Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አንድ ድርጅት አክሬዲቴሽን ሲሰጠው ያለምንም ጥርጥር ተቀበለው የሚል መልዕክት አለው››

አቶ አርአያ ፍሥሐ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት የተቋቋመው በ2003 ዓ.ም. ሲሆን፣ በጀት ተመድቦለት መንቀሳቀስ የጀመረው ግን በ2004 ዓ.ም. ነው፡፡ መሥሪያ ቤቱ ራሱን ችሎ እንዲወጣ የተደረገው መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ በተጀመረበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም አጠቃላይ የጥራት ጉዳይን በተመለከተ ሲሠራ የነበረው ጥራትና ደረጃዎች ነበር፡፡ አሠራሩ ካለው ዓለም አቀፋዊ አሠራር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ በጥራትና ደረጃዎች ሥር በዳይሬክቶሬት ተለይተው ይከናወኑ የነበሩ ዘርፎች ራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙ ተደረገ፡፡ የፍተሻ ላብራቶሪ፣ የኢንስፔክሽን ሥራ የሚሠራው የተስማሚነትና ምዘና ኢንተርፕራይዝ ተብሎ ለብቻው ተቋቋመ፡፡ ደረጃ የሚያዘጋጀው፣ የሚያስተምረው፣ የሚያሠለጥነውና የሚያማክር የነበረው ዳይሬክቶሬትም የደረጃዎች ኤጀንሲ ተብሎ እንዲቋቋም ሆነ፡፡ ሌላኛው ዘርፍ የዕቃዎችን ትክክለኛነት የሚፈትሸው የሥነ ልክ ኢንስቲትዩሽን ራሱን ችሎ እንዲዋቀር ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ግን እንደእነዚህ ተቋማት የራሱ ዳይሬክቶሬት ኖሮት አልነበረም ይሠራ የነበረው፡፡ በዓለም አቀፍ አሠራር ግን ራሱን ችሎ ነው የሚቋቋመው፡፡ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም የተደረገው በመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ በተደረገ ጥናት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡ የጽሕፈት ቤቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ዋና ዳይሬክተሩን አቶ አርአያን ፍሥሐን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የጽሕፈት ቤቱ ዋና ተግባር ምንድነው?

አቶ አርአያ፡- የደረጃዎች ኤጀንሲ ደረጃ ያወጣል፣ ያስተምራል፣ ያሠለጥናል እንዲተገበር ይደግፋል፡፡ ምርቶችና አገልግሎቶች ደግሞ በአግባቡ እየተሠሩ መሆናቸውን የተስማሚነትና ምዘና ይፈትሻል፡፡ እነዚህ ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን መተግበር የሚያስችለቸው ብቃት አላቸው የላቸውም የሚለውን ደግሞ የሚፈትሸው የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ አክሬዲቴሽን ሦስተኛ ወገን ሆኖ ስህተቶች እንዳይፈጠሩ ብቁነትን ያረጋግጣል፡፡ ወይም ተቋማት የላቀ ብቃት እንዳላቸው ነው የሚፈትሸው፡፡ ተግባሩን የብቃት ማረጋገጥ ሥራ ብሎ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ስለሆነ ነው አክሬዲቴሽን የሚለውን ቃል እንዳለ መጠቀም የመረጥነው፡፡ የላቀ ብቃት የሚለካው ለምሳሌ ፍተሻ ሲደረግ አንድን የላቦራቶሪ ውጤት ትክክለኛ ወይም የተሳሳተ የሚያደርጉ የተለያዩ ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል የሰው ወይም የሠራተኛ ብቃት አንዱ ነው፡፡ ብቃት በሌለው የሰው ኃይል የሚሠራ ሥራ ውጤቱ የተዛባ ነው፡፡ ስለዚህ ጽሕፈት ቤቱ ባለው የሠራተኛ ብቃት መለኪያ መስፈርቶች መሠረት የሠራተኞችን ብቃት ይፈትሻል ማለት ነው፡፡ ለውጤቱ ተፅዕኖ አለው የሚባለው ሌላው ደግሞ የሚሠራባቸው ቁሳቁሶች ናቸው፡፡ መሣሪያው የሚሰጠንን ውጤት በትክክል እናምነዋለን ወይ የሚለውን እርግጠኛ ለመሆን መሣሪያውን በየጊዜው ይፍተሻል፡፡ ከዚህ ሌላ የሙቀት፣ የግፊት፣ የይዘትና ሌሎች የተለያዩ ነገሮች መለኪያዎች አሉ፡፡ እነዚህ መለኪያዎች የሚሰጡት ውጤት ምን ያህል ትክክለኛ ነው የሚለውን ለማወቅ መሣሪያዎቹ በአግባቡ መሥራት አለመሥራታቸውን የሚለካበት ሁኔታ አለ፡፡ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ክፍሎች፣ ውጤቱን ለማግኘት የሚከተሏቸው ሥነ ሥርዓቶችና ሕግጋቶች ሳይቀሩ ይፈተሻል፡፡ ይህንን ሲያልፉ ነው አክሬዲት የምናደርገው፡፡ አንድ ድርጅት አክሬዲቴሽን አገኘ ማለት የሚሰጠውን ውጤት አለምንም ጥርጥር ትክክለኛ መሆኑን አምነህ ተቀበለው የሚል መልዕክት አለው፡፡

