Sunday, June 4, 2023

ምርጫ 2007

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ እሑድ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ይካሄዳል፡፡ ምርጫውን የተሳካ ለማድረግ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አሳካን የሚሉዋቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችና ዕቅዶች የመጨረሻው ግባቸው፣ ሕዝቡ ድምፅ የሚሰጥበት ይኼው ምርጫ ነው፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መንግሥት፣ መራጩ ሕዝብ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የሕዝብ ታዛቢዎችና የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የፍትሕና የፀጥታ አካላትና ሌሎች አካላት ምርጫው በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ያከናወኗቸውን ተግባራት አጠናቀው፣ የድምፅ መስጫውን ቀን እየተጠባበቁ ነው፡፡ ቀኑም ደርሶ ሕዝብ ድምፁን ይሰጣል፡፡

በዚህ የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ ክስተቶች በተለያዩ ወቅቶች ተከስተው መፍትሔ እያገኙና እየተንጠለጠሉ፣ እንዲሁም በይደር እየቆዩ እዚህ ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ ዓይነት ክስተቶች መካከል ለአብነት ያህል በማንሳት፣ አንዳንዶቹ በምርጫው ተሳታፊ የሆኑ አካላት ያለፉበትን መንገድ መልሰው የሚያስቃኙ በመሆናቸው እንዲህ ይቀርባሉ፡፡

ከቅርቡ ክስተት  ሲጀመር ምርጫው ሊካሄድ የቀናት ዕድሜ ሲቀሩት በደቡብ ክልል በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ፣ ጊምቦ የምርጫ ክልል ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን የወከሉት የዶ/ር መብራቱ ገብረ ማርያም ደጋፊዎች፣ በግል ዕጩነት ከሚወዳደሩት ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጋር በመጋጨታቸው ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለሌላ ጊዜ አስተላልፏል፡፡ ይህ ውሳኔም ግራ መጋባትን ፈጥሮ ነበር፡፡

ቦርዱ በሕግ ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅ 532/99 ላይ የተቀመጠው አንዱ ነው፡፡

‹‹በምርጫ ሒደት የተፈጸመ የሕግ መጣስ የማጭበርበር ወይም የሰላምና ፀጥታ ማደፍረስ ድርጊት፣ በስፋቱና በዓይነቱ የምርጫውን ውጤት እንደሚያዛንፍ ከተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከግል ዕጩዎች፣ ከታዛቢዎች፣ ከምርጫ አስፈጻሚዎች ወይም ከሌላ ከማንኛውም ምንጭ መረጃ ደርሶት ተጨባጭነቱን በራሱ ማጣራት ሲያረጋግጥ፣ ወይም ተፈጽሟል ብሎ በራሱ ሲያምን ሁኔታውን የመመርመር፣ ውጤቱን የመሰረዝና አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ወይም ድርጊቱ እንዲቆም የማዘዝ፣ ጥፋተኞችም በሕግ እንዲጠየቁ ያደርጋል፤›› የሚለው አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 10 ላይ በተቀመጠው የቦርዱ ሥልጣን መሠረት ምርጫውን በተመቻቸ ሁኔታ ለማካሄድ ይቻል ዘንድ፣ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ግንቦት 13  ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ይህ ምርጫ ጣቢያ ለጊዜው ምርጫ አይካሄድበትም፡፡

ምርጫውን በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሰሌዳውን ይፋ ከማድረጉ ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ፣ በቦርዱ ዕውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ውጤታማ ለመሆንና ገዢው ፓርቲን ለማሸነፍ ትብብር መመሥረታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

የዚህ ትብብር ዋነኛ ዓላማ ደግሞ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ አሳታፊና ተዓማኒ ምርጫ በማድረግ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት፣ እንዲሁም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር እንደሆነም የትብብሩ ጸሐፊ አቶ ግርማ በቀለ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙኃን አስታውቀው ነበር፡፡

