ብዙዎቹ አጥቢዎች ብዙ ሴቶች ጋ ይሄዳሉ፡፡ ከሁሉም ግን የባህር ዳርቻ ነዋሪ የሆነው ፈርሲል (Furseal) ሻምፒዮን ነው፡፡ ከ40 እስከ 60 ሚስት በአማካይ ይኖረዋል፡፡ ከሁሉም ለየት ያለ ጠንካራ ወንድ ደግሞ ከ100 በላይ ሊኖረው ይችላል፡፡ የሚፎካከሩት አጥቢዎች ቢኖሩ (ሰውን ሳይጨምር) ኢልክ (Elk) እና ካሪቡ (Caribou) ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ጠንካራው ወንድ ከ200 እስከ 300 ሴቶች ሲኖሩት ደካማውና እርጅና የተጫጫነው ደግሞ አንድ ወይም ሁለት ይኖሩታል፡፡
ቃል ኪዳን አክባሪዎቹ
ከአንድ የሚፀነሱ እንስሳት ጥቂት ናቸው፡፡ በአጠቃላይ 5,000 ያህል ከሚሆኑት የአጥቢ ዝርያዎች ውስጥ ዕድሜ ልካቸውን ተጣምረው የሚኖሩት ከሦስት እስከ አምስት በመቶ ያህሉ ብቻ ቢሆኑ ነው፡፡ እኒህም ገድቤ አይጥ (Beaver)፣ ኦተር (Otter)፣ ቀበሮ (Jackal) ቀበሮችና አንዳንድ የሌሊት ወፎች፣ ጥቂት ድንክዬ ዲሮችና አንቴሎፕ ናቸው፡፡
ታማኝ ሆኖ መቆየት በእንስሳት ዓለም ውስጥ የተለመደ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የወንዶቹ አፈጣጠር በተቻለ መጠን ዘር ማብዛት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ነው፡፡ ሴቶቹም ጠንካራና የበላይ የሆነ ወንድ ፈልገው ነው ልጅ መውለድ የሚፈልጉት፡፡ በአንፃሩ የአንድ ለአንድ ጥምረት፣ ለእንስሳት የመራባት አቅማቸውን ውስን ያደርግባቸዋል፡፡
- ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹ባለአከርካሪዎች›› (2004 ዓ.ም.)