ሪፖርተር፡- በምን በምን ዘርፎች ነው አክሬዲት የምታደርጉት?

አቶ አርአያ፡- በኢንስፔክሽን፣ በሕክምና ፍተሻ፣ በፍተሻ ላቦራቶሪ አክሬዲት እንዳርጋለን፡፡ እንዲሁም በሰው ሀይል ሰርተፊኬሽን የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅታችንን ጨርሰናል፡፡ በእነዚህ ዘርፎች አክሬዲት የምናደርግባቸው ወሰኖች ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሕክምና ላቦራቶሪ በምግብ፣ የባዮሎጂ፣ የኬሚካል፣ ለመሳሰሉት አክሬዲት እናደርጋለን፡፡ እነዚህን ወሰኖች የምንፈትሽበት መለኪያ ISO 17025 ነው፡፡ ይህንን ስታንዳርድ ላሟሉ ነው አክሬዲቴሽን የምንሰጠው፡፡ በዚህ የተሰማራ ለመንግሥት ሆነ  ለግል ተቋም፣ ዩኒቨርሲቲም ይሁን ሌላ የምርምር ተቋም በዚህ ISO 17025 እውቅና የሚሰጠው የላቦራቶሪ ውጤቱ በመለኪያው መሠረት ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ አክሬዲት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሌላው በሜዲካል ላቦራቶሪ ዘርፍ ለተሰማሩ የምንሰጠው ነው፡፡ ላቦራቶሪዎች የላቀ ውጤት እንዲሰጡ የተዘጋጀ ISO 15189 የሚባል ስታንዳርድ አለ፣ በዚህ አክሬዲት ይደረጋሉ፡፡ ሦስተኛው የኢንስፔክሽን ዘርፍ ነው፡፡ ለምሳሌ የምግብ ኢንስፔክሽን አለ፡፡ በየሱፐርማርኬቱ የሚሸጡ ምግብ ነክ ነገሮች የተጻፈው ክብደታቸው፣ አቀማመጣቸው ትክክለኛ መሆኑን ኢንስፔክት ይደረጋል፡፡ ከዚህም ሌላ የፊልድ፣ የጥራጥሬ፣ የቡና ደረጃ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የኮንስትራክሽን ኢንስፔክሽን አለ፡፡ ለምሳሌ የኮንስትራክሽን ኢንስፔክሽን ብንወስስድ አይተሽ ከሆነ አንድ ቤት ሲገነባ ኮንትራት የሚሰጥ፣ ኮንትራት የሚቀበል አካል አለ፡፡ ዳኛ ሰጪ የሚባለው ደግሞ ኮንሰልታንት (አማካሪ) አለ፡፡ አማካሪው ልክ ነው ልክ አይደለም ይከፈለው አይከፈለው እያለ ውሳኔ የሚሰጥ፣ የሚጠቀሙትን የግንባት ግብዓቶች ትክክለኛነትና የሚጠቀሙትን መጠን እያረጋገጠ ጨምሩ ቀንሱ እያለ ውሳኔ የሚያስተላልፍ አካል ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማየት ሆን ተብሎ የተቀመጠ አካል ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ቤቱ ቢበላሽ የሚጠየቀው ኮንትራክተሩ ሳይሆን ቀጥል ብሎ ግንባትውን ያስቀጠለው የኢንስፔክሽን አካል ነው፡፡ እነዚህ አካላት ዓለም አቀፉን ISO 17020 አሟልተው ሲገኙ ነው የጥራት ማረጋገጫ የምንሰጣቸው፡፡ ሌላው የምርት ሠርተፊኬሽን የሚባለው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ እሽግ ውኃን አንስተን ብንመረምር የምናገኘው ውጤት በተመሳሳይ የምርት ስም የሚመረቱ ሌሎቹን ምርቶች ላይወክል ይችላል፡፡ እንዲወክል ከተፈለገ ግን ከምንጩ ጀምሮ እስከ ማከፋፈያ ሥርዓቱ ድረስ ያለው ሂደት ሁሉ መፈተሽ አለበት ማለት ነው፡፡ የዚህኛው መሥፈርት መለኪያ ISO 17056 የምግብ ምርት ሠርተፊኬሽን ነው፡፡ ይህ በአግባቡ ሥራ ላይ ካልዋለ የምግብ ሠርተፊኬሽን መስጠት አይችልም፡፡ መስፈርቱን ተከትለው ለሚሠሩ ነው አክሬዲት የምናደርገው፡፡ በሲስተም ሠርተፊኬሽን ለተሰማሩ አካላትም አክሬዲት እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ ISO 9001 ኳሊቲ ማኔጅመንት ሲስተም (የጥራት ማረጋገጫ)፣ ለኢንቫይሮመንታል ማኔጅመንት ሲስተምም ይሰጣል፡፡ እንዲህ ያለ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ከንግድ አኳያ ለማያሟሉ ድርጅቶች ሠርተፊኬት እንዳይሰጡ ለማድረግ በISO 17021 መሥፈርት መሠረት ተፈትሸው አክሬዲት ይደረጋሉ፡፡ በዚህ መሠረት የሚሰጡት ሠርተፊኬሽን ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ የሰው ብቃት ለሚለኩ አካላትም አክሬዲቴሽን እንሰጣለን፡፡ ለአንድ ሥራ የሚመጥኑ ባለሙያዎችን ብቃት የሚለኩ አካላት አሉ እነሱን ደግሞ እኛ እንልካቸዋለን ማለት ነው፡፡ እነዚህ አካላት በሥርዓት ካልተለኩ ሌላውን መለካት ከባድ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ሲኦሲ፣ የመንጃ ፈቃድ የሚሰጡ ድርጅቶች በዚህ ሥር ይጠቃለላሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ሰው ለመለካት የሚያስችላቸው አሠራርና ሥርዓት እንዳላቸው ይለካሉ፡፡ የሚለኩበት መሥፈርትም ISO 17024 ይባላል፡፡ እነዚህ በሙሉ የምንሰጣቸው የአክሬዲቴሽን አገልግሎት ዘርፎቻችን ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያሉ የምሥክር ወረቀቶችን የሚሰጡ ተቋማት የትኞቹ ናቸው? በዘርፉ የተሰማሩ የግል ድርጅቶችስ ይኖራሉ?

አቶ አርአያ፡- ተስማሚነትና ምዘና ISO ካር፣ ዲኪኤስ የተባሉ ሠርተፊኬቶችን ይሰጣሉ፡፡፡ ለግልም ሆነ ለመንግሥት ተቋማት ክፍት ሲሆን አክሬዲቴሽን ተሰጣቸው ማለት የሚሰጡት ውጤት አለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀባይነት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምትሰጡት አገልግሎት ምንም ያህል ወሳኝ ቢሆንም አስገዳጅ ግን አይደለም፡፡ ይህ በሥራችሁ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖር ግልጽ ነው፡፡

