Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምርጫ በሰሜን ሸዋ ዞን

ምርጫ በሰሜን ሸዋ ዞን

ቀን:

በምርጫ 2007 በሰሜን ሸዋ ዞን ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት ዕጩዎቻቸውን በማቅረብ ዝግጅት ሲያደርጉ ከርመዋል፡፡ አሉ የሚሏቸውን ችግሮች ይዘው ወደ ምርጫ የገቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስሞታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የምርጫ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ ከበደ፣ በዞኑ  በሚገኙት 18 ምርጫ ክልሎች ብአዴን/ኢሕአዴግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 17 ለክልል ምክር ቤት 36 ተወዳዳሪዎችን ማቅረቡን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ሰማያዊ ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስት፣ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ 16 ማቅረቡን፣ መኢአድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰባት ለክልል 14፣ ኢዴፓ ለተወካዮች ምክር ቤት አራት ለክልል ምክር ቤት አላቀረበም፡፡ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት ለክልል ምክር ቤት አንድ ተወዳዳሪ ሲያቀርብ፣ መኢብን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ ለክልል ምክር ቤት ደግሞ ሁለት አቅርቧል፡፡ አዲስ ትውልድ ፓርቲ ለክልል ምክር ቤት አንድ ሲያቀርብ ለክልል ምክር ቤት አላቀረበም፡፡ አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራት፣ ለክልል ምክር ቤት አራት ሲያቀርብ፣ የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አብዴን) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ ለክልል ምክር ቤት አላቀረበም፡፡ የአርጎባ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አሕዴድ) በተመሳሳይ ለተወካዮች ምክር ቤት አንድ ተወዳዳሪ ሲያቀርብ ለክልል ምክር ቤት አለማቅረቡን አቶ ተሰማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ በዞኑ ባሉት የምርጫ ክልሎች ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች  ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫውን ሒደት ለሚከታተሉ ተቀማጭና ተንቀሳቃሾች ወኪሎች፣ በጊዜውና በሰዓቱ መታወቂያ ተሰጥቷል፡፡ ለአብነትም ሰማያዊ ፓርቲ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙትን 44 ምርጫ ጣቢያዎች ጨምሮ በሁሉም ወረዳዎች ተቀማጭና ተንቀሳቃሽ ወኪሎቹን አቅርቦ ለሁሉም መታወቂያው መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡ በምርጫው ዕለት ግን የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሲከውኑ የተገኙት በደብረ ብርሃን ከተማ በሦስት ቀበሌዎች በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች ብቻ እንደነበረ፣ ቦርዱም ምናልባት ችግሩ ከገዥው ፓርቲ በሚደርስባቸው ጫናና ማስፈራት ሊሆን ይችላል በሚል ለማጣራት ባደረገው ሙከራ፣ አንድም የቀረበለት አቤቱታ እንደሌለ ነው ያስረዱት፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ አስተባባሪ ወ/ሮ ሰርካለም ከበደ በበኩላቸው፣ የዞኑ ምርጫ ቦርድ አስተባባሪ እንዳሉት በዞኑ ደብረ ብርሃን ከተማን ጨምሮ በወረዳዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር በአብዛኛው ለምርጫ ታዛቢ ወኪሎቻቸው መታወቂያ ተሰጥቶ ምደባውም የተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ በምርጫው ዕለት ግን በአብዛኛው በሚያስብል ሁኔታ ወኪሎቻቸው በየምርጫ ጣቢያው ለምን እንዳልተገኙ የደረሳቸው መረጃ እንደሌለ ነው የተናገሩት፡፡ ኃላፊዋ ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጥያቄዎች ይቀርቡላቸው የነበረ መሆኑን ግን አልሸሸጉም፡፡

