Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምርጫ በአዲስ አበባ

ምርጫ በአዲስ አበባ

ቀን:

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አምስት የፓርላማ ምርጫዎችን (1948-1965)፣  በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ብሔራዊ ሸንጎን አንድ ምርጫ (1979)፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) አራት የፓርላማ ምርጫዎችን (1987-2002) ያካሄደችው አዲስ አበባ ከተማ፣ አምስተኛውን ምርጫ ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. አድርጋለች፡፡

ባለፈው እሑድ በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ለመሳተፍ አዲስ አበቤዎች ማልደው ነበር ከየምርጫ ጣቢያዎች የተገኙት፡፡ የመዲናይቱ ነዋሪዎች የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ጥሎት በሄደው ጠባሳ ምክንያት እንደሌላው ኢትዮጵያዊ በእኩል ጊዜ ሁለቱንም ማለትም የክልልና የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ባንዴ ለማካሄድ አልታደሉም፡፡ ከሌላው ሕዝብ በሁለት ዓመት ወደኋላ ዘግይተው ነው የክልል ምርጫውን የሚያካሂዱት፡፡ በመሆኑም በዕለቱ ለተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ይመጥናሉ የሚሏቸውን ፓርቲዎች ሲመርጡ ውለዋል፡፡

 ከ2002 ምርጫ ጋር ሲነፃፀር በዛ ያለ የሕዝብ ቁጥርና ሠልፍ የታየበትም ነው፡፡ በ2002 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ምርጫ ለመዘገብ ሪፖርተር ከተዘዋወረባቸው አካባቢዎች አብዛኞቹ ምርጫ ጣቢያዎች ሠልፍም ሆነ የወጣቱ ክፍል አይበዛባቸውም ነበር፡፡ አመዝነው የሚታዩት እናቶች ነበሩ፡፡ የ2007ቱ ምርጫ ከ1997ቱ ጋር ሲነፃፀር ተቀራራቢ የሕዝብ መነቃቃት ነበረው ለማለት ባያስደፍርም ከ2002 ዓ.ም. ግን የሕዝቡ ተሳትፎ የተሻለ ነበር፡፡ መነቃቃትም ታይቶበታል፡፡

ከዚህ ቀደም በተደረጉ ሁለት ጠቅላላ ምርጫዎች ሁለት ፈጽሞ የተራራቁ ውጤቶችን ያስተናገደችው አዲስ አበባ፣ በምርጫ 2007 ተቃዋሚዎች ለማሸነፍ ተስፋ ያደረጉባት ሆና ነበር፡፡ በምርጫ 1997 ኢሕአዴግ አንድ ወንበር ከማሸነፍ ውጪ 22 ወንበሮችን ያሸነፈው በወቅቱ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ቅንጅት ነበር፡፡ በ2002 ዓ.ም. ይህ ውጤት ተገልብጦ ኢሕአዴግ 22 ወንበሮችን ሲያሸንፍ በወቅቱ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው መድረክ ውስጥ የታቀፈው የአንድነት ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ብቸኛዋን ወንበር ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡

በምርጫ 2007 ምርጫ በተደረገባቸው አብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች በአዲስ አበባም የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ መስጠት ተጀምሮ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ተጠናቋል፡፡

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 36,851,461 ሕዝብ የምርጫ ካርድ የወሰደ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1,481, 521 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ያገኘነው መረጃ ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ለመምረጥ ከተመዘገቡት ውስጥ ድምፅ የሰጡት 1,342,582 እንደሆኑ ያሳያል፡፡

በሁለት መደዳ የተሠለፉት በርካታ መራጮች ድምፅ መስጫ ሰዓት እስከሚደርስ ይጠባበቃሉ፡፡ ጎህ ሳይቀድ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ (ምርጫ ክልል 26/27) ወረዳ ሰባት ምርጫ ጣቢያ አንድ ከተገኙት የመጀመርያዎቹ ተሠላፊዎች የ19 ዓመቷ ሰላም አስካለ  አንዷ ነች፡፡ የመጀመርያ ዓመት ሕክምና ተማሪ ናት፡፡ ‹‹የመጀመሪያዬ ምርጫ ስለሆነ ድምፅ ለመስጠት ጓጉቻለሁ፤ በለሊት የተገኘሁትም ለዚሁ ነው፤›› ትላለች፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተደረገው ክርክር የምትመርጠውን እንደተገነዘበችና በፓርቲዎቹ መካከል የነበረውን ፉክክር ጠንካራ እንደነበር ትገልጻለች፡፡ ‹‹የአንድ ሰው ተሳትፎ ትልቅ ሚና ስላለው ያመንኩበትን ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ፤›› ብላለች፡፡