አቶ አርአያ፡- አክሬዲቴሽን የሚሰጠው በፈቃደኝነት ነው፡፡ ካልመጣችሁ እናሽጋችኋለን፣ እናሥራችኋለን፣ ፈቃዳችሁን እንነጥቃለን አይልም፡፡ አንድ ድርጀት አክሬዲትድ አልሆነም ማለት ዕርምጃ ይወሰድበታል ማለት አይደለም፡፡ ዕርምጃ ወሰድን ማለት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ሆን ማለት ነው፡፡ አክሬዲቴሽን በነፃነት ሦስተኛ ወገን ሆኖ ምሥክርነት የሚሰጥ ተቋም እንጂ አስገዳጅ አይደለም፡፡ ካልመጣሽ ድርጅትሽን እዘጋለሁ፣ ፈቃድሽን እነጥቃለሁ አይልም፡፡ ይህንን የሚለው አካል ተቆጣጣሪ ተቋም ነው፡፡ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት አክሬዲቴሽንን አስገዳጅ የማድረግ መብት አላቸው፡፡ በሌላው ዓለም ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት አክሬዲትን ያስገድዳሉ፡፡ አክሬዲቴሽን ተቋም ግን አያስገድድም፡፡ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ግን ለሕዝቡ ጤንነት፣ ደኅንነት፣ ፍትኃዊ ገበያ እንዲኖር ሲል፣ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ገበያ ላይ እንዳያጡ ሲሉ አክሬዲቴሽንን አስገዳጅ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ውስጥ አክሬዲቴሽን አስገዳጅ መሆን አለበት ብለው ያምናሉ?

አቶ አርአያ፡- አዎ አስገዳጅ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ በአገሪቱ ትልቅ በጀት እየወሰደ የሚገኘው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው፡፡ ይህ በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ ለሙስና የተጋለጠ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ኮንትራክተር የሠራውን ሕንፃ ለአማካሪው እባክህ ገንዘብ ልስጥህና አሳልፍልኝ ቢለው አማካሪው ከሚያገኘው ገንዘብ የበለጠ እንደሚከፍል ስለሚያውቅ አያሳልፍለትም፡፡ ከተበላሸ የሚጠየቀው አማካሪው ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ልዳንና በእኔ ችግር አንተ ተጠየቅልኝ የሚለውን አካል አይቀበለውም፡፡ ይህም ሙስና እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ደረጃውን ያልጠበቀ ግንባታ እንዳይኖርም ይረዳል፡፡ አሁን የሚገቡ ግብዓቶች በእምነት ነው እንጂ ከአፈር ቢቀላቀሉ፣ ወይም ከሌላ ባዕድ ነገር ጋር ቢቀላቀሉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ሥርዓት ሲኖር ግን ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች እንዳይገቡ፣ የብረት አጠቃቀም ትክክል ነው አይደለም፣ በተባለው መጠን እየገባ ነው አይደለም የሚለውን ማወቅ ይቻላል፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ ብቁ የሰው ኃይል መኖር አለመኖሩን ያረጋግጣል፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች ሁሉ በሥርዓት ተናበው ስለሚያልፉ ለሙስና የሚያጋልጡ ድርድሮች አይኖሩም ማለት ነው፡፡ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በራሱ ሲሄድ ግን ለድርድር የተጋለጠ ነው፡፡ እኛ የምንለው ወደ ድርድር አትሂድ፣ መረጃ እንሰጥሃለን በመረጃው መሠረት ዕርምጃ ውሰድ ነው፡፡ የምንሰጠው መረጃ ስህተት ከሆነ እኛ እንጠየቃለን፡፡ ነገር ግን ራሱ ሄዶ ከፈተሸ፣ ራሱ ሄደ ከቀጣ ለሁሉም ነገር የተጋጠ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ያለው አሠራር ክፍተት አለበት፣ ተቆጣጣሪው ድርጅት ለሙስና ድርድር ተጋልጧል እያሉ ነው?

አቶ አርአያ፡- በአሁኑ ወቅት ተቆጣጣሪ ድርጅት በራሱ ሄዶ መረጃ እየሰበሰበ ነው፡፡ ሁሉን ነገር በሥርዓት ካልመለስን መፍትሔ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ በተዘጋጀው ሥርዓት መመራት ካልተቻለ በሰዎች ግላዊ አመለካከትና አሠራር መቀጠል ዋጋ ያስከፍላል፡፡፡

ሪፖርተር፡- ጽሕፈት ቤቱ ሥራውን ለማከናወን ያሉበት ሌሎች ማነቆዎች ምንድናቸው?