በወረዳዎች በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በአባሎቻቸውና በደጋፊዎቻቸው ላይ በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች አልፎ አልፎ ድብደባዎች፣ ማስፈራራቶችና ወከባዎች እያደረሱባቸው መሆኑን ሪፖርቶች እንደደረሷቸው፣ በደብረ ብርሃንና በአካባቢው ግን በተለይ ጠዋት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መራጭ በየምርጫ ጣቢያው ተሠልፎ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ሲመርጥ እንደነበረ መመልከታቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በመሀል ሜዳና አካባቢው የሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ አስተባባሪ አቶ ካሳዬ ዳኜ በበኩላቸው፣ ከምርጫ ዋዜማ ጀምሮ በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች እጅግ አሳዛኝ የሆነ እንግልትና ማስፈራራት እንደደረሰባቸው፣ በዚህም የተነሳ በመሀል ሜዳና አካባቢው በነበሩ 93 ምርጫ ጣቢያ የሰማያዊ ፓርቲ ወኪሎች በሙሉ የምርጫውን ሒደት እንዳይከታተሉ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ዛቻና ማስፈራሪያውን ወደ ጎን ብለው የሄዱት ለእስራት እየተዳረጉ ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው መፈታታቸውን ጭምር አስረድተዋል፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች ‹‹በዚህ ምርጫ  አንድ ነገር ቢከሰት የመጀመርያው ዕርምጃ በአንተ ነው የሚጀመረው፤›› ብለው ስላስፈራሯቸው ቤት ውስጥ መቀመጣቸውን በስልክ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የዞኑ የምርጫ ቦርድ ኃላፊው አቶ ተሰማ ከበደ በበኩላቸው፣ ምርጫው በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በሰላም እየተከናወነ መሆኑን፣ ‹‹ችግር ተፈጥሯል›› በሚል ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የቀረበላቸው አቤቱታ እንደሌለ ነው የተናገሩት፡፡

በዞኑ ከሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኢአድ ይጠቀሳል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን የመኢአድ ምርጫ አስተባባሪ ሻምበል ባሻ አበበ በቀለ፣ ከምርጫ ዋዜማ ጀምሮ በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች በደረሰባቸው ወከባና ማስፈራራት እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በምርጫ ካርዳቸው አማካይነት መብታቸውን ከመጠቀም ባለፈ፣ እንደ ፓርቲ የምርጫውን ሒደት ለመከታተልም ሆነ ለመቆጣጠር አለመቻላቸውን ነው ያስረዱት፡፡ በመሆኑም በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ምንም ዓይነት የምርጫ ታዛቢ ወኪሎቻቸውን እንዳልመደቡም ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው ለዚህ ያበቃቸውን ውሳኔ ሲገልጹ፣ በባሶና ወረና በቀይት ምርጫ ጣቢያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መኢአድ ያቀረባቸው ወ/ሮ ደስታ ካሳና በደብረ ብርሃን ከተማ በተመሳሳይ አቶ ጌራ ፍቅረ የተባሉ ተወዳዳሪዎቻቸው ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ በአካልም ሆነ በስልክ ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ፣ ይህንኑም ወደ ማዕከል አስተላልፈው መፍትሔ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በወረዳ ደረጃ ከቀረቡት ተወዳሪዎቻቸው ለምሳሌ በሸዋ ሮቢት፣ በቀወት ወረዳ፣ በአጣየ፣ በጣርማ በር፣ በደብረ ሲናና በሌሎችም አካባቢዎች መኢአድ ያቀረባቸው ተወዳዳሪዎች በገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ደጋፊዎች በደረሰባቸው እንግልት፣ ዛቻና ማስፈራራት ሁሉም ችግሩን በመግለጽ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ እያጋጠመው ያለውን እንግልት፣ ወከባና ማስፈራት ለዞኑ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት በስልክና በተለያዩ አጋጣሚዎች ቢያሳውቅም ምንም ዓይነት መፍትሔ ሊያገኝ ባለመቻሉ፣ ለሁሉም አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው እንደ ፓርቲ ሳይሆን እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ካርዶቻቸውን ብቻ እንዲጠቀሙ ጥሪ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ የዞኑ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ ከመኢአድም ሆነ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ተቃዋሚ በመሆናቸው ምክንያት ከገዥው ፓርቲ ደርሶብናል ሲሉ በአካልም ሆነ በጽሑፍ የቀረበላቸው አንዳችም አቤቱታ እንደሌለ ነው ያስረዱት፡፡

ከዚህ ባለፈ ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ እስከ ምርጫው ፍፃሜ ከገዥው ፓርቲ ብአዴን/ኢሕአዴግ፣ ከሰማያዊና ከመኢአድ በስተቀር ሌሎቹን የፖለቲካ ፓርቲዎች  በቅስቀሳው ወቅት መራጮች እንደማያውቋቸው ነው ለሪፖርተር የገለጹት፡፡ ከእነዚህ አንዳንዶቹ በተለይ በገጠር ቀበሌዎች ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው መራጮች በሚመርጡበት ምርጫ ጣቢያ ከብአዴን/ኢሕአዴግ ውጪ የሌሎች ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተወካዮች እንዳልነበሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...