆኑ ከከሰል ድንጋዩ የሚገኘው እንፋሎት ፋብሪካው ለራሱ ኃይል ፍጆታ የሚጠቀምበት 83 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል፡፡ 1.5 ሚሊዮን ቶን የከሰል ድንጋይ በዓመት ይመረትበታል፡፡ በዋናነት ግን ከ300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ዩሪያ የተባለውን ማዳበሪያ ያመርታል፡፡ በውጥኑ መሠረት ከተጠናቀቀም ከ30 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ በተፈለገው ፍጥነት ለመጓዝ ካልቻሉ ፕሮጀክቶች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ አቶ ሰይፉም ይህንን ይስማማሉ፡፡ በየመካከሉ የተፈጠሩ ክፍተቶች ፕሮጀክቱ እንደተፈለገው እንዳይሄድ አድርገው ነበር፡፡ አሁን ግን ችግሩ ስለተቀረፈ ሥራውም እየፈጠነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንና በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መካከል በተፈጠረ ያለመግባባት ሥራው የተስተጓጎለበት ወቅት እንደነበር ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ አቶ ሰይፉ ግን ይህን አስተያየት አይቀበሉትም፡፡ በመሃል ላይ ፕሮጀክቱ ሥራ ተቀዛቅዞ የነበረው ከኮርፖሬሽኑ ጋር በተፈጠረ ያለመግባባት አይደለም ይላሉ፡፡
ዋነኛ ችግር የነበረውና ሥራው ለተወሰነ ጊዜ የቆመበት ምክንያት ሥራው ሲጀመር የኢትዮጵያ ኬሚካል ኮርፖሬሽን ያልተቋቋመ ስለነበርና ከተቋቋመ በኋላ ደግሞ የፕሮጀክቱ ባለቤት ለሆነው ለኬሚካል ኮርፖሬሽኑን በሚዛወርበት ጊዜ በተፈጠረ ክፍተት እንጂ እንደተባለው ያለመግባባት ተፈጥሮ አልነበረም በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አገር በቀል ኮንትራክተሮችና መፍጠር ያልቻሉት ጥምረት
የአገር በቀል ኮንትራክተሮችን እንቅስቃሴ በተመለከተ በተደጋጋሚ ትችት ሲቀርብበት የቆየው ጉዳይ ቢኖር፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተወዳዳሪ ለመሆን ለምን በጥምረት (በጆይንት ቬንቸር) አይሠሩም የሚል ነው፡፡ የየራሳቸውን ሥራ እየሠሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በጥምረት ቢሠሩ ለእነርሱም ሆነ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ዕድገት ሊሆን ይችላል የሚል ሐሳብ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይም ይህንን አመለካከት የሚያንፀባርቁ ጥያቄዎች ተሰንዝረው ነበር፡፡
በዚህ አስተያየት ዙሪያ አቶ ሰይፉ የተለየ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ጥምረቱን ፈጥሮ ትልቅ ሥራዎች ለመሥራት በርካታ ችግሮች ቢኖሩም፣ በጨረታዎች ላይ የሚቀመጡት መስፈርቶች ከፍተኛ መሆን ዋነኛ ችግር ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት የሚሠሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን አራትና አምስት የአገር ውስጥ ተቋራጮች ተጣምረው ለመውሰድ ቢቀርቡ እንኳን የጨረታ መስፈርቱን ሊያሟሉ አይችሉም፤›› ይላሉ፡፡
ይህም የሚሆነው በአብዛኛው ጨረታዎች ውስጥ ለመሳተፍ የሚቀመጠው የኮንትራክተሮች ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት (ተርን ኦቨር) ከፍተኛ ከመሆን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንደ አቶ ሰይፉ ገለጻ፣ አንድ ኮንትራክተር በትላልቅ ፕሮጀክቶች በጨረታ ላይ ለመሳተፍ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰቱ ስድስት ቢሊዮን ብር መሆን አለበት የሚል መስፈርት የሚቀመጥባቸው አጋጣሚዎች በርካታ መሆናቸው፣ አገር በቀል ኮንትራክተሮች ቢጣመሩም እንኳን የተጠቀሰውን የገንዘብ ፍሰት መጠን ሊያሟሉ አይችሉም፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየወጡ ያሉ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ጨረታዎች ውስጥ አንድ ኮንትራክተር ቢያንስ ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰቱ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መሆን አለበት የሚሉ ናቸው፡፡