በወቅቱ ‹‹ለምርጫ ቦርድ ምንም ዓይነት ሪፖርት ማድረግ አይጠበቅብንም፤›› በማለት ተከራክረው የነበረ ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ ግን በሕግ አግባብ መሠረት ፓርቲዎች ማድረግ የሚችሉት መቀናጀት፣ መዋሀድ፣ አሊያም ደግሞ ግንባር መፍጠር እንጂ ትብብር የሚባል አሠራር በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ባለመኖሩ የትብብሩን እንቅስቃሴ ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡ አሁንም ቦርዱ በዚሁ አቋሙ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ትብብር የመሠረቱት ፓርቲዎችም የተወሰኑት ወደ ሰማያዊ ፓርቲ አባልነት ተሸጋግረው ለምርጫ ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡

በጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ያስችለኛል ያለውን የምርጫ ሰሌዳ ይፋ ያደረገበት ወቅት ነበር፡፡

ሒልተን ሆቴል በተካሄደው በቦርዱ ከፍተኛ ኃላፊዎች በተሰጠ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፣ ዝርዝር የምርጫ ሰሌዳው 30 የሚሆኑ ዓበይት ክንውኖችን በቀናት ከፋፍሎ አስቀምጦ ነበር፡፡ ከእነዚህ ዕቅዶችም ውስጥ የድምፅ መስጠትና የድምፅ ቆጠራን ጨምሮ 25 ዕቅዶች በቅደሙ ተከተል ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

የሚቀሩት አምስት ክንውኖችም የድምፅ መስጫው ዕለትን ተከትለው የሚካሄዱ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. የድምፅ ቆጠራ ውጤት በየምርጫ ጣቢያው ለሕዝብ በማስታወቂያ ሰሌዳ በይፋ የሚገለጽበት፣ ግንቦት 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በየምርጫ ጣቢያዎች የተገኙት ውጤቶች በምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት የሚደመሩበትና ውጤቱ በማስታወቂያ ሰሌዳ ለሕዝብ ይፋ የሚሆንበት፣ እንዲሁም ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚከናወነው የምርጫው አጠቃላይ ውጤት በብሔራዊ ደረጃ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚፀድቅበትና ውጤት በይፋ ለሕዝብ የሚገለጽበት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የምርጫው አጠቃላይ የጊዜ ሰሌዳን ይፋ መሆን ተከትሎ፣ የተለያዩ ፓርቲዎች በምርጫው ለመሳተፍ እያደረጉ ያሉትን ዝግጅት እየገለጹ የቆዩ የነበረ ሲሆን፣ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ በሚያወጡት መግለጫ ደግሞ የመንግሥት ጫና ከምንጊዜውም በላይ እየጠነከረ መምጣቱን ሲናገሩ ነበር፡፡

ከእነዚህ ፓርቲዎች መካከል በተደጋጋሚ እንግልት፣ ወከባና እስር በአባላቶቹ ላይ እየተፈጸመ እንደሆነ ሲገልጽ የቆየው ደግሞ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ነበር፡፡ ፓርቲው አዲስ አመራር በምርጫው ቦርድ ውሳኔ ከማግኘቱ በፊት ይህን ጉዳይ በተለያዩ መግለጫዎቹ ያስታውቅ ነበር፡፡

ለአብነት ያህልም ‹‹በአገሪቱ ላሉት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ችግሮች እስርና ወከባ መፍትሔ አይሆንም›› በማለት በኅዳር ወር በሰጠው መግለጫ፣ ፓርቲው ከምሥረታው ጀምሮ ወከባ ይደርስበት እንደነበር አስታውቆ ነበር፡፡ ‹‹በቅርብ ደግሞ ለየት ብሎ አጠቃላይ ፓርቲውን በሚያዳክም ሁኔታ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የአንድነት አባላትን እያሳደደ በማሰር ላይ ይገኛል፤›› በማለት በመንግሥት ላይ ክስ አቅርቦ ነበር፡፡

በወቅቱ መግለጫውን ሲሰጡ የነበሩት አመራሮች አንስተውት የነበረው ጉዳይ በፓርቲው አባላት ላይ እየተካሄደ የሚገኘው እስር፣ ዛቻና ወከባ ዘንድሮ የሚደረገውን ጠቅላላ ምርጫ በብቸኝነት ለማሸነፍ ነው በሚል ነበር፡፡ መግለጫውን ሰጥተው የነበሩት የፓርቲው አመራሮች በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ከፓርቲው ተወግደው፣ በምትካቸው ሌሎች በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተሰጣቸው አመራሮች ዛሬ አንድነትን ፓርቲን ወክለው በምርጫው ይወዳደራሉ፡፡

