ከንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እስከ ደርግ ሥርዓት ሶማሊያን አብጠርጥረው በማወቅና ከኢትዮጵያ ወገን የሶማሌ ክልልን በማስተዳደር፣ ብዙ እንደሠሩ የሚነገርላቸው ቀኝ አዝማች ግርማ አበበ በተወለዱ በ86 ዓመታቸው አረፉ፡፡
ቀኝ አዝማች ግርማ መንግሥታዊ ኃላፊነት ባለባቸው የሥራ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ከ1943 ዓ.ም. ጀምሮ በጡረታ እስከተገለሉበት እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ በተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች እየተሾሙ አገልግለዋል፡፡ በ1943 ዓ.ም. የጋራ ሙለታ አውራጃ ዋና ፀሐፊ በመሆን የተመደቡ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜም በአውራጃው ዘመናዊ ትህምርት እንዲስፋፋ ማድረጋቸውን ሐሙስ ግንቦት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው በተፈጸመበት ወቅት የተነበበው የሕይወት ታሪካቸው ይዘክራል፡፡
በ1965 ዓ.ም. የኤልከሬ አውራጃ ገዥ፣ በ1966 ዓ.ም. የገናሌ አውረጃ ገዥ፣ በዚያው ዓመት የጅጅጋ አውራጃ ገዥ፣ እንዲሁም በደርግ መንግሥት በ1967 ዓ.ም. የጨርጨር አውራጃ ገዥ በመሆን ያገለገሉት ቀኝ አዝማች ግርማ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ግንኙነት መንግሥታቱን በመምከርና መተግበር አለባቸው ስለሚሏቸው የአስተዳደር ሥርዓቶች ሲናገሩም ይታወቃሉ፡፡ ቀኝ አዝማች ግርማ የሶማሊያን ታሪክ በአራቱም አቅጣጫ አብጠርጥረው ያውቃሉ ከሚባሉ ጥቂት አንጋፋ ሰዎች አንዱ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለሶማሌ ላንድ ዕውቅና የመስጠት የህልውና ግዴታ አለባት፤›› በማለት የተናገሩት የሚታወስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ የአልሸባብ ጥቃቶችን ለመመከት ጥሩ አማራጭ አድርገው ከሚያቀርቧቸው የመፍትሔ ሐሳቦች አንዱ የሆነው ለሶማሌ ላንድ እንደ አገር ዕውቅና መስጠትን ሲሆን፣ ምንም እንኳ የሞቃዲሾ ሶማሊያም ኢትዮጵያን በድንበር የሚያዋስን አገር ቢሆንም፣ የሶማሌ ላንድ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ካለው ወዳጅነት፣ ካለው የባህር በርና ሌሎች የኢኮኖሚ ጥቅሞች አኳያ መንግሥት ለሶማሌ ላንድ ዕውቅና መስጠት አለበት ብለው ያምኑ ነበር፡፡
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንግሊዞች የኢትዮጵያን ጦር ለመርዳት መጥተው እንደነበር ለሪፖርተር ሲያስረዱ እንዳስታወሱት፣ በኦጋዴን ማረፊያቸውን አድርገው በቆዩ ጊዜ ሐርጌሳንም ይዘው ስለነበር፣ የኬንያ ሶማሌን ጨምሮ አምስቱን ሶማሌዎች በማዋሀድ አንድ አድርገው ለመግዛት አቅደው ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ግን በ1941 ዓ.ም. ኦጋዴንን ለኢትዮጵያ ቢያስረክቡም፣ እንግሊዞች የኦጋዴንን ባላባቶች በመደለል ከኢትዮጵያ እንዲገነጠሉ ለማድረግ ሲሞክሩ እንደነበር ቀኝ አዝማች ግርማ አስታውሰዋል፡፡
