Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ደይረመዳ›› - የኢትዮጵያ ‹‹የቅርብ ዘመድ››

‹‹ደይረመዳ›› – የኢትዮጵያ ‹‹የቅርብ ዘመድ››

ቀን:

ከቀናት በፊት ‹‹አውስትራሎፒቲከስ ደይረመዳ›› (Australopithecus Deyiremeta) ብለው ጉግል ቢያደርጉ ተዛማጅ መረጃ እንደሌለ ድረ ገጹ ይገልጽልዎታል፡፡ ሳይንሳዊ መረጃ በሚሰጡ መጻሕፍትም አንዳች መልስ አይገኝም ነበር፡፡ ከግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 በኋላ ግን የዓለም ዕውቅ መገናኛ ብዙኃን ቀዳሚ ዜና ሆኗል፡፡ ‹‹ኔቸር›› የሚባለውን ዓለም አቀፍ የሳይንስ መጽሔትን ጨምሮ በበርካታ የዜና ማሠራጫዎች የሰሞኑ ትኩስ ወሬ የአውስትራሎፒቲከስ ደይረመዳ ግኝት ነው፡፡

አውስትራሎፒቲከስ ደይረመዳ በአፋር ክልል፣ ሚሌ ወረዳ ቡርተሌና ዋይታሌይታ በመባል በሚታወቁ አካባቢዎች በቅርቡ ለተገኙ ቅሪተ አካሎች የተሰጠ መጠሪያ ነው፡፡ ቅሪተ አካላቱ ሁለት የላይኛው መንጋጋና ሁለት የታችኛው መንጋጋ ናቸው፡፡ ከ3.3 – 3.5 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ አላቸው፡፡

ግኝቱ በተመሳሳይ ዘመን በአካባቢው ይኖር ከነበረው የአውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ማለትም የሉሲ (ድንቅነሽ) ዝርያ በጥርሶቹ መጠንና በመንጋጋዎቹ ቅርፅ የተለየ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም መሰል መረጃ ስላልተገኘ ቅሪተ አካሎቹ በአዲስ የቅድመ ሰው ዝርያ ተመድበዋል፡፡

አዲሱ ግኝት ኢትዮጵያ የቅድመ ሰው ዘር መገኛነቷን ዳግም አስተጋብቷል፡፡ የዘርፉ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችም እንደቀድሞው ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ አዙረዋል፡፡ የሰው ዘር መገኛ፣ የሥልጣኔ መነሻ በመባል ለምትሞካሸው ኢትዮጵያ ታላቅ ግኝት ነው፡፡ ቅሪተ አካሉ የተገኘበት የአፋር ክልል ነዋሪዎች ለግኝቱ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት ግኝቱ የአፋርኛ ስያሜ አግኝቷል፡፡ በአፋርኛ ‹‹ደይ›› ቅርብ ማለት ሲሆን፣ ‹‹ረመዳ›› ደግሞ ዘመድ ማለት ነው፡፡

‹‹ቅርብ ዘመድ›› የሚለው ሐረግ አዲሱ የቅድመ ሰው ዝርያ በነበረበት ወቅት ከኖሩ ሌሎች የቅድመ ሰው ዝርያዎች የበለጠ የቀረበ ወይም ለሰው የቅርብ ዘመድ መሆኑን አንደሚያመላክት በአሜሪካ የሚገኘው የክሊቭላንድ የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዚየም ኩሬተር ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ ይናገራሉ፡፡ ቅሪተ አካሉን ያገኘው የጥናት ቡድን መሪ ናቸው፡፡

የቡድኑ ግኝት በመጀመሪያ ይፋ የተደረገው ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ኢትዮጵያ ለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ነው፡፡ በዛው ዕለት ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት በኋላ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተለቋል፡፡ ግንቦት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ደግሞ በኔቸር መጽሔት ቀርቧል፡፡

አጥኚዎቹ የወራንሶ ሚሌ የቅድመ ታሪክ ጥናት ፕሮጀክት በሚል በአፋር ክልል ምርምር ከጀመሩ ዓመታት ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ቅሪተ አካሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ ቀደም ከተገኙ ዝርያዎች በተጨማሪ ሌሎችም ዝርያዎች እንዳሉ እንደሚያመላክት ዶ/ር ዮሐንስ ይናገራሉ፡፡ በአፍሪካ እንዲሁም በተቀረው ዓለም መሰል ግኝት እንዳልተመዘገበና አውስትራሎፒቲከስ ደይረመዳ በሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ዶክተሩ ያስረዳሉ፡፡

የላይኛው መንጋጋ የተገኘው የካቲት 25 ቀን 2003 ዓ.ም. የፕሮጀክቱ ተሳታፊ በሆነ መሀመድ ባሮ የተባለ የአፋር ተወላጅ ነው፡፡ ሁለት የታችኛው መንጋጋ ቅሪቶች የፕሮጀክቱ ተባባሪ በሆነው ዓለማየሁ አስፋው የካቲት 25 እና 26 ላይ ተገኝተዋል፡፡

የጥናት ቡድኑ የተዋቀረው ከኢትዮጵያ፣ ከአሜሪካ፣ ከፈረንሳይ፣ ከስፔንና ከስዊድን በተውጣጡ የሥነ ምድርና የፖሊዮአንቶሎጂ ሳይንቲስቶች ነው፡፡ ቡድኑ ኢትዮጵያውያንና አሜሪካውያን ተማሪዎችን በመስክና በላቦራቶሪ ሥራ ያሳትፋል፡፡ ጥናቶቹ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በሚሰጥ ፈቃድ ይካሄዳሉ፡፡ ለዚህ ግኝት ጥናት የገንዘብ ድጋፍ ካደረጉ ተቋማት መካከል ናሽናል ሳይንስ ፋውንዴሽን፣ ሊኪ ፋውንዴሽን፣ ናሽናል ጂኦግራፊክ ሶሳይቲና ዌነር-ግሬን ፋውንዴሽን ይጠቀሳሉ፡፡

እንደ ዶ/ር ዮሐንስ ገለጻ፣ ከአውስትራሎፒቲከስ ደይረመዳ በፊት እ.ኤ.አ. በ2009 በአፋር ክልል ሚሌ ወረዳ በዞን አንድ በሚገኘው ቡርተሌ አካባቢ 3.4 ሚሊዮን ዓመት ያስቆጠረ ከፊል የእግር ቅሪተ አካል አግኝተዋል፡፡ ቅሪተ አካሉ ሉሲ ከምትገኝበት የአውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ዝርያ ጋር በሚቀራረብ አካባቢ የተገኘ እንዲሁም በቅርጽ ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም ከአውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ የተለየ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ቅሪተ አካሉ ከተገኘ በኋላ ጥናትና ምርምሩን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ አዳዲሶቹ ቅሪተ አካሎች የተገኙባቸው ሁለት የአፋር ክልል አካባቢዎች መካከለኛው የአፋር ክልል ቡርተሌና ሉሲ ከተገኘችበት በስተደቡብ የሚገኘው ዋይታሌይታ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምድር ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ሙሉጌታ አለነን በማጠቀስ የቅሪተ አካላቱ ዕድሜ እንዴት እንደተለካ ዶ/ር ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ ቅሪተ አካላቱ ከተገኙበት የአለት ንብብሮች የተሰበሰቡ ናሙናዎች በዕድሜ መለኪያ መሣሪያ ተፈትሸው የተገኘው ውጤት ከሌሎች ሥነ ምድራዊ መረጃዎች ጋር ተደማምሮ የቅሪተ አካሎቹን ዕድሜ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዶክተሩ እንደተናገሩት፣ የአውስትራሎፒቲከስ ደይረመዳ መገኘት አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ብቸኛ የሰው መገኛ ዝርያ አለመሆኑን ያመላክታል፡፡ ግኝቱ በተመሳሳይ ዘመን ተቀራራቢ ስፍራ የኖሩ ቢያንስ ሁለት ወይም ሦስት ዝርያዎች እንደነበሩ ያሳያል፡፡ የሉሲ ዝርያ አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ከ2.9 ሚሊዮን 3.8 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የኖረ ሲሆን፣ ከአውስትራሎፒቲከስ ደይረመዳ ጋር ዘመኑን ይጋራሉ፡፡

የዘርፉ ተመራማሪዎች ከ3-4 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በአንድ ወቅት አንድ የቅድመ ሰው ዝርያ ብቻ እንደሚኖር ያምኑ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ከአንድ ዝርያ በላይ ሊኖር እንደማይችልም ይገለፅ ነበር፡፡ እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ የተገኙ ቅሪተ አካሎችም ይህን መላምት የሚያጠናክሩ ነበሩ፡፡ ከሉሲ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የኖሩት የቻዱ አውስትራሎፒቲከስ ባህሬልጋዛሊና የኬንያው ኬንያንትሮፐስ ፕላትዮፕስ ግኝቶች ግን ጥያቄ አስነስተዋል፡፡ ዶ/ር ዮሐንስ እንደሚናገሩት፣ ‹‹ከአዲሱ ቅሪተ አካል በፊት የተገኘው ከፊል የእግር ቅሪተ አካል በአንድ ወቅት ሁለት ዝርያዎች መኖር እንደሚችሉ ያሳየ ነው፡፡ ከዚህ በላይ አውስትራሎፒቲከስ ደይረመዳ እውነታውን ያረጋገጠ ግኝት ነው፡፡››

ዶ/ር ዮሐንስ ግኝቱ ለዘርፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዲኖረው ያስቻሉትን ምክንያቶች ዘርዝረዋል፡፡ የመጀመርያው የተለያዩ ዝርያዎች በተመሳሳይ ወቅት መኖራቸውን በማሳየት በተመራማሪዎች ዘንድ የነበረውን ብዥታ ማጥራቱ ነው፡፡

ሌላው እስከቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች ከሚያመላክቱት በተቃራኒው ከአንድ በላይ ዝርያዎች በተመሳሳይ አካባቢ መኖራቸውን ማሳየቱ ነው፡፡ አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስና አውስትራሎፒቲከስ ደይረመዳ በተመሳሳይ ዘመን በኖሩበት ወቅት የነበረው አኗኗር፣ አመጋገብና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በቀጣይ ይጠናሉ ብለዋል፡፡

ግኝቱ በቱሪዝም ዘርፍም አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዘርፉ ባሏት ሀብቶች በአግባቡ አለመጠቀሟን ያስረዳሉ፡፡ ዶክተሩ እንደሚሉት፣ የቅድመ ታሪክ ቦታዎች ለቱሪዝም አመቺ ሆነው አይገኙም፡፡ ግኝቱ መንገድ፣ ሆቴልና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉና የቅድመ ታሪክ ሥራዎች ቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጠው ያደርጋል፡፡ ‹‹ግኝቱ ከሳይንሱ በተጨማሪ የአገሪቱን አዎንታዊ ገፅታ በመገንባት ረገድ ይጠቅማል፡፡ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች ሲባል አገሪቱን ለመጎብኘት የሚጓጉ ቱሪስቶች ቁጥርም ይጨምራል፤›› ብለዋል፡፡

በግኝቱ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር ስለ ሰው ዘር አመጣጥ መረጃ የሚሰጡና የጥናት ክፍተቶችን የሚሞሉ በርካታ ቅሪተ አካሎች በኢትዮጵያ መገኘታቸውን በማጣቀስ ‹‹እነዚህ ግኝቶች የሰው ዘር ምንጭነታችንን የሚመሰክሩ ብቻ ሳይሆን ለአገራችን የቱሪስት ፍሰት መጨመር ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ‹‹በየዓመቱ በርካታ ተመራማሪዎች ጥናት ያካሂዳሉ፤ በቅርብ የተገኙት ቅሪተ አካሎች የሰው ዘር መነሻ የትና መቼ ነው የሚለውን እንቆቅልሽ ለመፍታትና የዘመናት የመረጃ ክፍተትን በመጠኑም ቢሆን ለመሙላት የሚያስችሉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የሚያደርጓትንና በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡትን አሥር ቅርሶች ሚኒስትሩ ጠቅሰው፣ ተጨማሪ አምስት ቅርሶችን ለማስመዝገብ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ፣ ለተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተልኮ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህም በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከታቀዱ ቅርሶች ቁጥር አንጻር ጥሩ ውጤት እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታም ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹አገራችን የዘርፉን ተመራማሪዎች ቀልብ በእጅጉ በመሳብ በሰው ዘር አመጣጥ የጥናትና ምርምር ማዕከል ነች፤›› ያሉት አቶ ዮናስ፣ ዘርፉ የአገሪቱን የጥናትና ምርምር ቱሪዝም በማሳደግና የውጪ ምንዛሬ በማስገኘት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ይሆናል በማለት ያስረዳሉ፡፡

አቶ ዮናስ እንደሚናገሩት፣ በተለይ በዚህ ዓመት ይፋ የተደረጉ ቅሪተ አካሎች በታዋቂ ዓለም አቀፍ የሳይንስ መጽሔቶች የታተሙ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካም ስኬት ሆነዋል፡፡ ‹‹ግኝቱ የአገራችንን የሰው ዘር መገኛነት የበለጠ የሚያረጋግጥ ከመሆኑ ባሻገር ታላላቅና ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በአንድ አንደበት፣ በተመሳሳይ ሰዓት ስለአገራችን የቅድመ ታሪክ መነሻነትና የሰው ዘር መገኛነት እንዲያስተጋቡ የሚያደርግ ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡

ኢትዮጵያ በባህላዊና የተፈጥሮ ሀብቶች የተሞላች አገር ብትሆንም ቅርሶችን የማጥናት፣ የመንከባከብ፣ የመጠበቅና ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራዎች  አናሳ እንደሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘርፉ አበረታች ለውጥ እያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የሰሞኑ መወያያ አጀንዳ የሆነው ግኝት ከሳይንስ ድረ ገጾች በተጨማሪም በቢቢሲ፣ በሲኤንኤን፣ በኤኤፍፒ፣ በኤፒ፣ በሮይተርስና በሌሎችም ዜና ማሠራጫዎች ተዘግቧል፡፡ ብዙዎቹ ዘገባዎች የኔቸር መጽሔት ሐተታን የተመረኮዙ ናቸው፡፡ በኔቸር ማብራሪያ የሰጡት ፓሊዮአንቶሎጂ ባለሙያ ፍሬድ ስፑርን አዲሱ ዝርያና አውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ምግብ፣ መጠለያና መኖርያ የሚሻሙ ሳይሆን ጎን ለጎን ይኖሩ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

የዝርያዎቹ ጥርስ በቅርፅና በመጠን ልዩነት ያለው መሆኑ የተለያየ ምግብ እንደሚመገቡና ተፎካካሪ እንዳልነበሩ ያሳያል፡፡ ተመራማሪው ተጨማሪ መረጃዎች እስከሚገኙ ድረስ ስለአኗኗራቸው ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደማይቻልም አክለዋል፡፡ ግኝቱ የሰው ዘር መነሻ አውስትራሎፒቲከስ አፍረንሲስ ብቻ አለመሆኑን እንደሚጠቁምም ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ጥር ወር በመካከለኛው አዋሽ የተገኘው በዶ/ር ብርሃኔ አስፋውና ፕሮፌሰር ቲም ኃይት ይፋ የተደረገው ግኝት ከ160 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠሩ የሰውና እንስሳት ቅሪተ አካሎችና ቁሳቁሶችን ያካተተ ነበር፡፡ በሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ መረጃ ያልተገኘበትና ‹‹የጨለማ ዘመን›› በመባል ከሚጠራው ወቅት የተገኙት ቅሪቶች ለዘርፉ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በወቅቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...