Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናምርጫ በቦሎሶ ሶሬ

ምርጫ በቦሎሶ ሶሬ

ቀን:

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የምትገኘው የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በዘንድሮው አምስተኛው አገራዊ ምርጫ ትኩረትን ከሳቡ የምርጫ ክልሎች ቀዳሚነቱን ትይዛለች፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የትውልድ ቦታ መሆኗና በዘንድሮ ምርጫ ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን በመወከል የሚወዳደሩባት ቦታ መሆኗ ጭምር ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰማያዊ ፓርቲንና የአዲስ ትውልድ ፓርቲን (አትፓ) በመወከል ከቀረቡትና ብዙም በፖለቲካው መድረክ ዕውቅና ካልነበራቸው ግለሰቦች ጋር ነበር የተወዳዳሩት፡፡ በተለይ ከአረካ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘውና ጉኑኖ የተባለችው አነስተኛ የገጠር ከተማ ነበረች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ለምርጫ ውድድር ያገናኛቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫው ዕለት ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ በምርጫ ጣቢያው ደርሰው እንደ ማንኛውም ድምፅ ሰጪ ሠልፍ በመያዝ ወረፋ ይዘዋል፡፡ እንደ አብዛኛው መራጭ የመራጭ ካርድ በእጃቸው ያልታየ ቢሆንም፣ በመደበኛው አሠራር መሠረት በሚስጥራዊ ክፍል በመግባት በምርጫ ወረቀቱ ላይ ከሰፈሩት የተወዳዳሪ ፓርቲ ምልክቶች በመምረጥ፣ በምርጫ ኮሮጆ ውስጥ ድምፃቸውን አስገብተዋል፡፡

- Advertisement -

ድምፅ ሰጥተው እንደጨረሱም በአካባቢው የነበሩ ጋዜጠኞች ከበዋቸው ስለምርጫው የጠየቋቸው ሲሆን፣ የ47 ሰከንድ ብቻ ዕድሜ የነበራት ንግግር አድርገዋል፡፡

‹‹ከማለዳ ጀምሮ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እየተጓዘ ነው፡፡ ሕዝቡም በነቂስ ወጥቶ ድምፁን እየሰጠ ነው፡፡ እኔም በምርጫ ጣቢያ ተገኝቼ ድምፅ በመስጠቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና በተረጋጋ ሁኔታ እየተካሄደ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ የብዙ መስዋዕትነት ውጤት ነው፡፡ ዴሞክራሲያችን እያደገ እንዳለ የሚያሳይ ነውና ለሕዝቡ ታላቅ ምሥጋና ነው ያለኝ፤›› በማለት ነበር ወዲያው የምርጫ ጣቢያውን ለቀው የሄዱት፡፡

በአቶ ኃይለ ማርያም የምርጫ ክልል ከተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪዎች በኩል ተቃውሞም ሆነ አቤቱታ አልተደመጠም፡፡

በምርጫው ማግሥትም በዚሁ በወላይታ ዞን ሪፖርተር ተዘዋውሮ የተመረጡ የምርጫ ጣቢያዎች ለመታዘብ ችሏል፡፡ በተለይ በአረካ ምርጫ ጣቢያዎች እስከ ጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ድረስ በየምርጫ ጣቢያዎች የቆጠራ ውጤቶች ተገልጸዋል፡፡ ቦሎሶ ሶሬ በአምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሁለት አመራሮች፣ ገዥውን ፓርቲ በመወከል በተለያዩ ሁለት የምርጫ ክልሎች የተወዳደሩባት ቦታ  ነች፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም፣ እንዲሁም የአገሪቱን ገንዘብ ተቋማትንና አጠቃላይ የገንዘብ ዝውውርን በበላይነት የሚመራውና የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ በዚህ ወረዳ ተወዳዳሪ በመሆን ደኢሕዴን/ኢሕአዴግን በመወከል ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም ሁለቱም ታላላቅ ባለሥልጣናት በአካል በመገኘት ድምፃቸውን በየጣቢያው ሰጥተው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከ40 ዓመቱ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ አቶ ቃኙ ሴባና በወላይትኛ ዘፈን በአካባቢው ታዋቂ እንደሆኑ ከተነገረላቸው በተመሳሳይ ዕድሜ ከሚገኙት የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዕጩ አርቲስት ደስታ ደአ ጋር ለምርጫው ቀርበዋል፡፡ ሁለቱም የተቃዋሚ ፓርቲ ዕጩዎች በምርጫው ምንም ቅሬታ ዓይነት እንዳልነበራቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ወላይታ ወጋቢያሱ››

በወቅቱ ከተስተዋሉ ክስተቶች በዋናነት የሚጠቀሰው አቶ ኃይለ ማርያም፣ በአገሪቱ ትልቅ የሚባለው የሥልጣን እርከን ላይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ ከተቀመጡ አንስቶ ለመጀመርያ ጊዜ የትውልድ አካባቢያቸውን መጎብኘታቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሺሕ የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከሕፃናት እስከ አዛውንት እሳቸውን ለማየት የነበረው ትግልና የእርስ በእርስ ግፊያ ቀልብን የሳበ ነበር፡፡ የምርጫ ጣቢያ በነበረው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በኋላም ለግማሽ ሰዓት ለምሳ ዕረፍት አድርገውበት በነበረው ሔለን የባህል ምግብ ቤት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ከፀጥታ አስከባሪዎችና ከልዩ የፖሊስ ኃይል ጋር ሲጋፉ ተስተውሏል፡፡

ከእነዚህ ሁለት አካባቢዎች ባሻገር ከከተማዋ ወጣ ብሎ በተንጣለለ ሰፊ ሜዳ ላይ አርፈው የነበሩትን አቶ ኃይለ ማርያምንና ሌሎች ባለሥልጣናትን ይዘው የመጡ ሁለት ሔሊኮፕተሮችን ለማየት በሩጫ ደርሰው የተሰባሰቡ ነዋሪዎችም ነበሩ፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሳፈሩበት አነስተኛ ሔሊኮፕተርና ጠባቂዎቻቸው የተሳፈሩበት ሌላኛው ሔሊኮፕተር ሲነሱ አብዛኛዎቹ በከተፍኛ ጩኸትና ፉጨት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሸኝተዋል፡፡ አብዛኛውን ቁጥር ከያዙት ሕፃናትና ወጣቶች ጩኸት መካከል አንዲት በግምት በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ አዛውንት በቀጭን ድምፃቸው፣ ‹‹ወላይታ ወጋቢያሱ፣ ወላይታ ቢታፌ ክያደ፣ ክኬ ምጮና ክያዳስ ኔና ጦሳይ ናጎ›› ሲሉ ተደመጡ፡፡ ‹‹ወላይታ ዓለሟን አየች፣ ከደጄ አፈር ተፈጥረሃል፣ አምላኬ አንተን ይጠብቅልኝ፤›› የሚል ነበር ትርጓሜው፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ድምፅ በሰጡበት የምርጫ ጣቢያ (ቦሎሶ ሶሬ 02) የምርጫ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ እያሱ ቦርሳሞ የነበረውን የምርጫ ሒደት ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ ‹‹በነበረን ዝግጅት መሠረት የምርጫ ሒደቱ በአግባቡ ተከናውኗል፡፡ ከመራጩ ሕዝብ ባሻገር ተወዳዳሪ ዕጩዎች ተገኝተው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ከመድረክ ተወካይ በስተቀር ሁሉም በዚህ ክልል የተመዘገቡ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል፤›› ብለዋል፡፡

ሶዶና የቅስቀሳ ፖስተሮች

የወላይታ ዞን መቀመጫ በሆነችው ሶዶ ከተማ በምርጫ ዋዜማ፣ በምርጫ ዕለትና ማግሥት በመዘዋወር ቅኝት ተደርጎ ነበር፡፡ ሙሉ ከተማዋ የምርጫ ድባብ በደማቁ ይታይባት የነበረ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ዕይታን በመያዝ ረገድ ብቸኛውን ቦታ ይዞ የነበረው የገዥው ፓርቲ ተወካይ የሆነው የደኢሕዴን/ኢሕአዴግ ዓርማና የንብ ምልክት ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምሥል የያዙ ትላልቅ ፖስተሮችና ‹ኢሕአዴግን ምረጡ› የሚሉ የንብ ዓርማዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በአደባባዮች፣ በንግድ ሥፍራዎችና እንዲሁም በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ሳይቀር በስፋት ይታያሉ፡፡ በከተማዋ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው ቢሳተፉም ከገዥው ፓርቲ በስተቀር፣ የሌሎች ፓርቲዎችን ቅስቀሳ የሚያሳዩ ጽሑፎችም ሆኑ የመወዳደርያ ምልክት አይታዩም፡፡ የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ዓርማዎች ለሕዝብ የሚታዩት በምርጫ ጣቢያዎች ብቻ በተለጠፉ የምርጫ ቦርድ ቅጽ ወይም ማስታወቂያ ላይ ብቻ ነበር፡፡