በምርጫ ጣቢያው በተጣለው ድንኳን ድምፃቸውን ሰጥተው ሲወጡ ያነጋገርናቸው የ68 ዓመቱ አቶ ሀብተማርያም ምሕረትአብ፣ በአገሪቱ በተካሄዱ ምርጫዎች ባጠቃላይ ድምፅ መስጠታቸውንና የዘንድሮው ምርጫ ከቀደሙት የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሰው ያለምንም ጫና እየመረጠ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የ69 ዓመቱ አቶ ተፈራ ድሩ ሐሳቡን ይጋሯቸዋል፡፡ የዘንድሮውን ጨምሮ በሁሉም በኢሕአዴግ መንግሥት በተካሄዱ ምርጫዎች የሕዝብ ታዛቢ ሆነዋል፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ የዘንድሮው ምርጫ ‹‹የተረጋጋና የሠለጠነ አካሄድ ያለው›› ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ አስቀድመው ያደረጉት እንቅስቃሴ አገርን ለማሳደግ በቁጭት እንደተነሳሱ ያሳያል ይላሉ፡፡ ‹‹እንደቀደሙት ጊዜያት መናቆር የለም፤›› በማለት የሚሸነፉ ፓርቲዎች ከአሸናፊው ጋር በሰላም እጅ ለእጅ ተጨባብጠው ኑሮ በሰላም እንደሚቀጥል እምነታቸው ነው፡፡

በምርጫ ጣቢያው የሕዝብ ታዛቢዎችና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ተገኝተው ሒደቱን ይከታተሉ ነበር፡፡ የጣቢያው የምርጫ አስተባባሪዎችም የምርጫ ቅደም ተከተል ለሕዝቡ ያብራሩ ነበር፡፡ የምርጫ ክልሉ ኃላፊ አቶ ተሾመ አበበ በክልሉ በሚገኙ 110 የምርጫ ጣቢያዎች መሰል ሒደት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ በሒደቱ ይህ ነው የሚባል ችግር እንዳልገጠማቸውና ቅሬታዎችም እንዳልተነሱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ረፋድ ላይ ሳር ቤት አካባቢ በምርጫ ክልል 20 በሚገኙ 59 የምርጫ ጣቢያዎች ኢሕአዴግን ወክለው የሚወዳደሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ ድምፅ ሲሰጡ ሪፖርተር አግኝቷቸዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በሰላማዊ መንገድ መምረጡ አገሪቱን ለአፍሪካና የዓለም አገሮች ተምሳሌት ያደርጋታል፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው የዴሞክራሲ ባህል እየዳበረ መሆኑን አመላካች እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ሕዝቡ የሚመራውን ፓርቲ በራሱ ድምፅ መርጦ እንደሚያስቀምጥና በሰላማዊ መንገድ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በምርጫ ጣቢያው የመኢአድ ተወካይ ታዛቢ አቶ በለጠ የሺጥላ ምርጫው በጥሩ ሁኔታ መከናወኑን ይናገራሉ፡፡ በቦታው ከገጠማቸው ችግሮች አንዱ የምርጫ ካርድ ሳይዙ ወደ ጣቢያው የሚሄዱ ሰዎች ሲሆኑ፣ ግለሰቦቹ በምዝገባ ላይ ምርጫ ካርድ መውሰዳቸው ተረጋግጦ ተስተናግደዋል ብለዋል፡፡

ተመሳሳይ ችግር የተስተዋለው የምርጫ ክልል 19 ውስጥ ከተካተቱ አካባቢዎች በአንዱ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም ነው፡፡ መታወቂያ ሳይዙ ድምፅ ለመስጠት ወይም የምርጫ ካርድ ሳይኖራቸው (እንደጠፋባቸው የሚናገሩም አሉ) ድምፅ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ያመሩ ግለሰቦች ተስተውለዋል፡፡ በወረዳ 6 ምርጫ ጣቢያ 20 የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢ የነበሩና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብ ያቀረቡት ቅሬታም ይኼው ነው፡፡

‹‹መታወቂያ የሌለው ወይም የጠፋበት ሰው የሕዝብ ታዛቢዎች የሚያውቁት ከሆነ እንዲመርጥ ይደረጋል፡፡ ሕጉ ባያስማማኝም ከምርጫ ቦርድ የወረደ ስለሆነ ተቀብያለሁ፡፡ መራጮች በዚህ ምርጫ ጣቢያ ያለመታወቂያ መምረጥ እንደማይቻል ሲገለጽላቸው፣ መጀመርያ ያለመታወቂያ ምርጫ ካርድ ሰጥታችሁናል፡፡ ስለዚህ መምረጥ እንችላለን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፤›› የሚሉት ታዛቢው፣ በሕጉ መሠረት መታወቂያ የሌላቸውን ሰዎች እናውቃቸዋለን ብለው ምስክርነት የሚሰጡት የሕዝብ ታዛቢዎች ብቻ ሳይሆኑ የኢሕአዴግ ታዛቢዎች ጭምር እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ አሠራሩ የአገሪቱን ሕግ የሚፃረር መሆኑን በማስረገጥ ታዛቢው ተከራክረው ያለመታወቂያ እንዳይመርጡ ያደረጓቸው ግለሰቦች ቢኖሩም የመረጡም አሉ ይላሉ፡፡

የምርጫ ጣቢያው ኃላፊ አቶ ታደሰ አሽኔ ቅሬታውን እንደማይቀበሉት ነው የገለጹት፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ መታወቂያ የጠፋባቸው ወይም ያልያዙ የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች የሕዝብ ታዛቢዎች ማንነታቸውን እስካወቁ ድረስ ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ ከሕዝብ ታዛቢዎች ውጪ ግን የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ስለግለሰቦቹ ማንነት ምስክርነት አልሰጠም ይላሉ፡፡

በጣቢያው የኢሕአዴግ ታዛቢ ወ/ሪት ጽጌ ፀጋዬ በበኩላቸው የምርጫ ካርድ ሲወስዱ መታወቂያ ኖሯቸው የጠፋባቸው ግለሰቦች በሕዝብ ታዛቢዎች እስከታወቁ ድረስ ድምፅ መስጠታቸው አግባብ ነው ይላሉ፡፡ የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች በርካታ በመሆናቸው የሁሉንም ማንነት ለማወቅ አይቻልም የሚሉት ታዛቢዋ፣ ማንነታቸው ሳይታወቅ የመረጡና ፓርቲያቸውም ጣልቃ ገብቶ እናውቃቸዋለን ያላቸው ግለሰቦች እንደሌሉ ገልጸዋል፡፡ በጣቢያው የሕዝብ ታዛቢ ወ/ሮ ዘውድነሽ ድንቁ እንደሚናገሩት፣ መታወቂያ የሌላቸውና እሳቸውና የተቀሩት የሕዝብ ታዛቢዎች ያላወቋቸው ሰዎች ድምፅ እንዳይሰጡ አግደዋል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሳሪስ የተካሄደውን የድምፅ ቆጠራ ሪፖርተር የተከታተለው በወረዳ 10 ምርጫ ጣቢያ ሰባትና ስምንት ነበር፡፡ 12 ሰዓት ካለፈ በኋላ የድምፅ መስጫ ኮሮጆዎች ተቆልፈው በአቆጣጠሩ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች፣ የሕዝብ ታዛቢዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮችና የምርጫ አስፈጻሚዎች ተወያይተዋል፡፡

መራጮች ድምፅ በሚሰጡበት ወቅት ‹‹X›› ምልክት ማድረግ እንዳለባቸው ቢገለጽም፣ በመዘንጋት ወይም በተለያየ ምክንያት ‹‹ü›› ያደረጉት ድምፅ እንደሰጡ መቆጠር አለበት የሚል ክርክር በምርጫ ጣቢያ ሰባት ቢነሳም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ከአሻራና ‹‹X›› ምልክት ውጪ ያሉ ወረቀቶች ፊርማ ወይም ጽሑፍ የተቀመጠባቸውና ከአንድ በላይ ፓርቲ ላይ ምልክት የተደረገባቸው ድምፅ አልባ ሆነዋል፡፡

