Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየጃኮብ ዙማ ፀሐይ ስትጠልቅ

የጃኮብ ዙማ ፀሐይ ስትጠልቅ

ቀን:

ምናልባትም ከዚምባቡዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ ቀጥሎ በአፍሪካ አወዛጋቢው መሪ የደቡብ አፍሪካ መሪ ጃኮብ ጌድልዬሌኪዛ ዙማ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ዙማ አልተማሩም፣ ይህንንም በኩራት ይናገራሉ፡፡ ዙማ ስድስት ሚስቶች አግብተው 22 ልጆችም ከተለያዩ እናቶች ወልደዋል፡፡

ኑሯቸውም የመሀል ስማቸውን ይመስላል የሚሏቸውም ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹እያጠፋሁህ እስቃለሁ›› የሚባለው የመሀል ስማቸው በዙሉ ቋንቋ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 ዙማ በአገሪቱ ካሉ ትምህርት ቤቶች ቀደምት የሆነውን የማርሁላና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ሲጎበኙ፣ ‹‹እኔ ትምህርት ቤት አልሄድኩም፣ ነገር ግን ራሴን አስተምሬአለሁ፡፡ አባቴ ሞቶ ስለነበረ ምንም አማራጭ አልነበረኝም፡፡ በዚህም ኩራት ይሰማኛል፤›› ብለው መነጋገሪያ ሆነው ነበር፡፡

ዙማ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ የቀረቡ መሪ ሲሆኑ በሙስናም በእጅጉ ይታማሉ፡፡ የአንድ አገር መሪ ሆነው በሙስና፣ በማጭበርበር፣ ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብን በማካበት፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብና በታክስ ማጭበርበር ፍርድ ቤት ከደረሱ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡

የጃኮብ ዙማ ፀሐይ ስትጠልቅ

 

የዙማ የገንዘብ አማካሪ የነበሩትና የደርባኑ ነጋዴ ሻቢር ሻይክ ለዙማ  ከፈረንሣይ የጦር መሣሪያ ሻጭ ድርጅት ጉቦ ተቀብለው አስተላልፈዋል ተብለው ተከሰው የ15 ዓመት እስር ሲፈረድባቸው ዙማ ላይ ግን ዝር ያለባቸው አልነበረም፡፡ ዙማ እስር ቤት ሳይሆን ቤተ መንግሥት ነበር የጠበቃቸው፡፡

ሻይክ ፍርድ ቤት ሲቀርቡና ሲፈረድባቸው ዙማ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ ምክትል ሆነው ሲሠሩ ነበር፡፡ ከፍርዱ በኋላ ምቤኪ ዘማን ከሥልጣናቸው አንስተዋቸው ነበር፡፡

ዙማ በሙስና ብቻ ሳይሆን በአስገድዶ መድፈርም ክስ ቀርቦባቸው ያውቃል፡፡ የሙት ጓደኛቸው ልጅ የሆነችውን የ31 ዓመት የኤድስ ንቅናቄ መሪ ወጣት ዙማ ደፍረዋል ተብለው ቢከሰሱም፣ ፍርድ ቤቱ ክሳቸውን ውድቅ አድርጎታል፡፡ ሆኖም ግንኙነቱ ሙሉ በሙሉ በስምምነት የተደረገ ነው የሚሉት ዙማ፣ ከዚህ ይልቅ ኤችአይቪ እንዳለባት ገልጻ ኅብረተሰቡን በማስተማር ላይ ካለች ግለሰብ ጋር ግንኙነት አድርገው ሲያበቁ ቫይረሱ እንዳይዘኝ ገላዬን ታጥቢያለሁ ማለታቸው በእጅጉ አስወቅሷቸዋል፡፡

