የሰው ሕይወት በከንቱ እየጠፋ አሁንም ችግር በችግር ላይ እየተደራረበ የአገር ህልውናን እየተፈታተነ ነው፡፡ ሰሞኑን በሐረር ከተማ ሐማሬሳ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል በተቀሰቀሱ የተለያዩ ግጭቶች በርካቶች ሞተዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልል የደረሱ አደጋዎችን መፍትሔ ፈልጎ ማስቆም ሲገባ፣ በፖለቲካ አመራር ውድቀት ምክንያት ከፍተኛ ጥፋት ደርሷል፡፡ በተለያዩ ግጭቶች ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ንፁኃን ዜጎች ደም ሳይደርቅ ሌላ እየተጨመረ ሕዝብ እየተሳቀቀ ነው፡፡ በአገር ደረጃ ላጋጠሙ ዙሪያ ገብ ችግሮች ከሕዝብ ጋር በመነጋገር ፍቱን መፍትሔ ለማግኘት መረባረብ ሲገባ፣ በፖለቲካው ውስጥ ባሉ ባለድርሻ አካላት የፖለቲካ ቁማር ምክንያት የአደጋው አድማስ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰፋ ነው፡፡ መንግሥትን የሚመራው ኢሕአዴግ ከተሃድሶና ከግምገማ ስብሰባዎች በኋላ መግለጫዎችን ቢደረድርም፣ አሁንም ተቃውሞዎች እየቀጠሉ የሰው ሕይወትም እየጠፋ ነው፡፡ የአገር አንጡራ ሀብትም እየወደመ ነው፡፡ ችግሩን ከሥር መሠረቱ አውቆ መፍትሔ አለመፈለግ ለባሰ ቀውስ ይዳርጋል፡፡
የኢሕአዴግ አመራሮች ውስጣቸው በተፈጠረ መቃቃር ምክንያት መናበብ ባለመቻላቸው ምክንያት ችግሮች ሲፈጠሩ ገፈት ቀማሹ ሕዝብ እየሆነ ነው፡፡ ሕዝብ ላቀረባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ ስለማይሰጥ ተቃውሞዎች የበለጠ እየተጋጋሙ ሲሄዱ ግጭት ይፈጠራል፡፡ ተቃውሞን ለማስቆም የሚሰጠው ምላሽ ኃይል እየተቀላቀለበት የሰዎች ሕይወት ያልፋል፡፡ በሕዝብ ሕይወት ላይ መቆመር ውጤቱ አስከፊ ከመሆኑም በላይ በአገር ህልውና ላይ አደገኛ ቀውስ ይጋርጣል፡፡ አገርን መምራት ጥበብ ይፈልጋል፡፡ የመጀመርያው ጥበብ የሕግ የበላይነትን በማስከበር የሕዝብ ደኅንነትን መጠበቅ ነው፡፡ ይህ መሆን ስላልቻለ ግን በየጊዜው የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፡፡ የፖለቲካ አመራሩ አገሪቱ ለገጠማት ሕመም የሚፈውስ መደኃኒት ከመፈለግ ይልቅ፣ ማስታገሻ እየሰጠ በችግር ላይ ችግር እየደራረበ ነው፡፡ ነጋ ጠባ ተግባራዊ የማይሆን መግለጫ ከማንጋጋትና በተለያዩ ገጽታዎች ተቃውሞዎች እንዲቀሰቀሱ ምክንያት ከመሆን ይልቅ፣ የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎት ተረድቶ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ይገባ ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን የዜጎች ሕይወት እንደ ቀልድ እየጠፋ ነው፡፡
መንግሥትንና ሕዝብን ከሚያጋጩ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ መንግሥት ሕዝብን አለማዳመጡ መሆኑ ብዙ ተብሎበታል፡፡ ኢሕአዴግ ዘግይቶም ቢሆን ይህንን ችግር ቢያምንም፣ አሁንም መደማመጥ ያለ አይመስልም፡፡ ሕዝብ በሚፈለገው ደረጃ ቢደመጥ እንኳንስ የሰውን ሕይወት የሚያጠፋ ግጭት ሊቀሰቀስ ቀርቶ፣ አሁን በስፋት እየታየ ያለው ተቃውሞ በፊት በቆመ ነበር፡፡ በአሻጥርና በሴራ የተተበተበው የአገሪቱ ፖለቲካ ሰከን ማለት አቅቶት ብሔር ተኮር ግጭት እየተቀሰቀሰ፣ ንፁኃን እየሞቱ የደሃ አገር ንብረት ውድመት እስከ መቼ ይቀጥላል? ይህንን ችግር መፍታት ያቃተው መንግሥትና የፖለቲካ አመራርስ በዚህ ሁኔታ አገር እንዴት ነው የሚመራው? በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ችግሮች ሲፈጠሩ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በፊት በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ለምን ያቅታል? በፖለቲካ ውሳኔዎች ሳቢያ ሕዝብ በተለይም ወጣቶች ደስተኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ ፍላጎታቸውን ተገንዝቦ የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ? ወይስ የሰውን ሕይወት ለአደጋ ማጋለጥ ይሻላል? ይህንን መራር እውነት ተረድቶ ከተገባበት አረንቋ ውስጥ መውጣት ካልተቻለ መጪው ጊዜ ያሳስባል፡፡
