ከሃያ አራት ዓመት በፊት ግንቦት 20 ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ምዕራፍ የያዘ ዕለት ነበር፡፡ ለ17 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆየው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ)፣ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ከነጓዙ ከሥልጣን የተወገደበት ዕለት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ለአንድ ወር በኢትዮጵያ ጊዜያዊ መንግሥትነት አገሪቱን ከመራ በኋላ ከተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ለአራት ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥትን መርቷል፡፡ ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ገዢ ፓርቲ ሆኖ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን እየመራ ይገኛል፡፡ በደርግ ውድቀት ዋዜማ በእንግሊዝ መዲና ለንደን የኢሕዲሪ መንግሥት ተወካዮች ከኢሕአዴግ፣ ከሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ)፣ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በአሜሪካ መንግሥት አማካይነት ድርድር ተቀምጠው ነበር፡፡ ድርድሩ ባለመሳካቱ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ግንቦት 20፣ ሻዕቢያ አሥመራን ግንቦት 16 ቀን መቆጣጠራቸው ይታወሳል፡፡ ከሮይተርስ የተገኘው ፎቶግራፍ የሚያሳየው ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በለንደን ከተማ አሜሪካዊው የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሔርማን ኮኾን መግለጫ ሲሰጡ (በግራ)፣ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ፣ የኦነግ ምክትል አቶ ዮሐንስ (ሌንጮ) ለታ እና የሻዕቢያ ዋና ጸሐፊ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ይታያሉ፡፡
(ሔኖክ መደብር)
* * *
አዲስ አበባ ምን ነበረች?
ስለ አዲስ አበባ ጠይቁና ዕወቁ
ፓሪስና ለንደን ብሎ ከማድነቁ፣
እስኪ እርሳሳችሁን ከወረቀት ጋር፡፡
አገናኙትና እስበርሱ ይናገር
ስላዲስ አበባ ታሪክ ስታወሩ
የቀድሞውን ካሁን ብታነፃፅሩ
ታገኙታላችሁ ቅርብ ነው ነገሩ፡፡
ቀድሞ እንዴት ነበረች? ዛሬስ እንደምን ነች?
መነፅር አንሻም ከፊታችን አለች፤
አሁን ትናንትና አሁን በቀደምለት
ማለት ይቻላል ወይ እሷን ነው ያየኋት፡፡
ነበር ለዚህ ጊዜ ዋጋውን አያጣም
ከነበረችበት ተነሥታለች በጣም
እንደዚህ እንዳለች አልተፈጠረችም
የገንዘብ የጉልበት ልዩ ልዩ ድካም
ፈጅታለች በብዙ ቁጥሩ አይዘለቅም፡፡
ውድ አዲስ አበባ ሀገረ ገነት
ገና ሳትደራጅ ሳታገኝ ዕድገት
የነበራት ጥረት ጎጆ ለመውጣት
በበሬ ትከሻ በበሬ ጉልበት
ጠርብና ሳንቃውን ስታስግዝ ለቤት
የትልቅ ትንሹን ስትፈልግ እርዳታ
ዱር ስታስመነጥር ከጥዋት እስከ ማታ፡፡
ድንጋይ ስታስፈልጥ ስታስግዝ በአህያ
ጭቃ ስታስረግጥ ለቤት መከለያ
እደርሳለሁ ብላ ለእንደዚህ ያለ ክብር
ምንም ቢሆን ከቶ አይታሰብም ነበር
በምኒልክ ጊዜ በሳዱላነትዋ
እንደዚህ ኑሩዋል ወይ መልክና ውበትዋ፡፡
እንኳንስ ልታጌጥ ፊትዋን ልትጠራርግ
አጋምና ቀጋ ሸፍኗት ያለ ወግ
አትታይም ነበር ከቶ ምን ቢደረግ፡፡
መንገዶቹዋ ሁሉ በጊዜው ያሉት
አቧራ ኰረኰንች ጭቃው እስከባት
አላስኬድ እያለ ስንቱን አዛውንት
ያስቸግር ነበረ ሁኖን እንቅፋት፡፡
እስኪ ሁኔታዋን ልመርምር ልረዳ
ከኔ የሚያውቅ የለም የታሪኳን ጓዳ፤
እኔም ያገኘሁዋት እንዲህ ሳትደረጅ
ከመላው ዓለም ጋር ወዳጆች ሳታበጅ
አንገትዋ ሳይጠና በዕውቀት ሳትፈረጅ
የዛሬ አርባ ዓመት ነው ያየሁዋት በወዳጅ፡፡
ከአርባ ዘመን በላይ ባደረግሁት ጥናት
ጠባዩዋን ለማወቅ በውል ለመረዳት
በጣም ደክሜአለሁ ስዞር ስንከራተት፡፡
በመኪና እንኳ አይደል ያለጫማ በእግር
ከእንጦጦ ጀምሬ ለመድረስ ለገሀር
የመንገዱ ርቀት እንደ ውሎ ነበር፡፡
- ያሬድ ገ/ሚካኤል ‹‹ይምጡ በዝና ወደአዲስ አበባ›› (1958)
* * *
ሰውየውና እባቡ
በድሮ ጊዜ የዱር እንስሳትና የቤት እንስሳት እንደሰዎች ነበሩ፡፡ የሚግባቡበትም ቋንቋ ነበራቸው፡፡ ፀሃፊያችን ብለው የሚጠሩት ገዢም ነበራቸው፡፡ ይህም ፀሃፊ ቀበሮ ነበር፡፡ ቀበሮውም ከሌሎቹ እንስሳት ተለይቶ ለብቻው ይኖር ነበር፡፡ እንስሳቱ በተጣሉ ጊዜ ቀበሮው ዘንድ ሄደው ፍትህ ይሰጣቸዋል፡፡
ታዲያ አንድ ቀን አንድ ሰው ብቻውን እየተጓዘ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሰዎች እንስሳትን ማናገር ይችሉ ነበር፡፡ ሰውየውም እየተጓዘ ሳለ አንድ እባብ ያገኛል፡፡
እባቡ በእግር መሄድ የማይችል አሳዛኝ ፍጡር ሲሆን ሰውየው ግን ይህን ማድረግ ስለሚችል እባቡም “አንተ ወደፈለክበት መሄድ ትችላለህ፡፡ እኔ ግን ሽባና መራመድ የማልችል ስለሆነ እባክህ ተሸከመኝ?” ብሎ ለመነው፡፡
ሰውየውም እባቡን ተሸክሞ ይጓዝ ጀመር፡፡
ከረጅም ጉዞም በኋላ ሰውየው “አሁን ደክሞኛል፡፡ ብዙ መንገድም ስለተጓዝን እባክህ ውረድልኝ፡፡ እዚህ ትቼህም እሄዳለሁ፡፡” አለው፡፡
ነገር ግን በዚህ ተጣሉ፡፡
እባቡም “አልወርድልህም” አለው፡፡
ሰውየውም “ውረድ” ብሎ ሲጠይቀው “አልወርድም፡፡ እንዲያውም እነድፍሃለሁ፡፡” ብሎ አስፈራራው
እባቡም ወደ ሰውየው ፊት ዞሮ ምላሱን በማውጣት እንደሚነድፈውና እንደሚመርዘው ነግሮት ስላስፈራራው ሰውየው ከፍራቻው የተነሳ እባቡን ተሸክሞ ጉዞውን ቀጠለ፡፡
በዚህን ጊዜ ሰውየው አንድ ሃሳብ መጥቶለት “ለምን ወደ ዳኞች አንሄድም?” አለው፡፡
ከዚያም ወደ ዝሆን፣ ጎሽ እና ወደሌሎች ትልልቅ እንስሳትና ወደ አንበሳና ነብር ተያይዘው ሄዱ፡፡ ነገር ግን እንስሳቱ ዘንድ በደረሱ ጊዜ እባቡ ሁሉንም አንድ በአንድ እነድፋችኋለሁ ብሎ ስላስፈራራቸው ሁሉም ፈርተውት ነበር፡፡
በዚህ ምክንያት ሰውየው ፍትህ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ ግራም ስለገባው የተሻለ ዳኛ ለማግኘት ሞከረ፡፡ በመጨረሻም ቀበሮው አለቃቸው መሆኑን ሳያውቅ ወደ እርሱ ሄደ፡፡
በዚህም ጊዜ እባቡ በሰውየው አንገት ዙሪያ ተጠምጥሞበት ነበር፡፡
“እዚህ ድረስ አንገቴ ላይ ተጠምጥሞ ይዤው መጣሁ፡፡ እናም አሁን ውረድልኝ ብለው እምቢ አለኝ፡፡” በማለት ሰውየው ክሱን አቀረበ፡፡
በዚህ ጊዜ ቀበሮው “እንግዲያውማ ይህ ቀላል ነው፡፡ ፍርዱንም እኔ እሰጣለሁ፡፡ ሁለታችሁም ቁጭ በሉ፡፡” አላቸው፡፡
ሁለቱም ከተቀመጡ በኋላ ቀበሮው እንዲህ አለ “አሁን ፍርድ እሰጥ ዘንድ ጥያቄዎች ስለምጠይቅ ሰውየው ብዙ መናገር አለበት፡፡ አንተ ግን አንገቱ ላይ ስለተጠመጠምክ እንዴት መናገር ይችላል? ስለዚህ ካንገቱ ላይ ውረድና እኔም ፍርዱን እሰጣለሁ፡፡”
በዚህን ጊዜ እባቡ ከሰውየው አንገት ላይ ወርዶ አጠገቡ ቁጭ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ ቀበሮው ወደ ሰውየው ዞር ብሎ “በል በዱላህ ቀጥቅጠህ ግደለው::” ብሎ መከረው፡፡
ሰውየውም እባቡን ጭንቅላቱን ቀጥቅጦ ከገደለው በኋላ በጣም ደስ አለው፡፡ ቀበሮውንም እንዲህ አለው “ባለውለታዬ ነህ፡፡ ህይወቴንም አትርፈህልኛል፡፡ ምስጋናም ማቅረብ ስላለብኝ አንዲት ግልገል ወይም በግ አመጣልሃለሁና እባክህ እንዳገኝህ ከዚህ የትም አትሂድ?”
በስጦታውም ቀበሮው በጣም ተደስቶ እንደሚጠባበቅ ሲነግረው ሰውየውም በተንኮል ቃሉን ባለመጠበቅ አንድ ውሻ ሸማው ስር ደብቆ ይዞ መጣ፡፡ ወደ ቀበሮውም ተጠግቶ ውሻውን ለቀቀበት ውሻና ቀበሮ ባላንጣዎች ስለሆኑ ውሻው የቀበሮውን አንገት በጫጭቆ ገደለው፡፡ ስለዚህም ሰውየው ታማኝነት ጎድሎት የገባውን ቃል አፈረሰ፡፡
ቀበሮው ሊሞት እያጣጣረ “ሰው እንዴት ተንኮለኛ ነው?” ያለውን አባባል ቀበሮዎች ሁሉ እስካሁን ሲያስታውሱት ይኖራሉ፡፡
በአብዱራሂም ባላህ የተተረከ የበርታ ተረት
*******
ልዩ ልዩ ማስታወቂያ
ለሰውነት የሚጠቅም መጠጥ
ስማ የኢትዮጵያ ሕዝብ፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ በሥዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ክቡር መንግሥት ጠላቶችን ሁሉ ላሸነፍኽ ለበረታችህ ሕዝብ ላንተ ሰላም ይሁን፡፡ ሁልጊዜ ብርቱ ሁን ብርቱም እንድትሆን መልካም ወይን ጠጣ፡፡ ኮላ ላሮጌ ሰው ጉልበትን ይመልሳል፣ የጎልማሳ ሰውን ብርታት ይጠብቃል፣ ለሁሉም ደኅንነትና ጤናን ይሰጣል፡፡ የኮላ መገኛው ከአፍሪቅያ ነው በራቱ ማእዘን ስሙ ተጠርቷል ለረጀም ሕይወትን የሚፈልግ ሰው ሁሉ ይመኘዋል፡፡
ቶኒ ኮላን ወይም ኮላ ክሪን ወይ ኮክተል ኮላን ወይም ለክርስታት የሚባል ታላቅ የኮላን አረቂ የጠጣ ሰው ሌላን መጠጥ አይፈልግም፡፡ እነዚህን መጠጦች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ የሚያመጣቸው የንግድ ማኅበር ሉኢስ ዱባይል ኮ አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡
* * *
የምግብ ማስታወቂያ
ካቶ ከበደ ቤት የክርስቲያን ምግብ የጦም የብሎት ምግብ አለ የተመሰገነ፡፡
ካቶ አለሙ ቤት የተመሰከረለት ጥሩ ምግብ ከሻይ ጭምር አለ፡፡
ባዲስ አበባ ተሁሉ የሚበልጥ ጥሩ ዳቦ ቤት በመንግሥት የታወቀ፤ ጥሩ መጠጥም በየዓይነቱ አለ፡፡
የአቶ አየለ ልኳዳ ጥሩ የክርስቲያን ምግብ አለ፡፡ ግቡ ግዙ የጦም ወጥ የብሎት ወጥ አለ፡፡
- ማጆር ዴ.አይ.ኢዲ (መግቢያ ኃይሉ ሃብቱ) ‹‹የአማርና መድበለ ምንባብ›› (1993)
************