Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምርጫ በነቀምት

ምርጫ በነቀምት

ቀን:

ቅዳሜ ግንቦት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ነቀምት ከወትሮ በተለየ በእጅጉ ሞቃለች፡፡ በዕለቱ የነበረው የጋለው የአየር ንብረት ብዙም ያልተለመደ ነበር፡፡ አመሻሹ ላይ ግን ቀዝቃዛና ነፋሻማ አየሯ ተመልሷል፡፡ ከአዲስ አበባ 328 ኪሎ ሜትር የምትርቀው የምሥራቅ ወለጋ ዞን ርዕሰ ከተማ ነቀምት በማግሥቱ የሚካሄደውን ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት የተጠናቀቀባት ቢሆንም፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ምልክትና የዕጩዎችን ምሥል የያዙ ፖስተሮች በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ አይታዩም፡፡

በተለይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖስተሮችን ፈልጎ ለማግኘት አይቻልም፡፡ በነቀምት ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ሪፖርተር ተዘዋውሮ መመልከት እንደቻለው፣ የተፎካካሪ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶችና የዕጩዎችን ምሥል የያዙ ፖስተሮች በነቀምት አይታዩም፡፡ የኦሕዴድ ዕጩዎችን የያዙ አነስተኛ ባነሮች ግን በተወሰኑ አካባቢዎች አሉ፡፡ የኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ዕጩዎችን የሚያሳዩት የማስታወቂያ ሰሌዳዎችም ቢሆኑ ትልቅ የሚባሉ  አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ ኦሕደድ/ኢሕአዴግ የተወዳዳሪዎቹን ምሥልና የመወዳደሪያ ምልክቶችን የያዙት ፖስተሮች መኖር ቢያንስ በነቀምት ከተማ አንድ ተወዳዳሪ ፓርቲ እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ ከምሥራቅ ወለጋ ነቀምት የምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ የሚያሳየው ግን፣ በምርጫ ክልሉ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወዳደሩ መሆኑን ነው፡፡

በምርጫ ዋዜማው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የከተማ ነዋሪዎች እንዳመለከቱት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ምልክትና ፖስተር አላዩም፡፡ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምት ምርጫ ክልል ኢዴፓን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩትና የአካባቢው የኢዴፓ ወኪል አቶ ኃይለ የሱስ ፊጤ እንደሚሉት፣ ምርጫው ከመድረሱ በፊት የፓርቲያቸውን መወዳደሪያ ምልክት (አበባ) ያለበትን ፖስተርና የተወዳዳሪዎችን ስም የያዙ በራሪ ወረቀቶች ተሠራጭተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች በምርጫ ክልሉ ከሚወዳደሩ ፓርቲዎች መካከል የመድረክ፣ የኢዴፓና የመኦሕዴፓ ፖስተሮችን አለማየታቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ኃይለ የሱስ ግን፣ ‹‹በተቻለ መጠን ፓርቲያችንን ለማስተዋወቅ ፖስተርና በራሪ ወረቀቶች በትነናል፤›› ይላሉ፡፡ መድረክ ግን ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተሻለ ሕዝብ ማወያየቱን አስረድተዋል፡፡

በምርጫ ዋዜማው ቀኑን በሙቀት የዘለቀችው ነቀምት እኩለ ሌሊት (ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ) ጀምሮ ዝናብ ይወርድባት ጀመር፡፡ ዝናቡ የማያቋርጥ ነበርና እስከ ምርጫው ቀን ረፋድ ድረስ ዘለቀ፡፡ ዝናቡ ምርጫ የሚጀመርበትን ጊዜ ያዘገያል፣ መራጮችም ዝናቡ እስኪያባራ ሊጠብቁ ይችላሉ የሚል ሥጋት አሳድሮ ነበር፡፡ የተፈራው ሥጋት ግን ሳይሆን ቀረ፡፡ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች በርካታ መራጮች ከ12 ሰዓት በፊት ደርሰዋል፡፡ ብዙዎቹ መራጮችም በማለዳ መምረጥን የሻቱ መሆናቸውን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 03/01/ሐ የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ደምሰው ሻረው እንደገለጹት፣ እርሳቸው በሚያስተባብሩት የምርጫ ጣቢያ መራጩ ከዘጠኝ ሰዓት ተኩል ጀምሮ የመጣ ቢሆንም፣ ዝናቡን እንዲጠለል ተደርጎ በሰዓቱ ምርጫው እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ በማለዳ በተጀመረው ምርጫ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ከ95 በመቶ በላይ መራጮች ድምፅ የሰጡት ከአሥር ሰዓት በፊት ነው፡፡ አሥር ሰዓት ላይ ሦስት መራጮችን ብቻ ይጠብቁ የነበሩት የ04/01/ሐ ምርጫ አስፈጻሚ አቶ ተመስገን ቱፋ፣ ‹‹ሕዝቡ በጊዜ መርጦ መሄድን መርጧል፤›› ብለዋል፡፡

እርሳቸው በሚያስተባብሩት ጣቢያ 1,119 መራጮች የተመዘገቡ ሲሆን፣ እስከ አሥር ሰዓት 1,116 ድምፃቸውን ሰጥተዋል ብለዋል፡፡ በዚያ ጣቢያ የመድረክ ታዛቢ አቶ ክብረአብ አብረሃ በበኩላቸው፣ ከማለዳ ጀምሮ የተመለከቱት ሒደት ጥሩ እንደነበርና ምርጫውም በጊዜ ማለቁን ተናግረዋል፡፡

በከተማው መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ በሚገኘው የምርጫ ጣቢያ አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ ከ16 በላይ መራጮች ዣንጥላ ይዘው ተራ እየጠበቁ ነበር፡፡ ከምርጫ ጣቢያው አስፈጻሚዎች ድምፅ ከሰጡ በኋላ የመጀመሪያው መራጭ የሆኑት አቶ ታደሰ ገብሬ ናቸው፡፡ 12 ሰዓት ከአሥር ደቂቃ ላይ ድምፃቸውን ሰጥተው ወጥተዋል፡፡ ‹‹በጊዜ ድምፅ መስጠት ጥሩ ነው፤›› ያሉት የ60 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ገብሬ፣ አምስቱንም ምርጫዎች ለመምረጥ የቻሉ ሲሆን በ1997 ዓ.ም. ደግሞ ምርጫ አስፈጻሚ ነበሩ፡፡ የዘንድሮው ቅድመ ምርጫ ሒደት የተረጋጋ እንደነበርና ጥሩ ምርጫ ይሆናል ብለው እንደሚገምቱም ገልጸዋል፡፡

ከምሥራቅ ወለጋ ነቀምት ምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዘጠና ዘጠኙ የምርጫ ክልሎች 75,074 ተመራጮች ተመዝግበዋል፡፡ ከጠቅላላ መራጮች ውስጥ 38,670 ወንዶች፤ 36,404 ሴቶች ናቸው፡፡ 495 ታዛቢዎች በምርጫ ክልሉ እንዲታዘቡ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል፡፡ 495 የምርጫ አስፈጻሚዎች መሰማራታቸውንም መረጃው ይገልጻል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ በነቀምት ከተማ ውስጥ 36 ታዛቢዎችን ማሰማራት የሚችልበት ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ ለሦስት ተዘዋዋሪ ታዛቢዎችም ፈቃድ አግኝቷል፡፡

ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ደግሞ በሁሉም ጣቢያዎች ታዛቢዎች አስቀምጧል፡፡ በምርጫ ክልሉ ከሚወዳደሩት አራት ፓርቲዎች ውስጥ መኦሕዴፓና ኢዴፓ በዘጠና ዘጠኙም የምርጫ ጣቢያዎች አንድም ታዛቢ አላስቀመጡም፡፡ ፈቃድም አልወሰዱም፡፡ በምርጫ ክልሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ ሦስት ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

በምርጫ ክልሉ የሚፎካከሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ፣ መድረክ፣ ኢዴፓና መኦሕዴፓ (የመላው ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ) ናቸው፡፡ አራቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ለክልል ምክር ቤት ኦሕዴድ፣ መድረክና ኢዴፓ ሦስት ሦስት ዕጩዎችን አቅርበዋል፡፡ የመኦሕዴፓ ግን ለክልል ምክር ቤት ተወዳዳሪ ያላቀረበ መሆኑን የነቀምት የምርጫ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ኤቢሴ ጉያሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አድርጎ ያቀረባቸው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነን ነው፡፡ ከፕሮፌሰር ፈቃዱ ጋር በነቀምት ዙሪያ ተፎካካሪ የሆኑት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩዎች ደግሞ የኢዴፓው አቶ ኃይለየሱስ ፊጤ፣ የመድረኩ አቶ ታሪኩ ደሳለኝና የመኦሕዴፓው አቶ ሰኚ ታደሰ ናቸው፡፡

ሪፖርተር ተዘዋውሮ በተመለከታቸው የነቀምት ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ መድረክና ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ብቻ ታዛቢዎቻቸውን አስቀምጠዋል፡፡ በአራት የምርጫ ጣቢያዎች ሪፖርተር ያገኛቸው የመድረክ ተወካዮች የምርጫ ሒደቱ መልካም እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ኢሕአዴግ በዕጩነት ያቀረባቸው ፕሮፌሰር ፈቃዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የምርጫው ሒደት ጥሩ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ከሌሊት ጀምሮ ሲዘንብ የነበረው ዝናብ ሳያግደው ሕዝቡ ለምርጫ መውጣቱ የሚደነቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በምርጫ ክልሉ ኢዴፓን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር በዕጩነት የቀረቡት አቶ ኃይለየሱስ በበኩላቸው፣ ፓርቲያቸው በምርጫ ክልሉ ሲፎካከር ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በአቅማቸው የፓርቲያቸውን ዓላማ የሚያስረዱ ብሮሸሮች መበተናቸውንና በከተማ ውስጥ ለሁለት ቀን በተሽከርካሪ ዞረው ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በቅድመ ምርጫው ሒደት ምንም ችግር አላጋጠመም ብለዋል፡፡

ለሁለቱም ምክር ቤቶች ዕጩ ማቅረብ መቻላቸውን የገለጹት አቶ ኃይለየሱስ፣ በ77 ጣቢያዎች ታዛቢ ለማስቀመጥ እንዳልቻሉ፣ ይህ የሆነው ደግሞ ፓርቲውን ወክለው በታዛቢነት ለሚቀመጡ ወኪሎቻቸው አበል የሚሆን በጀት ባለመኖሩ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የምርጫውን ሒደት በተመለከተ በሰጡት አስተያየትም በምርጫ ክልሉ ምንም ችግር ያለመመልከታቸውንና በዚህ ምርጫ የሚገኘው ውጤት ምንም ይሁን ምን እንደሚቀበሉ ገልጸዋል፡፡

የመድረኩ አቶ ታሪኩ ግን በምርጫ ሒደቱ ላይ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች በኦሕዴድ/ኢሕአዴግ ያልተገባ ሥራ መሥራቱን ጠቁመዋል፡፡ በአንዳንድ ጣቢያዎች በመሄድም ይህንን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን በተለይ በኩምሳ ሞረዳ የምርጫ ጣቢያ የኢሕአዴግ ታዛቢዎችና የምርጫ አስተባባሪዎች ሁለት አባሎቻቸው ያለፈቃድ እስከ ድምፅ መስጫ ቦታ ድረስ ሄደዋል በሚል ለምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤት አቤት ብለዋል፡፡

ያለ ፈቃድ መግባት አልነበረባቸውም የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ ለምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ድርጊቱ ተፈጸመ ወደተባለበት ቦታ ቢሄዱም እነ አቶ ታሪኩ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ማድረግ አግባብ አለመሆኑን በስልክ እንደተገለጸላቸው፣ የምሥራቅ ወለጋ ነቀምት የምርጫ ክልል ኃላፊ አቶ አበራ ኢሬሳ ገልጸዋል፡፡

አቶ ታሪኩ ግን በምርጫ ጣቢያዎቹ የተገኙት እየተሠራ ነው የተባለውን ፍትሐዊ ያልሆነ ሥራ ለመመልከት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በአንዳንድ ቦታዎችም ችግሮች አጋጥመውናል፤›› ብለዋል፡፡ ለዚህም መረጃ አለኝ የሚሉት አቶ ታሪኩ መረጃቸው የተፈጠረውን ችግር በሚመለከት ዝርዝር መረጃ እንዲሰጡ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ግን አሁን ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጥም ብለዋል፡፡

ችግሩን በጽሑፍ ለምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤት አቅርበዋል ወይ? የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው አለማቅረባቸውን ነገር ግን በስልክና በአካል መናገራቸውን አስታውቀዋል፡፡ ጥያቄውንም ቢያቀርቡ በቂ መልስ ይገኛል ብለው እንደሚያምኑም ጠቁመዋል፡፡ አቶ አበራ ግን ምርጫው እስከተጠናቀቀ ድረስ በየትኛውም ጣቢያ ምንም ዓይነት ችግር ያለማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡ ከመድረክ ተወካይ እየቀረበ ያለው ክስ መሠረት የሌለውና ለጽሕፈት ቤታቸውም በጽሑፍ ያልቀረበ እነደሆነም አስረድተዋል፡፡ ሌላው መድረክ ለክልል ምክር ቤት ዕጩ ያደረጋቸው ተወዳዳሪ አቶ ፍቅሩ አምሳሉ ደግሞ ከአቶ ታሪኩ የተለየ ሐሳብ አላቸው፡፡ ለአንድ ፓርቲ የሚወዳደሩ ቢሆንም፣ ምርጫው ላይ አለ የሚሉት ችግር ያለመኖሩና በጥሩ እየሄደ መሆኑን በስልክ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በነቀምት ከተማ ውስጥ ከነበሩ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በነቀምት አንዱ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጣቢያ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከ10,500 በላይ ተማሪዎች አሉት፡፡ በመራጭነት የተመዘገቡት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች 6,824 ናቸው፡፡ በጠቅላላ በመራጭነት ከተመዘገቡት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች 5,052 ወንዶች፣ 1,772 ሴቶች መሆናቸውን የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ ወጣት አስማረ አንዳርጌ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርጫ ጣቢያ ሰባት ታዛቢዎች አሉ፡፡ ሰባቱም ታዛቢዎች ከተማሪዎች የተወከሉ ሲሆን፣ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ በዩኒቨርሲቲው የምርጫ ጣቢያ ወኪል ታዛቢውን አላስቀመጠም፡፡ በዩኒቨርሲቲው ለመምረጥ ከተመዘገቡት ተማሪዎች ውስጥ እስከ አሥር ሰዓት ድረስ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት መምረጣቸውን ለማየት ተችሏል፡፡ ሆኖም የተወሰኑ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በመጉደላቸው ድምፅ ለመስጠት ያልቻሉ ተማሪዎች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንንም የምርጫ ጽሕፈት ቤቱ አረጋግጧል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...