እንዲህ ያሉ መስፈርቶች የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ተጣምረው እንኳን የተጠየቀውን ዓመታዊ ተርን ኦቨር ማሟላት አላስቻላቸውም፡፡ በአሁኑ ወቅት አንድ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት አማካይ 500 እና 600 ሚሊዮን ብር ነው ያሉት አቶ ሰይፉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሠሩ ያሉት የውጭ ኮንትራክተሮች ግን ይዘው የሚቀርቡት ዓመታዊ የገንዘብ ፍሰት 15 እና 16 ቢሊዮን ዶላር በመሆኑ አገር በቀል ኮንትራክተሮች እንዲህ ያሉ ሥራዎችን እንዳይሠሩ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ተጣምሮ ለመሥራት ከተፈለገ ግን አሁንም የአቅም ማጎልበቱ ሥራ ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባም አስገንዝበዋል፡፡ ችግሩ የራሳችን የኮንትራክተሮችም ነው የሚሉት አቶ ሰይፉ፣ ራስን ማጠናከር ከሌሎች ጋር ተጣምሮ ለመሥራትም እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ኢንጂነር ሀብታሙ ደግሞ አቶ ሰይፉ በጠቀሷቸው ምክንያቶች ከአገር ውስጥ ተቋራጮች ጋር ጥምረት መፍጠር አመቺ ጊዜ ነው ተብሎ ባይገመትም፣ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ግን የተጀመሩ ሥራዎች አሉን ይላሉ፡፡
ለምሳሌ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይኖርበታል ተብሎ በሚጠበቀው የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ተክለብርሃን አምባዬ ከንስትራክሽን ፒናክል ከሚባል የሲውዚላንድ ኩባንያ ጋር ጥምረት መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ጥምረት ለቤቶች ፕሮጀክት ሥራ ተሳታፊ ለመሆን ከቀረቡ ተቋማት ውስጥ የመጀመርያውን ዙር ካለፉት 14 ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ መሆን ተችሏልም ይላሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ጥምረቶች እየተሠራባቸው መሆኑም ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ልምድ ከማግኘት ባሻገር ወደ ውጭ ወጥቶ የመሥራት ዕድል ይፈጥራል በማለት ገልጸዋል፡፡
ተክለብርሃን አምባዬና ሁለተኛው ሽልማት
ኮንስትራክሽን ኩባንያው ማብራሪያ የሰጠበት ሌላው ጉዳይ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ ሽልማት ማግኘት መቻሉን የሚመለከት ነው፡፡ ተክለብርሃን አምባዬ ለሁለተኛ ጊዜ አገኘሁ ብሎ ይፋ ያደረገውን ሽልማትን ያገኘው መቀመጫውን ስፔን ካደረገው ግሎባል ትሬድስ ክለብ ነው፡፡
እንደ አቶ ሰይፉ ገለጻ ይህ ሽልማት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ‹‹የዓለም አቀፍ ኮንስትራክሽን ሽልማት›› ነው፡፡ ይህንን ሽልማት ከተክለብርሃን አምባዬ ሌላ ከአፍሪካ ተሸላሚ የሆነው አንድ የግብፅ ኩባንያ ነው ተብሏል፡፡
በዘርፉ ሥራውን በብቃትና በጥራት በመሥራት የተሰጠ ሽልማት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰይፉ፣ በንግድ ምክር ቤቶች፣ በሽልማት ሰጪው ባለሙያዎችና በሌሎች ገለልተኛ አካላት የተደረገ ምዘናን ተከትሎ በተገኘው ውጤት የተሰጠ ሽልማት ነው ብለዋል፡፡
አቶ ሀብታሙ እንደገለጹት ደግሞ ይህንን ሽልማት ሊያገኙ የቻሉት በኮንስትራክሽን ዘርፉ በጥራት አገልግሎት በመስጠታቸው ጭምር ነው፡፡ ለተገልጋዩ ተገቢውንና ሙሉ አገልግሎት መስጠት በመቻሉ፣ ሽልማት ባገኘንባቸው ዘርፎች የደረስንበትን ደረጃ አመላካች ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ከዚህ የተሻለ በመሥራት ማለትም በሌሎች ዘርፎች ተሸላሚ ለመሆን አዲሱ የኩባንያው አደረጃጀት መልካም ዕድል ይፈጥራል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ባለፈው ዓመታትም በተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ሽልማት ማግኘቱ ይታወሳል፡፡