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ከኦጋዴን ባሻገር ደገ ሃቡርንና ጅግጅጋን ከእንግሊዞች እጅ ቢረከብም፣ እግሊዞች ግን ጂቡቲን ጨምሮ የኬንያ ሶማሌን፣ ሶማሌ ላንድን፣ በወቅቱ በጣሊያን እጅ የነበረችውን ሞቃዲሾ ሶማሌን አንድ ላይ አዋህደው የመግዛት ሐሳባቸው አልተገታም ነበር፡፡ እንግሊዞች እንዳሰቡት አምስቱን ሶማሌዎች በማዋሀድ አንዲት የሶማሊያ አገር ለመመሥረት የነበራቸው ዕቅድ በኢትዮጵያ መንግሥት የወቅቱ ፖለቲካ እየጠነከረ መምጣት፣ በኦጋዴን በተነሳ ተቃውሞ ምክንያት ህልማቸው ሳይሳካ ቀርቷል የሚሉት ቀኝ አዝማች ግርማ፣ እንግሊዞች በእጃቸው ለነበሩት ሶማሌ ላንዶች ነፃነት ለመስጠት መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ግን የሞቃዲሾ አዲሱ አስተዳደር የአምስቱን ሶማሌዎች ውህደት ዕውን ለማድረግ ሶማሌ ላንድን ወዲያውኑ ወደ ራሳቸው በመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያም መምጣት ጀምረው ነበር፡፡ በዚህ አካሄዳቸውም የኢትዮጵያን ሶማሌ ለመገንጠል የመጀመሪያውን ወረራ በ1956 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ እንደፈጸሙ ቀኝ አዝማች ግርማ ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ የሞቃዲሾ ሶማሊያ ከሶማሌ ላንድ መለየት የአምስቱን ሶማሌዎች ውህደትና የታላቋን ሶማሊያ መመሥረት ህልም ቢያከሽፍም፣ ሞቃዲሾ አሁንም ድረስ በሕገ መንግሥቷ ውስጥ ያስቀመጠችው በመሆኑ ይህ አቋም አሁንም ድረስ ለኢትዮጵያና ለሌሎች አገሮች ሥጋት እንደሆነ ቀኝ አዝማች ግርማ ዕምነታቸውን ገልጸው ነበር፡፡
‹‹ለጦርነት ስትራቴጂም ሆነ ለፖለቲካ ከሶማሌ ላንድ ጋር መተቃቀፉ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም ይሰጣታል፤›› ያሉት ቀኝ አዝማች ግርማ፣ ለኢትዮጵያ ደኅንነትና ለወሰኗ መከበር ሶማሌ ላንድ ወሳኝ ሚና እንዳላት ገልጸው ነበር፡፡ ለሶማሌ ላንድ ዕውቅና መስጠት አፍሪካውያን ከቅኝ ገዦቻቸው በተረከቡት ወሰን ይፅኑ በሚለው ስምምነት መሠረትም ሶማሌ ላንድ ዕውቅና ማግኘት እንደሚገባት፣ ሞቃዲሾም በዚህ ስምምነት መሠረት ሶማሌ ላንድን ለግዛቷ አካልነት የምትጠይቅበት ምንም ዓይነት የታሪክ አብነት የላትም ብለዋል፡፡
ቀኝ አዝማች ግርማ ከወረዳ አስተዳዳሪነት እስከ ምክትል ገዥነት ከዚያም በዋና አገረ ገዥነት በተለያዩ ደረጃዎች የሶማሌ ግዛትንና የሐረር አውራጃዎችን ማስተዳደራቸው ይገራል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ አራት ጊዜ የተለያየ ሹመት ተሰጥቷቸው አስቸጋሪውን የሶማሌ ክልል፣ ከአጎራባቾቹ ሶማሌ ላንድና ከሞቃዲሾ ሶማሊያ ጋር ተፋጠው እንዳስተዳደሩም የሕወይት ታሪካቸው ይዘክራል፡፡
የሁለት ወንዶችና የአንድ ሴት ልጅ አባት የነበሩት ቀኝ አዝማች ግርማ፣ በቀድሞው ሐረርጌ ክፍለ ሀገር በሐብሮ አውራጃ፣ ገለምሶ ከተማ ተወልደው አድገዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት 60ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸው በትዳር አብረዋቸው ከኖሩት ከወ/ሮ ጥሩ ወርቅ ሽፈራው ካፈሯቸው ልጆች በተጨማሪ የአሥር ልጆች አያትና የሁለት ልጆች ቅደመ አያት ለመሆን በቅተዋል፡፡ በሚያዝያ ወር ባለቤታቸው ከዚህ ዓለም ሲለዩ፣ ቀኝ አዝማች ግርማ ከወር በኋላ ተከትለዋቸዋል፡፡
ከመንግሥት አገልግሎት በጡረታ ከተገለሉ በኋላ በ1984 ዓ.ም. የሐረርጌ ተወላጆችና ነዋሪዎች መረዳጃ ማኅበርን በመመሥረትና በምክትል ሰብበሳቢነት በመምራት ተሳትፈዋል፡፡