በኦሮሚያ ክልል ከሰኞ የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንደ አዲስ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች በሙሉ ተገትተው ከመቆየታቸውም በላይ በሰው ሕይወትና በአካል ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በንብረት ላይም ቀላል የማይባል ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡
በተለይ የምዕራብ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እምብርት በሆነችው ጅማ ከተማ ኃይል የተቀላቀለበት አመፅ ሲከሰት በበደሌ፣ በነቀምትና በመቱ ከተሞች ደግሞ የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ቆሟል፡፡ ከምዕራብ ኢትዮጵያ በተጨማሪ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በምሥራቅ ሐረርጌና በምሥራቅ ሸዋ ዞኖች ኃይል የተቀላቀለበት ተቃውሞ ተከስቷል፡፡
በተለይ ከጅማ ዞን ወረዳዎች ከእሑድ የካቲት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. አመሻሽ ጀምሮ በርካታ ወጣቶች ወደ ጅማ ከተማ ገብተው አድረዋል፡፡ ወጣቶቹ በማለዳ መንገዶችን በመዝጋት፣ የንግድ መደብሮች በይፋ እንዲዘጉ ማሳሰቢያ በመስጠት፣ ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዳይሄዱ በመከልከል ከተማው ወትሮ ከሚታወቅበት ሞቅ ያለ እንቅስቃሴ እንዲገታ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም አመፁ እየተጋጋለ ሄዶ ሆቴሎችና ባንኮች በድንጋይ የተሰባበሩ ሲሆን፣ አንድ የሰላም ባስ ድርጅት አውቶቡስ ተቃጥሏል፡፡ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ1978 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው የጅማ አውቶቡስ መናኸሪያም ተቃጥሏል፡፡ የጅማ ከተማ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚነሳው ከዚህ 32 ዓመታትን ካስቆጠረው መናኸሪያ ሲሆን፣ የመናኸሪያው መቃጠል በከተማው ነዋሪዎች መደናገር መፍጠሩን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የጅማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መኪዩ መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጅማ ከተማ የዚህ ዓይነት አመፅ አጋጥሞ አያውቅም፡፡ ‹‹መናኸሪያው ግማሹ ተቃጥሏል፣ ግማሹ ተርፏል፤›› ያሉት አቶ መኪዩ፣ ከዞኑ ወረዳዎች በርካታ ወጣቶች ወደ ከተማው ገብተው ነበር፡፡ በዋናነት የሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች፣ ‹‹እኛ ስለማናምፅና ሁሌም እሺ ስለምንል ሰዎቻችን ታስረው ይሰነብታሉ፡፡ አህመዲን ጀበልን የመሳሰሉ ታሳሪዎችን ፍቱልን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት የሚገደሉ የኦሮሞ ሰዎች ስለበዙ ይህ በፍጹም መቆም አለበት፡፡ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ፤›› የሚሉ መሆናቸውን ከንቲባ መኪዩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከጅማ ከተማ ባለፉት ሁለት ቀናት አንድም አውቶቡስ አለመውጣቱ፣ ከሌሎች አካባቢዎችም አለመግባቱ ታውቋል፡፡ ሱቆች በሙሉ ተዘግተው የከረሙ ሲሆን፣ ፖሊስ ወጣቶችን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅሟል፡፡ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በከተማው እየተካሄደ ያለው ውድመትና ውጥረት እየበረታ በመሄዱ፣ የምዕራብ ዕዝ 43ኛ ክፍለ ጦር የመከላከያ ኃይል መግባቱን እማኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከንቲባ መኪዩ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹የአመፅ ድርጊቱን ለማስቆም ውይይት አድርገናል፡፡ በተወሰነ ደረጃ መግባባት ላይ በመድረሳችን በርካታ ወጣቶች ከከተማው በመውጣት ወደ መጡባቸው ወረዳዎች ተመልሰዋል፤›› ሲሉ አቶ መኪዩ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩልም የጅማ ዞን አጎራባች በሆነው ቡኖ በደሌ ዞን ተመሳሳይ ተቃውሞ ነበር፡፡ የቡኖ በደሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሻፊ ሁሴን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወጣቶቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች የታሰሩ እንዲፈቱና ግድያ እንዲቆም የሚሉ ናቸው፡፡
ሁለቱን ቀናት በተለይ የበደሌ ከተማ ከትራንስፖርትና ከንግድ እንቅስቃሴ ነፃ ሆኖ አሳልፏል፡፡ በኢሉ አባቦራ ዞን መቱ ከተማም ተመሳሳይ ሲሆን፣ የኦሮሚያ የተቃውሞ ወላፈን ጋምቤላ ከተማንና የሸካ ዞን መቀመጫ የሆነችውን ማሻ ከተማን መንካቱ ተሰምቷል፡፡
የጋምቤላ ከተማ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጋምቤላ አድማ እንዲደረግ ወረቀት ተበትኖ ነበር፡፡ ነገር ግን በጋምቤላ አድማ ሳይነሳ ቀርቷል፡፡ ነገር ግን የጋምቤላ ከተማ ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል ጋር የሚገናኝባቸው ሁለት መንገዶች ማለትም ጋምቤላ-ደምቢዶሎ ነቀምትም ሆነ ጋምቤላ-ጎሬ-መቱ መስመሮች በመዘጋታቸው ከተማው ተቀዛቅዞ ሁለቱን ቀናት ማሳለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሌላኛው የምዕራብ ኢትዮጵያ አካል ነቀምትም እንዲሁ ከንግድና ከትራንስፖርት እንቅስቃሴ ታቅባ አሳልፋለች፡፡ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ተመስገን ዳሮማ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እሳቸው ለስብሰባ አዳማ የሚገኙ ቢሆንም በነቀምት ከተማ የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መገታቱን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹ተማሪዎች ፈተና ላይ ናቸው፡፡ የከተማው የንግድ እንቅስቃሴ በመገታቱ በውጭ ሆነው ትምህርታቸውን የሚከታተሉ የማስተርስና የፒኤችዲ ተማሪዎች የምግብ አቅርቦት ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ይህንን ችግር በመገንዘብ ተማሪዎቹ ከግቢ ምግብ የሚያገኙበትን ሁኔታ አመቻችቷል፤›› ሲሉ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
መደበኛ ባልሆነ መንገድ በተጠራው የሦስት ቀናት አድማ፣ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ በኦሮሚያና በአጎራባች ከተሞች መጠነ ሰፊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መከሰታቸው እየተገለጸ ነው፡፡
የተፈጠረውን የንግድ እንቅስቃሴ ማቆምና የመንገድ መዝጋት፣ እንዲሁም የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ኡሚ አባጀማል አባጆርጋ፣ ማክሰኞ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ወ/ሮ ኡሚ እንዳሉት ከሰኞ ጀምሮ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የንግድ ሥራ ማቆም፣ መንገድ መዝጋት ብሎም ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚያመሩ አዝማሚያዎች ታይተዋል፡፡
‹‹ቀሪ እስረኞች ይፈቱ›› የሚልና የልማት ተጠቃሚነትን መነሻ በማድረግ እየቀረበ ያለው የሰሞኑ እንቅስቃሴ አሁን ወደ ሁከት እየተቀየረ መሆኑ በመግለጫው ተገልጿል፡፡
በዚህም በዝዋይ፣ በለገጣፎና በጅማ ስምንት ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን፣ በግልና በመንግሥት ድርጅቶችና ተሽከርካሪዎች ላይም ጥፋት መድረሱን ወ/ሮ ኡሚ አስታውቀዋል፡፡
በመግለጫው ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በኦሮሚያ አማሬሳ ካምፕ ከተጠለሉ ወገኖች አራት፣ እንዲሁም በባሌ ዞን መደወላቡ ወረዳ በተፈጠረ ግጭት ሦስት በድምሩ የሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተጠቅሷል፡፡
መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ባለበት በዚህ ወቅት ይህን መሰል ክስተት መፈጠሩ አግባብ አለመሆኑን ያስረዱት ወ/ሮ ኡሚ፣ የክልሉ መንግሥት አሁንም አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
‹‹የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ መሠረት የተቀመጡ ተግባራትን የክልሉ መንግሥት እንዲሠራ ሕዝቡ ጊዜ ሊሰጥ ይገባል፤›› ያሉት ወ/ሮ ኡሚ፣ መንግሥት ጥፋት ያደረሱ አካላት ላይ ማጣራት በማድረግ ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑን፣ ኅብረተሰቡም በሕዝብና በመንግሥት መካከል የተጀመረውን የመደማመጥ ሒደት ከሚያደናቅፍ አፍራሽ ድርጊት እንዲታቀብ ወ/ሮ ኡሚ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በአሰላ ከተማ ነዋሪ የሆነውና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ ወጣት ለሪፖርተር እንደተናገረው፣ ከሰኞ የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ረፋድ ጀምሮ በከተማዋ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የንግድ ተቋማትና የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፡፡ እንደ ወጣቱ ገለጻ በከተማዋ መግቢያና መውጫ ያሉ መንገዶች ሙሉ በሙሉ የትንስፖርት አገልግሎት መስጠታቸው ከመቋረጡም በላይ፣ በድንጋይ ተዘግተዋል፡፡ በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶችም ጎማ በማቃጠልና መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ ሲገለጽ ነበር፡፡ ወጣቶች በመሰባሰብ የተለያዩ መፈክሮችን ሲያሰሙ እንደነበርም ታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ባሉ ከተሞችም ተመሳሳይ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ሪፖርተር ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ ማክሰኞ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በለገጣፎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ መንገዶች ተዘግተው ነበር፡፡ መንገዶች በድንጋይ ከመዘጋታቸውም በላይ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መፈክሮች ሲስተጋቡ ነበር፡፡ ጎማና ሌሎች ተቀጣጣይ ቁሶችን በማቀጣጠል ተሳታፊ የነበሩ ወጣቶችንም የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው ታውቋል፡፡
ሰኞ የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው የተቃውሞ እንቅስቃሴም በሱሉልታ፣ በቢሾፍቱ፣ በሰበታ፣ በጀሞ፣ በቡራዩ፣ በአሸዋ ሜዳና በሌሎች በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ባሉ ከተሞች ሲካሄድ ነበር፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማክሰኞ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ለክልሉ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በክልሉ ባሉ ከተሞች መንገድና የንግድ ተቋማትን የመዝጋት ችግር ገጥሟል፡፡ ይኼ ድርጊትም እንዲቆም ጥሪ አስተላለፈዋል፡፡
‹‹ሕዝብ አንድ ላይ በመደራጀት ሰላማዊ በሆነ መንገድ የራሱን መንግሥት ማስገደድ፣ ጫና መፍጠርና የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ይኼ በሚሆንበት ጊዜ ግን የሕዝብና የአገርን ሀብት ሳይጎዳ መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡
እየተነሱ ካሉ ጥያቄዎች መካከል የታሰሩት ይፈቱ የሚል ጥያቄ እየተነሳ እንደሆነ ጠቁመው፣ ጉዳዩን የክልሉ አመራር ዋና ሥራው አድርጎ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹እስር ከበዛ ሕዝብ ይቸገራል፣ ማደግም ሆነ መለወጥ አይችልም፤›› ብለው፣ ‹‹ስለዚህ የእስረኞች መለቀቅ ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳችን በማድረግ እየሠራን ቆይተናል፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም በኦሮሚያ ክልል ሥልጣን ሥር የነበሩ ከ30 ሺሕ በላይ ሰዎችን ከእስር መፍታት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት መሥራት ባለበት ጉዳይም ድርጅታቸው ጠንካራ ትግል ማካሄዱን ጠቁመው፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከስምምነት ላይ የተደረሰባቸውና ለሕዝብ ይፋ የተደረጉ ጉዳዮች ያለምንም መሸራረፍ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ፣ ድርጅቱ ታላላቅ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት ወቅት የሥራ ማቆም አድማን በማሳበብ በኦሮሞ ስም የግለሰቦችና የመንግሥት ሀብት የመዝረፍና የማውደም ተግባራት እየተፈጸመ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ በሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችም ላይ ጥቃት መፈጸም፣ የፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት ማድረስና መሰል ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይኼ ድርጊት ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸው፣ ይኼን ጉዳይ ከላላ በማድረግ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አካላት እንዳሉና ጉዳዩ በሕግ የበላይነት መስተካከል እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
ወጣቶች ሁሉንም ነገር በትዕግሥት መጠባበቅ እንዳለባቸውና መንገድ መዝጋትና ሰዎች የንግድ ተቋማቸውን እንዲዘጉ ማስገደድ ትክክል እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ አሁን እየተካሄደ ያለው ተግባርም በአስቸኳይ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ከፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ጋር በተያያዘ በክልሉ ወጣቶች በተደጋጋሚ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሲከሰቱ ተስተውሏል፡፡ በክልሉም ሆነ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ቀውስ ለማስወገድ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራሁ ነው እያለ ሲገልጽ ቢሰማም፣ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም አልተቻለም፡፡
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የሰዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ከመገታቱ በተጨማሪ፣ ሥራ ውሎ መግባት እንዳልተቻለ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በክልሉ ከተሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እየተደራረቡ እንደሆነ ለማረጋገጥ ቢቻልም፣ በዚህ ሳቢያ የደረሰውን ጉዳት በትክክል ማወቅ ግን አልተቻለም፡፡
በውድነህ ዘነበና ዘመኑ ተናኘ