Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ገበያ ከፍተኛ የሰሊጥና የቡና ግብይት ማከናወኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2010 ግማሽ በጀት ዓመት 317,607 ቶን የግብርና ምርቶች ያገበያየ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 133,818 ቶን ቡና በማገበያየት ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ በማስመዝገብ ቀዳሚውን ድርሻ መውሰዱ ተገለጸ፡፡ 

ምርት ገበያው የግማሽ ዓመቱን አፈጻጸሙን በማስመልከት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በስድስት ወራት ውስጥ የተገበያየው ምርት የ14.47 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ነው፡፡ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ የተገበያየው የምርት መጠን በዕቅድ ከተያዘው የ23 በመቶ፣ በግብይት ዋጋም የ42 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ29 በመቶ በዋጋ ደግሞ የ49 መቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

በምርት ገበያው አዲሱ የቡና ግብይት ሥርዓት ተግባራዊ የተደረገው በተገባደደው ግማሽ ዓመት ውስጥ ሲሆን፣ በቡና ግብይት ማሻሻያው መሠረት ‹‹e-Auction›› ተብሎ የተሰየመውን አዲስ በኤሌክትሮኒክስ የሚካሄድ የጨረታ ግብይት ዘዴ አዘጋጅቶ አባላቱንና ተገበያዮችን በማሠልጠን ሥራ ላይ ማዋሉ ታውቋል፡፡ ይህም ግብይት የሚፈጸምበት ምርት መገኛ ቦታና ባለቤትነትን መሠረት ካደረገው አዲሱ የግብይት ሥርዓት ጋር ተጣጥሞ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ምርት ገበያው ገልጾ፣ ከዚህ በተጨማሪም በማሻሻያው መሠረት አባል ያልሆኑ ተገበያዮችም እንዲካተቱ በመፈቀዱ ምክንያት 63 ተገበያዮች አስፈላጊውን መሥፈርት አሟልተው ወደ ገበያው ሥርዓት ተቀላቅለዋል፡፡

በመንፈቅ ዓመቱ ውስጥ 133,818 ቶን ቡና በዘጠኝ ቢሊዮን ብር እንዳገበያየ የሚያመለክተው መረጃ፣ የቡና ምርት ከአጠቃላይ ግብይቱ ውስጥ በመጠን የ42 በመቶ፣ በዋጋም የ62 በመቶ  ድርሻ  ሲኖረው፣  የግብይት መጠኑ  ከዕቅዱ  17 በመቶ፣  ካለፈው  ዓመት  ተመሳሳይ  ወቅት  አኳያ  ሲነፃፀርም  በ22 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ጠቅሷል፡፡ የግብይት ዋጋውም ከቀዳሚ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ በ24 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ በመጠን ረገድ በ28 በመቶ ጨምሯል፡፡ በምርት ገበያ ከተገበያየው ቡና ውስጥ 82 በመቶ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከሰሊጥ ግብይት ጋር በተያያዘ የቀረበው የስድስት ወራት አፈጻጸምም እንዲሁ፣ የ5.2 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው 166,691 ቶን ምርት ግብይት እንደተፈጸመ አመላክቷል፡፡ የሰሊጥ ግብይት በመጠን ቀዳሚ ድርሻ ሲይዝ፣ በዋጋ በኩል ግን ከቡና ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ይገበያያል ተብሎ ከታቀደው 37 በመቶ ብልጫ ያለው አፈጻጸም ሲመዘገብ፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀርም፣ በ42 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ የግብይቱ ዋጋም ከዕቅዱ 107 በመቶ፣ ካለፈው ዓመት ክንውን አንፃር በ114 በመቶ ዕድገት በማሳየት ሰሊጥ በከፍተኛ ሁኔታ የግብይት ዕድገት የታየበት ሆኗል፡፡ ነጭ  የሁመራ/ጎንደር  ሰሊጥ  በመጠንና  በዋጋ  78 በመቶና 80 በመቶ በቅደም  ተከተል  ድርሻ ይዟል፡፡

የቡና ግብይት መጠን በዚህ መንፈቅ ከፍ ያለው ባለፈው ዓመት የተመረተው ምርት ከፍተኛ በመሆኑና በወቅቱ ከነበረው ክምችት ወደዚህ በጀት ዓመት የተሸጋገረ ቡና መጠን በመጨመሩ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በሰሊጥ ግብይት በኩልም ምርቱ ዘንድሮ የተሻለ በመሆኑና ዋጋው የጨመረውም በዓለም  የምርቱ ዋና ዋና ገዥዎች እጅ ውስጥ የሚገኘው ምርት መጠን ክምችት በመቀነሱ፣ የሰሊጥ ዋጋ እንዲያንሰራራ ምክንያት ስለመሆኑ ይገመታል፡፡

