Friday, March 1, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አፋርና ስደት

በሐናንያ መሐመድ

ለመጀመርያ ከሆነ ወደ አፋር ክልል የመጣኸው አቅልጥ ሙቀትና አስፈሪ ጥቋቁር ድንጋይ ስታይ፣ በፊልም ያየኸውን የአፍጋኒስታንን በረሃ ወይንም የሊቢያውን  ሰሐራ እንዳይመስልህ፡፡ ከእነዚህ ጥቋቁር ድንጋዮች ጀርባ ምርጥ ሕዝቦች ይገኛሉ፡፡ በዚህ ቦታ የሚኖሩ ሰዎች አይሰደዱም፣ አይለምኑም፣ አይሰርቁም፣ አይዋሹም፡፡ በደንብ ላስገርምህ  እንዴ? አሜሪካ ኦሳማን ላገኘ ወረታ እከፍላለሁ ያለችውን ያህል ዶላር ቢዘረጋልህ የአፋር ሴተኛ አዳሪ አታገኝም፡፡ ከሁሉ የሚደንቅህ ግን በሙቀት እየተቃጠለ፣ አቧራ ላይ እየተንከባለለ ‹‹ይ ባሮ›› ሲል ነው፡፡ ‹‹ይህ አገሬ (ቀየዬ) ነው›› ማለት ነው፡፡ በአገሩ ፍቅር የተለከፈ ትውልድ መሆኑን የግንባሩን መስመር ዓይተህ ያለ አስተርጓሚ ትረዳዋለህ፡፡

ወደ አፋር ክልል የሚመጣ ሁሉ ሊያያቸው የሚቋምጥላቸው ታሪካዊ ቦታዎች ሞልተዋል፡፡  አፋር የብዙ ታሪክ ባለቤት ነች፡፡ የኤርታአሌ እሳተ ገሞራ (የሚነደው ተራራ)፣ የሉሲ አጽም መገኛ ሐዳር፣ የዶቢና አፍዴራ የጨው ባህር፣ የዳሎል ዝቅተኛ ቦታዎች፣ ጭስ ውኃ፣ ሐይቆች ወዘተ… በእርግጥም ሊታዩና ሊጎበኙ ይገባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ እንደነዚህ ቦታዎች ሁሉ ገራሚና አስገራሚ የጋብቻ፣ የሐዘንና የእርቅ ሥርዓቶች በክልላችን አፋር አሉ፡፡

ከአዲስ አበባ ተነስተህ የአፋርን ታሪካዊ ቦታዎች ለማየት መጣህ እንበል፡፡ ኧረ እንደዚህ አንልም የትኛው ኢትዮጵያዊ ነው አገሩን ለመጎብኘት የሚወጣ አገሩን ትቶ ለመሰደድ እንጂ፡፡ ለምን እንወሻሻለን፡፡ በሩ ላይ የተደገፋቸውን ቅርስና ታሪካዊ ቦታዎች መጎብኘት ይቅርና ሲነግሩትም የማያዳምጥ ከዕውቀቱና ከማንነቱ የሸፈተ የስንፍና አርበኛ በየቤታችን እየቀፈቀፍን አይደል? ከተሳሳትኩ አርሙኝ፡፡ ያው በጅምላ ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ለምሳሌ የሐሮማያና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያን ያህል ዓመት ሲቆዩ የለገአዳ ጥንታዊ ሥዕሎች የሚገኙበትን ዋሻ ይጎበኛሉ? የአክሱምና የአዲግራት ተማሪዎችም የየሐን ግንብና የአፄ ካሌብን መቃብር ያያሉ? የጎንደርና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችስ? በደቡብና በኦሮሚያ በሌሎችም የአገራችን ክልሎች ስንት ገራሚ የተፈጥሮ መስህቦች እንዳሉ እናውቃለን? የአገራችን ከፍተኛ ተቋማትስ ይህን ለማድረግ ፍላጎት አላቸው? መንግሥትስ ይህን ትውልዱን ስለአገሩ እንዲያውቅ ምን ያህል እየሠራ ነው ማለት ይቻላል? ለምን? ብጠየቅ እኔም አላውቅም፡፡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ መልስ ቢሰጣቸውም የማያስደስቱ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንዲሉ፡፡ ለነገሩ ተፈጥሮን የማድነቅና የመጎብኘት ፍቅር ያላቸው ሰዎች ቢኖሩም  ይሳቅባቸዋል፡፡ ተባብረን እንሳለቅባቸዋለን፡፡ ‹‹ለጉብኝት ልሄድ ነው›› ብለህ ብታወራ ተማረ ተመራመረ የምትለው  ጓደኛህ፣  ‹‹ብር ተርፎህ ከሆነ ለምን አትሰጠኝም?›› ይልሃል፡፡ ፍቅረኛህም ብትሆን መዝናኛ ቦታ እንጂ ታሪካዊ ቦታ አይመስጣት ይሆናል፡፡ አደራ ከዚህም የባሰ ብትታዘብ ዘመንህን እንዳትኮንን፡፡

ምልናልባት ጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱምና ጀጎል  ብለን የምናዎራቸውን ቦታዎች  በተለያየ አጋጣሚ የሚሄዱ ሰዎችን ለመታዘብ ዕድሉ ከገጠመህ አብዛኛዎቹ ታሪኩን ሳይሆን የሚፈለጉት ፎቶ መነሳት ነው፡፡ ምክንያቱም ፌስቡክ ላይ ይለጥፉታላ፡፡ ነገር ግን ምን አያችሁ? ቢባል ምንም፡፡ አስጎብኚዎችን መጠየቅ ይቅርና ቶሎ እንጨርስ በሚል ሰበብ የታሪክ ሰው አለመሆናችንን እናሳብቃለን፡፡ ጊዜ የለሌን ሰዎች በመምሰል ‹‹ቶሎ ቶሎ በሉ›› የሚል የአስተባባሪዎችን ትዕዛዝ ትሰማለህ፡፡ ወንድ ከሆንክ ያኔ ነው ለምን እንደመጣህ ራስህን መጠየቅ? ታሪክ መሥራት ቢያቅተን ምናለበት ታሪካችንን በአግባቡ ብናውቅ፡፡ ያ ትውልድ ቢኖር ምን ይለን ይሆን? ዓይን ከማየት ጆሮ ከመስማት አይቦዝንም፡፡

