Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልየካም የ20 ዓመት ከዋክብት

  የካም የ20 ዓመት ከዋክብት

  ቀን:

  ‹‹ስውሩ እስረኛ››፣ ‹‹በራሪ ልቦች›› እና ‹‹ፍቅር ሲመነዘር›› ሰለሞን ቦጋለ ከተወነባቸው ፊልሞች ጥቂቱ ናቸው፡፡ ማህደር አሰፋ በቅርብ ከሠራቻቸው ፊልሞች ‹‹አማላዩ›› እና ‹‹ሼፉ›› ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱ ተዋንያን ካም ግሎባል ፒክቸርስ የክብር ሽልማት ካበረከተላቸው ስድስት ተዋንያን መካከል ናቸው፡፡ የተጠቀሱት ፊልሞች በካም ግሎባል ፒክቸርስ ከተዘጋጁና ፕሮዲስውስ ከተደረጉ ፊልሞች ይጠቀሳሉ፡፡ ድርጅቱ 20ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ በፊልሞቹ ላይ ልዩ ተሰጥኦ ላሳዩ ተዋንያን ሽልማት ሰጥቷል፡፡

  ድርጅቱ በ‹‹ወደ ገደለው›› ፊልም ላይ ለተወነው ኪሮስ ኃይለሥላሴም ሽልማት ሰጥቷል፡፡ አማኑኤል ሀብታሙ በ‹‹አማረኝ›› ፊልምና የትናየት ታምራት በ‹‹ፍቅር ሲመነዘር›› የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

  ካም ግሎባል ፒክቸርስ ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ የነበረውን ጉዞ ለመዘከር ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋሽንግተን ሆቴል ባዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ ተዋንያኑ ‹‹የካም የምንጊዜም ምርጥ ተዋንያን›› ተብለዋል፡፡

  ‹‹በፊልም ዘርፍ ብዙም አልሠራሁም፤ ላለፉት 31 ዓመታት በኪነ ጥበብ ለአገር፣ ለሕዝብና ለመንግሥት አገልግያለሁ፡፡ ከወርኃዊ ደሞዜ ባለፈ ግን ምንም አልተደረገልኝም፡፡ አንድ ፊልም ሠርቼ በካም መሸለሜ ለልጆቼ ቅርስና መታሰቢያ ይሆናል፡፡ ሽልማቱ ከገንዘብና ከሹመት በላይ ነው፤›› በማለት ነበር ኪሮስ ስሜቱን የገለጸው፡፡ ኪሮስ የካም ግሎባል ፒክቸርስ ማኔጅንግ ዳይሬክተር የሆነውን ኪሩቤል ተስፋዬን አባት ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ ቀድሞ በአቶ ተስፋዬ አማካይነት ሲኒማ ዓድዋ ውስጥ ፊልም የሚመለከቱበትን ዘመንም በትውስታ አውስቷል፡፡

  ሰለሞን በበኩሉ መሰል ሽልማቶች በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ላይ አደራ ይጥላሉ ብሏል፡፡ ‹‹ሽልማቶች የተሻለ እንድንሠራ ያነቃቃሉ፤ ያበረታታሉ፤›› በማለት ገልጿል፡፡ በ‹‹ፍቅር ሲመነዘር›› ላይ ከሰለሞን ጋር የምትተውነት የትናየት ‹‹በመሸለሜ ክብርና ኩራት ተሰምቶኛል፤›› ብላለች፡፡

  ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ኪሩቤል ድርጅቱ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ የላቀ አስተዋጽኦ ያደረጉ ተዋንያን ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጣቸው ተናግሯል፡፡ ‹‹በአተዋወን ብቃታቸው በተመሰገኑና ከምንም በላይ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚወጡ ውድ የአገራችን ባለሙያዎች የጋራ ጥረት አሁን ያለንበት ደረጃ ደርሰናል፤›› ብሏል፡፡

  ኪሩቤል ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በድርጅቱ በሚሠሩ ፊልሞች ላይ የሚሳተፉ ተዋንያንን ለማበረታታትና ምስጋና ለማቅረብ ሽልማቱ ተዘጋጅቷል፡፡ በቀጣይ ከተዋንያን በተጨማሪ በካሜራ፣ በድምፅና በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ባሙያዎችን እንደሚሸልሙ አስታውቋል፡፡

  ድርጅቱ በተለይ ከ1983 እስከ 1997 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በደብረ ብርሃንና በሐረር ከ2,000 በላይ ተማሪዎችን በቪዲዮግራፊና በፎቶግራፍ ማሠልጠኑን በመጥቀስ፣ ለሲኒማው የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ይናገራል፡፡

  በተደጋጋሚ ከሚስተዋሉ የአስቂኝ የፍቅር ፊልሞች በተለየ ድራማና የወንጀል ፊልሞችን በመሥራት የዘውግ ልዩነት እንደፈጠሩ ያምናል፡፡ በ2000 ዓ.ም. የተሠራውን ‹‹በራሪ ልቦች›› እና በ2005 ዓ.ም. ለዕይታ የበቃውን ‹‹ወደበገደለው›› ፊልምን ጠቅሷል፡፡ ‹‹ወደ ገደለው›› ከታዋቂዋ የወንጀል ጽሑፎች ደራሲ አጋታ ክርስቲ የተወረሰ የትርጉም ሥራ ነው፡፡

  ከካም ግሎባል ፒክቸርስ ጋር በጥምረት ከሠሩ ባለሙያዎች በተጨማሪ በሲኒማው ላሉ ሌሎች ሙያተኞች ሽልማት የመስጠት ዕቅድ እንዳላቸው ኪሩቤልን ጠይቀነው ነበር፡፡ እሱ እንደሚለው፣ የድርጅቱ ቀዳሚ ትኩረት ከነሱ ጋር በጥምረት የሚሠሩትን ባለሙያዎች ማበረታታት ነው፡፡ ባለሙያዎችን አወዳድሮ ሽልማት የመስጠት ኃላፊነት የፊልም ማኅበራትና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንደሆነ ገልጿል፡፡

  በ2004 ዓ.ም. ‹‹ሼፉ›› የተሰኘ ፊልም ያዘጋጀው ድርጅቱ ቁጥር ሁለቱን ሼፉ ፊልም ሰኔ 1 ቀን ተመርቆ በተለያዩ ሲኒማ ቤቶች ይታያል፡፡ ፊልሙ አራት ተከታይ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በየሁለት ዓመቱ ለዕይታ ይበቃሉ፡፡ ኪሩቤል ለሪፖርተር እንደገለጸው በ‹‹ሼፉ›› ተከታታይ ፊልሞች ላይ ከሚተውኑ ተዋንያን መካከል የተመረጡት ህንድ አገር የሚገኘው አኩስቲክ ዲጂ ዲዛይን ትምህርት ቤት እየላከ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡

  ህንድ የሚገኘው የድርጅቱ አጋር ትምህርት ቤት የተማሪዎቹን ግማሽ ወጪ ይሸፍናል፤ ቀሪው በካም ግሎባል ፒክቸርስ ይሸፈናል፡፡ የትምህርት ዕድሉን የሚሰጡት በፊልሞቹ ከሚተውኑት መካከል የላቀ ብቃት ላላቸው እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ‹‹ልምድ ካላቸው አገሮች ተሞክሮ መማር አለብን፤ ትምህርቱ ለዕውቀት ሽግግር እንዲሁም ለባህል ልውውጥ መንገድ ይከፍታል፤›› ሲል ገልጿል፡፡

  ከዚህ ቀደም ሲኒማቶግራፈር ኢብራሒም ካሳ የሦስት ወር ሥልጠና እንዲወስድ ወደ ትምህርት ቤቱ እንደተላከና ቀጣዩ ተማሪ ከ‹‹ሼፉ›› ሁለት እንደሚመረጥ ጠቁሟል፡፡ ‹‹ሼፉ›› ሁለት የተጻፈው በቢንያም ወርቁ ሲሆን፣ አዘጋጁና ፕሮዲውሰሩ ኪሩቤል ነው፡፡ በፊልሙ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ደሳለኝ ኃይሉ፣ የትናየት ታምራትና ሌሎችም ተውነዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...