Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኦሮሚያ ክልል አምስት በካይ ፋብሪካዎችን ዘጋ

የኦሮሚያ ክልል አምስት በካይ ፋብሪካዎችን ዘጋ

ቀን:

ከአዲስ አበባ ዙሪያ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ አምስት በካይ ፋብሪካዎች መዝጋቱን የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በበኩሉ ከተማውንና ዙሪያውን የሚገኙ የኦሮሚያ አካባቢዎችን የሚበክሉ ፋብሪካዎችን ቢያግድም፣ ዕግዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ትዕዛዝ ተነስቶ፣ ተጨማሪ የዕፎይታ ጊዜ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ጥበቃ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሐሰን የሱፍ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከአዲስ አበባ መቶ ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ በሚገኙ ፋብሪካዎች ላይ የአካባቢ ጉዳዮች አፈጻጸም የሚዳስስ የአንድ ዓመት ጥናት ተካሂዷል፡፡

‹‹በጥናቱ በተለይ የብክለት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ፋብሪካዎች በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፣ አመራረታቸውን ሊያስተካክሉ ባለመቻላቸው እንዲዘጉ ተደርገዋል›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የተዘጉት ፋብሪካዎች በሰበታ የሚገኘው አፈዳ ቆዳ ፋብሪካ፣ ቢሾፍቱ የሚገኙት ወንደር ፒቪሲ ፋብሪካና ኤልፎራ ዶሮ ዕርባታ፣ አደቡ አቦቴ የሚገኘው ኢስት ሲሜንት፣ ጉጂ ዞን የሚገኘው ቀንጢቻ የታንታለም ማዕድን ማምረቻ ናቸው፡፡

ዋና ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ በተለይ አፈደ ቆዳ ፋብሪካ ተረፈ ምርቱን በቀጥታ ወደ ወንዝ ይለቃል፡፡ በታችኛው አዋሽ ተፋሰስ በመስኖ እርሻ ሥራ ተሰማርተው የሚገኙ አርሶ አደሮች በተበከለው ውኃ ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጡ ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት እየሠራ መሆኑን፣ በአዋሽ ተፋሰስ ክልል ውስጥ በተለይ በአዲስ አበባ የሚገኙ በካይ ፋብሪካዎች ዕጣ ፈንታ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር እየመከረ መሆኑ ታውቋል፡፡

‹‹ከአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ከወር በፊት ስድስት በካይ የቆዳ ፋብሪካዎች ላይ ዕርምጃ ቢወስድም፣ ፋብሪካዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቅሬታ በማቅረባቸው ተጨማሪ የስድስት ወራት ዕፎይታ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ፋብሪካዎች ከዚህ ቀደም የአምስት ዓመት የማስተካከያ ጊዜ ተሰጥቷቸው አልተጠቀሙበትም፡፡ አሁን ደግሞ የስድስት ወራት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በከተማው የሚገኙ ስድስት በካይ የቆዳ ፋብሪካዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን፣ በኋላም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የወሰደው ዕርምጃ መቀልበሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