ወጣቶች ከዚህ ቀደም በመብት ጥሰቶች፣ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ምክንያት ብሶታቸው ገንፍሎ አደባባይ ሲወጡ የደረሰው አደጋ የቅርብ ጊዜ ምስክር ነው፡፡ ሕዝብ ብሶቱ ከመጠን በላይ ሆኖ ለመንግሥት ጀርባውን ሲሰጥ የተፈጠረው ምስቅልቅል አይዘነጋም፡፡ መንግሥት አገርን በወጉ መምራት ስላልቻለ ብቻ መሪው የማይታወቅ ተቃውሞ በየቦታው እየተቀሰቀሰ ንፁኃን ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ተሞክረው ያልሠሩ የመፍትሔ ሐሳቦችን በመደጋገም ብቻ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ ተቃውሞዎች በተሰሙ ቁጥር ወደ ኃይል ዕርምጃ ከመግባት፣ ተቃውሞን ማሰማት ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን በመቀበል ሰላማዊ እንዲሆን ማገዝና ማበረታታት ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን የኃይል ዕርምጃ እየተመረጠ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች በመንግሥት ደረጃ ሐዘን ማወጅና የህሊና ፀሎት ማድረስ የተለመደ አይደለም፡፡ ከስንትና ስንት ጊዜያት በኋላ የይስሙላ የሚመስሉ ሥርዓቶች ሲካሄዱ ደግሞ ያስተዛዝባል፡፡ በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ መገናኛ ብዙኃን በአገር ላይ ስንትና ስንት ችግሮች እየተፈጠሩ እንዳሉ የማይቆጠሩበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው የችግሩን ክብደት ያሳያል፡፡
የኢሕአዴግ አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች መሪዎች ለሕዝብ በገቡት ቃል መሠረት እየተናበቡ ላለመሆናቸው ማሳያው ለውሳኔዎቻቸው ተግባራዊነት ያላቸው የቅልጥፍና መለያየት ነው፡፡ እስረኞች እየተፈቱ ቢሆንም፣ በውሳኔው መሠረት ተግባራዊ እየሆነ ነው ወይ ሲባል ጉራማይሌ ነገሮች ይታያሉ፡፡ የተፈረደባቸውም ሆኑ ክሳቸው የተተወ እስረኞችን በፍጥነት በመፍታት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ማድረግ ሲገባ፣ የበለጠ ሁከት የሚቀሰቅሱ ድርጊቶች ይሰማሉ፡፡ የፖለቲካ አመራሩ በሚፈጥረው ቀውስ ምክንያት አገሪቱ ከድጡ ወደ ማጡ እየተሸጋገረች ቋፍ ውስጥ ናት፡፡ አመራሩ ይህንን ሥጋት በግዴለሽነት ቸል እያለ በተለመደው ሁኔታ መቀጠል እንደማይቻል ማመን አለበት፡፡ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ እየሆኑ ሥርዓተ አልበኝነት ሲነግሥና ግለሰቦች ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያፈሩት ሀብት ሲወድም ጉዳቱ የሕዝብና የአገር ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንን ለማጠባበቅ ብቻ የሚወሰዱ አደናጋሪ ዕርምጃዎች አገርን ከማተራመስ ውጪ የፈየዱት የለም፡፡ የዜጎችን ሕይወት ለበለጠ አደጋ የሚዳርጉ ድርጊቶች በፍጥነት መቆም የሚችሉት፣ የፖለቲካ አመራሩ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ ሲችል ብቻ ነው፡፡ ይህ ዕርምጃ ደግሞ ሕዝብን ማሳመን ይኖርበታል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ በጣም ግዙፍ ነው፡፡ መንግሥትም በዚህ መጠን ለሰላም ዋጋ በመስጠት ለሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ይዞ መቅረብ አለበት፡፡ ካሁን በኋላ በዚህች አገር አንድም ሰው በግጭት መሞት የለበትም፡፡ የፀጥታ ኃይሎች አንድም ጥይት መተኮስ የለባቸውም፡፡ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ በነፃነት ጥያቄ እንዲያቀርብ ወይም መንግሥትን እንዲሞግት የሚረዳ የፖለቲካ ዓውድ እንዲፈጠር መደረግ አለበት፡፡ ‹እንቢ ላለ ሰው ጥይት አጉርሰው› የሚለው አላስፈላጊ መፈክር ሊበቃው ይገባል፡፡ የሰው ሕይወት እየጠፋ አገር መምራት አይቻልም፡፡ ተቃውሞ ወደ አመፅና ሁከት እየተቀየረ አውዳሚ እየሆነ ያለው ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመታፈናቸውና ሰብዓዊ መብቶች በመጣሳቸው ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን መሆን የሚችለው ደግሞ እነዚህ መብቶች ሲከበሩ ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲሰፍን ነው፡፡ ሰዎች በነፃነት ሲነጋገሩና ሲወያዩ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ሲጠናከሩ ነው፡፡ በሰላማዊው የፖለቲካ ትግል የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት ሲወዳደሩ ነው፡፡ መራጩ ሕዝብ በነፃነት የሚፈልገውን የመምረጥ መብቱ ሲከበርለት ነው፡፡ ይህ በትክክል ዕውን ሲሆን መግደልም ሆነ መሞት ያበቃል፡፡ ለአገሪቱ ሁለገብ ችግሮች መፍትሔ ማግኘት የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ የሰው ሕይወት ሳይጠፋ መፍትሔ ይፈለግ የሚባለውም ለዚህ ነው!