ለማንኛውም ለመጎብኘትም ሆነ፣ ለሥራ ጉዳይ፣ አለዚያም አገርህን ጥለህ በጅቡቲ በኩል ለመሰደድ ከመጣህ አፋርን ከሌሎች ክልሎች የሚያገናኟትና በከፍተኛ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ ሦስት ታላላቅ አውራ ጎዳናዎችን ልንገርህ፡፡ አንዱ ከመዲናችን  አዲስ አበባ ተነስቶ እስከ ጁቡቲ የተንጣለለው የከባድ መኪናዎች መፈንጫ መንገድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የአፋርን ሕዝብ የምግብ ፍላጎት በከፊል የሚያሟላው (አኩራፊው መንገድ) ወሎን የሚያስተሳስረው ጥርጊያ ነው፡፡ ሦስተኛውና በቅርቡ አገልገሎት እየሰጠ ያለው የወልድያ ሚሌ መንገድ ሲሆን፣ ትግራይን ከአፋር በማገናኘት ረገድ የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አፋር ክልል የነበራት በር አንድ የሚሌ መውጫ ብቻ ነበር፡፡ ያቺ በር ከተዘጋች ሌባም ሆነ ኮንትሮባንድ ማለፍ አይችልም፡፡ አሁን ግን ብዙ መንገዶች በመሠራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እሰይ…፡፡

‹‹አኩራፊው መንገድ›› በኢጣልያ የተሠራ ሲሆን ወሎን ከአፋር የሚያስተሳስር ጥንታዊ መንገድ ነው፡፡  ነገር ግን  እጅግ ቢያረፍድም በአሁን ሰዓት በመታደስ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ መንገድ አሰብን ከአስመራ የሚያገናኝ ጥንታዊ መንገድ ጭምር ነው ብዬ ብልህ እንዳትገረም፡፡ ከአስመራ አሰብ መንገድ ባልነበረበት ጊዜ ይህ መንገድ አስመራና አሰብን በደሴ በኩል በማገናኘት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ መንገዳችን አዛውንት ነው፡፡ ያኮረፈበት ምክንያትም ደግሞ አዳዲስ መንገዶች በሚሌ ወልድያ፣ በአፍደራና በሰመራ ትግራይን የሚያገኛኑ መንገዶች አዳዲስ ሲሠሩ ለመጠገን እንኳ ችላ ተብሎ የነበረ መንገድ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ ወደ አፋር ክልል አስቤዛዎች ተጭነው የሚገቡት በዚህ አኩራፊ መንገድ ሲሆን የጥጥ፣ የጨውና የቦቆሎ ምርቶች የመሳሰሉት ከአፋር ክልል ወደ ኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ቦታዎች የሚጓጓዙትም በዚሁ መንገድ ነው፡፡ ያለማካበድ ለሁለቱ ክልሎች ዕድገት ሊገመት የማይችል አገልግሎት አበርክቷል፡፡ እያበረከተም ይገኛል፡፡ ምናልባት በቅርቡ ሲጠናቀቅ ፈገግታውን አብረነው እናይ ይሆናል፡፡ የዚያ ሰው ይበለን፡፡ ይቅር ይበለን እስኪ፡፡ ዘይገርም መንገድም ያኩርፈን!!፡፡

ስለመንገዶች የማወራው ዝም ብዬ እንዳይመስላችሁ፡፡ እነዚህ መንገዶች ለኢትዮጵያ ትልቅ ጉሮሮ ናቸው፡፡ እንዴት ቡሉኝማ? እንዴት ማለት ጥሩ ነው፡፡ በተለይ ትልቁ አውራ ጎዳና የጁቡቲ መስመር ሲሆን ይኼው መስመር በደርግ ጊዜም ቢሆን ከአሰብ ጋር የሚያገናኘን በጣም ቅርቡ የወደብ መስመር ነው፡፡ በዚህ መስመር በቀላሉ በቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ከባድና ቀላል መኪኖች ይመላለሱበታል፡፡ ይህ መንገድ ለቀናት ቢዘጋ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለዕቃ ማስቀመጫ ኪራይ ብቻ ጂቡቲ ትመጠምጠናለች፡፡ አይ… እንደሠራ አይገድል፡፡ ብቻ ይህ መንገዱ በቢሊዬን የሚገመቱ ሥራዎችን ሳይሰለች እያጧጧፈ ነው፡፡ ‹‹አሊያ›› ግደለህም! ከየትም ቢሆን ና! እንቀበልሃለን፡፡ ከአዲስ አበባ ከሆነ የተነሳሃው በአዲሱ የፍጥነት መንገድ የሚገባህን ብር ጣል አድርገህ ክነፍ፡፡ ግን በፍቅር እንዳትወድቅ ጠንቀቅ ብለህ ተጓዝ፡፡  ከአዲስ አበባ እስከ ናዝሬት ያለችው የፍጥነት መንገድና የበረሃ ፍቅር ይመሳሰሉብኛል፡፡

የፍጥነት መንገድ ገብተህ ተው ቁም የሚልህ ትራፊክ፣ እንዳይገባብህ የምትፈራው ሰካራም፣ አለዚያም እንስሳቶች እንደማይኖርብህ ሁሉ በበረሃም ፍቅር ይበቃሃል፣ ዕድሜሽ ገና ነው፣ ተው አንተ ከእንትና ልጅ ጋር ይቅርብህ አትባልም፡፡ በነገራችን ላይ አብዘሃኛው የበረሃ ነዋሪ ብዙ የፍቅር እንቆቅልሾችን ያለፈ ሲሆን፣ እንዲያውም አንዳዶቹ በፍቅር ተሰደው በረሃ ገብተው የከተሙ ናቸው፡፡ የሚገርመኝ ግን ይህ ሁሉ ፍቅር ሞልቶ አፋርና ሌላ ሕዝብ የመጋባት ሁኔታቸው የለም ቢባል ይቀላል፡፡ አስረግጠህ ከሰማኸኝ የአፋር ሴቶችና መጤ ወንዶች ማለቴ ነው፡፡ ከሌላ አገር የመጡ ሴቶች ግን አብዛኛዎቹ የአፋር ወንድ ያገባሉ፡፡ አባቱ አፋር ከሆነ ልጁም አፋር ነው የሚል ማኅበረሰባዊ አሰተሳሰብም አለ፡፡ ምክንያቱም የዘር ግንድ የሚቆጠረው በአባት በኩል ሲለሚሆን ነው፡፡

