በአዲስ አበባ ከተማ በዋና ዋና ጐዳናዎች ላይ ከ132.6 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ መንገድ ጠቋሚ ምልክቶችን ለማኖር፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከአንድ አገር በቀል ኩባንያ ጋር ተፈራረመ፡፡ ከ388 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ አምስት የመንገድ ግንባታዎች ለኮንትራክተሮች ተሰጡ፡፡
ዓርብ ግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ ዋና መሥሪያ ቤት በተደረገው የኮንትራት ስምምነት ላይ እንደተገለጸው፣ በአዲስ አበባ በ52 መንገዶች ላይ የታቀዱትን መንገድ ጠቋሚ ምልክቶች ለመትከል ጨረታውን አሸንፎ ሥራውን የተረከበው፣ ዩኢ ኢንደስትሪያል የተባለው ኩባንያ ነው፡፡ በዚህ ጨረታ ላይ ሦስት ኩባንያዎች ተወዳዳሪ ቢሆኑም፣ ዩኢ ኢንደስትሪያል ያቀረበው ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ አሸናፊ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከዩኢ ኢንደስትሪያል ጋር ተፎካካሪ በመሆን ቀርበው የነበሩት ጐልድስቶን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ 145.2 ሚሊዮን ብር፣ ሲልክ ትሬዲንግ ኢንተርናሽናል ደግሞ 160.1 ሚሊዮን ብር አቅርበው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመንገድ ጠቋሚ ምልክቶቹን ለመትከል አሸናፊ የሆነው ኩባንያ ከ700 በላይ የሚሆኑ ምልክቶችን ተክሎ የሚያጠናቅቀው የኮንትራት ውሉ ከተፈረመበት ቀን አንስቶ በ270 ቀናት ውስጥ እንደሆነ በኮንትራት ስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡ ምልክቶቹ አንፀባራቂ በሆነ አልሙኒየም የሚዘጋጁ ናቸው ተብሏል፡፡ ምልክቶቹ የመንገድ ስያሜዎችን፣ ርዝመትና ሌሎች መረጃዎችን የሚይዙ መሆኑን፣ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ምልክቶች የሚታዩት በቀለበት መንገዱ ላይ ብቻ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ 5.73 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸውን አምስት የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶችን ለማስገንባት ባለሥልጣኑ ከአራት ኮንትራክተሮች ጋር ስምምነት ፈጽሟል፡፡ በጥቅሉ ከ388.3 ሚሊዮን ብር በላይ ከሚወጣባቸው ከአምስቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ እንይ ኮንስትራክሽን የሁለቱን ፕሮጀክቶች ጨረታ አሸንፏል፡፡
እንይ ኮንስትራክሽን ያሸነፈው አንዱ መንገድ ከሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ እስከ ቅድስት ማርያም – ምኒልክ ሆስፒታል – ጃንሜዳ ድረስ የሚዘልቀው 1.7 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ነው፡፡ ይኼንን መንገድ በ74.9 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባው ታውቋል፡፡ እንይ ኮንስትራክሽን ከዚህ ፕሮጀክት በተጨማሪ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ግቢ ውስጥ የአስፋልትና የኮብልስቶን መንገድ ለመገንባት የወጣውን ጨረታም አሸንፎ ሁለት የኮንትራት ስምምነቶችን ፈጽሟል፡፡
ሁለተኛውን የኢሲኤ ፕሮጀክት ያሸነፈበት ዋጋ 27.7 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የኢሲኤ የአስፋልትና የኮብልስቶን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ግማሽ ኪሎ ሜትር በአስፋልትና በኮብልስቶን ሲሆን፣ የመኪና ማቆሚያና የአስፋልት መንገድ ነው ተብሏል፡፡ የኢሲኤው ሥራ በ35 ቀናት መጠናቀቅ እንዳለበት ተገልጿል፡፡
ይህ ፕሮጀክት በፍጥነት ተሠርቶ እንዲያልቅ የተፈለገው ከሐምሌ 3 ቀን እስከ ሐምሌ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የፋይናንሲንግ ፎር ዴቨሎፕመንት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ከመካሄዱ በፊት ለማድረስ እንደሆነ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡
ከአቦ አደባባይ – ብሥራተ ገብርኤል ድረስ ያለውን 1.4 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ለማከናወን ጨረታውን በማሸነፍ ሥራውን የተረከበው አይኤፍኤች ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ 30 ሜትር ስፋት ያለውን መንገድ ለመገንባት አይኤፍኤች አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 99.4 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ሥራውም በ365 ቀናት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
የኮንትራት ስምምነቱ እንደሚያመለክተው ከሽሮሜዳ – ሐመረ ኖህ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለውን 2.1 ኪሎ ሜትር መንገድ እንዲገነባ ጨረታውን ያሸነፈው የማነ ግርማይ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ይህንን መንገድ ለመገንባት አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 187.02 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ መንገዱ ጠባብ በመሆኑ አሁን በ20 ሜትር ስፋት በአስፋልት ኮንክሪት ይገነባል፡፡ በስምምነቱ መሠረት መንገዱ 540 ቀናት ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