Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትጊዜ ያላሻሻለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግና የሻምፒዮንነት ሚዛኑ

ጊዜ ያላሻሻለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግና የሻምፒዮንነት ሚዛኑ

ቀን:

–  የተጨዋቾች የዝውውር መመርያ ከሐምሌ 1 ጀምሮ ሥራ ላይ ይውላል

ፕሪሚየር ሊግ የሚለውን ስያሜ አግኝቶ ከተጀመረ 17ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርም በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ክብረሰወሰኑን ይዞ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ  ለ12ኛ ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ የአገሪቱ እግር ኳስ ተወዳዳሪነትና ተወዳጅነት እንዲሁም ደረጃውም ጭምር እየጨመረና እየተሻሻለ ሊሄድ ሲገባው፣ በአንፃሩ እየባሰበት ለጥቂት ጊዜ ብቅ ሲሉ የታዩ ተጨዋቾች ለብዙ ሲጠበቁ ድምፃቸው የሚጠፋበት መሆኑ በሌላ ወገን ማነጋገሩ አልቀረም፡፡

ደጋፊ ሳያጣ፣ ኳስ ወዳድ፣ በኳስ ፍቅር የማለለ ሕዝብ ሳይታጣ ለእግር ኳስ መሲህ የሚሆን ጠፍቶ የእግር ኳሱ ጉዞ የኤሊ ከሆነ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ የክለቦች የእርስ በርስ ሽኩቻ፣ ያረጁና ያፈጁ ተጨዋቾች የተለየ ችሎታና ክህሎት ሳያካብቱ የገንዘብ ቁልል ላይ ስማቸውን መትከል የእግር ኳሱ መለያም ከሆነ ቆይቷል፡፡ ክለቦችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ ሁሉም በየፊናቸው ሲራኮቱ፣ ተገቢውን የለውጥና የመዋቅር ማስተካከያ ማድረግ እየተሳናቸው ኳሱን ቁልቁል ወደ ታች የሚያንደረድሩ አካሎች ተጠያቂነት ስለሌለ ብቻ የፈለጉትን ሲሆኑበት ይስተዋላል፡፡

- Advertisement -

ይህም በመሆኑ የአገር ውስጥ ተጫዋቾች የቱንም ያህል የፊርማም ሆነ የወር ደመወዝ ክፍያ ከሌሎች ጥቅማጥቅሞች ጋር ቢመቻችላቸውም እግር ኳሱን ሊለውጡ፣ ደጋፈዎችን ሊያቋምጡ አልቻሉም፡፡ በዚህም የውጪ ተጨዋቾች የአገር ውስጥ ክለቦችን መቀላቀል ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ የአንድ ወቅት የሱናሚ ማዕበል ክፉኛ ያንቀጠቀጣት ሐይቲ ሳይቀር ተጨዋቾቿን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መላክ ጀምራለች፡፡ እነዚህንና የሌሎችም አገሮች ተጨዋቾች ከሚስተዋሉባቸው ክለቦች በአንድ ወቅት የአገሪቱ እግር ኳስ መዘውር፣ የወጣት ተጨዋቾች መፍለቂያ የነበረው ቀድሞ መብራት ኃይል የአሁኑ ኤሌክትሪክ ይጠቀሳል፡፡

የበርካታ ታዳጊ ወጣቶች መፍለቂያ የነበረው ኤሌክትሪክ ካለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ደረጃው ላለመውረድ ከሚጫወቱ ክለቦች አንዱና የመጀመሪያው መሆኑ አቶ ደበበ እንግዳወርቅ ይናገራሉ፡፡ ከ1958 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያየ ስያሜ ሲከናወን ዛሬ ላይ የደረሰውን የሊግ ውድድር እንደተመለከቱ የሚናገሩት አቶ ደበበ፣ እግር ኳሱ በጊዜ ሒደት ከመሻሻል ይልቅ እንዲያሽቆለቁል ካደረጉት ውስጥ የተጠያቂነት መጥፋትና የመዋቅር ችግሮችን በዋናነት ይጠቅሳሉ፡፡

17ኛ ዓመቱን እየደፈነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ ውድድሩ ሲጀመር በ1990 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ዋንጫ ያነሳው የቀድሞ መብራት ኃይል በአሁኑ ኤሌክትሪክ ነው፡፡ በ1991 እና 92 ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በ1993 ኤሌክትሪክ፣ በ1994 እና 95 ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በ1996 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በክለቦች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የተወሰኑ ክለቦች ከመደበኛው የሊግ ውድድር ውጪ በመሆናቸው ሐዋሳ ከነማ የዋንጫው ባለቤት ለመሆን በቅቷል፡፡ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑና በክለቦቹ መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት እልባት ካገኘ በኋላ፣ ከ2000 እስከ 2002 ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በ2003 ኢትዮጵያ ቡና፣ በ2004 ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በ2005 ደደቢት፣ በ2006 እና የዘንድሮውን ጨምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉን ዋንጫ ያነሱ ክለቦች ናቸው፡፡

ፕሪሚየር ሊጉ ከተጀመረ ጀምሮም ሆነ ከዚያ በፊት የተደረጉ የሊግ ውድድሮችን አስመልክቶ አቶ ደበበ፣ እንደተናገሩት ‹‹እግር ኳሱ ችግር ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም በአገሪቱ በተለይም በአሁኑ ወቅት በየክለቡ የሚገኙ የውጪ ተጨዋቾች በአገራቸው በዝቅተኛ ዲቪዚዮን እንኳ የመውጣት ዕድል የሌላቸው ሆነው ሳለ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ የክለብ ተጨዋችነትና ኮከብ ጎል አስቆጣሪነትን ክብር የተቀዳጁ ናቸው፡፡ የአገር ውስጥ ተጨዋቾች ከውጪዎቹ አንፃር ያላቸው ወቅታዊ ብቃት በሁሉ ነገር ያነሰ ነው፡፡ ይኼ ጉዳይ በሚመለከታቸው ወገኖች ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሔ ሊቀመጥለት ይገባል፤›› ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ መድን ድርጅትና ብዙዎቹ የከነማ ቡድኖች ክለብ ሲያቋቋሙ በዋናነት ማኅበራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ቢሆንም እየሆነ ያለው ግን ከዚሁ በተቃራኒው ነው የሚሉት አቶ ደበበ፣ ‹‹የአገሪቱ ወጣቶች የፊርማና ተያያዥ ጥቅማ ጥቅሞች ስለማይወጣባቸው ተመልካች እያገኙ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡ አያይዘውም በአገሪቱ በሁሉም የሊግ ውድድር ሙሉ ለሙሉ የውጭ ተጨዋቾች መሳተፍ የለባቸውም የሚል መከራከሪያ እያቀረቡ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ዝውውሩ የነገዎቹን ወጣቶችና እግር ኳሱን በማይጎዳ መልኩ መሆን እንደሚገባው ጭምር ይጠቁማሉ፡፡ ሌሎችም በርካታ ባለሙያተኞች በተለይም በአሁኑ ወቅት ከተጨዋቾች ዝውውር ጋር በተያያዘ ሁሉም የክለብ አመራሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቆም ብለው ሊያስቡ እንደሚገባ ጭምር ይመክራሉ፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከወራት በፊት የተጨዋቾችን ዝውውር አስመልክቶ አዲስ መመርያ አዘጋጅቶ ለውይይት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹም ይኼው መመርያ ሕግ ሆኖ ተግባር ላይ መዋል እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ወንድምኩን አላዩ በበኩላቸው፣ ደንቡ ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚውል፤ በመሀል ግን ግንቦት 28 እና 29 ጠቅላላ የመመርያው ይዘት አስመልክቶ የፕሪሚየርና የብሔራዊ ሊግ ክለቦች እንዲሁም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንዲብራራላቸው የሚፈልጉት ነገር ካለ ለመጨረሻ ጊዜ ውይይት እንደሚያደርጉበት ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