በሁለቱ ምርጫ ጣቢያዎች ለሰዓታት የዘለቀው ቆጠራ ሁሉንም ታዛቢ አካላት ለማሳተፍ የተሞከረበት ነበር፡፡ በምርጫ ጣቢያ ሰባት ታዛቢ የነበሩት የመድረክ ተወካይ አቶ ኪሳ ተመስገን፣ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ሕግ መሠረት ቆጠራው መካሄዱንና ሒደቱም ‹‹ፍትሐዊ ነው›› ብለዋል፡፡ በጣቢያው የኢሕአዴግ ተወካይ አቶ የሥጋት ፈጠነም ቅሬታ እንደሌላቸው ነው የተናገሩት፡፡

በዞን ሁለት ምርጫ ክልል 24 ጦር ኃይሎች አካባቢ የተወዳደሩት የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ ምርጫ ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፣ ምርጫው ካልተጭበረበረ እንደሚያሸንፉ ነው፡፡ አቶ አበባው በዕለቱ ለመምረጥ የምርጫ ካርዳቸውን ይዘው የነበረ ቢሆንም ከሚመርጡበት ጣቢያ ስምዎት የለም በመባላቸው ሲንከራተቱ ነበር፡፡ ሆኖም ተሳክቶላቸው በዞን ሁለት ምርጫ ክልል 24 ምርጫ ጣቢያ ስምንት ላይ መምረጥ ችለዋል፡፡

በዞን ሦስት ምርጫ ክልል 18 የተወዳደሩት የ32 ዓመቷ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በአዲስ አበባ ኢሕአዴግን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት ከቀረቡ 23 ዕጩዎች አንዷ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቅም ግንባታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙት ወ/ሮ ዳግማዊት፣ የምርጫ ጣቢያዎቹ ሒደት ጥሩ ሊባል የሚችል፣ እናቶች፣ ወጣቶችና አዛውንቶች ያዩባቸውና ይኽም ኅብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም ያለውን ዝግጅት ያሳየ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ዳግማዊ የ2007 ዓ.ም. ምርጫ ከ2002 ጋር ሲነፃፀር በሒደቱ የተሻለ ነው፡፡

በዞን ሁለት ምርጫ ክልል 24 ጣቢያ 2 ድምፅ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ ምርጫው ሰላማዊና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የሒደቱን ሰላማዊነትና አሳታፊነት በቃላቸው የገለጹበት መሆኑን ጥቃቅን ችግሮች ሲከሰቱ ወዲያው የመፍታት ሒደት እንደነበር አመልክተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ካሉ የምርጫ ክልሎች ውስጥ በምርጫ ክልል 17 (ቦሌ) የተሻለና የተቀራረበ ውጤት እንዲጠበቅ ላደረገው ግምት መነሻ የሆነው ደግሞ በክልሉ የሚወዳደሩት እጩዎች ማንነት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ በአቶ ዮሐንስ በቀለ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በአቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ኢዴፓ በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በአቶ ወንድወሰን ተሾመ እንዲሁም ኢራፓ በፕሬዚዳንቱ በአቶ ተሻለ ሰብሮ ተወክለው ነበር፡፡

ሪፖርተር በምርጫ ክልሉ በሚገኙ ጣቢያዎች ውስጥ ያገኛቸው የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ሒደቱን ያልተረዱት መራጮች እጅግ ትንሽ እንደሆኑና አብዛኛዎቹ ግን ስለ ሒደቱ አስቀድመው ግንዛቤው ያላቸው እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በምርጫ ክልሉ በሚገኘው ወረዳ 13 ውስጥ 18 የምርጫ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን፣ ገርጂ ታክሲ ተራ አካባቢ የሚገኘው ምርጫ ጣቢያ 4 ኃላፊ አልማዝ ደሳለኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጣቢያው ድምፃቸውን የሰጡት መራጮች ያለምንም ግራ መጋባት ሒደቱን ፈጽመዋል፡፡ የወረዳ 6 የምርጫ አስተባባሪ አቶ ታምራት ፍርድአወቅ በተመሳሳይ መራጩ ሒደቱን አስቀድሞ ተረድቶ በመምጣቱ አስረዱኝ ብሎ የሚጠይቀው እጅግ ጥቂቱ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በምርጫ ሒደት ውስጥ ከሽግግር መንግሥቱ አንስተው ተካፋይ እንደሆኑ የገለጹት አቶ ታምራት፣ የሕዝቡ ንቃተ ህሊና ከምንጊዜውም በላይ አሁን ያደገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በወረዳ 3 ከሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በአንዱ ያገኘናቸው የኢሕአዴግ ታዛቢ አቶ አዲሱ አካለ የምርጫ አስፈጻሚዎች የተሻለ አቅምና አደረጃጀት በመገንባታቸው መራጩ በቀላሉ በምርጫው ሒደት እንዲያልፉ አስችሏል፡፡ በዚያው የምርጫ ጣቢያ ያገኘናት የሰማያዊ ፓርቲ የምርጫ ታዛቢ ወጣት ቅድስት ግርማ መራጮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው በሚገባ የተረዱ እንደሆኑ አስገንዝባለች፡፡ ይሁንና በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎች አልነበሩም፡፡

በምርጫ ሒደቱ ሲሳተፉ ካገኘናቸው መካከል አቶ ገናናው ጃቢር፣ ወጣት ሔኖክ ተስፋዬና ወጣት አሰገደች አብርሃም በሒደቱ በመሳተፍ በአገራቸው ጉዳይ ላይ ውሳኔ በማሳረፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የ21 ዓመቱ ወጣት ሔኖክ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ መሳተፉ ነበር፡፡ ‹‹የምፈልገውን ተወካይ በነፃነት በመምረጥ በአገሬ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ የምችልበት ዕድሜ ላይ በመድረሴ ደስተኛ ነኝ፤›› ብሏል፡፡

በምርጫ ጣቢያ 4 የድምፅ መስጠት ሒደቱ 12 ሰዓት ምሽት ላይ ተጠናቆ ቆጠራው 1 ሰዓት ተጀምሮ ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ እስኪጠናቀቅ ሪፖርተር ሒደቱን የተከታተለ ሲሆን፣ በጣቢያው የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች ተገኝተው ነበር፡፡

በምርጫ ክልል 5 መርካቶ አካባቢ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ማልደው ከመጡ መራጮች ውስጥ አንዱ በሠላሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ታሪኩ ደምሴ ነበር፡፡

ታሪኩ በ1997 ዓ.ም. እና 2002 ዓ.ም. በተደረጉት ጠቅላላ ምርጫዎች ተሳትፏል፡፡ ‹‹የሚበጀኝን ፓርቲ የመረጥኩበት መሥፈርት የፓርቲው የወደፊት ራዕይና እስካሁን ያሳያቸው ነገሮች ናቸው፡፡ ይህንንም ከተከታተልኳቸው የምርጫ ክርክሮች ተረድቻለሁ›› ሲል አስተያየቱን ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

በምርጫ ክልል 5 በ2002 ዓ.ም. በተደረገው ጠቅላላ ምርጫ መድረክ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ያሸነፈበት ነው፡፡ መድረክን የወከሉት አቶ ግርማ ሰይፉ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ መሆናቸው ይታወሳል፡፡

በዚሁ የምርጫ ክልል ዘንድሮ ኢሕአዴግና መድረክን ጨምሮ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፎካክረዋል፡፡ ምርጫ ክልል 5 የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በዕጣ ከተወዳዳሪነት ውጪ በመሆናቸው ፓርቲው በዚህ ክልል ተወዳዳሪ አልነበረውም፡፡

ቲና ወልደ ማርያም፣ ከእህቷ ከቤዛ ወልደ ማርያምና ከጎረቤቷ ውድነሽ ወርቁ ጋር በመሆን ቲና የስድስት ወር ውድነሽ ዓመት ከሁለት ወር የሆናቸውን ወንድ ልጆቻቸውን ታቅፈው ድምፅ ለመስጠት ማልደው ካዛንቺስ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ተገኝተዋል፡፡

ቲናና ውድነሽ በምርጫ ክልል 15 የነባር ቀበሌ 31 ምርጫ ጣቢያ አዳራሽ ውስጥ የተገኙት በዕለቱ ወንድ ልጆቻቸውን ኪዳነ ምሕረት ከማቁረባቸው በፊት ለመምረጥ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

በእነዚህ ጣቢያዎች ከሚወዳደሩት 12 ፓርቲዎች መካከል የኢሕአዴግ፣ የሰማያዊ፣ የመድረክና የመኢአድ ታዛቢዎች የተገኙ ሲሆን፣ በድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ችግር እንዳላጋጠማቸው ገልጸዋል፡፡

ሾላ መገናኛ አካባቢን ከያዘው ምርጫ ክልል 16 ውስጥ ከሚገኙት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች አንዱ የሆነውና መገናኛ የካ ተራራ ላይ የሚገኘው የወረዳ 5 ምርጫ ጣቢያ 4 የቦታው አቀማመጥና አቀበታማው መልክዓ ምድርና ወደ ጣቢያው የሚወስዱት መንገዶች በቀላሉ ለመንቀሳቀስ አዳጋች ነበሩ፡፡

ምንም እንኳ ጣቢያው የሚገኝበት ቦታ አቀማመጥ ቀና ባይሆንም መራጮችን በሰዓቱ ተገኝተው ድምፅ የመስጠቱን ሒደት እንዳልገደበው የጣቢያው አስተባባሪ አቶ ሰለሞን አሞኘ ገልጸውልናል፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በወረዳ ዘጠኝ ከሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ሦስት ቅጥር ግቢ አጠገብ አንዲት በዕድሜ የገፉ ባልቴት በምርኩዛቸው እየተደገፉ ወደ ቤታቸው ሲያመሩ አግኝተናቸዋል፡፡ ባልቴቷ ወ/ሮ ጠይባ አቡበከር ይባላሉ፡፡ ወይዘሮ ጠይባ እንዳጫወቱን ከሆነ ዕድሜያቸው 100 ሊሞላ ሦስት ዓመት ብቻ ነው የቀረው፡፡ “ሌላ የምርጫ ካርድ ለማምጣት ወደ ቤቴ እየሄድኩ ነው፤” አሉን፡፡

ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ደበበ የጣቢያው ምርጫ አስፈጻሚ የሚሉት ደግሞ ባልቴቷ ለመምረጥ በቅድሚያ መመዝገባቸው ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ ሳይመርጡ የተመለሱትም በ2005 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ የተመዘገቡበትን የምርጫ ካርድ ይዘው በመምጣታቸው በመሆኑ የአሁኑን ምርጫ ካርድ ይዘው መጥተው እንዲመርጡ ተነግሯቸዋል፡፡ 

ሽሮ ሜዳ አካባቢ በሚገኘው የዞን 4 ምርጫ ክልል 11 ጣቢያ ጧት 2፡20 ሰዓት ላይ ተገኝተው ድምፅ የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩው አቶ ስለሺ ፈይሳ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትና የምርጫ ጉዳዮች አስተባባሪ ናቸው፡፡ በምርጫው ሒደት ታዛቢዎቻቸው በተዘዋዋሪ ታዛቢዎች ምርጫውን ለመከታተል እንደሞከሩ ገልጸውልናል፡፡

በወረዳ 11 ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የተለያዩ የምርጫ ታዛቢዎችን የተመለከተ ቢሆንም፣ በ20 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የተገኘው አንድ የሰማያዊ ፓርቲ ታዛቢን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የኢሕአዴግ፣ የሲቪክ ማኅበራት ጥምረትና የሕዝብ ታዛቢዎችን ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚገኙ 17 የምርጫ ጣቢያዎችም የክልል ተወላጆች ሲመርጡ ውለዋል፡፡ ሆኖም እስከ ቀኑ 8፡30 ድረስ ለአንዳንዶቹ የመምረጫ ሰነድ ተማልቶ ባለመቅረቡ መራጮች ተቸግረው ነበር፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሥር በሚገኙ 15 ካምፓሶች የሚማሩ 7,029 የክልል ተወላጆች በክልልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ለመሳተፍ ካርድ የወሰዱ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ ከትግራይ አክሱም፣ ከጋምቤላ አንዳንድ አካባቢዎች፣ ከአማራ አምባሰል፣ ከሐረሪ አንዳንድ አካባቢ ለመጡ ተማሪዎች በምርጫው ሙሉ ለሙሉ ለመሳተፍ የሚያስችላቸው ሰነድ እስከተጠቀሰው ሰዓት ድረስ ተሟልቶ አልቀረበም፡፡

የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ጫኔ እንደሚሉት፣ ችግሩ የተፈጠረው በዩኒቨርሲቲው ሳይሆን በምርጫ ቦርድ ነው፡፡ በመሆኑም ችግሩን ለምርጫ ቦርድ አሳውቀዋል፡፡ የምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በክልል በሚገኙ ከፍተኛ ተቋማት ምርጫ ሒደት ላይ ለተፈጠረው ክፍተት ይቅርታ ጠይቋል፡፡ አንድም ተማሪ ሳይመርጥ እንደማይቀርና ችግሩም እንደሚፈታ አሳውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዕለቱ ሰነድ ተሟልቶላቸው ምርጫ ያጠናቀቁ ሲሆን የክልል ተማሪዎች ግን ምርጫውን ያጠናቀቁት በማግስቱ ሰኞ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ሲመርጥ ያገኘነው የ23 ዓመቱ ይድነቃቸው ጥላሁን ውልደቱ ኢሉአባቡራ ዞን ጎሬ ከተማ ሲሆን፣ የሁለተኛ ዓመት የሶሻል ወርክ ተማሪ ነው፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ በምርጫ እንደተሳተፈ የሚናገረው ይድነቃቸው በያሉበት ዩኒቨርሲቲ ሆነው መምረጣቸው መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ተከልለው መምረጣቸውም ምንም ጫና እንደማይፈጥርበት፣ የመምረጥም ሆነ ያለመመረጥ መብቱን ሊጠቀም እንደሚችልም ነው የገለጸልን፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢሾፍቱና በፍቼ የሚገኙት ካምፓሶችን ጨምሮ በ17 የምርጫ ጣቢያዎች የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የደቡብ፣ የትግራይ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የሐረሪና የጋምቤላ ተወላጅ ተማሪዎች ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

በተያያዘም በአዲስ አበባ ከተማ በዞን 5 የምርጫ ክልል በወረዳ 2 እና 14 ምርጫ ጣቢያ፣ በብሔራዊ ሎተሪ ግቢ ድምፅ መስጫ የተዘጋጀላቸው የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች፣ ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ሦስት ቢሆኑም፣ ለውድድሩ ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበው ሐብሊ (የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ) መሆኑን አስተባባሪው አቶ አደም አቡበከር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ነዋሪ ለሆኑት ሐረሪዎች ክልላቸውን የሚመሩላቸው 14፣ በፓርላማ የሚወክሏቸውን አንድ ዕጩ ለመምረጥ በአዲስ አበባ በተለያዩ አምስት ጣቢያዎች ሲመርጡ መዋላቸውን አውስተዋል፡፡ ለፓርላማው ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ወ/ሮ ኑሪያ አብዱራህማን ኡመር ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሐረሪዎች ለሚኖሩበት ወረዳ በፓርላማ የሚወክላቸውን፣ በሐረሪነታቸውም ከሐረር በፓርላማ ለሚወክላቸው ድምፆች ይሰጣሉ፡፡

የሐረሪ ተወላጆች ከሌሎች ክልሎች በተለየ ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ ከ1987 ዓ.ም. የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ጀምሮ እንደሚመርጡ ይታወቃል፡፡

(ዘገባውን ያጠናቀሩት ምሕረተሥላሴ መኰንን፣ ምሕረት ሞገስ፣ ታምሩ ጽጌ፣ ታደሰ ገብረማርያም፣ ይበቃል ጌታሁን፣ ቴዎድሮስ ክብካብ፣ ሚኪያስ ሰብስቤ፣ ሰሎሞን ጎሹና ሔኖክ ያሬድ ናቸው)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...