የአፋር ሴቶች ካልተሳሳትኩ እስከ 1994 ዓ.ም. ድረስ ከአፋር ውጪ የማግባት መብት አልነበራቸወም፡፡ ሕጉ ከፀደቀ በኋላም ቢሆን የማግባታቸው ነገር ‹‹ተከድኖ ይብሰል›› ነው፡፡  የአፋር ሴቶችን ለማግባት የሚታትር መጤም ሆነ ተወላጅ ወንድ አልገጠመኝም፡፡ እንግዲህ በሁለቱም በኩል ያለው ርቀት እስካልጠበበ ድረስ የአፋር ሴቶች የፈለጉትን የማግባት መብታቸው ለወሬ ማድመቂያ እንጂ ከአንጀት አለመሆኑን እንረዳለን፡፡ በተቃራኒው ወንድ አፋሮች ከጥንት ጀምሮ የአማራ፣ የትግራይና የኦሮሚያ ሴቶችን በማግባት ሪከርድ ሰብረዋል፡፡ ‹‹አሳ ባራ ጌይቴ አውቶቡስ ቴሜቴ›› የሚል ቅኔ አዘል ሁሉ ጨዋታ አላቸው፡፡ ትርጉሙም ‹‹አውቶቡሱ መጣ ቀይ ሴት አገኛለሁ›› እንደ ማለት ነው፡፡ ለወንድ አፋር ከመኪና ተቀብሎ ወደ ቤቱ መውሰድ ምንም እንደ ቀላል ቢቆጠር አንዲት የአፋር ሴት ግን ሌላን ሰው አፍቅራ ብትቃጠል እንኳ ማግባት ቀርቶ ፍቅሯን መግለጽ የማትችልበት ማኅበረሰባዊ ቀኖና ነበር፡፡ ዓይን ከማየት ጆሮም ከመስማት አይቦዝንም፡፡ የአፋር ሴቶች ብዙ ልፋትና ድካም በነሱ ጫንቃ ላይ የወደቀ ነው፡፡ ቤት መሥራት፣ ልጅ ማሳደግና ብዙ ብዙ ነገሮች፡፡ በሌሎች ቦታዎች በተለምዶ የወንድ ሥራ የሚመስሉትን ሁሉ የአፋር ሴቶች ያለማዛነፍ ያከናውኗቸዋል፡፡.

የበረሃ ፍቅር እንደ ፍጥነት መንገድ ነው ያልኩህ ትልቁን አውራ ጎዳና ተከትለው የተቆረቆሩ ከተሞችን ማለቴ ነው፡፡ አዳማ፣ መተሐራ፣ አዋሽ፣ ገዳማይቱ፣ ገዋኔ፣ እንድፎ፣ አዳይቱ፣ ሚሌ፣ ሎግያ፣ ሰመራ፣ ድችኦቱ ኤሊዳር፣ ጋላፊ፣ ጁቡቲ ድረስ የምታገኛቸውን ነው፡፡ የእነዚህ ከተማዎች የፍቅር ፍጥነት ከፈጣን መንገድ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ጠዋት የጠየቃት ልጅ ማታ አብራችሁ እንዳደራችሁ፣ ትናንት አብራህ የነበረችው ልጅ ትነግርሃለች፡፡ ችግር የለም፡፡ ዛሬ ካንተ ጋር ያደረችው ልጅ ምናልባት ከወራት በፊት የወንድምህ አለዚያም የጓደኛህ ልትሆን ትችላለች፡፡ መገረምም መደነቅም አያስፈልግም፡፡ ዓይን ከማየት ጆሮ ከመስማት አይቦዝንምና፡፡ አታካብደው ቀለል አድርገህ ማየት ነው፡፡ የስምንት ዓመት ልጅ አፍቅራ እየተገረሙ እናቶች ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡ ምና አውቃ ብለህ አትጠይቀኝ፡፡ እኔም አላውቅም፡፡ ግን ነፃ ትውልድ ማለት እንደዚህ መስለኛል፡፡

በነገራችን ላይ በረሃ ‹‹ለሴቶችና ለእንትን… ይመቻል›› ይባላል፡፡ ‹‹ለወንድና ለብረት ደግሞ ያዝጋል›› ይላሉ፡፡ ብዙ ወንዶች ለጫትና ለቢራ እንጂ ለሴት አይንሰፈሰፉም፡፡ አብዛኛው ወጣት ከምንም በላይ የሚያፈቅረው ጫትን ነው፡፡ ጫት ከሌለ ሥራ የማይገባ ሺሕ ሰው ልቆጥርልህ እችላለሁ፡፡ አዲስ አበባ ሸዋ ዳቦ ተሠልፈው ከሚገዙት ሰዎች የሚበልጡ በብዙ እጥፍ ረፋዱ ላይ ጫት ለመግዛት የተሠለፈ ከሕፃን እስከ አዛውንት፣ ከቤት እመቤት እስከ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ከተማሪ እስከ ነጋዴና የመንግሥት ሠራተኞች ተራ ይዘው እንደ ጠራራ እባብ ሲወራጩ ታገኛለህ፡፡ ጫት ምናልባት ሳይመጣ ካረፈደ ሰዎቹ ብቻ ሳይሆን አስፋልቱም ቆሌው ይገፈፋል፣ ይደብረዋል፣ ለስላሳው መንገድ ይሻክራል፣ እንዴት አደርክ የሚለው ቅዱስ ሰላምታ በራሱ ከማሰልቸት አልፎ እንደ እሬት ይመራል፡፡ በዚህ ሰዓት ጫት ይዞ የሚመጣ  መኪና ድምፅ እንጂ ማንም የማንንም ድምፅ መስማት አይፈልግም፡፡ አንዳንዶቹ ሰዎች በሐራራ ሰዓት አታናግረኝ ይሉሃል፡፡ ስለሚወድህ እንዳያስቀይምህ አስቦ ነው፡፡ አንተ የማትቅም ከሆነ በዚህ ሰዓት ያለውን ድባብ ስትታዘብ የቃሚና የወጨጌ ልዩነት ግልጽ ይሆንልሃል፡፡