ይሁንና ከፓርቲያቸው በደረሰባቸው ጫና ታቦ ምቤኪ ሥልጣናቸውን ሲለቁ መንበሩን ተረካቢው ዙማ ሆኑ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2009 የፓርቲያቸው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ሊቀመንበርነቱን ከታቦ ምቤኪ ሲረከቡ የአገሪቱም ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ እንደመጣ ሲነገር የቆየ ሲሆን፣ የፓርቲያቸው ደጋፊዎችም በፓርቲው ላይ ጥርጣሬ ማሳደር ጀምረው ነበር፡፡ በተደጋጋሚ በሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ፕሬዚዳንቱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት እየቀነሰ መጥቷል፡፡

የጃኮብ ዙማ ፀሐይ ስትጠልቅ

 

ለአብነትም እ.ኤ.አ. በ2010 ከአምስት ሚሊዮን በላይ የደቡብ አፍሪካ ራንድ በማውጣት የገዙት ቤት ብዙዎችን ያስቆጣ ነበር፡፡ ይህንንም ገንዘብ ከተለያዩ የንግድ ተቋማት ጋር በነበሩዋቸው ግንኙነቶች፣ በተለይም የጉፕታ ቤተሰቦች ከሚባሉ የህንድ የነጋዴ ቤተሰቦች ጋር በነበራቸው ግንኙነት ያገኙት የማይገባ ጥቅም ነው ተብለው ተብጠልጥለው ነበር፡፡

አሁን ግን የዙማ ፀሐይ እየጠለቀች ያለች ይመስላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ነሐሴ ወር ከተደረገው የመተማመኛ ድምፅ ለትንሽ ያመለጡት ዙማ፣ አሁን በድጋሚ ያኔ እንዳደረጉት ‹‹አንተማመንባቸውም›› በማለት ያልመረጡትን የፓርቲያቸውን አባላት ለማመስገን ወደ ምክር ቤቱ የሚያቀኑበት ዕድል የሚያገኙ አይመስልም፡፡

ፓርቲያቸው ኤኤንሲ በ48 ሰዓታት ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ፣ ካልሆነ ግን የ‹‹አንተማመንባቸውም›› ምርጫን እንደሚጋፈጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው የፓርቲውን ሊቀመንበር ለመምረጥ በተደረገ ምርጫ ዙማን በማሸነፍ የሊቀመንበርነት ኃላፊነቱን ከተረከቡት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሲሪል ራማፎዛ ጋር የነበረው ዝግ ውይይት ፍሬ አልባ በመሆኑ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የኤኤንሲ ፓርቲ በምክር ቤቱ ከፍተኛው ድምፅ ያለው ሲሆን፣ የፓርቲውን ሊቀመንበር ለፕሬዚዳንትነት ያስመርጣል፡፡ ዙማ ከሥልጣናቸው የሚነሱ ከሆነም ራማፎዛ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከአፓርታይድ ማብቃት በኋላ ደቡብ አፍሪካ በኔልሰን ማንዴላ፣ ታቦ ምቤኪና አሁን ሥልጣን ላይ ባሉት ጃኮብ ዙማ ተመርታለች፡፡

ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በምክር ቤቱ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉ ቢጠበቅምመ የፕሬዚዳንቱ ንግግር እንዲተላለፍ ተደረጎ ነበር፡፡ ይህ ግን የፕሬዚዳንቱን የፍርድ ቀን አራዘመው እንጂ መፍትሔ አይሰጥም ሲሉ ብዙዎቹ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ነበር፡፡

የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸውን እ.ኤ.አ. በ2019 የሚጨርሱት ፕሬዚዳንት ዙማ፣ የሁለተኛ የምርጫ ዘመናቸው ማብቂያ ላይ ሳይደርሱ ከሥልጣናቸው ሊነሱ ይችላሉም እየተባለ ነው፡፡

ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን በፈቃዳው የማይለቁ ከሆነ በግድ በምክር ቤቱ ምርጫ ከሥልጣናቸው ሊወገዱ ይችላሉ የሚሉ ግን ብዙዎችን ያስማማል፡፡

የጃኮብ ዙማ ፀሐይ ስትጠልቅ

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...