Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያና የኢራን ጥበባዊ ትስስር

የኢትዮጵያና የኢራን ጥበባዊ ትስስር

ቀን:

የምሽቱ መርሐ ግብር የተጀመረው በመሶብ ባንድ ባህላዊ ሙዚቃዎች ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተገኙትን ታዳሚዎች በሙዚቃዎቻቸው ዘና አድርገዋል፡፡ ባንዱ በተለይም ግጥም በጃዝ በሚቀርብባቸው የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች በባህላዊ ሙዚቃ የግጥም ሥራዎችን በማጀብ ይታወቃል፡፡ በክራር፣ በመሰንቆ፣ በዋሽንትና በከበሮ ውህድ ግጥሞቻቸውን ያስደመጡ ጸሐፍትም በርካታ ናቸው፡፡

መሶብ ባንክ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተገኙት የኢራን አብዮትን 39ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ መርሐ ግብር ነበር፡፡ ምሽቱ ኢትዮጵያውያን ገጣሚዎች ሥራዎቻቸውን ያቀረቡበትና ከኢራን የመጡ ሙዚቀኞች የአገራቸውን ባህላዊ ዘፈኖች ያስደመጡበትም ነበር፡፡ መሶብ ባንድ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃዎች ሲያስደምጡ፣ የኢራኑ ናሱት ባንድ የኢራን ሙዚቃዎችን አቅርበዋል፡፡

ምሽቱ በግጥምና በሙዚቃ በኢትዮጵያና በኢራን መካከል የባህል ልውውጥ ለማድረግ መሰናዳቱን አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የኢራን ኤምባሲና እናት ማስታወቂያ በጋራ ያዘጋጁት የባህል ልውውጥ መድረክ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የሥነ ጽሑፍ ትስስር የጎላበት ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ጸሐፍት የኢራን ደራሲዎችን ሥራዎች እንደ መነሻ ከመውሰድ ባሻገር ጽሑፎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችም ተርጉመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኦመር ኻያምና ባባ ታሒርን ጨምሮ የበርካታ የኢራን ገጣሚያን ሥራዎች ወደ አማርኛ ተተርጉመዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ መጻሕፍት መካከል የበረከት በላይነህ ‹‹የመንፈስ ከፍታ›› የተሰኘ የግጥም ስብስብ መጽሐፍ ይጠቀሳል፡፡ እንደ አብዛኞቹ ወጣት ገጣሚዎች በኢራን ግጥሞች መሳቡ፣ ሥራዎቻቸውን ወደ አማርኛ እንዲተረጉም አድርጎታል፡፡

ፒያሳ አካባቢ ይገኝ የነበረውና አሁን በዕድሳት ምክንያት አገልግሎት የማይሰጠው ኦመር ኻያም ባር፣ ኢትዮጵያውያን በኢራን ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ስለመሳባቸው ማሳያ ናቸው፡፡ ቦታው በርካታ ጸሐፍት የሚገናኙበት እንደነበረም ይታወሳል፡፡

የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው የግጥምና የሙዚቃ ምሽት ገጣሚያኑ ትዕግስት ማሞና ሰሎሞን ሳህለ ግጥም አቅርበዋል፡፡ ትዕግስት ‹‹ይድረስ ለወንድሜ›› የተሰኘውን ግጥሟን አስደምጣለች፡፡ ግጥሙ በብሔር መከፋፈል ከስሞ ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርግ አገራዊ ስሜት እንዲጎላ የሚያሳሰብ ሲሆን፣ በመሶብ ባንድ ታጅባ አቅርባዋለች፡፡ ሰሎሞንም ከባንዱ ጋር ተዋህዶ ግጥሙን አስደምጧል፡፡

ገጣሚያኑን ተከትለው ወደ መድረክ የወጣው ናሱት የሙዚቃ ባንድ ሲሆን፣ ሁለት ሴትና አራት ወንድ ኢራናውያን ሙዚቀኞች ይገኙበታል፡፡ መሪ ድምጻዊው ካስደመጠው ዘፈኖች ተጨማሪ በመሣሪያ ብቻ የተቀናበሩ ሙዚቃዎችም ቀርበዋል፡፡ ከናሱት ቀደም ብለው ሙዚቃ እንዳቀረቡት መሶብ ባንዶች፣ የአገራቸውን ሙዚቃ በባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ታጅበው ለታዳሚያኑ አስደምጠዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል ካለው ሥነ ጽሑፋዊ ትስስር በተጨማሪ ሙዚቃዊ ውህደቱም ይጠቀሳል፡፡ የትንፋሽና የምት መሣሪያዎቻቸው ከኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር ተቀራራቢነት አላቸው፡፡ ሙዚቀኞቹ ሥራዎቻቸውን ከማቅረባቸው አስቀድሞ ለታዳሚው ያላቸውን ክብር ከማሳየታቸውም በላይ ኢትዮጵያን እንደሚወዱም ተናግረዋል፡፡

ናሱት፣ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሙዚቃቸውን አቅርበዋል፡፡ ወደ አውሮፓና እስያ በማቅናትም ኮንሰርቶች አካሂደዋል፡፡ የባንዱ አባላት የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን በመጠቀም መድረክ ላይ የተለያዩ ድምፆችን በመፍጠር (ኢምፕሮቫይዝ በማድረግ) ይታወቃሉ፡፡ በብሔራዊ ቴአትር መድረክም በተመሳሳይ ሁኔታ ልዩ ልዩ ድምፆችን ሲፈጥሩ ከታዳሚው አድናቆትን ተችሯቸዋል፡፡

የኢራን ሙዚቃ፣ ከሥነ ጽሑፋቸው ቀጥሎ በኢትዮጵያውያን ይወደዳል፡፡ ፕርዥያን ሚውዚክ ወይም የፐርዥያ ሙዚቃ በሚል በመላው ዓለም የሚታወቀው የኢራን ሙዚቃ፣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ታዋቂ ነው፡፡ በምዕራብ እስያ የምትገኘው ኢራን (ኢስላሚክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኢራን) ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡

በኢትዮጵያና በኢራን በኩልም ያሉት የመርሐ ግብሩ አዘጋጆች፣ በኢትዮጵያና በኢራን መካከል ያለውን የረዥም ጊዜ ግንኙነት ከግምት በማስገባት፣ በርካታ የባህል ልውውጥ መሰናዶዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል፡፡ በመድረኩ ንግግር ያደረጉ የሁለቱ አገሮች ተወካዮች ከኢራንም ከኢትዮጵያም ግጥሞች በማስደመጥ የአገሪቱ ትስስር ጥብቅ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ሙዚቀኞቹ ሥራዎቻቸውን ሲያቀርቡ፣ ታዳሚዎቹ የሙዚቃውን ምት ተከትለው በማጨብጨብ ያጅቡ ነበር፡፡ ምሽቱ ሥነ ጽሑፍ፣ ሙዚቃና ባህል የተጣመሩበትም ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያና ሌሎችም አገሮች የባህል ልውውጥ መድረኮቹ ይዘጋጃሉ፡፡ ሆኖም ከየአገሮቹ አምባሳደሮችና ጥቂት የጥበብ አድናቂዎች ባለፈ በመርሐ ግብሮቹ በርካታ ታዳሚዎች ሲገኙ አይስተዋልም፡፡

የባህል ልውውጥ መድረኮች የሁለትና ካዛም በላይ አገሮች፣ ባህላዊ እሴቶች የሚታዩበት እንደመሆኑ ብዙዎች እንዲታደሙ ማስታወቂያ መሥራት ይቻላል፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን ጎን ለጎን ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ተጠቅሞ በማስተዋወቅ ተደራሽነቱን ማስፋትም ይቻላል፡፡ በኢራንና በኢትዮጵያ የባህል ልውውጥ መድረክ የተገኙት ሰዎች እምብዛም አልነበሩም፡፡

በተለያዩ አጋጣሚዎች የሥነ ጽሑፍና ሙዚቃ መርሐ ግብሮች ሲዘጋጁ ታዳሚዎች አዳራሽ ሲሞሉ ይስተዋላል፡፡ እነዚህን ታዳሚዎች ወደ ባህል ልውውጥ ዝግጅቶች መጋበዝ ሌላው አማራጭ ነው፡፡

ወደ 12 ሰዓት ገደማ የተጀመረው የኢትዮ ኢራን የሥነ ጸሑፍ፣ ሙዚቃና ባህል መሰናዶ የተገባደደው በናሱት ባንድ ሙዚቃ ነበር፡፡ የባንዱ አባላት በታዳሚው ጭብጨባ ታጅበው ባህላዊ ሙዚቃ አቅርበው፣ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...