በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በአርባ ምንጭ የዶርዜ ማኅበረሰብ አባላት የጣሊያን መንግሥት ለዋርካ ፕሮጀክት ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ የንፁህ ውኃ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ዋርካ የውኃ ማማ ፕሮጀክት ተራራማና መደበኛ የቧንቧ መስመሮች ሊዘረጉ በማይችሉባቸው ሥፍራዎች አዋጭ የንፁህ ውኃ አቅርቦትን የሚያመቻች ነው፡፡ በመሆኑም በክልሉ የሚገኙት የዶርዜ ማኅበረሰብ አባላት ከፕሮጀክቱ ተቋድሰዋል፡፡ ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. የዋርካ ውኃ ማማ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሪታ እንዲሁም በጣሊያን የትብብር ቢሮ የሰብአዊ ድጋፍ ፕሮግራም አስተባባሪ አሊሳንድራ ቴስቶኒ በተገኙበት ተመርቋል፡፡ የጣሊያን ኤምባሲ በላከው መግለጫ እንደተመለከተው፣ የተሠራው የዋርካ ውኃ ፕሮጀክት ለዶርዜ መንደር ነዋሪዎች የተሰጠ ሲሆን፣ እነሱው የሚያስተዳድሩትም ይሆናል፡፡ ፎቶግራፎቹ አምባሳደሩ ባህላዊ ልብስ ሲበረከትላቸውና የውኃ ማማውን ያሳያሉ፡፡