የዘንድሮ ምርጫ መጣሁ መጣሁ እያለ በነበረበት ወቅት ሌላ የብዙዎችን ቀልብ ስቦ የነበረው ክስተት ደግሞ፣ የአንድነትና የመድረክ የመለያየት ዜና ነበር፡፡ በኅዳር ወር የተሰማው የእነዚህ የሁለት ፓርቲዎች ፍቺ ዋነኛ ምክንያት፣ የትግል መስመር አካሄድና ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ሰጥተውታል የተባለ አስተያየት ነበር፡፡

ኢንጂነር ግዛቸው ሰጡ የተባለው አስተያየት አንድነት ከመድረክ ጋር ለመጓዝ መዋሀድ ብቸኛው አማራጭ ነው ማለታቸው ሲሆን፣ ይህን አስተያየት ተከትሎ መድረክ አንድነት ይቅርታ እንዲጠይቀው ያሳስባል፡፡ አንድነት በበኩሉ መድረክን ይቅርታ እንደማይጠይቅ በማስታወቁ ለመለያየታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ መድረክና አንድነት ለስድስት ዓመታት ገደማ በጋራ ሲሠሩ ነበር፡፡

ኅዳር ወርን ተሻግሮ ታኅሣሥ የደረሰው የጊዜ ቆጣሪ በዚህ ወር ደግሞ ሌሎች ከምርጫው ጋር የተገናኙ ዓበይት ክስተቶችን አስተናግዷል፡፡ በዚህ መሠረት በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው መሠረት ሦስተኛ የሥራ ክንውን ሆኖ የተቀመጠው የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በዚሁ ወር ሁለተኛ ሳምንት ተከናውኖ ነበር፡፡

በሁሉም ቀበሌዎች የተከናወነው የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ከ250,000 በላይ ታዛቢዎችን በመምረጥ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሒደቱንና ተመራጮቹን ክፉኛ ሲተቹ ቦርዱ በበኩሉ የተከናወነው ሕግን መሠረት ባደረገ መንገድ እንደሆነ ጠንከር ብሎ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

በወቅቱ ሒደቱን ክፉኛ የተቸው መድረክ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በድጋሚ እንዲካሄድ ጠይቆ ነበር፡፡ በዚህ የምርጫ ወቅት ከፍተኛውን ትኩረት ከሳቡት ዓበይት ክንውኖች እንዲሁ በዋነኛነት የሚጠቀሰው በምርጫ ቦርድ፣ በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና በአንድነት ፓርቲ መካከል ተፈጥሮ ዘለግ ያለ ጊዜ የወሰደው ውዝግብ ነበር፡፡

ቦርዱ በሁለቱ ፓርቲዎች የአመራር ሹመትና አጠቃላይ የሥራ ክንውኖች ግልጽነት ይጎድላቸዋል በማለት የየፓርቲዎቹን አመራሮች በማገድና እንደ አዲስ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት፣ ፕሬዚዳንታቸውን እንዲመርጡ ትዕዛዝ መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ ፓርቲዎቹ ግን ቦርዱ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት የለበትም በሚል ትዕዛዙን እንደማይቀበሉት ሲገልጹ ቆይተው ነበር፡፡

ፓርቲዎቹ የምርጫ ቦርዱን ውሳኔ በሚቃወሙበት ወቅት ደግሞ ከየፓርቲዎቹ የተወሰኑት አባላት የውስጥ አሠራሮችን በመቃወም መግለጫ ማውጣት ጀመሩ፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹መርህ ይከበር›› የሚሉ የአንድነት አባላት በፓርቲው ውስጥ የተካሄደውን የአመራር ለውጥ የተቃወሙ ሲሆን፣ ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ከሥልጣን በመልቀቃቸው ምክንያት፣ የፓርቲውን አመራር የተቆጣጠሩት ግለሰቦች የፓርቲውን ዴሞክራሲያዊ ባህል ሳይጠብቁ በድንገት ውጭ አገር ባለ ቡድን እጅ ጠምዛዥነት የግል አጀንዳ ባላቸው ጥቂት ግለሰቦች መፈንቅለ ሥልጣን ፈጽመዋል በማለት ተቃውሞ ተነስቶ ነበር፡፡