በከተማችን ስኬታማው ማኅበር የጫት ማኅበር ነው፡፡ ምክንያቱም ሰውን ታታሪ ሠራተኛ ከማድረግ ይልቅ ቃሚ ማድረግ እጅግ በጣም ቀላል ሥራ ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ ቡና  ቤቶች ማታ ማታ ያስጨፍራሉ፤ ጫት ሻጮች ሙሉ ቀን ያመረቅናሉ፡፡ እኛ ወጣቶችም ተጎልተን ወሬና ጫትን እንሰልቃለን፡፡ ሲመሽ ምርቃናችንን ለመስበር ከአረቄ እስከ ቢራ እንጋታለን፡፡ ከምርቃና በኋላ ኪሳችን ካልበረደው የስካር ማብረጃ ጉብል ይዘን እንጋደማለን፡፡ የሥራ ሳይሆን ለጫት፣ ለቢራና ለሴት የምናተርፍበትን የማጭበርበሪያ ሥልት በሌሊት ተነስተን እንነድፋለን፡፡ መልሰን ለአዲሱም ቀን የትናንትናውን ዕጣ ፈንታ ጀባ እንለዋለን፡፡  ስንፍናም ይቀጥላል፡፡ ትውልዱም በዚህ ተግባሩ ይቀጥላል፡፡ መንግሥትም ይህን አለማሁ ይላል፡፡ ማጭበርበርም፣ ሙስናም ዘመናዊ እየሆኑ ይደልባሉ፡፡ ዓይን ከማየት ጆሮም ከመስማት አይቦዝንም፡፡ ግን የመጨረሻው ጨረሻ መቼ ይሆን?

የአብዛኛዎቹ ከተማዎች ዋነኛ ደንበኞች ሾፌሮች ናቸው፡፡ ሾፌሮችም በየከተማው አንዳንድ ቅምጥ አላቸው፡፡ ለአንዷ ኦሞ፣ ለሌላዋ የጁቡቲ ፓስታና ለሌላዋ ኤሌክትሮኒክስ በማምጣት የሥጋቸውንም የሆዳቸውንም ጥም ይቆርጣሉ፡፡ በነገራችን ላይ ሾፌሮች 12 ዓመትና  13 ዓመት ልጅ ፍቅረኛ ይይዛሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ከህሊና ነፃ ናቸው፡፡ ደስ ባይልም እንኳን ቅሉ የሾፌሮችን ልጅ ደግሞ ሌላው ጩልሌ ‹‹አባቷ ሾፌር ነው እባክህ አይመጣም›› እያለ ዋጋዋን ስለሚሰጥለት የጁን ማገኘቱ አይቀርም፡፡ ብድር በምድር አይደል የሚባል? ግን ችግሩ ሁሉ ወደ ማኅበረሰባችን ይመጣና የሁላችንንም ቤት ያንኳኳል፡፡ ‹‹ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት›› እንዳሉት፡፡ የበረሃ ልጆች በፍጥነት አድገው በፍጥነት ያረጃሉ፡፡ የሰመረ ፍቅር ያላቸው ወጣቶችም በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከፍጥነት መንገድ ጋር አብዝተው የሚመሳሳሉትም በዚህ ነው፡፡ በፍጥነት ፍቅርን መቀያየር በፍጥነት ተጉዘህ መድረስ፡፡ በፍጥነት መዋደድ በፍጥነት ሌላ መልመድ፡፡

ይህን ስልህ መለየት ያለብህ የከተማውን ማኅበረሰብና በገጠር የሚኖረውን ሰው ነው፡፡ እስካሁን ሳወራ ፎቶ ላይ የምታያት የተዋጋ በሬ ቀንድ የሚመስል ጡቷ  የታደለች፣ በባህላዊ ልብስ ሰውነቷን አጋልጣ ሊፈርጥ የደረሰ ለስላሳ ፊት ያላት፣ ጥርሷ ከንጣቱ የተነሳ ሃጫ በረዶን የሚተች፣ ባገኘኋት ብለህ እንድትጓጓ የሚያደርግ ተክለ ሰውነት የተቸረች ወጣት እያሰብክ እንዳይሆን? ይቺን ወጣት እማ ሲያምርህ ይቀራል እንጂ አታገኛትም፡፡ ልታገኛት ብታስብ በራሱ ብዙ ዋጋ ያስከፍልሃል፡፡ ያወራሁህ ስለከተሜ ፍቅር ነበር፡፡

በአፋር ባህል ማፍቀርም ሆነ ማግባት የሚችለው የተፈቀደለት አካል ብቻ ነው፡፡ ያ ማለት ቤተ መንግሥትን ማየት ትችላለህ እንጂ እንደፈለግክ ወደ ውስጥ መግባት አትችልም አይደል? አዎ፡፡ ቤተ መንግሥትን እንደ ቅርስ ቦታዎች ሁሉ ትኬት ቆርጠህ መጎብኘት ትችላላሁ እንዴ? አትችልም፡፡ በቃ አንተም ያችን ጉብል ስለወደድካት አታገኛትም፡፡ አጠገቧ የሚያደርስብህም የለም፡፡ አሁን እየተግባባን ይመስለኛል፡፡ አዲስ ነገር የለውም ጥንትም ቢሆን ዛሬ ቤተ መንግሥት ለመግባት ስንት ውጣ ውረድ አለው፡፡ ጠባቂዎቹ፣ አማካሪዎቹ (እልፍኝ አስከልካዮቹ) ስንቱን አስፈቅደህ ከተሳካልህ ወደ ውስጥ ትዘልቃለህ፡፡ ካልሆነም ያው ባለጉዳይ ነህና ሳትሰለች ለማስፈቅድ ትጥራለህ፡፡  መርሳት የሌለብህ ነገር አንተ ለመግባት አብዝተህ ብትፈልግም የጉዳይህ ነገር ይወስነዋል፡፡ አይ ይኼ ጉዳይ እዚህ አይታይም ብሎ ተራ ጥበቃው ከመለሰህ በቃ ምኞትህን ሁሉ ውኃ በላው ማለት ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ አንዲት የገጠር የአፋር ኮረዳ አይተህ ብትቋምጥ አታገኛትም፡፡ አብዝተህ ብትፈልጋት፣ ሳትሰለች ብታስባት፣ በፍቅሯ ነሁልለህ ትቀራለህ እንጂ ላይሳካልህ ይችላል፡፡ ግን እንደ ቤተ መንግሥቱ ተስፋ አላስቆርጥህም፡፡ ደስ የሚለው ነገር ባታገኛትም፣ አብረሃት ለመኖር ባትታደልም፣ ብቻህን ልታፈቅራት ትችላለህ እስካልታወቀብህ ድረስ፡፡ ማንም አይከለክልህም፡፡ ብቻህን መቃጠል ካማረህ ማለቴ ነው፡፡

 እንዴነሽ አይባል ሰው በሰው መካከል

ሄጄ አይቻት መጣሁ ዓይን አይከለከል’ ይባል የለ፡፡ ከዚያ ባለፈ ቁምነገር ካሰብክ ከቤተ መንግሥት ጠባቂዎች በላይ አስፈሪና ተቆርቋሪ የጎሳዎቿ ወጣቶች ዓመድ ያደርጉሃል፡፡ ማነህ? ምንድን ነህ? ብቻ ሳይሆን በሕይወትህም ዋጋ ሊያስከፍልህ ይችላሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው በመጀመሪያ እሷን ለማናገር ድፍረቱ ካለህ ብቻ ነው፡፡ የቤተ መንግሥት ጠባቂዎች ለደኅንነታቸው ከሚያስቡት የበለጠ፣ የአፋር ጎሳዎችም ከጋብቻ የሚገኘው የማኅበራዊ ሕይወት ትስስርና ጥሪት አብዝተው ያስባሉ፡፡ እንዳትሸወድ ወዳጄ፡፡

እንግዲህ የአፋርን አዳ (ባህል) አለዚያም ሥርዓት ልንገርህ፡፡ አንድ ሰው ማግባት ከፈለገ ጥሎሽ ያካሄዳል፡፡ ብር ስላለኝ ማግባት እችላለሁ እንዳትል፡፡ ይህ ማለት እኮ ጉዳይ ስላለኝ ቤተ መንግሥት ልግባ እንደማለት ይቆጠራል፡፡ መጀመርያ  የማን ጎሳ እንደሆንክ ይጣራል፡፡ ለምሳሌ ለአንዱ ጎሳ አሥር ግመል ቢባል ራቅ ላለው ደግሞ 20 ግመል ይባላል፡፡ ጭራሽ ሲያቅነዘንዝህ ፎቶ ስታሰነሳ አለዚያም ለሥራ ጉዳይ መጥተህ  ከሆነ ፍቅር የያዘህ አለቀልህ፡፡ ሃይማኖትህና ማንነትህ ታውቆ የተወሰኑ የጎሳው አባላት ቢስማሙ እንኳን ከ30 እስከ 50 ግመል አምጣ ልትባል ትችላለህ፡፡ ሴት ልጅ ወልዶ መክበር ይሉሃል እንዲህ ነው፡፡ ምናልባት የፍቅር አምላክ አንጀታቸውን አራራልህ እንበልና 30 ግመል ቢደረግልህ እንኳ በቀላሉ 600,000 (ስድስት መቶ ሺሕ ብር) ለጥሎሽ ብቻ ያስፈልገሃል ማለት ነው፡፡ እንዴት ይህን ያህል ግመል እየሰጡ አፋሮች ይጋባሉ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል፡፡ እነዚህን ግመሎች የሚከፍለው አግቢው ሳይሆን ጎሳው ነው፡፡ የሚያገባው ሰው እንደ ሌሎቹ አንድ ግመል ይሆናል የሚደርስበት፡፡ ‹ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል› ብሎ መተረት ብቻ ሳይሆን መተጋገዝ በተግባር እንዲህ ነው፡፡

ታዲያ አንተ ሻይ አጋጭተህ የምትጠጣ ሰው፣ ማነው ይህን ሁሉ የሚሸፍንልህ? ‹‹Sharing is Happiness›› እያልክ ኑሮን በየግል ጠምዶ የሚያርስ ማኅበረሰብ ውስጥ ካለህ ማነው ያፈቀርካትን አፋር እንድታገባ ከጎንህ የሚቆመው?  አይደለም ይህን ሁሉ ሊሰጥህ ይቅርና የሚያበድርህም ዘመድ እንደማይኖርህ እገምታለሁ፡፡ አንተ ንፁህ አፍቃሪ ሆነህ ብታብድም ገንዘብ አውጥቶ የሚድርህ ይገኛል ብዬ አላስብም፡፡ ችግር የለም ያለህ አማራጭ እውነተኛ አፍቃሪ ከሆነክ ማበድ ነው፡፡ እበድ፡፡ ቤተሰቦችህም ብዙ ብር ስለማያስወጣ ፀበል ያፀብሉሃል፣ አለዚያም ወደ ሼሕ ከባሰም ጠንቋይ ጋ ይወስዱሃል፡፡ ሁሉም የየራሱን ሐሳብ ባንተ ላይ ሲሰነዝር አንተ አርፈህ በፍቅርህ ብገን፡፡ እኔ ግን ወዳጄ ስለሆንክ ልምከርህ እንደዚህ ከምትጎዳ አፋር ሆነህ እንደገና ተወለድ፡፡ ከዚያም የእሷ ‹አብሱማ› ከሆንክ ብታረጅም የሚነካብህ የለም፡፡ አንድ የሰባ ዓመት ሰው የአሥር ዓመት አብሱማ ልትኖረው ትችላለች፡፡ ዕድሉ ነው፡፡ ለእሷ ደግሞ ክፉ ዕጣዋ፡፡ አንተም የምትወዳት አርጅታ ትጠብቀሃለች፡፡ ከተመቸህ ይኼ ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ የምታፈቅረውን ከምታጣ ተስፋ መቆነን ይሻላል፡፡ በቃ እንደገና አፋር ሆነህ ከእሷ ጎሳ አብሱማዋ ሆነህ ተወለድ፡፡

በአብሱማ ሕግ ቆንጆም ሆነች ውሻ በጨው የማይበላት ማግባት ግዴታ ነበር፡፡ አሁን ግን በመርህ ደረጃ ተቀይሯል፡፡ ሰንብቼ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ሕግ ባህልን ፣ ወግን፣ ሥርዓትን የመቀየር አቅም እንደሌለው ነው፡፡ ሰዎች ሳያምኑበት ሕግን ሊያስከብሩ ፍርድም ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ባህላዊ ሥርዓቶች ግን ያለ ማንም አዛዥ እያንዳንዱን ሰው በህሊናው እንዲኖር ያደርጉታል፡፡ ከሕግ በላይ ማንም የለም የሚለውን ብሂል እዚህ ጋ በጎን ታልፈዋለህ፡፡ እናም ወዳጄ ለአንድ ሆድህ ከምትሰደድ ለፍቅር ብትሰደድ የትኛውንም ዓይነት ዋጋ ብትከፍል ይሻልሃል፡፡ ምናልባት አንዳንዱ ዳግመኛ የመወለድ ዕድል ቢገጠው አሜሪካዊና እስራኤላዊ አለዚያም ዓረብ ሆኖ መፈጠርን እንደሚመርጥ አትጠራጠር፡፡ አንተ የተሻልክ ስው ነህ ስለፍቅር  ዳግመኛ አፋር ሆነህ መወለድ ካሰኘህ፡፡ ምክንያቱም ‹ኢትዮጵያ ከመወለድ አሜሪካ ችግኝ መሆን ይሻላል› የሚል ሰው ሞልቷል እኮ፡፡ አስበው እስኪ የአሜሪካ ችግኝ የቱ ደስታ ኖሮት ነው? መንፈቁን በበረዶ መንሰፍሰፍ መንፈቁን በሙቀት መቃጠሉ እንዳይሆን፡፡ በየጊዜው በመቀስ መቆረጥ … እስኪ የቱ ነው የአሜሪካ ችግኝ ደስታ፡፡ ሰው ሆኖ የመወለድ ክብር የማያውቁ ተናጋሪዎች መሆናቸውን በዚህ ትረዳለህ፡፡ አንተ ጎበዝ ስለሆንክ አስቀድሜ ልምከርህ፡፡ አፋር ስደትን አጥብቆ ይጠላል፡፡ የመሰደድም ህልም ፈጽሞ የለውም፡፡ ኑሮትም አያውቅም፡፡ አገሩንም የሚክድ አብዝቶ ይንቃል፡፡ አንተንም ካገኘህ ‹‹ይ ባሮ›› በማለት በጓሮ በቀየህ እንድትመካ የአገር መውደድን ሀ ሁ በመጀመርያ ያስቆጥርሃል፡፡ ለነገሩ አፋር ሆነህ ልትወለድ አይደል? አብሮህ የአገር ፍቅር ስለሚወለድ ችግር የለውም፡፡

ሁሌ የሚገርመኝ ነገር ይህ ነው፡፡ በአፋር መንገድ ዳር የሚገኙ ሕዝቦች ስደተኛ አሳፍረው የሚሄዱ መኪኖችን ጭምር ውኃ ይለምናሉ፡፡ የከባድ መኪና ሾፌሮችም ለእነሱ ብለው ገዝተው ውኃ ሲሰጧቸውም አይቻለሁ፡፡ ነገር ግን ለመሰደድ የሚያስብ የአፋር ወጣት በባትሪ ፈልገህ አታገኝም፡፡ ተገረም፡፡ ኧረ በደንብ ተገረም፡፡ ዓይን ከማየት ጆሮም ከመስማት አይቦዝንም፡፡  ምን የመሰለ ለም ቦታና ለምለም አገር ትተው የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠር ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረቅ ቦታ በዚህ አቧራ ላይ የሚኖረው  የአፋር ሕዝብ ወደየትም አይሰደድም፡፡ ምክንያቱም አፋሮች ሁሌም ከአፋቸው የማትለይ አንዲት ቃል አላቸው ‹‹ይ ባሮ›› (ቀዬየ) አገሬ ይላሉ፡፡ ይህቺ ቃል ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› እንደምትለው መፈክር የአገር ፍቅርን ሰርክ የምትቆሰቁስ ቃል ብቻ ሳትሆን ሰደድ እሳትም ጭምር ነች፡፡ ነገር ግን የሚጠጣው ውኃ የለውም፣ አማርጦ የሚመገበው ምግብ የለውም፣ አማርጦ የሚለብሰውም የለውም፡፡ ብዙ የሌለው ነገር አለ፡፡ ነገር ግን  ማንኛውም የአፋር ሕፃን ልጅ በአገሩ ይኮራል፡፡ አገሬ ምን ሠራችልኝ? ሳይሆን የሚለው ‹‹ይ ባሮ›› ነው፡፡ ዘወትር ቆሜ ባጨብጭበለት የማይቆይጨኝ ሕዝብ እዚህ አለ፡፡

ከመሥሪያ ቤት ቦዘኔ ኃላፊው ሲያባርረው አገሩን የሚሳደበው፣ ለማጭበርበር ሳይመቸው ሲቀር ፍትሕ የለም የሚለው ሁሉ አገሩን በአደባባይ ይሳደባል፡፡ እሺ ይኼስ ይሁን ብትል ሕግን ተገን አድርጎ የአገሪቷን ሀብት የሚሞጨሙጨው፣ በሥልጣን ሰበብ ከጨረታ እስከ አበል ብር የሚያግበሰብሰው ሁሉ፣ ከአስመጪና ላኪ እስከ አከፋፋይ አንዴ በማኅበር አንዴ በኢቨስትመንት ስም ያለቀረጥ ገንዘብ የሚጓፍፈው ሳይቀር ‹‹አገሬ (ቀዬየ)›› ሲል አይደመጥም፡፡ እንዲያውም ብሩን ሁሉ እያሸሸ ውጭ አገር ባሉ ባንኮች ያስቀምጣሉ ሲባል እሰማለሁ፡፡ አገር ማለት ምን ማለት ነው?፡፡ ሲመቸን የምናመሰግናት ሲጎድልብን የምናንቋሽሻት ናት እንዴ? መቼም አንተ ከኔ የተሻለ ታውቃለህ፡፡ ካልዋሸኸኝ አንተ ወዳጄ ‹‹ይቺ መርፌ የማትሠራ አገር፣ የማያልፍላት ደሃ…›› በማለት አገሩን የሚንቅና የሚሳደብ እስካሁን አልገጠመህም? አንተም ራስህ ብለህ ከሆነም አትደብቀኝ፡፡ እኔ አይገርመኝም፡፡ እንኳን አንተ በምቾት የሚኖሩ ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ስንት የሀብታምና የባለሥልጣናት ልጆች እንኳን አሉ፡፡ ልጆቻቸው ዜግነት እንዲያገኙ በሚፈልጉት አገር ሄደው ይወልዷቸዋል፡፡ እንግዲህ አስበው ኢትዮጵያ የመሆንን ትርጉም ያልተገለጠላቸው ባለሥልጣኖችንም ጭምር ተሸክመናል፡፡ ነገር ግን ናና ተመልከት፣ ወደ አፋር መጥተህ ታዘብ፡፡  አቧራ ለብሶ አባራ ላይ እየተኛ ‹‹ይ ባሮ›› አገሬ (ቀዬየ) የሚል ሕዝብ ታገኛለህ፡፡

በነገራችን ላይ አፋር ቢፈልግ መሰደድ ሳያስፈልገው ያለ ምንም መታወቂያ በሦስት አገሮች ውስጥ መኖር ይችላል፡፡ በጂቡቲ፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ እንደፈለገ ቢዘዋወር ፓስፖርት አያስፈልገውም፡፡ ሌላው ሕዝብ በየመን ለመሰደድ ስንት ብር አውጥቶ የሚጓዝባትን አገር አፋር ያለ ማንም ከልካይ በእግሩ በጂቡቲ አድርጎ በቀላሉ ይሻገራል፡፡ ግን አፋር አይሰደድም፡፡ አፋር የማይሰደደው ሀብታም ሆኖ ሳይሆን ሌላው ኢትዮጵያዊ ያጣውን ‹‹ይ ባሮ›› የኔ አገር ማለትን  ከማንቱ ውስጥ ቀብሮ ስላስቀመጣት ብቻ ነው፡፡ ‹‹አክሊልህን ማንም እንዳይወስድብህ ያለህን አጥበቀህ ያዝ›› ያለው የራዕይ ጸሐፊም ማንነት የሰው ልጅ የማይናወጥ መሠረት ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት አለመስለጠን ሊሆን ይችላል ብለህ ካሰብክ ‹‹ከፊተኛዋ ስህተት ይልቅ የኋለኛዋ ስህተት ትብሳለች›› ማለት አሁን ነው፡፡ ለነገሩ ስደቱ እኮ በአካል ብቻ አይደለም በመንፈስም ጭምር እንጂ፡፡  ሞልቃቃ ልጆቻችን እንደ መንግሥተ ሰማይ መግቢያ  ትኬት የፈረንጅ አፍን  ሲቆጥሩ እያየን አለማስቆማችን ቦታ ጊዜ ቢገጥመን ሁላችንም ለመሰደድ ዝግጁ እንደሆን ሥራችን ይመሰክርብናል፡፡ ይገርመኛል ተሠልጥኖ ተሙቷል፡፡ ‹‹የሰው ወርቅ አያደምቅ›› ሲሉ ነበር የምንሰማው ዛሬ ደግሞ ዓይናችን ሁሉ አሻግሮ ተመልካች ሆነ፡፡ አንበሳ ጫማን እንኳ የኢትዮጵያ ምርት ነው ስትለው ትቶህ የሚሄድ ስንት ሰው አለ፡፡ አንበሳ ጫማ እኮ ወይ እግርህ አድጎ አለዚያም ሰልችቶህ እንጂ የምትጥለው እንደ ቻይና ዕቃ በሳምንቱ ተቀርድዶ አይደለም፡፡ ይሁን ግዴለም እውነቱን ከተነጋገርን እንግሊዝኛና አፋርኛ አገልግሎታቸው ምንድነው? መግባቢያ፡፡ በቃ አለቀ፡፡ የሰው ውድቀት የሚጀምረው ራሱን መናቅ የጀመረ ቀን ነው፡፡ ሰውረነ፡፡

ለሕፃን ልጆቻችን ስንት የማይጠቅም የፈረንጅ ተረት ከመንገር በማንነታቸው እንዲኮሩ አድርገን ለምን አናሳድጋቸውም? እስኪ የትኛው የከተማ ልጅ ነው እንቆቅልሽ የሚረዳ? ገበጣ የሚጫወት? እንካ ሰላንቲያ የሚያውቅ? ዕቃ ዕቃ፣  ወዘተ… የሚጫወት? ሁሉ ነገር እኮ በፍጥነት ተቀይሯል፡፡ ዛሬ እኮ የገጠር ጎረምሳዎች እንኳ ከንፈር ወዳጅ፣ ሳዱላና ጉብል የሚሉት ቃላትን የፋራ አድርገዋቸው ‹‹ቺክ እንጀንጅን›› ማለት ጀምረዋል፡፡ አፋር ግን ለማንም ነጫጭባ ባህል ሲያጎበድድ አታየውም፡፡ ይህ ዳጎስ ያለ ያልተሸረሸረ ማንነት ውጤት ነው፡፡ የማይሰደደውና የማይለምነው ችግሩን በቀበቶው በጠፍር ጠፍንጎ የሚኖረውም፣ ሴተኛ አዳሪ አፋር የማታገኘውም ለዚህ ነው፡፡

በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ታቅፎ መሰደድ የድህነት ነው? ብዙ ሺሕ ብር አጭቆ ቀየውን ትቶ የሚወጣ ገበሬ ድህነት አማሮት ነው? ለሰፈራ እንኳን ከአንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ወደሌላው አገር አልሄድም ብሎ የሚያስቸግር በቀየው ፍቅር የሚንገበገብ ትውልድ ቅሪት የት ገባ? እንጃ፡፡ እንዲህ ቢሆንስ? ስግብግብነት ሲደመር፣ አገርን ያለ መውደድ ሲደመር፣ የሕዝብ ፍቅር የሌላቸው አስተዳዳሪዎች እኩል ይሆናል ሕገወጥ ስደት ለማለት አያስደፍረን ይሆን? ድህነት የሌለበት አገር አለ እንዴ? የለም፡፡ የማይወለድ ምኞት በውስጣችን ተዘርግቷል ይመስለኛል፡፡

ብዙ ጊዜ የምሰማት አንዲት መፈክር አለች፡፡ ኢትዮጵያ እያደገች ከሆነ ለምን ሰው ይሰደዳል? አፋር ኢትዮጵያዊ አይደለም እንዴ? ችግር የለም ነገሩን ቀለል አድርገን እንየው፡፡ ቻይና በዕድገት አሜሪካን በመቅደም ላይ ያለች አገር ነች፡፡ አብዛኛዎቹ ቻይናዎች ግን አሜሪካዊና አውሮፓዊ እንደመሆን የሚያስደስታቸው ነገር የለም ይባላል፡፡ ለእኛ ሁሉም ፈረንጅ እንላቸዋለን፡፡ ለቻይናዎች ደግሞ ፈረንጅ ማለት አሜሪካዊና አውሮፓዊ ነው፡፡ የቻይና ሕዝብ በየቀኑ ወደነዚህ አገሮች እንደሚሰደድ የተገለጠ ዓለም አቀፋዊ ሀቅ ነው፡፡ ቻይናውያን ታዲያ አገራቸው እያደገች መሆኗን ስላልሰሙ ይሆን? የአሜሪካ ቢሆንም የሥራ አጥ ቁጥሯ በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ ወዳጄ ከሰው በታች ሆኖ  ነጭ እየተፋበት ባጠራቀመው ብር ከመጠጥ እስከ ቆንጃጅቶች ሲያሳሳድድ፣ ብሩን ሲነዛ ስታየው የወጣ ሁሉ የሚደላው እንዳይመስለህ፡፡ ያየኸው ሰው በራሱ የደላው አይደለም የጨነቀው እንጂ፡፡ አሜሪካ ልውሰድሽ ብሎ ከሰው ፍቅረኛ ጋር የሚተኛ ጤነኛ ይመስልሃል እንዴ? በሰው አገር ደምህ የወፍ ደም ሆኖ ለዚህ ሞኝነትም አለመብቃት አለ፡፡ መታረድም፣ ከፎቅ መወርወርም  ካገሩ ለወጣ ሰው ብርቅ አይደለም፡፡ አካለ ጎደሎ ቢያደርጉህም ሰብዓዊ መብት ላንተ አይጠቅምህም፡፡ ነገር ግን ይኑርህም አይኑርህ እንደ አፋር ማሰብ ስትጀምር አትሰደድም፡፡ ኢትዮጵያዊ በመሆንህ አታፍርም፡፡ በትምህርትና በዕውቀት ደረጃህ አትሳቀቅም፡፡ ምክንያቱም በቃ አንተ አንተ ብቻ ነህና፡፡

እስኪ የሕዝብ ፍቅር የሌላቸው አስተዳዳሪዎች ማለት ምን ማለት እንደሆነ ላውራልህ፡፡ ለሕገወጥ የሰው ዝውውር ተጠያቂዎቹ ለእኔ ደላላዎች ሳይሆኑ አገር አስተዳደሪዎቹ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ወደ አፋር ስለሚመጡ ስደተኞች ብዙ ማውራት ባልፈልግም ትንሽ ልበል፡፡ ከትግራይ ስለሚመጡት፣ ከአማራ ስለሚመጡትና ከኦሮሚያ ስለሚመጡት ስደተኞች የመንግሥት ባለሥልጣናት ምንም የማያውቁ ከሆነ እጅግ ሚስጥር ስለሆነው ሽብርተኝነት እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? ወይስ ስደተኞች በአየር ላይ ይበራሉ? ቤተሰቡን ተሰናብቶ ለመሰደድ የወጣን ሰው መለየት ነው የሚከብደው? አገር ለማሸበር ታጥቆ ተዘጋጅቶ የሚንቀሳቀስን አካል ማደን? ለእኔ የሚያስቅ እውነት ነው፡፡ ሚስጥሩ ያለው ከሽብርተኞች የሚገኘው ጭንቅና እልቂት ስለሆነ የሚያዩ ዓይኖች ሁሉ ምሕረት የለሽ ናቸው፡፡ ከሕገወጥ ስደተኞች የሚገኘው ደጎስ ያለ ብር መሆኑ ደግሞ ምሕረት የለሽ ቡጨቃ ይመስለኛል፡፡ ከመንግሥትም ሆነ ከመንግሥት አስተዳዳሪዎች የተደበቀ ሚስጥር አለ ብዬ አላምንም፡፡ በመረጃ ቢሆንም አይደለም የሰውን የትንኝም አደረጃጀት ለማወቅ አያዳግትም፡፡ በዚህ ጊዜ ከመንግሥት የሚደበቅ ሚስጥር ይኖራል ብዬም አላስብም፡፡

በማስኮብለል ሥራ ከቪላ ቤት እስከ ከባድ መኪና የገዙ ባለሀብቶች ሞልተዋል፡፡ አይደለም የመንግሥት አካል ሊስትሮዎችን ብትጠይቅ እንትና ይህንን ቤት የሠራው እኮ በማስኮብለል ሥራ ነው ይሉሃል፡፡ ኮብላዮችም ለማን ምን ያህል እንደሚሰጡ ያውቃሉ፡፡ አንዱን ከስደት የተመለሰ ሰው ብትጠይቀው ለማን እንደሰጠና ማን እንዳጭበረበረው አብጠርጥሮ ይነግርሃል፡፡ ዋናው ነገር ብዙ ድሮች ይበጠሳሉ፡፡ ለነገሩ ብረት የሚያቀልጥ ምላስ ያላቸው ደላላዎችም አይደለም ተራ ባለሥልጣን ኦባማንም ቢያገኙት በወሬ ያሰምጡታል፡፡ በአንድ ጊዜ የዕድሜ ልኩን የማያገኘውን ከደሃ አደጉ የቀረጩሙትን ብር አስታቅፈው አፍን መዝጋት ተክነውበታል፡፡ ያም ሆነ ይህ ‹‹ለኔ እናት የጠቀማት የለም እኩሉ ድንጋይ እኩሉ አፈር ጫነባት አለች›› አሉ በእናቷ ሞት ያዘነች ወጣት፡፡ ስደት ይብቃ ካላችሁ ኑና አፋርን ጎብኙ፡፡ ምሳሌ የሚሆን ትውልድ በዚህ አለ፡፡ ካልሆነም ሕዝቡንም አገሩን ጥሎ ይኮበልላል፡፡ ኑሮም ይቀጥላል፡፡ እኛም ወሬያችንን እንቀጥላለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles