የምዕራብ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እምብርት በሆነችው ጅማ፣ በተካሄደው ምርጫ የኦሮሚያ ክልል ገዢ ፓርቲ ኦሕዴድ ከመድረክ፣ ከሰማያዊና ኢዴፓን ጨምሮ ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተወዳድሯል፡፡
ሪፖርተር በምርጫው ዋዜማ፣ በምርጫው ቀንና በምርጫው ማግሥት በተለይ በጅማ ከተማና በአጋሮ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ተወካዮችን ከማነጋገሩም በላይ በምርጫ ጣቢያዎች ቅኝት አድርጓል፡፡
በምርጫው ዋዜማ የጅማ ከተማ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤትና የዞኑ ምርጫ ጣቢያ ማስተባበሪያ ሲያካሂድ የቆየውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቆ ነበር፡፡ ኦሕዴድ የምርጫ ካርድ የወሰዱ መራጮች በምርጫው ቀን ጠዋት ወጥተው ድምፅ እንዲሰጡ ያሉትን አደራጃጀቶች በመጠቀም ሲያሳስብ ተስተውሏል፡፡
ነገር ግን በምርጫው ዕለት ከሌሊት ጀምሮ በጅማ ከተማና በአብዛኛው ጅማ ዞን ክልል ውስጥ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ የመምረጫ ሰዓታትን መሸራረፉ አልቀረም፡፡ ይህም ቢሆን ግን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል መራጮች በዝናብ ውስጥ ሲመርጡ ተስተውሏል፡፡
ረፋዱ ላይ ዝናቡ ካባራ በኋላ በርካታ መራጮች በረዣዥም ሠልፎችና በድንኳን ውስጥ በመቀመጥ ተራቸውን ጠብቀው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ የጅማ ዞን ጅማ ከተማን ሳይጨምር 1.9 ሚሊዮን ሔክታር ስፋት አለው፡፡ በዞኑ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚኖር የዞኑ አስተዳደር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዞኑ ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ 1.3 ሚሊዮን የሚሆነው በምርጫው ድምፅ ለመስጠት ተመዝግቧል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጅማ ከተማ ምርጫ ጣቢያ ኃላፊና የጅማ ዞን ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ አወጣኸኝ ኪዳነ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጅማ ከተማን ጨምሮ በአጠቃላይ በጅማ ዞን 18 ምርጫ ክልሎች አሉ፡፡ በእነዚህ 18 የምርጫ ክልሎች 1,551 ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡
በጅማ ዞን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎችን አቅርበዋል፡፡ ኦሕዴድ፣ መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓና አንድነት በምርጫው ተሳታፊ ነበሩ፡፡
ኦሕዴድ በሁሉም መወዳደርያ ጣቢያዎች ዕጩ ሲያቀርብ መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓና አንድነት በተነፃፃሪ ቁጥሩ የቀነሰ ዕጩ አቅርበው ተወዳድረዋል፡፡ ኦሕዴድ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካባ ኡርጌሳ የጅማ ከተማ የፓርላማ ተመራጭ አድርጎ ሲያቀርብ፣ 17 ነባር የፓርላማ ተመራጮችን በሌሎቹ የምርጫ ክልሎች እንዲወዳደሩ አድርጓል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድርን ጨምሮ 54 አባላቶቹን ደግሞ ለክልሉ ምክር ቤት ዕጩ አድርጎ አቅርቧል፡፡