ከቡናና ሰሊጥ በተጨማሪ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የቦለቄ፣ የአደንጓሬና የማሾ ምርቶች ግብይት ተፈጽሟል፡፡ በዚህም መሠረት 16,734 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ266 ሚሊዮን ብር ተገበያይቷል፡፡ ከአጠቃላዩ ግብይት ውስጥ ነጭ ቦሎቄ በመጠን የአምስት በመቶ፣ በግብይት ዋጋው ደግሞ የሁለት በመቶ ድርሻ አለው፡፡ እንዲሁም የ227 ቶን አረንጓዴ ማሽላና የ87 ቶን ቀይ ቦለቄ ግብይት ተከናውኗል፡፡

እንደ ምርት ገበያው መረጃ፣ ቀይ  ቦለቄና  አረንጓዴ  ማሽላ  በኢትዮጵያ  ምርት ገበያ በኩል ግብይታቸው ተፈጽሞ ወደ ውጭ መላክ እንዳለባቸው በሕግ ቢደነገግም፤ ከምርት ገበያው የግብይት መድረክ ውጭ ምርቱን በመግዛት ቀጥታ ወደ ውጭ የሚልኩ ድርጅቶች በመኖራቸው፣ የምርቶቹ ግብይት በማዕከላዊ ገበያው በኩል ይካሄድ የሚችለው አስገዳጅ ሕግ እንዲከበር ንግድ ሚኒስቴር ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች በቅርቡ መመርያ አስተላልፏል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያም ከዚህ መመርያ ጋር በተቀናጀ መልኩ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአማራ፣  በኦሮሚያ፣  በደቡብ  ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች  ክልሎች  ከሚመለከታቸው ጋር ሲመከርበት እንደሰነበተ አስታውቋል፡፡

ምርት ገበያው ባሉበት 21 ቅርንጫፎች በግማሽ ዓመቱ ከዕቅዱ አምስት በመቶ በላይ ብልጫ ያለውንና 338,563 ቶን ምርት ከአቅራቢዎች የተረከበ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ክንውን ጋር ሲነፃፀር በ34 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጿል፡፡ በዚህ ጭማሪ መሠረት ባለፈው ዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና በመመረቱ፣ በኮንትሮባንድ ላይ ተከታታይ ዕርምጃዎች በመወሰዳቸውና የዘንድሮ የሰሊጥ ምርት የተሻለ መሆኑ  ለተገበያየው ምርት ከፍተኛነት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ እንዲሁም በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት ውስጥ ከ21ዱ ቅርንጫፎች ለግብይት የቀረቡት ምርቶች ካለፈው  ዓመት አኳያ በ26 በመቶ ጨምረው የ33,256 ምርቶች ናሙና ተወስዶ በላቦራቶሪ የምርት ጥራት ፍተሻ ስለመደረጉም ምርት ገበያው አውስቷል፡፡

የግብይት መድረኩን ፍትሐዊ፣ ጤናማና ስኬታማ እንዲሆን በሚደረገው የገበያ ደኅንነት ክትትል ሥርዓት መሠረት፣ በስድስት ወራት ውስጥ 79 የሕግ ጥሰቶች በተገበያዮች መፈጸማቸው ታውቋል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ የቀነሰ ሲሆን፣ ተከታታይ ሥልጠና ለአባላቱና ለተገበያዮች በመሰጠቱ፣ እነሱም የግብይት ሥርዓቱን አካሄድ ይበልጥ እያወቁ በመምጣታቸውና አፋጣኝ የማስተካከያ ዕርምጃ በመወሰዱ ጥፋቶቹ እየቀነሱ ለመምጣታቸው የተሰጠ ማብራሪያ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ የግብይት መድረክነቱ አንዱ መገለጫ፣ የገበያ መረጃን በሰከንዶች ውስጥ ለአርሶ አደሩ፣ ለተገበያዮችና ለባለድርሻ አካላት ማሠራጨት መቻሉ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በአጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ በስልክ፣ በድምፅ ጥሪ ምላሽ በመስጠት በአራት ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠቱ፣ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃንና በድረ ገጽ የታገዘ የገበያ መረጃ ማቅረቡም ይጠቀሳል፡፡ በግማሽ ዓመቱ ከቡናና ከሰሊጥ የተገኘው የግብይት አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገበያ ላይ አወንታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ከወዲሁ ተገምቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች