ፕሮፌሰር ደምሴ ሀብቴ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያው ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋኩልቲ በአሁኑ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ1972 ዓ.ም. ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ ከሦስት ዓመታት በኋላ ደግሞ ሙሉ ፕሮፌሰር ሆነዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የፔዲያትሪክስና የቻይልድ ኸልዝ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆነው ከማገልገላቸውም በላይ የፋክልቲው ዲን ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከዚህም ሌላ በዓለም ባንክ ለአፍሪካ ከፍተኛ የጤና አማካሪ፣ ባንግላዴሽ በሚገኘው ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎ ዲያሪያ ሪሰርች ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር፣ እንዲሁም የባራክ ስኩል ኦፍ ሔልዝ መሥራች ከሆኑት አንዱ ሲሆኑ፣ አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር ደምሴ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ መሥራችና የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዕውቅናና ክብር ከቸራቸው አንጋፋ ፕሮፌሰሮች መካከል ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ደምሴ ዕውቅናውን አስመልክተው ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት ይህ ዓይነቱ ዕውቅና ለዩኒቨርሲቲው ዕድገትና ጥንኮሬ እንዲሁም ለወጣቱ ትውልድ ዕውቀት ለማስተላለፍ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ ዕውቅና በኮሌጁ ብቻ ሳይወሰን በሌሎችም የመንግሥት ተቋማት መዘውተር እንዳለበት ጠቁመው ዕድገትና ልማት የሚመጣው ዕውቀትና የሥራ ልምድ ተወራራሽ በሆነ ለትውልድ ሲተላለፍ መልኩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ባለፉት 54 ዓመታት በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማኅበረሰብ ጤና አገልግሎት በመስጠት ማኅበረሰቡን ካገለገሉ 48 አንጋፋ ፕሮፌሰሮች ዕውቅናና ክብር የተቸራቸው ፕሮፌሰር ደምሴን ጨምሮ በሕይወት የሚገኙ 32 ፕሮፌሰሮች ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ደምሴ የቅድሚያ ዕውቅናና ክብር ከተቸራቸው በኋላ ባደረጉት የምስጋና ንግግር ‹‹ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በጤናው ዘርፍ ብዙ ለውጥ ተካሂዷል፡፡ አሁን ግን ቆም ብለን ይህ ለውጥ ምንድነው ያስከተለው? ምን ማስተካከል አለብን ብለን ማሰብ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡
አገሪቱን በጤናው መስክ ለአገሪቱ ትልቅ ባለውለታ የሆኑና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ፕሮፌሰሮችን በዚህ አጋጣሚ ማሰብ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የጥቂቶችን ስም እየጠሩ ታዳሚዎቹ ዕውቅናና ክብር እንዲሰጡዋቸው ጠይቀውም ነበር፡፡
ታዳሚዎቹም ጥያቄያቸውን በመቀበል በጋለ ጭብጨባ የታጀበ ዕውቅናና ክብር ሰጥተዋቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ዕውቅናና ክብር ከተቸራቸው መካከል ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ፣ ፕሮፌሰር ጀማል አብደልቃድር፣ ፕሮፌሰር ዕደማርያም ፀጋ እና ፕሮፌሰር ታዬ መኩሪያ ይገኙበታል፡፡
የውጭ አገር ዜግነት ካላቸው ፕሮፌሰሮች መካከል በአሁኑ ጤና ኮሌጅ በቀድሞው ፋኩልቲ ኦፍ ሜድስን መሥራችና ዲን ሆነው ከ1958 ዓ.ም. እስከ 1961 ዓ.ም. ድረስ ያገለገሉት እንግሊዛዊው ፕሮፌሰር ኤፍ ዋርትም (F HOWARTH) ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች አገልግሎትና አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ማቴዎስ ኢንሴርሞ (ዶ/ር) ‹‹በአገራችን አንድ ፕሮፌሰር ለማምረት ቢያንስ 50 ዓመት ይፈጃል፡፡ በሆነ ምክንያት ተቋሙን ቢለቅ ደግሞ ተቋሙ የ50 ዓመት ዕውቀት ያጣል፣ ወይም ሌላ ፕሮፌሰር ለማግኘት 50 ዓመት ይፈጅበታል›› በማለት የፕሮፌሰሮችን ቀን አስፈላጊነት በፅንኦት አስረድተዋል፡፡
በመላ አገሪቱ ወደ 46 የሚጠጉ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ሲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ግን ልዩ የሚያደርገው አብዛኞቹን ፕሮፌሰሮች በማፍራቱና በማቀፉ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ቋሚና ወጥ የሆነ መድረክ እየተዘጋጀላቸው ዕውቀታቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ቢደረግ መልካም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምክትል ፕሬዚዳንትነት የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳዊት ወንድምአገኝ (ዶ/ር)፣ ‹‹አንጋፋዎቹ ምሁራን በውስጣቸው ያላቸውን ሐሳቦችና ምኞቶችን ወጣቱ ትውልድ እንዲያወርሱት ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ለብዙ ዓመታት ተንጠልጥለው የቆዩ ሐሳቦችንና ምኞቶችን ተግባራዊ የማድረግ ዕድሉ የሰፋ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሊቀጥል የሚችለው የአንጋፋዎቹ ምሁራን ትውስታዎች በሥርዓት ተስተካክለው ሲያዙ ነው፡፡ የምኞትና የትውስታ ምንጮች ደግሞ አንጋፋዎቹ ፕሮፌሰሮች ስለሆኑ ክብርና ሞገስ ሊቸራቸው እንደሚገባ አመልክተው ይህ ዓይነቱን ፕሮግራም የዩኒቨርሲትው ባህል እንዲሆን ማስፈለጉን አሳስበዋል፡፡
ከዚህም ፍላጎት በመነሳት ዕውቅና የመስጠት ሁኔታ በፕሮፌሰሮች ላይ ብቻ ሳይወሰን በኮሌጅ ሥር ለሚተዳደረው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሠራተኞችንም ተቋዳሽ እንደሚያደርግ ከዶ/ር ዳዊት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