አብዛኛዎቹ መራጮች ለሚዲያ አስተያየት ለመስጠት እንደማይደፍሩ ሪፖርተር ለማነጋገር በሞከረበት ጊዜ የተስተዋለ ሌላው ክስተት ነበር፡፡ ስለምርጫው እርስ በራሳቸው በአብዛኛው ሲወያዩ ይደመጣሉ፡፡ ነገር ግን ከሚዲያ የመጣ ሰው ሊያነጋግራቸው ሲሞክር ዝምታን የሚመርጡ ብዙዎቹ ቢሆኑም፣ ለመናገር የሚሞክሩም ከፍተኛ ጥንቃቄ ይስተዋልባቸዋል፡፡

በወላይታ ዞን 13 የምርጫ ክልሎች ሲኖሩ፣ 882 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉ ከምርጫ አስፈጻሚዎች ለማወቅ ችሏል፡፡ በአጠቃላይ 694,735 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወዳድረዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ በተወዳደሩበት በሌላኛው የአረካ ምርጫ ጣቢያ ሦስት ከንጋቱ 12 ሰዓት ተገኝተው የመጀመርያ መራጭ የነበሩት አቶ አበራ ለማ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው፡፡ ‹‹እኔ ለወገንና ለአገር ያልኩትን መርጫለሁ፡፡ በተቀረው እግዚአብሔር አንተ ተጨመርበት፤›› በማለት የድምፅ መስጫ ወረቀቱን በኮሮጆው ውስጥ እያስገቡ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ጣቢያ ድምፅ ለመስጠት መጥተው ሪፖርተር ያገኛቸው የ80 ዓመት ማየት የተሳናቸው አዛውንት አቶ ሙለጌ መሐመድ ይባላሉ፡፡ እንዴት ለመምረጥ እንደመጡ ሲጠየቁ፣ ‹‹የራሴን አስተዳዳሪ ልወክል ነው የመጣሁት፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ቦታም ለመጀመርያ ጊዜ ምርጫ ለመምረጥ መመዝገቡን የሚናገረው ማቲዎስ የተባለ የ19 ዓመት ወጣት ስለምርጫው ሲጠየቅ፣ በቀጥታ አቶ ተክለ ወልድን ለመምረጥ መገኘቱን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

ስለሚመርጠው ፓርቲ ምን ያህል ግንዛቤ እንዳለውና እርግጠኝነቱን ሲናገር፣ ‹‹እኔማ የምመርጠውን አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ሌላው ቢቀር በየቀኑ ከኪሴ መዝዤ በማውጣት ብር ላይ ያለችው ፊርማ እንዴት ትጠፋኛለች?›› ሲል በአገሪቱ ጥቅም ላይ ያሉ የብር ኖቶች ላይ የብሔራዊ ባንኩ ገዥ ፊርማን በማስታወስ፣ በአካባቢው ስለተገኙት አቶ ተክለወልድ ያለውን ግንዛቤ ተናግሯል፡፡

በወላይታ ዞን ከምርጫው ቀን በፊትም ሆነ በኋላ ያለው አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ የደሕኢዴን/ኢሕአዴግን ጠንካራ መሠረት የሚያሳይ ሲሆን፣ በተቃውሞ ጎራ ያለውን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ የዋጠው ይመስላል፡፡ ይህ ታዲያ በአካባቢው የነበረውን የምርጫ ፉክክር ከማቀዝቀዙም በላይ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተመጣጠነ አቅም እንዳልነበራቸው በግልጽ ያሳያል፡፡

በአካባቢው ያሉ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ ስለሚታየው ክፍተት ለመናገር ብዙ አልደፈሩም፡፡ በሌላ በኩል ምርጫ በሚካሄድበት ቀን በወላይታ ዞኖች ባሉ አካባቢዎች ፀጥታው እንደ ወትሮው የተረጋጋ ነበር፡፡ ከአጎራባች አካባቢዎች ወደ ሶዶ ወይም ከሶዶ ወደሌላ አካባቢ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ብዙም አልነበረም፡፡ የአውቶብስ ተራዎችም እንደ ወትሮው ሥራ አልበዛባቸውም ነበር፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...