- ሰብሳቢው ከፊፋ ጋር መላተም ጀምረዋል
መቋጫው የሚናፈቀው፣ ከውዝግብና ንትርክ አልፀዳ ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ምርጫ አልያዝ፣ አልጨበጥ ብሏል፡፡ ለምርጫው አመቻች እንዲሆን በጠቅላላ ጉባዔ የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴው ከዋናው ምርጫ ያላነሰ የአወዛጋቢነት ድርሻ ይታይበት ጀምሯል፡፡ በተለይም የኮሚቴው ሰብሳቢ ከዓለም አቀፍ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ፊፋ) ጋር የገጠሙት እሰጣ ገባ ለብዙዎች ግርምት መፍጠሩ አልቀረም፡፡
የአስመራጭ ኮሚቴው አስፈላጊነትና አካሄድ ፍትሕን በማፈላለግ ጭምር በተለይም የምርጫ ሒደቱ ዴሞክራሲያዊ መንገድን የተከተለና ሀቀኛ እንዲሆን ማድረግ፣ ማረጋገጥ ቢሆንም፣ ከሰሞኑ ግን ከፊፋ ጋር ለመላተም የጀመረው አዲስ ውዝግብ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አቶ ዘሪሁን መኰንን እንደ እሳቸው ሁሉ በጠቅላላ ጉባዔ የተሰየሙ የሌሎች አባሎቻቸው ሐሳብና አስተያየት ባልተካተተበት በሰብሳቢነታቸው ብቻ የግል አመለካከታቸውን በደብዳቤያቸው ማንፀባረቃቸው የኮሚቴው አባላትን ጭምር አስቆጥቷል፡፡
ፊፋ፣ ከታኅሣሥ 16 ወደ የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በመንከባለል ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአመራሮች ምርጫ ጉዳይን አስመልክቶ ለአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢና በግልባጭ ለፌዴሬሽኑ ጥር 23 ቀን 2010 ዓ.ም. መልዕክት መላኩ የታወቀው ከሰሞኑ ነው፡፡ የመልዕክቱ ይዘትና ጭብጥ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ሊከተለው የሚገባው የምርጫ መመርያ የፊፋን ደንብና መመርያ መነሻ ያደረገ መሆን እንዳለበት ቀደም ሲል ማሳሰቡ፣ ይሁንና ይህንኑ ደንብና መመርያ ተግባራዊ መድረግ፤ አለመደረጉ የሚወሰነው ደግሞ በቃል ብቻ ‹‹እንቀበለዋለን›› ከሚለው ባሻገር ደንቡን በጠቅላላ ጉባዔ አፀድቆ መመርያ ሲያደርገው እንደሆነ በመግለጽ፣ ፌዴሬሽኑ ለጊዜው ቀደም ሲል ሲሄድበት በነበረው ዓይነት አሁንም ምርጫውን ማከናወን እንደሚችል፣ የምርጫ ኮዱን በሚመለከት ደግሞ ፊፋ ከአዲሱ አመራር ጋር በሒደት ተነጋግሮ ተፈጻሚ እንደሚያደርገው መግለጹ ታውቋል፡፡
ለሰብሳቢውም ሆነ ለፌዴሬሽኑ የደረሰው ይኸው የፊፋ ደብዳቤ ለሳምንታት ያህል የተወሰኑ ሰዎች ጉዳይ ብቻ ሆኖ ተደብቆ እንዲቆይ መደረጉ ሳያንስ፣ ይፋ ከሆነ በኋላ በሰብሳቢው አቶ ዘሪሁን መኰንን ተቀባይነት ሊያገኝ እንዳልቻለም ታውቋል፡፡ ሰብሳቢው በማያያዝም የደብዳቤው ይዘት ‹‹የቆሸሸ አሠራርን የሚያበረታታ ነው›› በሚል ለፊፋ መልስ መጻፋቸውም ታውቋል፡፡ በኃላፊነታቸው መቀጠል አለመቀጠላቸውን አስመልክቶም ውሳኔያቸውን በሒደት የሚያሳውቁ ስለመሆናቸው ጭምር ማካተታቸው ተነግሯል፡፡ ሌሎች የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ግን የሰብሳቢውን አካሄድ አይቀበሉትም፡፡
እንደ አስመራጭ ኮሚቴዎቹ ከሆነ፣ ‹‹ሰብሳቢው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በግላቸው ነው፡፡ እንደ አሠራር በጉዳዩ የሌሎቻችን ሐሳብና አስተያየት መጠየቅና መተካት ነበረበት፤›› በማለት አካሄዱን ጭምር ይተቹታል፡፡
የኮሚቴው አባላት ሲቀጥሉ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ለአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁንም ሆነ ለፌዴሬሽኑ ያስተላለፈው መልዕክት፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሕግ አድርጎ በጠቅላላ ጉባዔ ባላፀደቀውና ባልተቀበለው መመርያ ጊዜ ከሚያጠፋ፣ ምርጫውን ተቋሙ ባለውና በሚከተለው አሠራር አከናውኖ፣ የምርጫውን ኮድ በሚመለከት በሒደት ራሱ ፊፋ ጭምር ተሳትፎበት ወደ ትክክለኛው አሠራር መሄድ እንደሚቻል የሰጠው ምክረ ሐሳብ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እዚህ ላይ ሰብሳቢው ያላቸውን አስተያየት ለማወቅ አልተቻለም፡፡ አቶ ዘሪሁን የምርጫውን ሒደት አስመልክቶ ለፊፋ የጻፉት ደብዳቤ ‹‹እንዲህ ይላል›› ከሚለው ባለፈ ኃላፊው በአገሪቱ እግር ኳስ ጉዳይ ሕዝብ የማወቅ መብት እንዳለው በመገንዘብ እየሄዱበት ያለውን አሠራር ማብራሪያ ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ ታውቋል፡፡
በአቶ ዘሪሁን ተጻፈ የተባለውን የደብዳቤ ይዘት አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት፣ በጉዳዩ ምንም ማለት እንደማይፈልግ፣ ይሁንና ጉዳዩን ለምርጫ አስፈጻሚ ቦርድ እንደሚያቀርበው ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል በአስመራጭ ኮሚቴው ሳይሆን አገልግሎቱ በተጠናቀቀውና በወቅታዊው የፌዴሬሽኑ አመራር ከሁለት ሳምንት በኋላ በአፋር ሰመራ ሊደረግ ቀን ተወስኖለት የነበረው ምርጫ፣ ሰሞኑን ይፋ የሆነው የፊፋ ደብዳቤ ሳይታወቅ ምርጫውን ለተጨማሪ ወራት ለማራዘም ዕቅድ ተይዞ እንደነበር የሚናገሩ አሉ፡፡
ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች፣ በእግር ኳሱ እየተስተዋለ ያለው ተጠያቂነትና ግልጸኝነት የጎደለውን አሠራር መንግሥት ‹‹አስተካክሉ›› ብሎ ቢጠይቅ አግባብነት እንዳለውና ጣልቃ ገብነት ተብሎ መወሰድ እንደሌለበትም ያምናሉ፡፡