‹‹ዛፖሪዚያ አውቶሞቢል ቢውልዲንግ ፕላንት›› ወይም በአጭር አጠራሩ ‹‹ዛዝ›› በሚል ስያሜው የሚታወቀው የዩክሬኑ መኪና አምራች፣ በኢትዮጵያ የገጣጠማቸውን መኪኖች ለገበያ ማቅረብ መጀመሩን ይፋ አደረገ::
ኩባንያው ከአንድ ዓመት በፊት የአገር ውስጥ አጋሩ ከሆነው ኒማ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር ባደረገው የእሽሙር ስምምነት መሠረት በአዲስ አበባ ዊንጌት አካባቢ በ7,500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ዩክሬን ሠራሽ መኪኖችን የሚገጣጥም ፋብሪካ በመገንባት መኪኖችን ለገበያ ማቅረብ እንደጀመረ የኩባንያው ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡
የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ያኮቭ ዜለንዚያኮቭ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በኒማ አግሮ ኢንዱስትሪና በዛዝ ኩባንያዎች በጋራ የተመሠረተው ኒማ ሞተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አማካይነት እስካሁን ድረስ 35 መኪኖች ተገጣጥመዋል፡፡ የዩክሬኑ ኩባንያ በቀን 25 መኪኖችን ለመገጣጠም ዕቅድ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የኩባንያው የገበያና የሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ታምራት ናቸው፡፡ ሥራ አስኪያጁ ዜለንዚያኮቭ በዚህ ዓመት ብቻ እስከ 100 ተሽከርካሪዎች ለመገጣጠም ዝግጅት መደረጉን በመገልጽ፣ የኩባንያው ዕቅድም እንደሚሳካ ያላቸውን ተስፋ አስታውቀዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ሐሙስ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኘው የኒማ ሞተርስ ሽያጭ ቢሮ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት፣ የኒማ ሞተርስ ባለቤቶች የ57 ሚሊዮን ብር ካፒታል ኢንቨስትመንት አካሒደዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እያካሔዱ ያሉት ማስፋፍያዎች ጠቅላላ ኢንቨስትመንቱን ወደ 100 ሚሊዮን ብር ከፍ እንደሚያደርጉትም ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከመቶ ያላነሱ ሠራተኞችንም መቅጠራቸውንም አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፣ የአውሮፓ ሥሪት የሆኑትን መኪኖች እዚህ መገጣጠም መጀመራቸው ብቻም ሳይሆን በጄነራል ሞተርስና በዴው ሞተርስ የሚመረቱ መኪኖችን ውስጣዊና ውጫዊ ይዘቶች ያሟሉ ተሽከርካሪዎችን ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ መጀመሩም ለአገሪቱ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ላይ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው፡፡ ኩባንያው በአገር ውስጥ ለሚገጣጥማቸው መኪኖች በዚያው በመገጣጠሚያ ፋብሪካው የድኅረ ሽያጭ አገልግሎት አብሮ እንደሚሰጥም አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡
አራት ሞዴሎችን የሚገጣጥመው ኒማ ሞተርስ፣ ቼንስ፣ ቪዳ፣ ፎርዛና ሴንስ የተባሉትን የዛዝ ኩባንያ ምርት የሆኑትን ሴዳንና ሐችባክ መኪኖች አገር ውስጥ እየገጣጠመ የሚገኝ ሲሆን፣ በዋጋ ደረጃም ከ315 ሺሕ እስከ 480 ሺሕ ብር ድረስ ወይም ከ16 ሺሕ እስከ 24 ሺሕ ዶላር በሚገመት ዋጋ ለገበያ ሊቀርቡ እንደሚችሉ የኒማ ሞተርስ ድረ ገጽ ላይ የተለቀቁ የዋጋ መግለጫዎች ይጠቁማሉ፡፡
የዩክሬኑ መኪና አምራች ዛዝ የተመሠረተው እ.ኤ.አ. በ1923 እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ዛዝ ወደ ቤት አውቶሞቢል አምራችነት ከመቀየሩ ቀድሞ ሲመሠረት የግብርና ማሽነሪዎችን ለማምረት የተመሠረተ ተቋም እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከጊዜ በኋላ በሶቪየት ኅብረት መንግሥት ተወርሶ እ.ኤ.አ. እስከ 1929 ድረስ በግብርና ማሽነሪዎች አምራችነቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. ከ1954 ጀምሮ አነስተኛ የቤት መኪኖችን ‹‹ሞስቪች 401›› በሚል ስያሜ ለገበያ ማቅረብ ከጀመረ በኋላም የአውሮፓን የመኪና ገበያ ከ25 እስከ 40 ከመቶ ድርሻ መቆጣጠር ችሎ እንደነበርም ይነገርለታል፡፡ በዚያው ዓመት ወቅትም ‹‹ፊያት 600›› የተባሉ ሞዴሎች እንዲመረቱ የሶቪየት ኅብረት አውቶሞቲቭ ሚኒስቴር ውሳኔ አሳልፎ እንደነበርም የኩባንያው ቀድምት የታሪክ ድርሳናት መዝግበዋል፡፡
ዛዝ ኩባንያ እየተስፋፋ መጥቶ ወደ ዩክሬን በማቅናት እ.ኤ.አ. በ1990 አውቶዛዝ ከተሰኘው ኩባንያ ጋር በመቀላቀል አዲሱን ማምረቻ ፋብሪካ የተከለ ሲሆን፣ ዴዉ ሞተርስ ከተባለው ኩባንያ ጋር በእሽሙር ስምምነት አብሮ መሥራት የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1998 ነበር፡፡ ዴዉ ሞተርስ ትልቅ ኢንቨስትመንት በማካሔድ የራሱን ብራንድ መኪኖች ከዛዝ ጋር በማዋሐድ ማምረቱን ቀጥሎበት ቆይቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2004 ጀምሮም ከአሜሪካው ጄነራል ሞተርስ ጋር በነበረው ስምምነት መሠረት የሼቭሮሌት መኪኖችን ጨምሮ ቼሪ፣ ኪያ፣ ላዳ፣ ኦፔል እንዲሁም ሜርሴዲስ ቤንዝ ሠራሽ መኪኖችን በፋብሪካው በመገጣጠም ለምሥራቅ አውሮፓ ገበያዎች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ይህም ሆኖ ዛዝ ኩባንያ የቤት መኪኖችን፣ ቫኖችንና አውቶቢሶችን ከሥር መሠረታቸው ጀምሮ በማምረት የረጅም ዓመታት ልምድ ያለው ተቋም በመሆን በአውሮፓ የሚጠቀስ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ከሁለት ዓመታት በነበረው እንቅስቃሴ መሠረት 600 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እንዳገኘ፣ የተጣራ ገቢውም 27 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