አቶ አርአያ፡- ያሉብን ችግሮች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ አንደኛ ድርጅቶች እንዲያሟሉ የሚጠየቁት መሥፈርት ከባድ ስለሆነ ወደእኛ አይመጡም፡፡ በተለይ የተማረና ብቁ የሰው ኃይል ማግኘት ላይ ችግር አለ፡፡ ብዙ ገንዘብና ጊዜ ወቶባቸው የሚሠለጥኑ ባለሙያዎች ትንሽ እንደሠሩ ሥራ ይቀይራሉ፡፡ የአክሬዲቴሽን ሥራ ሰከን ባለ ሁኔታ የሚሠራ ነው፡፡ ያለው የሰው ኃይል ችግር ግን ለድርጅቶቹ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ነው፡፡ ሌላው በላቦራቶሪዎች ላይ የሚያግጥመው ችግር ነው፡፡ ተቋማት ላቦራቶሪያቸው ምን ያህል ብቁ መሆኑን የሚለኩበት ከባህር ማዶ የሚመጣ ሚስጥራዊ ውጤት የያዘ ሠርቲፊይድ ሪፈረንስን የተባለውን ቴስት (ናሙና) ዕውቅና ካለው ቦታ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ጉምሩክ ላይ የሚጠየቁት ቀረጥ ከፍተኛ መሆንም ሌላው ትልቅ ችግር ነው፡፡ ይህ ቴስት ለጥራት ማስጠበቂያ የሚውል የደም፣ የሽንት አልያም የሌላ ነገር ናሙና ነው፡፡ አንድን ማሽን ካሊብሬት ለማድረግ ሠርቲፋይድ ሪፈረንስ ማቴሪያል ተብሎ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ውጤቱ በሚስጥር የተያዘው የደም ናሙና አገር ውስጥ ባለ በአንድ ላቦራቶሪ ውስጥ ሲመራመር የሚሰጠው ውጤት በሚስጥር ከተያዘው ጋር ከተለያየ ላቦራቶሪው ችግር አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ናሙና ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ከቀረጥ ነፃ የሚባበት መንገድ ቢፈጠር ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አክሬዲቴሽን የሚሰጣቸውን ተቋማት ተከታትሎ የመፈተሹ ነገር ምን ይመስላል?

አቶ አርአያ፡- ተቋማት እንደምንም ብለው አክሬዲቴሽን ያገኛሉ፡፡ ከባዱ ነገር የተሰጣቸውን ዕውቅና ማስጠበቁ ላይ ነው፡፡ አንድ ድርጅት የተሰጠውን ዕውቅና አጣ ማለት ለዝናውም  ለስሙም ጥሩ አይደለም፡፡ ለአንድ ድርጅት ዕውቅና ከሰጠን ከስድስት ወራት በኋላ በድጋሚ ሄደን እንፈትሸዋለን፡፡ በነበራቸው ነገር ከቀጠሉ ሠርተፊኬቱ ይቀጥላል፡፡ መቀጠል ካልቻሉ ግን ሠርተፊኬቱን ይነጠቃሉ፡፡ ሠርተፊኬቱን ሲያገኙ በዌብ ሳይታችን ላይ ስማቸው ይገባል፡፡ ሠርተፊኬቱን ስያጡም ስማቸው ከስም ዝርዝሩ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ድርጅት ዕውቅና ማግኘቱን በመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያ በማስነገር ጉዳዩን እንዲራገብ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ዕውቅናውን ሲያጣ ጽሕፈት ቤቱ በዚያው መጠን ማስታወቂያ በማስነገር ማኅበረሰቡ እንዲጠነቀቅ የማድረግ ሥራ ይሠራልን?

አቶ አርአያ፡- በዚያው መጠን አናስነግርም፡፡ ለምን ቢባል ጀማሪ የሆነን አንድ ተቋም ማስደንገጥ ስለሚሆን ነው፡፡ ከዚህ ሌላም ቢዝነሳቸውን ይገድለዋል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች እኮ ካልመጡት ይሻላሉ፡፡ በመምጣታቸው ካልመጡት በለይ እንዲጎዱ መሆን የለባቸውም፡ አስገዳጅ ሲሆን በግድ እንዲመጡ ይደረጋል፡፡ በፈቃደኝነት የመጣውን እንዲህ ማድረግ ግን በመምጣቱ እንዲቀጣ ማድረግ፣ ሌላውም እንዲፈራ ማድረግ ነው፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...