በተመሳሳይም መኢአድ ውስጥ ፕሬዚዳንቱ አቶ አበባው መሐሪ ወደ ሥልጣን የመጡት ምልዓተ ጉባዔው ባልተሟላ ጠቅላላ ጉባዔ ነው በማለት የተቃወሙ የፓርቲው አባላት እንዲሁ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አስገብተው ነበር፡፡

በዚህ ምክንያት ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎቹ የውስጥ ችግሮቻቸውን ፈትተው እንዲቀርቡ ታኅሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ያስታውቃል፡፡ የሁለቱም ፓርቲዎች አመራሮች ጉዳዩን ክፉኛ በመተቸት፣ ቦርዱ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውሳኔ ከአስተዳደራዊ ይልቅ ፖለቲካዊነቱ ያመዝናል በሚል ተቃውሞ አሰሙ፡፡

ቦርዱም በሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲከናወኑ ያዘዝኳቸው ትዕዛዞች በአግባቡ አልተተገበሩም በማለት በጥር ወር አጋማሽ ላይ ታሪካዊ ያለውን ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ በዚህም መሠረት አንድነት ፓርቲን በአቶ ትዕግሥቱ አወሉ ለሚመራው ቡድን ሲሰጥ፣ መኢአድን ደግሞ መጀመርያ ላይ የተመረጡበት ምርጫ ምልዓተ ጉባዔ አላሟላም ይላቸው ለነበሩት ለአቶ አበባው መሐሪ አስረከበ፡፡ ይህ የቦርዱ ውሳኔም አንድነትንና መኢአድን ይመሩ የነበሩትን አቶ በላይ ፍቃዱንና አቶ ማሙሸት አማረን ከጨዋታ ውጪ አደረጋቸው፡፡

 በዚሁ ወር ሌላው ክስተት የነበረው ደግሞ የቦርዱና የሰማያዊ ፓርቲ ይቅርታ ጠይቀኝ አልጠይቅም ውዝግብ ነበር፡፡

ፓርቲው የቦርዱን ስም አጥፍቷል በማለት ይቅርታ እንዲጠይቅ የወሰነ መሆኑን ኃላፊዎቹ የገለጹ ሲሆን፣ ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ የቦርዱና የፓርቲዎች ግንኙነት ይቅርታ ‹ጠይቀኝ አትጠይቀኝ› የሚል መሆን የለበትም አለ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ አጥፍቶ ከሆነ በሕግ ይጠየቃል እንጂ፣ ይቅርታ መጠየቅ ከሕግ አግባብ ውጪ ነው በማለት ይቅርታ እንደማይጠይቅ በመግለጽ ተቃውሞውን አሰማ፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ፓርቲዎቹ የምርጫ ዝግጅታቸውን ቀጥለው ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሕዝቡ ለመድረስ ከሚያከናውኗቸው እንቅስቃሴዎች መካከል ደግሞ በየከተማው የተደረጉት ሰላማዊ ሠልፎች ይጠቀሳሉ፡፡

በዚህ ረገድ በዘንድሮው ምርጫ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ፓርቲዎች ይጠሯቸው የነበሩት አብዛኛዎቹ ሠልፎች ወይ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ዕውቅና ሳይሰጣቸው ቀርቶ በግብግብ ተጠናቀዋል፡፡ አሊያም ደግሞ ፓርቲዎች በሚፈልጉት ሳይሆን በሚዘጋጅላቸው ሥፍራ ሠልፉን እንዲያከናውኑ በመደረጉ በተቃውሞ ታጅበዋል፡፡

ከዚህ አንፃር የምርጫ ቦርድ አንድነት ፓርቲን ለአቶ ትዕግሥቱ አወሉ መስጠቱን ለመቃወም ለጥር 17 ቀን 2007 የተጠራው የተቃውሞ ሠልፍ የተበተነው፣ በፓርቲው አባላትና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግብግብ ነበር፡፡

በዕለቱ ፓርቲው ለጠራው ሠልፍ ምንም ዓይነት ፈቃድም ሆነ ዕውቅና እንዳልሰጠ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የገለጸ ሲሆን፣ ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ የለብኝም የሚለው ፓርቲው ደግሞ በዕቅዱ መሠረት የሠልፍ መነሻውን የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ከሚገኝበት ቀበና ተነስቶ፣ በአራት ኪሎና በፒያሳ በማድረግ መድረሻውን የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ (ድላችን ሐውልት) ለማድረግ አቅዶ ነበር፡፡

ሆኖም ሠልፉ ከፓርቲው ጽሕፈት ቤት በተወሰኑ ሜትሮች ርቀት ላይ በፀጥታ ኃይሎች አማካይነት ሕገወጥ መሆኑ ተገልጾ እንዲበተን ተደርጓል፡፡ በመሀል በተፈጠረ ግጭትም በርካታ የፓርቲው አባላት የፀጥታ ኃይሎችን ዱላ ቀምሰው ነበር፡፡ ይህም በአጠቃላይ ባይሆንም የበዛውን የዘንድሮ የሠልፍ ውጣ ውረድ የሚያሳይ ክስተት ነበር፡፡

ምርጫ ቦርድ በመኢአድና በአንድነት ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ፣ አብዛኛዎቹ የአንድነት አባላት ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቅለው እንደሚታገሉ የገለጹት በጥር ወር መጨረሻ ላይ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት የፓርቲው አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ፣ ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ ፀጋዬ አላምረው፣ እንዲሁም የፓርቲው የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት አቶ ስንታየሁ ቸኮልን ያካተተ ቡድን በሰማያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ የፓርቲው አባል መሆን የሚያስችለውን ፎርም በመሙላት ፓርቲውን በይፋ ተቀላቀሉ፡፡ በወቅቱም ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር መግለጫ ሰጡ፡፡

ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቅለው ሥራ እየሠሩ ከነበሩት የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አባላት መካከል አቶ ስንታየሁ ቸኮል መስቀል አደባባይ አይኤስን ለማውገዝ የተጠራው ሠልፍ በግጭት እንዲጠናቀቅ ካደረጉት ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው ተብለው፣ የስድስት ወራት እስራት ተፈርዶባቸው አሁን ማረሚያ ቤት ይገኛሉ፡፡

በዚሁ ወር መጨረሻ ላይ እንዲሁ በምርጫ ቦርድ አማካይነት ዕውቅና የተሰጠው የአቶ ትዕግሥቱ አወሉ አመራር ቀበና አካባቢ የሚገኘውን የፓርቲውን ጽሕፈት ቤት ተረክቦ፣ ለምርጫው ይረዱኛል የሚላቸውን ተግባራት ለማከናወን መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

የምርጫ ክንውን ማካሄጃው ቀን እየቀረበ ሲመጣና ጥቂት ወራት ሲቀሩት፣ የአብዛኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን አትኩሮት በዚሁ የምርጫ ጉዳይ ላይ ሆነ፡፡

በተመሳሳይ በየካቲት ወር የአብዛኞቹን ዜጎች ትኩረት ስቦ የነበረው ክስተት ደግሞ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ከሌሎች ሁለት የፓርቲው ሴት ዕጩዎች ጋር በዕጣ ተለይተው ከምርጫው ውጪ የመሆናቸው ጉዳይ ነበር፡፡

በዚሁ ወቅት ሌላው አነጋጋሪ የነበረው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የመንግሥት ቃል አቀባይ የነበሩት ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ፣ እንዲሁ በዕጣ ተለይተው ከምርጫው ውጪ የመሆናቸው ክስተት ነበር፡፡

ወ/ሮ ሰሎሜ፣ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንትና ሌሎች የፓርቲው ሴት ዕጩዎች ከምርጫ ውድድር ውጪ የሆኑት ደግሞ በምርጫ ሕጉ መሠረት በአንድ የምርጫ ጣቢያ መወዳደር የሚችሉት ተወዳዳሪዎች ብዛት 12 እንደሆነ በሚያዘው ሕግና ከዚያ ካለፈ ደግሞ ዕጩዎች በዕጣ የሚለዩ በመሆናቸው ምክንያት ነው፡፡ ይህ መሥፈርት ቅድሚያ የሚሰጠው ለፓርቲዎች ሲሆን፣ የግል ዕጩዎች ዕጣ ውስጥም ሳይገቡ ከውድድር ሊወጡ ይችላሉ፡፡

የምርጫው ወቅት መዳረስን ተከትሎ ፓርቲዎች ያሉዋቸውን አማራጭ ሐሳቦች የሚገልጹበት የምርጫ መወዳደርያ ማኒፌስቶአቸውን ይፋ ማድረግ የጀመሩበት ወር እንዲሁ የካቲት ነበር፡፡

በዚህም መሠረት በዘንድሮ ምርጫ ከሚካፈሉት ፓርቲዎች መካከል ማኔፌስቶውን በየካቲት ወር ይፋ በማድረግ የመጀመርያ ፓርቲ የሆነው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ነበር፡፡ ፓርቲው 30 ገጾች ያሉትን የዘንድሮ የምርጫ መወዳደርያ ማኔፌስቶውን ይፋ የደረገው የካቲት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡

ኢዴፓን ተከትሎ የምርጫ መወዳደርያ ማኒፌስቶውን ይፋ ያደረገው ደግሞ መድረክ ነው፡፡ መድረክ ባለ 13 ገጽ ማኒፌስቶውን ይፋ ያደረገው በመጋቢት ወር መጀመርያ ላይ ነበር፡፡ በተመሳሳይም በዚሁ ወር አጋማሽ ላይ እንዲሁ ሰማያዊ ፓርቲም የምርጫ መወዳደርያ ማኒፌስቶውን ይፋ አድርጓል፡፡

በምርጫው ፉክክር የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት፣ እንዲሁም ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ማስመዝገብ እየተሟሟቀ ባለበት ጊዜ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ በኢሕአዴግ ስም የተመዘገቡ ዕጩዎች እንዲሰረዙ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለምርጫ ቦርድ አስገባ፡፡

ፓርቲው በዚህ ደብዳቤው የጠየቀው በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 573/2000 አንቀጽ 2(9) ‹‹ግንባር›› ማለት ‹‹ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተናጠል ሕጋዊ ህልውናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ የሆነ ስያሜ፣ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደርያ ደንብ ኖሯቸው ለመንቀሳቀስ ሲወስኑ የሚደራጅ አካል ነው፤›› የሚለውን የአዋጁን አንቀጽ መሠረት በማድረግ ኢሕአዴግ የሚባል ፓርቲ የሌለ በመሆኑ ቦርዱ በዚህ ፓርቲ የቀረቡለትን ዕጩዎችን እንዲሰርዝ ነበር፡፡

ዕጩዎች ተመዝበው ከተጠናቀቀ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአርሶ አደርና ከአርቲስት ጋር እንደሚወዳደሩ የታወቀው በሚያዝያ ወር መጀመርያ ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመወዳደር ቀርበው ከነበሩት ዕጩዎች መካከል መድረክን ወክለው ይወዳደሩ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኃይሌ የተባሉ አርሶ አደር፣ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን አስታውቀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተፎካካሪዎች ቁጥር ቀንሷል፡፡

ምርጫው ሊካሄድ የአንድ ሳምንት ጊዜ ሲቀረው የመኢአድ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋሁን አለምነው የትጥቅ ትግል ለማድረግ ወደ ኤርትራ ሄደዋል የሚሉ ዘገባዎች ቢወጡም፣ ፓርቲው ግን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው የት እንደሚገኙ አላውቅም ብሎ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ሳምንት ለዘጠኝ ዙሮች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይካሄድ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክር በውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ተደርጎ ተጠናቋል፡፡

ምርጫ 2007 ለፓርላማ 547 መቀመጫዎች ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ ዕጩዎች ጠቅላላ ብዛት 1,827 ሲሆን፣ ለክልል ምክር ቤቶች 3,956 ዕጩዎች ይወዳደራሉ፡፡ እስካሁን 319 ሚሊዮን ብር እንደወጣበት በምርጫ ቦርድ የተነገረለት የዘንድሮ ምርጫ ከ36.8 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡበት ሲሆን፣ በ46 ሺሕ የምርጫ ጣቢያዎች ድምፃቸውን እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ በምርጫው 58 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይወዳደራሉ፡፡ ዘጠኝ ግለሰቦች ደግሞ በግል ቀርበዋል፡፡ መራጩ ሕዝብ ድምፁን ሰጥቶ ካበቃ በኋላ ቆጠራ የሚካሄድ ሲሆን፣ ውጤቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካልተነገረ በስተቀር ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሆነ አካል ውጤት መናገር እንደማይችል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -