Sunday, December 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርመነጣጠል ከቀበራቸው አገሮች የምንማራቸው እውነታዎች

መነጣጠል ከቀበራቸው አገሮች የምንማራቸው እውነታዎች

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

አሁን ባለችው ዓለም በተለያዩ ጫፎች የሚገኙ ሕዝቦች በማዕከላዊው መንግሥት በኩል ጥቅማችን አልተከበረም፣ መብታችን ተገፏል፣ የማንነት ትውፊቶቻችን  ተጨፍልቀዋል፣ ካለን ሀብት ማግኘት ያለብንን ሌሎች ባልተገባ መንገድ እየመዘበሩብን ነው፣ . . . ወዘተ ብለው ሲያስቡ በሕገ መንግሥት መሠረት ወይም በኃይል (በጉልበት) ተገንጥለው የራሳቸውን መንግሥት ሲመሠርቱ ተመልክተናል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ በተለይ በሦስተኛው ዓለም የፖለቲካ ሥልጣንን የሚሹና የጥገኝነት አባዜ የተጠናወታቸው ፖለቲከኞች ሕዝቡን ለዘመናት በኖረበት ምድር ጥቅሙን ለማስከበር  ከመታገል ይልቅ፣ ወደ መነጠል ዓላማ በመንዳት ከሰፊው አገራዊ ኅብረትና ሀብት ተቋዳሽ እንዳይሆን፣ ይልቁንም እርስ በርስ እየታመሰና ከጦርነት አዙሪት ሳይወጣ የጥቂቶች መጠቀሚያ እንዲሆን ሲያደርጉት ይስተዋላል፡፡

በተለይ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተምና የምሥራቅና ምዕራብ የውጥረት ፖለቲካ መጎተት በኋላ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት (USSR) ከ16 በላይ ራሳቸውን የቻሉ መንግሥታትን በመገነጣጣል ለመፍጠር ተገዳለች፡፡ እነዚህ አገሮች ከነበራቸው ታሪካዊ፣ ሥልጣኔና የትምህርት አትኩሮት አንፃር በመነጠላቸው ወደ ኋላቀርነት አዘቅት ወድቀዋል ባይባሉም፣ እንደ ጎረቤቶቻቸው አውሮፓውያንም ሆነ እንደ ቀሪዋ ምድረ ሩሲያ የበለፀጉና የበረቱ መሆን አልቻሉም፡፡ ከጥቂቶቹ በስተቀር አሁንም ድረስ የዴሞክራሲ ምልዑነት ተግዳሮት እየፈተናቸው ይገኛል፡፡  

አንዳንዶቹ የአውሮፓ አገሮችም ‹‹የለከፈ ሰይጣን ሳያቀስ አይመለስም››  እንዲሉ፣  እስከ ቅርብ ጊዜው የዩክሪን ሕዝብ ውሳኔ ድረስ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ እንዳሉ  ይታወቃል፡፡ በእርግጥ በዴሞክራሲም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዳብረዋል በሚባሉት የአውሮፓ አገሮችም ቢሆን ይኼ በሕገ መንግሥት ላይ ተመሥርቶ የመገንጠል ዝንባሌ መታየቱ አልቀረም፡፡ ለአብነት ያህል የስፔንና የካታሎኒያ ውዝግብን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በስቃየኛው የኢራቅ ሕዝብ ውስጥም የኩርድ ሕዝቦች (ምንም እንኳን የደረሰባቸው በደልና ግፍ እንደ ቀላል የሚቆጠር ባይሆንም) ከአራት አሠርት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ እየሞቱለት ያለው ዓላማ፣ መገንጠልና ራስን መቻል እንደሆነ እስካሁንም በመፋለም ላይ መሆናቸውን ማየት ይቻላል፡፡

ጉዳዩን በአኅጉረ አፍሪካ ስንመለከተው ደግሞ አሁን ካሉት 53 አገሮች  በተቀነጫጨበ መንገድ እየተገነጠሉ ብዙ ብጥስጥስ አገሮችን ለመመሥረት ያለው ሽኩቻ ሥር የሰደደ እንደሆነ፣ የፖለቲካ ተንታኞች ደጋግመው ሲገልጹት ይደመጣል፡፡ በተለይ በእኛ አኅጉር ፓና አፍሪካኒዝም እየተቀነቀነም ቢሆን የመነጣጣሉ አመለካካት  እንዲፋፋ የሚያደርጉ ምክንያቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

ቀዳሚው አፍሪካ የብዝኃነት ምድር የመሆኗ እውነታ ነው (በነገራችን ላይ በአኅጉሩ ከ3,500 በላይ ጎሳዎች (ብሔረሰቦች) እንደሚኖሩ ልብ ይሏል)፡፡ ሁለተኛው ቅኝ ገዥዎች የአፍሪካን ውህድ ሕዝቦች ሳይቀር ለአገዛዝ እንዲያሚቻቸው በመበታተንና በማለያየት መጥፎ ዘር እየዘሩ ያበቀሉት አረም እስካሁንም ተንሰራፍቶ የቆየ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ላይ ትንሽ በማይባሉ ልሂቃን በኩል ለሥልጣን ያለው የተውገረገረ አተያይና ኪራይ ሰብሳቢነቱ ሲባባስ፣ ፖለቲከኞች በየትም ተጠማዘው ሥልጣን ለመያዝና ሕዝብን መጠቀሚያ ፈረስ ለማድረግ የመሻታቸው እውነታ የራስ መንግሥት ለይስሙላም ቢሆን ለመመሥረት እንዲጓጉ እያደረጋቸው ነው፡፡ በዛሬው ምልከታችን ጎረቤት የሆኑትን ሁለት ግንጥል ምድሮችና የጥገኞች መፈንጫዎችን በማንሳት የክስረታቸውን ጫፍ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡ ይህን ሀቅም ልብ ያለው ልብ ይበል ለማለት እንወዳለን፡፡

የደቡብ ሱዳን የአዘቅት መንገድ!

ደቡብ ሱዳን ከቅርብ ጊዜዎቹ ነፃ ከወጡ የአፍሪካ አገሮች የመጨረሻዋ ስትሆን ከእናት ምድሯ (ሰሜን) ሱዳን ለመነጠል (መቶ ሺዎች መስዋዕት የሆኑበት፣ ከዚሁ በላይ የአካል ጉዳተኞችን የተሸከመች፣ እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቋሚ ተሰዳጆች እስካሁንም ያሏት) ረዥሙን የእርስ በርስ ጦርነት ካሳለፈች በኋላ የተደረሰበት የፖለቲካ ውጤት ነች፡፡ አጠቃላይ ሕዝቧ 12.8 ሚሊዮን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ያህሉ ዕርዳታ ጠባቂ ነው፡፡ አሁንም ድረስ ለችጋርና ለረሃብ የተጋለጠው ሕዝብ ትንሽ አይደለም፡፡ የዚህችው መከረኛ አገር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ  በስደተኛ ጣቢያዎች የሚንገላታ ሲሆን፣ ቁጥሩ በየጊዜው እንደሚዋዥቅም ይታወቃል፡፡

አገሪቱ ከሱዳን ተገንጥላ ራሷን ችላለች ከመባሉ በስተቀር በሙስናና በብልሹ አሠራር ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት የሚባክንባት፣ የሥልጣን ሽኩቻና በዚሁ መዘዝም የእርስ በርስ ግጭቶች የበረቱባት እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ካልተፈቱ ደግሞ አገሪቱ ከሁከትና ከረብሻ መውጫ የምታጣ ብቻ ሳትሆን፣ ብዙዎች  እንደሚሉትም ጉርብትናዋ ለአገራችን ጭምር ፈተና መሆኑም አይቀርም፡፡

ሱዳን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችው በ1956 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በካርቱምና በጁባ (በደቡብ ሱዳን) መካከል ሁል ጊዜም አለመግባባትና ጦርነት ለአሥርት ዓመታት ያህል ወጣ ገባ እያለ ቆይቶ ነው እ.ኤ.አ. 2011 ላይ የተቋጨው፡፡ በደቡብ ሱዳን የተካሄደው ከካርቱም ጋር አብሮ የመኖር ወይም የመለያየት ሪፈረንደምን ተከትሎ መለያየቱ (መፋታቱ) ስለተመረጠ፣ ደቡብ ሱዳን የራሷን ነፃ መንግሥት የመሠረተችበት ጊዜ ላይ ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአዲሱ መንግሥት አደረጃጀት ይዘትና ፖለቲካዊ ቁመና  የደቡብ ሱዳንን አንድነት ያመጣ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ሳይሰጥ ዳግም ትርምስን የሚጋብዝ ስግብግብነት ውስጥ ገብቷል፡፡ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ተያይዞ ገደል ይሉዋል ይህንኑ ነው፡፡

ደቡብ ሱዳን ጨቁናኛለች ከምትለው ሱዳን ነፃ ለመውጣት (ለመገንጠል) ለዓመታት በጦርነት ውስጥ መቆየቷ አንሶ አሁንም ወደ እርስ በርስ ግጭት አምርታለች፡፡ በእርግጥም አገሪቱ በአንድነት መንፈስ፣ በሆደ ሰፊነት፣ በመቻቻልና በጠንካራ ቁርጠኝነት ካልተመራች ለበርካታ የእርስ በርስ ግጭቶች የተጋለጠች መሆኗ  ቀድሞም የተገመተ ነበር፡፡ ብዙ ዓይነት ጐሳዎች ያሉባት፣ አንዱ በሌላው ላይ የበላይ ለመሆን ማንኛውንም አስከፊ ዕርምጃ ለመውሰድ ወደኋላ የማይልባት፣ ከቀላል እስከ ከባድ መሣሪያ ድረስ የታጠቁ ግለሰቦችና ቡድኖች የሞሉባትና አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት አስቸጋሪ የሆነባት አገር ናት፡፡ መዘዟ ከራስ አልፎ ለጎረቤቶችም የሚተርፍ ጠንቀኛ ምድር እየሆነች ትገኛለች፡፡

ሌላው ቀርቶ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ በፕሬዚዳንቱ ሳል ቫኪርና በቀድሞው ምክትላቸው ሬክ ማቻር ብሎም በደጋፊ የጎሳ አባሎቻቸው መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በተጫረ ጦርነት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐቻቸው ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩትም ሕይወታቸውን   አጥተዋል፡፡ በሁለቱ መሪዎች ራስ ወዳድነትም ይባል ለሕዝብ አለማሰብ የተሞከሩ ሽምግልናዎች ሁሉ እየከሸፉ፣ የግጭቱ ሒደትም ያዝ ለቀቅ እየለ እስካሁንም የሕዝቦቻቸውን ስቃይና መከራ እያበረከተው ቀጥሏል፡፡ እዚያ የተፈጠረው ችግር አልፎ አልፎ እዚህ ለእኛም የራስ ምታት (ቢያንስ በጋምቤላ አካባቢ ለሚታዩ የፀጥታ ችግሮች)  እስከ መሆን ደርሷል፡፡

ብዙዎቹ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ያሉት እኛ ዘንድ መሆኑም የሚፈጥረው ጫና ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ማቅረብና ፀጥታቸውን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ኃላፊነቱ የኢትዮጵያ ነው፡፡ ሁለቱን መሪዎች ለማደራደርና ለማስማማት ከፍተኛውን ሚና ስትጫወት የነበረችው (በሌሎች ጎረቤቶች አገሮች እስክትወቀስ ድረስ) አገራችን ናት፡፡ ድርድር ተደርጎና ስምምነት ላይ ተደርሶ፣ ሬክ ማቻር ጁባ ገብተው የምክትል ፕሬዚዳንቱን ሥልጣን ተረክበው የተረጋጋ ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ሲጠበቅ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ማቻር ጊዜ ገደቡን ባያከብሩም ጁባ ገብተው የብሔራዊ አንድነት መንግሥቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ቃለ መሐላ ለመፈጸም በቅተው ነበር፡፡ ግን ረዥም ርቀት መሄድ ባለመቻሉ አሁንም ማቻር አፈንግጠው ሲሸምቁ (ሲሰወሩ) በምትካቸው ሌላ ሰው ተሾሟል፡፡ በዚህ መዘዝ አሁንም የተገፉ የሚመስላቸውና ያኮረፉ ደቡብ ሱዳናዊን ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡ ምስቅልቅሉም አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖረው አገር እየበደለ እንደ ቀጠለ ነው፡፡

ስለሆነም አሁንም አገሪቱ እዚህ ግባ የሚባል ሰላም አላገኘችም፡፡ በውስጧ ካሉት ጐሳዎች ብዛትና በመካከላቸው ካለው ቅራኔ ጥልቀትና ስፋት አንፃር ሲታይ ጠንካራ የፌዴራል ባህርይ ያለው ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መመሥረት አስቸጋሪ የሆነባትም  መስሏል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደቡብ ሱዳን የሚያስፈልጋት ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ቢሆንም፣  ከቶውንም የማደግ ምልክት ያለውና አሳታፊ መንግሥታዊ ሥርዓት አልፈጠረችም የሚሉ ተንታኞች እየበዙ ነው፡፡ የአገሪቱ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብትም ያለ ውጤት እንዲመክን እየተደረገ ከመሆኑ ባሻገር፣ የዓለም የድህነት ጭራ ላይ የምትገኝና ወደ ውድቀት የምታመራ (Failed State) አገሮች ተርታ የተመደበችም ሆናለች፡፡ አሁንም አገራችንና ኢጋድ የተሰኘው ቀጣናዊ ማኅበር መታከታቸው ባይቀርም፡፡ 

በእንደዚህ ዓይነቶቹ የብዝኃነት ምድሮች ፌዴራሊዝም እንደ ሥርዓት ከሌለና ራስን በራስ የማስተዳደር የሕዝቦች መብት ካልተረጋገጠ፣ በተለይ ደግሞ ሁሉንም ጐሳዎች በአንድ ወይም ‹‹ሁለት ታላላቅ ጐሳዎች›› በተሞላ ማዕከላዊ መንግሥት ሥር ጨፍልቆ ለማስተዳዳር መሞከር በጐሳዎቹ መካከል መጨራረስ ያስከትላል፡፡ በዚህ ላይ የዴሞክራሲ ዕጦት፣ ድህነትና ሙስና ተጨምሮበት አገር ለመሆን ማሰብ ከንቱ ድካም ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ አደጋ ውጤቱ አስከፊ መሆኑንም ይህችው መከረኛ አገር እያሳየችን ነው፡፡

በጥቅሉ መገንጠል ለደቡብ ሱዳናዊያን ያመጣው እዚህ ግባ የሚባል ፋይዳ የለም፡፡ እንዲያውም ከአንዱ ያልተመቸ አገዛዝ ወደ ሌላ ጨፍላቂ አገዛዝ መሸጋገር ነው የተረፋቸው የሚሉ ወገኖች ብዙዎች ናቸው፡፡ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታና ሕዝቦቿም ያለመደማመጥ ተስፋ ደብዝዞ፣ ሥርዓቱ የውድቀት ምልክት እስከመሆን የደረሰው ዴሞክራሲያዊ አንድነት መገንባት የተሳነው የራስ ወዳድነት አካሄድን በመከተሉ ነው፡፡ ይህ እውነታ ነው እንግዲህ መነጠልም ይባል፣ መገንጠል ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ለዕድገት ዋስትና ሊሆን አይችልም የሚባለው፡፡

የኤርትራ ሕዝቦች የስቃይ ሦስት አሥርቶች

ሌላዋ ጎረቤት አገር ኤርትራ ከ6.2 ሚሊዮን ያልበለጡ ሕዝቦችን በአግባቡ ማስተዳዳር ያልቻለች የውድቀት ተምሳሌት አገር ከመሆን ያልዳነች ነች፡፡ አገሪቱ በተፈጥሮ ፀጋና በመልክዓ ምድር ለመቀየር ዕድል ቢኖራትም ጥገኛው ሥርዓት እየገዘገዛት፣ ስድስትና ሰባት ብሔረሰቦችን አጣጥሞ፣ ጥቂት የሃይማኖት ተከታዮችን አቻችሎ መምራት ያልቻለ፣ ዴሞክራሲ ማስፈን አይደለም መሞከር የተሳነው የፖለቲካ ሥርዓት የበቀለባት ምድርም ነች፡፡  

የኤርትራ ሕዝብ በጽንፈኛዎቹ የሻዕቢያ መሪዎች ገፋፊነትም ይባል በራሱ መነሳሳት ከእናት አገሩ ኢትዮጵያ የተገነጠለው ቢያንስ ለሦስት አሥርት ዓመታት ገደማ  ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ እንደ ነበረ ሊካድ አይችልም፡፡ ይህ ሕዝብ ምንም እንኳን በተለያዩ ባዕድ አገሮች በቅኝ ግዛት ተይዞ በመኖሩ፣ ጆኦ ፖለቲካዊ ሁኔታው ወደ ባህር ጠርዝ እንዲሠፍር ያደረገው ስለሆነና በቀድሞ የአገራችን ሥርዓቶች ላይም  ‹‹መብቴ አልተከበረም›› በማለቱ መገንጠልን ነፃ እንደ መውጣት ቆጥሮት ነበር፡፡ ነገር ግን ባለፉት 27 ዓመታት ገደማ ካገኘው ይልቅ ያጣው ነገር እየበዛ፣ በመከራና በስደት እየማሰነ በችግር ውስጥ ይገኛል፡፡  

አሁን የኤርትራ ወጣቶች ከሻዕቢያ የግፍ መንጋጋ አርነት የሚያወጣቸውን የሚመኙ ሆነዋል። ሕዝቡም ራሱን ከተጫነበት የአፈና ቀንበር በራሱ መንገድ ለማላቀቅ ከመባዘን አልወጣም። ኤርትራዊ ሁሉ በገዛ አገሩ የተሰቃየው፣ ‹‹ታግዬልሃለሁ›› በሚለውና በቀደሙት የትግል ዓመታት ምናልባትም እንደ ሌሎቹ ተስፋ ሰጪ የአፍሪካ አገሮች ሕዝቦች ሰላምን ያመጣልኝ ይሆናል ብሎ ባመነው ኃይል ነው፡፡ ሕዝቡ ተስፋ አድርጎበት የነበረውን እያገኘ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተገለለውና ከጎረቤት አገሮችም ጋር ሲባላ ከሚውል ከሚያድረው የሻዕቢያ ሥርዓት ጋር ከመኖር ‹‹ነፃነቱ›› በቀረብኝ እስከ ማለት መድረሱን የውጭ ሚዲያዎች ጽፈውት ተነቧል፡፡  

አሁንም ቢሆን የኤርትራ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ በአገሪቱ ራሱን ‹‹ሕግደፍ›› (ሕዝባዊ ግንባር ለፍትሕና ዴሞክራሲ) በሚል ውስጠ ወይራ ስያሜ በሚጠራው ሻዕቢያ ፍዳውን በማየት ላይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የኤርትራ ሕዝብ ከሕዝባዊነትም፣ ከፍትሑም ይሁን ከዴሞክራሲው ጋር ሆድና ጀርባ የሆነውን የሻዕቢያ የግፍ አስተዳደር በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገሮች የሚሰደደው አምራች ኃይልም በሺዎች የሚቆጠር ነው።

የኤርትራ ወጣት ከግዳጅ የወታደርነት ዘመቻ፣ ከሥራ አጥነትና ድህነት ለመላቀቅ ለጠረፍ ጠባቂዎች እስከ 100 ሺሕ ናቅፋ በመክፈል አገር ጥሎ ይሰደዳል፡፡ የባህርና የበረሃ ሲሳይ ይሆናል። አገሪቱም የአረጋዊያንና የአቅመ ደካሞች መኖሪያ  ከመሆን አልዳነችም፡፡ የመነጠል አሳዛኝ ውርደት ይሉዋል ይኼ ነው፡፡

ሻዕቢያ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኤርትራን የሰብዓዊ መብት አያያዝ አስመልክቶ በተለያዩ ወቅቶች ‹‹የሕዝብህን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚዘገንን ሁኔታ ትጥሳለህ፣ ተቃዋሚ ዜጎችህን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በየጎጡ በሠራሃቸው ኮንቴይነሮች ውስጥ አፍነህ ትገድላለህ፣ በግርፋት ታሰቃያለህ፣ አካል ታጎድላለህ፣ ዓይን ታጠፋለህ፣ . . . ወዘተ›› የሚለው ጉደኛ ሥርዓት ሆኖ አርፏል፡፡ ዓለም በማዕቀብ የሚያሽመደምደው የደካሞች ሁሉ ደካማ የአገር መሪ ሻዕቢያ ነው፡፡ እርሱ ግን ዓይኑን በጨው አጥቦ ሊከራከር መሞከሩ አይቀርም፡፡ እውነታው ሕዝቡ ያለበት የስቃይ ኑሮ ቢሆንም፡፡

ፀረ ዴሞክራሲ፣ ጥገኝነትና ዘረፋ ብቻ ሳይሆን ጦረኝነትም የሻዕቢያ እውነተኛ መገለጫ ነው። ሻዕቢያ ከሳህል በረሃ ወጥቶ ኤርትራን ሲያስተዳድር በጦረኛ ጥርሱ ያልነከሰው የጎረቤት አገር የለም። ምናልባት አሁን አሁን ተሻሽሎ ከሆነ የሚታይ ቢሆንም፣  በቅድሚያ ‹‹ሃኒሽ ደሴት የእኔ ነው›› ብሎ የመንን ወረረ፣ ወረራው በፍርድ ቤት ሲቀለበስበትም የወራሪ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ።

ይህም ቢሆን አልቀናውም፡፡ በአገራችን ሕዝቦችና በመከላከያ ሠራዊቱ ጥምረት ወደ አስመራ ቢገፋም፣ ከዚያም በሱዳን መንግሥት ላይ ‹‹የቤጃ እንቅስቃሴ›› የሚል አንጃዎችን በመፍጠር በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ይፈተፍት ገባ። ይህ አልበቃ ብሎትም ‹‹ራስ ዱሜራ›› የሚባለውን የጂቡቲን ግዛት ‹‹አሸዋ ልወስድ ነው›› በሚል ዘልቆ በመግባት ደፈረ። ‹‹ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል አሉ››፡፡

በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ በመግባትም ለአሸባሪው አልሸባብ የገንዘብና  የሎጂስቲክስ ድጋፍ ሲያደርግ እንደ ነበር በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጭምር ተረጋግጧል። በአንድ ወቅትም የሻዕቢያ ረዣዥም የሁከት እጆች በአዲሲቷ  ደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ገብተው እንደ ነበር የሚታወቅ ነው። ይህም ሻዕቢያ የአገሩን ሕዝብ በመቀጥቀጥ ብቻ ሳይሆን በጦርነት ዓውድ እንጂ፣ በሰላም ውስጥ መኖር የማይችል የጦር አምላኪዎች ስብስብ መሆኑን የሚያረጋግጥ እንደሆነ የምዕራባዊያኑ ስመ ጥር መገናኛ ብዙኃን አስቀምጠውታል። አሁንም ሥርዓቱ ከመካካለኛው ምሥራቅ ፍጥጫዎች ጀርባ በወደብ ኪራይና ለአገሮች የጦር ሠፈር መስጠት ስም የሚሠራውን ደባ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይበቀል›› ከሚለው ተረት ጋር አዛምደው የሚያዩት ትንሽ አይደሉም፡፡  

ሻዕቢያ ለኤርትራ ሕዝብ ያተረፈለት ምርጫ፣ ነፃ ሚዲያ፣ ይነስም ይብዛም ተቃዋሚ እንኳን የሚላወስበት አገርን ሳይሆን፣ ለ27 ዓመትም ሕገ መንግሥት አልባ የሆነች ትንሽ ደሃ ምድርን ነው፡፡ ከዓለም ደሃና ፀረ ዴሞክራሲ ሥርዓት ያደከማቸው አገሮች ተርታ ቀዳሚዋ ኤርትራ መሆኗ አባባሉን ከማሳየት አልፎ፣ መገንጠልም ይባል ነፃነት እውነተኛ ሕዝባዊ ሥርዓትን ካላገኘ የሚያፋጥነው አገራዊ ሞትን ብቻ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡

በአጠቃላይ ጎረቤት የሆኑትን ሁለት የመከኑ አገሮች ለአብነት በማንሳት ሕዝብን ባልተገባ መንገድ አነሳሳቶ የግል ፀረ ዴሞክራሲያዊ ፍላጎትንና ጥገኛ ምኞትን ለማሳካት መባዘን አገር ሊያቆም እንደማይችል ዓይተናል፡፡ መገንጠል በራሱም ደካማና ትንሽ አገር ለመፍጠር ያስችል እንደሆነ እንጂ  ለሰላም፣ ለዕድገትና ለዴሞክራሲ ዋስትና እንደማይሆን ጠቋቁመናል፡፡ ሁሉም ያለውን ፀጋ አዋጥቶና አቻችሎ ለአንድ ገራዊ ዓላማ እንዳይውል የሚያደናቅፍ ውትፍትፍ አካሄድ እንደሆነም ያመላክታል፡፡

በተለይ ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ የተዋሀደና የተዋለደ፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የኖረ ሕዝብን በቅኝ ገዥዎች ትልምና በጥላቻ ፖለቲካ ቀመር፣ እንዲሁም በተፈበረከ ታሪክ  ብቻ መነጣጣል ያለ ጥርጥር ውጤቱ ውድቀትና የዜሮ ድምር ፖለቲካ መሆኑን ለመገንዘብም አያዳግትም፡፡ የጠቀስናቸው የደቡብ ሱዳንና የኤርትራ አገርነትና የለውጥ ጉዞ መጀመር የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ወደፊት በታሪክ መነጽር የምንመለከተው ቢሆንም፣ መገንጠል ከቀበራቸው ግንጥል ምድሮች የምንማረው እውነት ግን ብዙ እንደሆነ ያሳዩናል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበለው!!፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...