በሁለቱ የጅማ ዞን ትላልቅ ከተሞች የኦሕዴድ ፖስተሮችን በስፋት መመልከት ቢቻልም፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ፖስተር ግን ማየት አዳጋች ነበር፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖስተሮች ሊኖሩ ያልቻሉበትን ምክንያት በሪፖርተር የተጠየቁት የአጋሮ ከተማ ከንቲባ አቶ ሞጋ አባቡልጋ፣ በአብዛኛው በግለሰቦች በተያዙ አካባቢዎች የሚለጠፉ በመሆናቸው ግለሰቦች ሲፈቅዱ ፖስተሮች ይለጠፋሉ ብለዋል፡፡ ኦሕዴድም አስፈቅዶ መለጠፉን ተናግረዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ በግለሰቦች ስላልተፈቀደላቸው መለጠፍ ባለመቻላቸው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በምርጫው ዕለት ልዩ ክስተት ከሆኑት መካከል በጅማ ዞን ሲግሞ ምርጫ ክልል ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ ድምፅ ተሰጥቶ መጠናቀቁ ነው፡፡ የጅማ ዞን የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ታምራት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሲግሞ ምርጫ ክልል 49 ሺሕ ነዋሪዎች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል፡፡ የአካባቢው አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች የእስልምና እምነት ተከታዮች በመሆናቸው፣ ከሌሊቱ 11 ሰዓት የሱቢህ ስግደት ከሰገዱ በኋላ ወደ ምርጫ ጣቢያ መሰማራታቸውን አስረድተዋል፡፡
‹‹በዚህ ምክንያት መራጮች ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ድምፅ ሰጥተው አጠናቀዋል፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የምርጫ ካርድ በሚሰጥበት ወቅት እነዚህ የሲግሞ ነዋሪዎች በሁለት ቀን ውስጥ የምርጫ ካርድ ወስደው አጠናቀዋል ብለዋል፡፡
የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት መቀመጫውን ጅማ ከተማ አድርጎ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተቃራኒ በጠንካራ መዋቅሩ አማካይነት የዞኑን የምርጫ ሒደት በቅርበት ተከታትሏል፡፡ ሪፖርተር በኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ተገኝቶ መረዳት እንደቻለው፣ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ኦሕዴድ በእያንዳንዱ ድምፅ መስጫ የሚካሄደውን እንቅስቃሴ ከመከታተሉም ባሻገር፣ ሪፖርት በማዘጋጀት ወደ ማዕከል ኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ይልካል፡፡
ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተደራጀ መረጃ ማግኘት ባይቻልም፣ በአጋሮ ጎማ አንድ ምርጫ ክልል የፓርላማ ተወዳዳሪ የሆኑት አቶ አብዱ አባዎሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የምርጫው ቅስቀሳም ሆነ ሒደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ‹‹ምርጫው ፍትሐዊ መሆኑን እስካየን ድረስ፣ ውጤቱን በፀጋ እንቀበላለን፤›› በማለት አቶ አብዱ ገልጸዋል፡፡
በጅማ ክልል በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች ተሟልተው አለመገኘት ተጠቃሽ ችግር ሆኖ ቀርቧል፡፡ ይኼ የታዛቢዎች አለመገኘት በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች ተስተውሏል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርጫ ቁሳቁስ እጥረት በመከሰቱ የድምፅ መስጠት ሒደቱ ተስተጓጉሏል፡፡ አቶ አወጣኸኝ እንዳሉት ሰኞ ከሰዓት በኋላ የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች በሔሊኮፕተር በመምጣታቸው ድምፅ መስጠቱ በምርጫው ቀን ማግሥት ተካሂዷል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የምርጫ ቁሳቁሶች እጥረት በመከሰቱ መምረጥ ያልቻሉ ተማሪዎች ጥያቄ አንስተው የተወሰነ አለመግባባት ተከስቶ ነበር፡፡
አቶ አወጣኸኝ ‹‹መምረጥ መብት ነው፡፡ ተማሪዎቹ ባልመረጡት አካል ሊተዳደሩ በመሆኑ ጥያቄ ማንሳታቸው አግባብ ነው፡፡ የምርጫው ሒደት በምርጫ ቦርድ የቴክኒክ ችግር መካሄድ ባለመቻሉ ድምፅ ያልሰጡ ተማሪዎች ድምፅ እንዲሰጡ ይደረጋል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