Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሚድሮክ የፒያሳውን መሬት ለማልማት አዲስ ውል ገባ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲስ በተከለሰው የአካባቢ ልማት ጥናት መሠረት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ እህት ኩባንያ ሁዳ ሪል ስቴት መሀል ፒያሳ ለመገንባት ያቀደው መንታ ሕንፃ ከፍታ እንዲያጥር በመወሰኑ አዲስ የውል ዕድሳት ተደረገ፡፡

በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ሥር የሚገኘውን ሁዳ ሪል ስቴት በመወከል አቶ አብነት ገብረ መስቀል፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከወ/ሮ አፀደ ዓባይ ጋር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተፈራርመዋል፡፡

በአዲሱ ስምምነት መሠረት ሁዳ ሪል ስቴት ቀደም ሲል ይዞት የነበረውን ባለ48 ፎቅ መንታ ሕንፃ ግንባታ ዕቅድ በመሰረዝ፣ አራት ወለል ያለው ግዙፍ የገበያ ማዕከል (ሞል) ለመገንባት አቅዷል፡፡

ሁዳ አዲሱን የሕንፃ ዲዛይን አሠርቶ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ ፕላን ኢንስቲትዩት አቅርቦ ማስተቸቱን፣ የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎችም ለቀረበው ዲዛይን አዎንታዊ ምላሽ እንደሰጡ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እየተዘጋጀ ባለው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን መሠረት ያደረገ የአካባቢ ልማት ጥናት ተካሂዷል፡፡ በጥናቱ መሠረት ፒያሳ የቆየ የከተማው ክፍል እንደመሆኑ መጠን፣ ከዚህ በኋላ የሚካሄዱ ልማቶች ከነባር ግንባታዎች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ተወስኗል፡፡

አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፣ ሁዳ ሪል ስቴት ያቀደው ግንባታ በዚህ መሠረት ተጣጥሞ መካሄድ ስላለበት የውል ዕድሳት እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ ሁዳ ሪል ስቴት ከ18 ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተረከበው 34,500 ካሬ ሜትር ቦታ ታጥሮ ቆይቷል፡፡ ሁዳ ሪል ስቴት 48 ፎቅ ከፍታ ያላቸውን መንታ ሕንፃዎችን፣ እንዲሁም ሌሎች ባለአራትና ስድስት ፎቅ ከፍታ ያላቸውን ሕንፃዎች ለመገንባት ዲዛይኑን አቅርቦ ቢያፀድቅም ግንባታው ግን መካሄድ አልቻለም፡፡  

በአካባቢው የተካሄደው ግንባታ መሠረት የማውጣት (ፋውንዴሽን) ብቻ ሲሆን፣ ይህ ፋውንዴሽን አራት ፎቅ ከፍታ ያለው ሞል ይገነባበታል ተብሏል፡፡ አቶ ሰለሞን እንዳሉት፣ አዲሱ የሁዳ ሪል ስቴት ዲዛይን በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲደረግ በተካሄደው ውይይት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ይህንን የሁዳ ሪል ስቴት ፕሮጀክት በቅርብ ይከታተሉ የነበሩት የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በነባሩ መሠረት ላይ (ፋውንዴሽን) አዲሱን ባለአራት ፎቅ ሕንፃ መገንባት ጉዳት የለውም፡፡

ይህ ፕሮጀክት ሊዘገይ የቻለበት ምክንያት አቶ ኃይሌ ሲናገሩ በአስተዳደሩም ሆነ በሁዳ ሪል ስቴት በኩል ችግር ነበር፡፡ ‹‹በወቅቱ ማንም የማያውቀውና በፕላን ያልተያዘ የቴሌና የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ተገኝቷል፤›› በማለት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለፕሮጀክቱ መዘግየት ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ግዙፎቹ መንታ ሕንፃዎች ተገንብተው ቢሆን የፍሳሽ መስመር ባለመኖሩ ከፍተኛ ችግር ሊፈጥር ይችል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ሚድሮክ ለመገንባት ያቀደው አዲሱ ዲዛይን ሙሉ በሙሉ ባለመጠናቀቁ በጀቱ ምን ያህል እንደሆነ አለመታወቁን አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች