Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ተለይተው እንዲቀርቡ ታዘዘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ግንባታ መሬት እንዲሰጣቸው ጥያቄ ካቀረቡ 600 ኢንቨስተሮች መካከል፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ ፕሮጀክቶችን ለይቶ እንዲያቀርብ ለአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊነት ተሰጠ፡፡ በአቶ ዮሐንስ በቀለ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ቢሮ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ያላቸውን ፕሮጀክቶች በመለየት ለመጀመርያ ዙር ውይይት ሰሞኑን አቅርቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሁለተኛው ዙር ጥናት ተጠናቆ ለካቢኔ ቀርቦ ከፀደቀ በኋላ የማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክቶች የቦታ ጥያቄ ምላሽ ያገኛል፡፡

ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላ ባለፈው ዓመት ለኢንዱስትሪ ልማት የሚውል ቦታ ለአልሚዎች ለማቅረብ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ቦታ ለመስጠት ማስታወቂያ ካስነገረ በኋላ 600 አልሚዎች የቦታ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ነገር ግን በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ፕሮጀክቶች ለይቶ ባለማስቀመጡ ከጥቃቅንና አነስተኛ ፕሮጀክቶች አንስቶ፣ እስከ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ድረስ ያሉ የቦታ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ የፕሮጀክቶቹ ተደበላልቆ መቅረብ ያሳሰበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የቦታ ጥያቄ መቀበል እንዲቆምና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ፕሮጀክቶች ተለይተው እንዲቀርቡ አዟል፡፡

አቶ ሰለሞን እንደገለጹት፣ ለቀረቡ ፕሮጀክቶች በሙሉ ቦታ ሊሰጥ አይችልም፡፡ መሬት አላቂ ሀብት እንደመሆኑ ከተማው ለሚፈልጋቸው ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት የመሬት ዝግጅት እየተካሄደ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ያልተያዘ መሬት የሌለ በመሆኑ የካሳ ክፍያ እየተፈጸመ የመሬት ዝግጅት እየተካሄደ ነው፤›› በማለት አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባለሙያዎች፣ እስካሁን ድረስ 70 የሚጠጉ ፕሮጀክቶችን በመለየትና በመተንተን ካቢኔው ውሳኔ እንዲሰጥ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡

ነገር ግን ካቢኔው በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ብቻ ሳይሆን ለአገልግሎት ዘርፍ የቀረቡ የቦታ ጥያቄዎችንም እያስተናገደ አለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ካቢኔው ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚቀርቡ የቦታ ጥያቄዎችን የማያስተናግደው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ለመለየት ቢሆንም፣ ለአገልግሎት ዘርፍ የሚቀርቡ የቦታ ጥያቄዎችን የማይወሰነው ግን በተለያዩ ጉዳዮች በመጠመዱና በሊዝ አዋጁ ምክንያት መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች