Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትምርጫም አልተሸነፈም መራጭም አላሸነፈም

ምርጫም አልተሸነፈም መራጭም አላሸነፈም

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ (ምናልባትም ከምርጫ 97 ወዲህ ይመስለኛል) ከሃይማኖታዊ የሕዝብ በዓላት ውሎ በኋላ ማምሻውን ወይም በማግሥቱ የፖሊስ ሪፖርት ዜና ሲቀርብ መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል፡፡ በዓሉ በሰላም ተጠናቀቀ የሚል፡፡ እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተጠናቀቀ ይባላል፡፡

ይህን የመሰለ ሥጋት ወይም ደንታ ወይም ፍርኃት አውርሶ ማለፍ የቻለ ምርጫ ደግሞ ራሱ በመጣና በወጣ ጊዜ ሁሉ በሰላም አለፈ ቢባል የሚያስደንቅና የሚያስደነግጥ ነገር የለውም፡፡ በዚህ ምክንያት ምርጫ 2007 በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ “ሁከት የሌለበት”፣ “የተረጋጋ ምርጫ” ሆኖ ተጠናቀቀ የሚል ወሬ ቢያተርፍ አይገርምም፡፡ ምርጫው በሰላም መጠናቀቁንም የአውሮፓ ኅብረትና የዩኤስ አሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. መግለጫዎች ጉዳዬ ብለው አሳውቀዋል፡፡

ወደ ምርጫ 2007 ሒደትና ውጤት ዘልቀን ከመግባታችን፣ እንግባ ከማለታችን በፊት በምርጫው ሒደትና ውጤት በገዛ ራሳቸው ምክንያት ከየአቅጣጫው የሚነሱ ጉዳዮች መኖራቸው ዱሮም ጭምር፣ አሁንም ገና ከወዲሁ ስለሚታወቅ፣ መጀመሪያ እነሱን መግለጽና ማጥራት ያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

በአንድ በኩል ዛሬም እንደ ቀድሞው በምርጫ 2007 ምክንያት ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል የማያዋጣ መሆኑን ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቡ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ዛሬም ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ሲባል እንደኖረው የምርጫ ድምፅና የሕዝብ ድጋፍ ገና ባልተግባቡበት አገር፣ ወዶ ሳይሆን ተገዶ ለምርጫ መውጣት፣ ያልወደዱትን መምረጥ ባለበት አገር በሕዝብ ድምፅ ስም ፕሮፓጋንዳ መንዛት አለ፡፡

እነዚህን አንድ በአንድና በተራ እንመልከት፡፡ አንደኛውና የመጀመሪያው የትግል ሥልት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ትኩረት በዴሞክራሲ፣ በፍትሕና በልማት ላይ ለማሰባሰብ መጠራራት፣ መሰባሰብና መታገል የኢትዮጵያ ምሁራንና ፖለቲከኞች ሁሉ መወጣት ያልቻሉት ሸክም ነው፡፡ ለፖለቲከኞች ወሳኝ ፈተና ሆኖ በየጊዜው የሚቀርበውም ይህንን አለማጤን ነው፡፡ የትግል ሥልት ጉዳይ ራሱም የዕድገት ወገን የመሆንና ያለመሆን ሌላ ፈተና ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ተደጋግሞ እንደተገለጸውና አስፈላጊ በሆነ ቁጥርም እንደገና ድጋሚ መገለጽ ያለበት አንድ ጉዳይ፣ “ሥልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ ይመነጫል” የሚል አስተሳሰብ ካረጀ ካፈጀ ቆይቷል፡፡ የዚህ ወይም የዚያ ሕዝብ “ነፃ አውጪ” ነኝ እያሉ ጥሬ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን በጠመንጃ ለማብሰልና የለውጥ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ይለፋ የነበረበት ዘመን አለፈ፡፡ የላቲን አሜሪካ፣ የእስያና የአፍሪካ መሬቶች ብዙ የጠመንጃ ትግል አስተናግደዋል፡፡ ተሳካላቸውም አልተሳካላቸውም፣ ፖለቲካቸው ቅዠትም ሆነም አልሆነም፣ እውነተኛ የሕዝብ ተቆርቋሪነት የሚገለጽባቸው ትግሎች የበረከቱበትም ጊዜ ሄዶ ሄዶ የትግል ሜዳው በሌሎች ተለውጧል፡፡ በእውነትና በትክክል ዱሮ የቀረ ይኸ ነው፡፡

ለውጭ ኃይል የግዛት፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ መሣሪያ የሆኑና በዚህም የሚተዳደሩ ቡድኖች፣ ከሥልጣን የተፈነገሉ አምባገነኖች፣ በሆነ የሕዝብ ጥላቻ የተመረዙ ፋሽስታዊ ቡድኖች ከጦርነት የሚያተርፉ የጦር ጌቶች፣ የአደንዛዥ ዕፅና የከበሩ ድንጋዮች ወንበዴዎች ሁሉ “ሕዝባዊ”፣ “አብዮታዊ” የሚል የስም ጉትቻ እያንጠለጠሉ ሲተኩሱ ይታያሉ፡፡

የለየላቸውን ጨፍጫፊዎች እንተወውና እስከዛሬ ካለው የትጥቅ ትግል ልምድ (የአገራችንን ጨምሮ) መናገር እንደሚቻለው፣ የፈለገውን ያህል ሕዝባዊነት ቢኖርም እንኳ የጠመንጃ ትግል ብዙ መራራ “መስዋዕትነት” የሚከፈልበት መንገድ ነው፡፡

  • በሁለቱም ወገን የውጊያ ወጪ አለ፡፡ ከዚህም ሌላ ያለውን መንግሥት ለማድቀቅ፣ የተዋጊዎችን አቅም ለማደራጀት፣ ፖለቲካዊ ትኩረት ለማግኘትና የጠላትን ዕርምጃ ለማደናቀፍ ሲባል የፋይናንስና የኢኮኖሚ ተቋማት የኃይልና የመገናኛ አውታሮች የጥቃት ዒላማ ይሆናሉ፡፡
  • የውጊያ ልውውጥ ከሚያደርሰው ጉዳት ባሻገር ተዋጊዎቹ ጥቃት በፈጸሙበትና አዘውትረው በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ያለ ሕዝብ (ወይም እንወክልሃለን ያሉት ዓይነተኛ ሕዝብ) የመንግሥት አፀፋና እልህ መውጫ ይሆናል፡፡ በጥርጣሬና በስለላ ይሰቃያል፡፡ ተዋጊዎቹም በበኩላቸው የመንግሥት ደጋፊና ወሬ አቀባይ የሚሉትን ያሳድዳሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ይረሽናሉ፡፡
  • በሁለቱም በኩል ለሚኖረው ዘመቻ ወታደርና ንብረት የማዋጣት ዕዳ የሕዝብ ነው፡፡ ከሁለቱ ወገን በኩል ከሚመጣ የውጊያ ጥቃትና መዋጮ እንዲሁም ከሰቀቀን ኑሮ ለማምለጥ መፈናቀልና ስደት ይከተላል፡፡

ይህን የመሰለና የሚያህል ውድ ዋጋ ለረዥም ዓመታት ተከፍሎም፣ በስተመጨረሻ ሰላም፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ለመገኘቱ ዋስትና የለም፡፡ የትጥቅ ትግሉን የመራው ቡድን ራሱ የትግሉም ውጤት (ድል) እየሆነ ያስቸግራል፡፡ ባለድሉ ቡድን ምርጫ አካሄደም አላካሄደም ራሱ በቀውስ እስኪፈነቀል ድረስ በሥልጣን ላይ ሙጭጭ ሲል ይታያል፡፡

በዛሬው የዓለምና የኢትዮጵያ ሁኔታ ኪሳራው የበዛ የትግል (የትጥቅ፣ የመሣሪያ ትግል) መንገድ ይዞ ለዓመታት መዳከር ድህነትን ማገዝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለሰላሳ ዓመታት ያሳለፉት የጦርነት ጊዜ አልበቃ ብሎ ከዚያ የተረፈውን፣ ከዚያም በኋላ የተፈራውንና የተካበተውን ሀብት ጊዜና ጉልበት እንደገና ወደ ጦርነት ለመምራት መሞከር ለሕዝብ መብት ከመቆርቆር ጋር ሊዛመድ አይችልም፡፡ ዋነኛውና በአሁኑ ጊዜ ትክክለኛው የትግል ሥልት የትጥቅ ትግል ወይም መሣሪያ ሳይሆን ሰላማዊ ፖለቲካ ነው፡፡

አሁን የምንገኝበት ዓላማዊ ሁኔታ በፍልስጤም እየሆነ እንደነበረውና እንዳለው አጥፍቶ የመጥፋት የትግል ሥልትን ሙጥኝ እስከማለት አማራጭ የታጣበት፣ ይህንንም ሥልት ለማውገዝ ችግር የሆነበት ሁኔታ ላይ እንዳደረሰ ሁሉ በሉዓላዊ ሕልውና ላይ የመጣ ወረራን በአርበኝነት ዘራፍ ብሎ መጋተርን በደፈናው ተገቢ ነው ብሎ ማሰብ እንኳ እንዳይቻል አድርጓል፡፡ ምሳሌ የዩጎዝላቪያው ግፈኛ ሚሎሶቪች፣ የአሜሪካ – ኔቶን ትዕዛዝ አለመስማቱና ወረራቸውን ለመቋቋም መሞከሩ ታላቅ ጥፋት ነበር፡፡

ከላይ ሆኖ ከታች ውኃ የምትጠጣውን አህያ “ለምን ታደፈርሽብኛለሽ” እንዳለው ጅብ፣ ያለ ጥሩ ሰበብ በኢራቅ ላይ ዳግም የተካሄደው የውድመት ወረራ ሌላ ምሳሌ ነው፡፡ ኢራቅ በአሜሪካ – እንግሊዝ ሥር ከወደቀች በኋላ ከጊዜ ጊዜ እየሰፋና እየበረታ የሄደው የከተማ ሽምቅ ትግል ወሮ መያዝ ቀላል አለመሆኑን ለአሜሪካና ለመሰሎቹ ያስተማረ ቢሆንም፣ ለኢራቅ ግን የውድመትና የፖለቲካ ቀውስ መባባሻ ከመሆን በቀር እየፈየደላት አይደለም፡፡ ዛሬ ጉዳዩ የት እንደደረሰ የየዕለቱ ትኩስ የዓለም ዜና ይናገራል፡፡

የሰላማዊ ትግል መንገድ ዝግ ሆኗል፤ ወያኔ/ኢሕአዴግ በመጣበት መንገድ እኛም መምጣት አያቅተንም በማለት በኢትዮጵያም ሆነ በብሔር ስም ወደ ጫካ የዞሩ ቡድኖች አካሄዳቸውን መመርመር ያለባቸው፣ የተቀየረው ዓለማዊ ሁኔታ የትጥቅ ታጋዮችንም ስለሚመለከት ነው፡፡ እንደቀድሞው የረጂዎችን ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ዕርዳታ እየተመገቡ፣ “የጫካ ኤንጂኦ” መሆን ቀላል አይደለም፡፡ አሜሪካ በቃህ ሥልጣን ቢጤ ተካፍለህ ኑር ብትለውም ማዕድን እየሸጡና እየተዋጉ መኖር በልጦበት ወደ ጫካ ተመልሶ የነበረው ጆናስ ሳቪምቢ (አንጎላ) በመጨረሻ እብድ ውሻን ከማስወገድ ባልተሻለ አኳኋን፣ የወታደሮቹን የእንባ ዘለላ እንኳን ሳያገኝ የተሰናበተበት የቅርብ ጊዜ ታሪክ (2002) ነው፡፡

የእኛዎቹም የእስከዛሬውን ልምድ ከአሁኑ ሁኔታ ጋር አገናዝበው የትጥቅ ትግል የመቀጠል “ተስፋቸውን” በወጉ ቢመረምሩ ጥሩ ነው፡፡ “ነፃ” እያወጣሁ አዲስ አበባ መግባት ባይቻለን በአዲስ አበባም ሆነ በሌላ ቦታ ፈንጂ እየጣልኩ ብሞክርስ የሚል አማራጭ መውሰድ የ“ቀይ” ወይስ የ“ጥቁር” ቁማር ውስጥ መግባት ነው፡፡ ራስንም ከሕዝብ ተነጥሎ ለመመታት ማመቻቸት ነው፡፡ ከ9/11 ወዲህ ከኒውዮርክ መንታ ሕንፃዎች መናድ በኋላ በአሸባሪዎች ላይ ሰፊ ዘመቻ መያዙ የታወቀ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለሰላማዊ ትግል ዕድሉ የለም ባይነት ሙልጭ ያለ ቅጥፈት ነው፡፡ ችግርም ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የኃይል መንገድን ሕገወጥና ፀረ ሰላም ነው ስላለ ብቻ አንተ ሥልጣን ላይ የወጣኸው በኃይል ነውና የማገድ መብት የለህም ብሎ እልህ መጋባት፣ በሰላማዊ የትግል ጎዳና ውስጥ መግባትን የኢሕአዴግን አገዛዝ እንደ መቀበል ወይም “ታማኝ ተቃዋሚ” መሆን አድርጎ መቁጠር የወጣለት እንጭጭነት ነው፡፡ አለዚያም የሁኔታዎችን አካሄድ እየተረዱና እያስረዱ በሚያዋጡ መንገዶች ለዴሞክራሲና ለዕድገት የመታገል ከባድ ፈተናዎችን የመሸሽ ዘዴ ነው፡፡

የፈለገውን ያህል ይጥበቡም ይስፉም ተደራጅቶ የመንቀሳቀስ፣ ስብሰባዎችንና ቅስቀሳዎችን የማካሄድ፣ ሐሳብንና ተቃውሞን የመግለጽ፣ በምርጫ የመወዳደር ቀዳዳዎች አሁንም አሉ፡፡ ለይቶላቸው እስካልተጠረቀሙ ድረስ በእነዚህ ቀዳዳዎች ብዙ መሥራት ይቻላል፡፡

ኢሕአዴግ ገና ሥልጣን እንደያዘ ከታወጁት የዴሞክራሲ መብቶች መካከል አንዱ በቻርተሩ የተመለከተው፣ “የእምነት፣ ሐሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት፣ በሰላም የመሰብሰብና የመቃወም ነፃነት”  ነው፡፡ አሁንም ከሌሎች መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር በሕገ መንግሥት የተደነገገ ነፃነት ነው፡፡

አንዳንዶች ተቃውሞ መሣሪያ ሳይሆን ሥራ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ የአንዳንዱ ግብ ኢሕአዴግን ጥሎ ቤተ መንግሥት ከመግባት ብዙም ያልረዘመ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዱም ባሉት የመጻፍ፣ የመደራጀትና በምርጫ የመወዳደር ቀዳዳዎች ላይ የሚያየው ጉልህ ጥቅም ኢሕአዴግን መፈታተንና ማሳጣት ሊሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ግን ማን ከሰረ? ማን አተረፈ? ማን ወረደ? ማን ወጣ? ሳይሆን የእነዚህ የዴሞክራሲ ቀዳዳዎች መስፋትና በደንብ መሥራት መቻል ነው፡፡ ኢሕአዴግ ራሱ የሚንደፋደፍበት (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረ) የልማት ጥረት መስተካከሉ ስፋት፣ ጥልቀትና ፍጥነት በገዛ ራሱ ምክንያት ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ለዴሞክራሲው ባህል ግንባታም መዋጮው ብዙ ነው፡፡

ሩቅም ታደረ ቅርብ ወደ ሰላማዊ ትግል ውስጥ መግባትና የሰላም መድረኮችን በደንብ መጠቀም በራሱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጥቅም ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታን የማልማት ፋይዳ አለው፡፡ ሰላም ለዕድገት ያለውን ዋጋ የማወቅና ዕድገትን የማገዝ የመጀመሪያ ዕርምጃም የሚጀምረው ከዚሁ ነው፡፡

ሕጋዊውንና ሰላማዊውን የትግል ሥልት ፋይዳ ቢስ ለማድረግ ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው፣ ምርጫ በራሱ ለምን ሥልጣን አላስገኘልንም የሚለው መከራከሪያ አንዱ ከሆነ፣ ችግሩ አሁንም እንደገና ከገዥው ፓርቲ ከኢሕአዴግ ሳይሆን ከራሳቸው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ነው፡፡

የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ ኃይሎች (የፖለቲካ ፓርቲዎች) በፊትም፣ ከስንት ጊዜ በኋላ የ97 ምርጫና ድኅረ ምርጫ ትግሉ፣ አሁንም በአሥር ዓመቱ የ2007 ምርጫ አሳድዶ የያዛቸውና ያሯሯጣቸው የፖለቲካ መስመሮቻቸውን በየቅልም ሳያጠሩ፣ በጋራም ሳያቀራርቡ፣ የራሳቸውን ኢዴሞክራሲያዊነትን ሳያራግፉ ውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲን ወግ ሳያደርጉ፣ ከተጠራጣሪነት፣ ከመሰሪ ሥሌትና ከጠባብ ሥልጣን አፍቃሪነት ሳይላቀቁ ነው፡፡

ይህን ችግርና ሌሎችንም በ2007 ምርጫ የተመሰከሩ የገዛ ራስን ድክመትና ድቀት ትቶ፣ ሁኔታውን የሰላማዊ ትግል ፋይዳ ቢስነት ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ የአብየን ለእምየ ነው፡፡ ያለጠመንጃ ትግል ኢሕአዴግ አይሸነፍም የሚል ዕምነት ያላቸውም በጩኸታቸው በጣም ብዙ ናቸው፡፡ የትጥቅ ትግል ከሰላማዊ ትግል የተሻለ ነው ማለት አንድ ችግር ነው፡፡ የኤርትራን መንግሥት ከፕሮፓጋንዳ እስከ ወታደራዊ መስክ መጠጊያ አድርጎ መያዝ ደግሞ የከፋ ችግር ነው፡፡

የሰላማዊና የሕጋዊ ትግል ፋይዳና ረብ ባልተሳኩ አጋጣሚዎች መምጣትና አለመምጣት ወይም ሥልጣን በማሸነፍና ባለማሸነፍ ብቻ መመዘን የለበትም፡፡ ወደ ግብ ለመድረስ በሚረዱ “እንጥብጣቢ” ውጤቶችም ይመዘናሉ፡፡ በዚህ ረገድ ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቁ የምርጫ፣ የፍትሕና የመንግሥት አውታራት እንዲኖሩ መታገል የምርጫ ሒደት ውስጥ የሚገኝ ዋናውና ቀጥተኛው አጋጣሚ ነው፡፡ እነዚህን የማሟያውን፣ ዋናውንና ቀጥተኛውን የትግል መስክና ትምህርት ቤት ረግጦ ወጥቶ እነሱ ሳይሟሉ ምርጫ ውስጥ መግባት የለበትም ማለት የፖለቲካ መሃይምነት ነው፡፡ የ87 ልምድ ለ92 አዋጥቶ ነበር፡፡ የ92 ልምድ ደግሞ ለ97 አስተዋጽኦ አበርክቶ ነበር፡፡ 97ም ከአሥር ዓመት በፊት ለወደፊቱ ብሎ ብዙ ትምህርት ሰጥቶ አልፎ ነበር፡፡ የማይናቁ የማሻሻያና የግንባታ ድሎችም ከመንግሥት መዳፍ ፈልቅቆ አውጥቶ ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የ2002 እና የ2007 ምርጫዎች በከንቱ የባከኑ ዕድሎች የሆኑት ሰላማዊ ትግል ማዋጣቱ ስለቀረ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ የትግል ሥልት መካን ወይም መሠልጠን ቀርቶ ስላላወቁበት ነው፡፡ ምርጫ 2007 ያስመዘገበው ውጤት የሚያሳየው፣ ወይም አንዳንድ የምዕራብ የመገናኛ ብዙኃን እያላገጡና በአሽሙር እንደገለጹት፣ የምርጫ 2007 “ድራማ” አልባ ሒደትና ውጤት ያሳየው የሰላማዊና የሕጋዊ መድረክ ትግል አለማዋጣቱን ለመመስከርና ለማሳጣት ሳይሆን፣ ይህ ዓይነት ትግል ብልሃተኝነትን እንደሚጠይቅና ብልኃትን ከኅብረት ጋር ያጣመረ ትግል አለመኖሩን ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሚባልም ሌላ ነገር አለ፡፡ ወይም ነበር፡፡ በምርጫ መሳተፍ የሚጠቅመው ኢሕአዴግን ነው የሚል እምነት፡፡ የሁሉንም ፓርቲዎች ስም ጥሩ፡፡ ዘርዝሩ፡፡ ሁሉም በምርጫ አንሳተፍም ቢሉ ኢሕአዴግን በጭራሽ አይጎዱትም፡፡

ካስፈለገ ከእነሱ የበለጠ ኢሕአዴግን “የሚናደፍ” የሰባ (ውሸት) ተቃዋሚ በአንድ ጀምበር ማዘጋጀትና ባሉት መናጆዎች ላይ መጨመር የሚሳነው አይደለም፡፡ ከኢሕአዴግ መናጆዎች ውጪ የሆኑ ተቃዋሚዎች በሕጋዊ መድረኩ ውስጥ መቆየታቸው ራሱ ብቻውን (የረባ ነገር ባይሠሩም እንኳን) ጥቅም ነው፡፡ የሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን አንጥሮ እያወጡ መልስ እንዲያገኙ ግፊት ማድረግ፣ የተዛቡ አስተሳሰቦችና ሽኩቻዎች በሕዝብ ላይ የሚያደርሱትን መከፋፈል በበሰለ ትችት ማምከንና በመንግሥትም ሆነ በሌላ ወገን ያሉ ጥፋቶችን ማጋለጥ ሕዝብን መጥቀም ነው፡፡

በዚህ ሁሉ ምክንያት የሕጋዊና የሰላማዊ ትግልን ተከራክሮ ውድቅ ማድረግ የሚቻልበት፣ በሕጋዊ መድረክ መንቀሳቀስን እንኳን በክህደት በጥቅም የለሽነት ለማየት የሚያበቃ መከራከሪያ ማቅረብ አይቻልም፡፡ አንደኛው ጉዳይ ይኼኛው ነው፡፡ ሁለተኛው ዓቢይ ጉዳይ በወዲህ በኩል ምርጫን የሕዝብ ድጋፍ፣ ምስክርና ማስረጃ አድርጎ የማቅረብ ጉዳይ ነው፡፡

ኢሕአዴግ ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለው ጥያቄ አንስቶ የሕዝብ የዕምነት ድጋፍ አግኝቶ ተዋግቶ ያሸነፈ ድርጅት መሆኑ እውነት ነው፡፡ ኢሕአዴግ ደርግን ማሸነፉ የሁሉም ነገር (የትግል ስትራቴጂ፣ የአደረጃጀቱ፣ የዓላማው የግቡ) ትክክለኛነት ማረጋገጫና ማስረጃ አይደለም፡፡  የመላው ሕዝብና ብቸኛው አማራጭ የሌለው ድርጅት አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት የድርጅቱ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ሕዝብ ለድርጅቱ ያለው ድጋፍ የማይቀለበስ የኢንሹራንስ ፖሊሲ የተገባለት አለመሆኑን ሲያስረዱ፣ የድጋፍ ካፒታል እንደ ባንክ ተቀማጭ እንዳልሆነና በጊዜ ውስጥ ሊሸረሸር መቻሉን ሲናገሩ ሰምተናል፡፡

ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶች ግን ከአባላት በተለይና በተጨማሪ ሰፊ ደጋፊ አለን ብለው ሲበዛ ከኩራት በላይ የመንቀባረር ወግ ያጠቃቸዋል፡፡ የኢሕአዴግ (ማለትም የአራቱ ድርጅቶች) የፓርቲ አባላት ቁጥር ከስድስት ሚሊዮን በላይ መሆኑን ከሰማን ቆይተናል፡፡ ደጋፊዎችም በዚያው ልክ ናቸው ሲባል እንሰማለን፡፡ በዚያ ላይ እውነቱ በሙሉና ሁሉም እውነት ደረትን ነፍተው የማይናገሩበት፣ የሕግ ማዕቀፍ የማይታወቅና የማይጠየቅ “አንድ ለአምስት” የሚባል መላውን የአገር ልጅ የሚገዛ ቁጥጥር፣ ቁርኝትና ትስሥር አለ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የገዥው ፓርቲ አባል መሆንና በፓርቲው አቋም ማመን ጭራሽ ተለያይቶ በድርጅቱ ውስጥ መላወስ የእንጀራ ጉዳይ፣ የተሻለ ሕይወት ጉዳይ መሆኑን ከኢሕአዴግ የበለጠ ምስክር የለም፡፡ አድራጊ ፈጣሪዎች እንደፈለጉ የሚዋኙበትን፣ ሲፈልጉም የሚንቦጫረቁበትን ምርጫ ለሕዝብ ድጋፍ ምስክር አድርጎ ማቅረብ ዶሮን በመጫኛ መጣል ነው፡፡

ተደጋግሞ እንደተባለው አገራችን ውስጥ ለመራጭነት መመዝገብ፣ ድምፅ ለመስጠት መውጣት ገና በመብትነት አጥር ግቢ ውስጥ የተከበረ ነፃነት አይደለም፡፡ በብዙ ምክንያት ግዴታ ነው፡፡ በደርግ ዘመን በተፈጠረው “አጉል” ቋንቋ (ሐረግ) መሠረት “የውዴታ ግዴታ” ነው፡፡ በወደሽ ነው ቆማጢት ንጉሥ ትመርቂ መንፈስ የሚገዛ “መብት” ነው፡፡ ድምፅ መስጠትም የሕዝብ ድጋፍ መግለጫ ገና አልሆነም፡፡

የድምፅ መስጠትን መብት ከማንኛቸውም ተፅዕኖ፣ ፍርኃት፣ ሥጋት፣ የውስጥ ሽብር ለመከላከል ሲባል ከምርጫ መርሆዎች አንዱ የሚደነግገው ሚስጥራዊ ድምፅ አሰጣጥን ነው፡፡ ይህን ለማረጋገጥ የምርጫ ሕጉ “ሚስጥር ድምፅ መስጫ ክፍል” እንዲኖር ግዴታ ያቋቁማል፡፡ የምርጫ ሕጉ ከዚህም በላይ ዘልቆ ይሄድና ድምፅ የተሰጠባቸው (የድምፅ መስጫ) ወረቀቶች ዋጋ አልባ ስለሚሆኑባቸው ምክንያቶች ሲደነግግ፣ የመራጩ ማንነት በስም የተገለጸ ከሆነ የተሰጠው ድምፅ ዋጋ አልባ ይሆናል፡፡ ውድቅ ያደርጋል ይላል፡፡

በሚስጥር ድምፅ መስጠት ለዴሞክራሲውና ለምርጫው ተዓማኒነት ይህን ያህል ፋይዳና የሕግ ጥበቃ ቢኖረውም፣ ከዚህ በላይ የሚያስተጋባና ተፈጻሚነት ያለው ሌላ ሕግ ግን አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ሕያው ነው፡፡ ይህ መደበኛ ያልሆነ ነገር ግን ሥር የሰደደ ሁሉም የሚያስከብረው ሕግና ደንብ ደግሞ “ወደ ሚስጥር ድምፅ መስጫው ክፍል ገብቶ የፈለጉትን ቢመርጡ ገልጦ የሚያይ…. አለ” ይላል፡፡ ይጮሃል፡፡ ያስተጋባል፡፡ ከተሸፋፍነው ቢተኙ ገልጦ እሚያይ አምላክ አለ በላይ ያስፈራል፡፡  

በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ገና የምርጫ ካርድ በሚስጥር መጣልና ትክክለኛ የሕዝብ ድጋፍ ገና አልተግባቡም፡፡ እርስ በርስ አይተዋወቁም፡፡ ሌላ አመለካከት ይወሰድብኛል፣ ችግር ይገጥመኛል ተብሎ በመራጭነት መመዝገብና ወደ ምርጫ መውጣት፣ ለምርጫ ወጥቶም ያልወደዱትን መምረጥ እንኳንስ ዳር አገር አዲስ አበባም ውስጥ አለ፡፡

የፍርኃቱ ሰለባዎች መራጮች ብቻ አይደሉም፡፡ ምርጫ በሚባለው በዚህ አገር አቀፍና መጠነ ሰፊ ድግስ ውስጥ የሚሳተፈው ተዋናይ፣ ባለጉዳይ፣ ሠራተኛ፣ አላፊ አግዳሚ ሁሉ በዚያው ተስተዳዳሪ በዚያው ውሎ አዳሪ ነው፡፡ ሁሉም ይህንን ያውቀዋል፡፡ በሽግግሩ ወቅት ቻርተር ውስጥ “ሁኔታዎች በፈቀዱበት ቦታ ሁሉ የሽግግር መንግሥቱ በተመሠረተ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ” የአጥቢያ (ሎካል) እና የክልላዊ ምክር ቤቶች ምርጫ ይካሄዳል ከተባለበት፣ ነገር ግን ከአንድ ዓመት በኋላ ከተደረገው (የሰኔ 14 ቀን 84 ዓ.ም.) ምርጫ ጀምሮ ይህንን ሁሉ አይተናል፡፡

ስለምርጫ 2007 ሒደትና ውጤት የሚወራው በዓይነቱና በይዘቱ የተለያየ፣ ዝርዝሩም ብዙ ነው፡፡ በውጤቱ ምክንያትና ውጤቱን ተከትሎ የሚወሩት ጉዳዮች ግን ሁለቱም ሲበዛ ጫፍ የረገጡ ከላይ የተመለከትናቸው ናቸው፡፡ የምርጫ 2007 ሒደትና ውጤት ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላማዊ ትግል ወገኖችን መረታት ያረጋገጠ ነው የሚሉት ፈጽሞ ውሸት ነው፡፡ አነሰም በዛም ከፋም መረረም በኢትዮጵያ ዛሬም ይህ መድረክ አለ፡፡

ከዚህ እኩል ምናልባትም ሲበዛ ምርጫው የሕዝብ ድምፅ ኮሮጆ ውስጥ ሲገባ በሕዝቡ ውሳኔና ብይን መሠረት መልክና ልክ አግኝቶ ሲደራጅ የተመሰከረበት ነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ “ሞዴል ሕዝብ” ነው ማለት ሁሉም የሚያውቀው ውሸት ነው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ይበልጥ የሚያሳዝነው ይህንን አፍ አውጥቶ ጮኾና ይፋ ወጥቶ መናገር አለመቻሉ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ራዕይዋን ማሳካት እንድትችል ከተፈለገ ገዢው ፓርቲና መንግሥት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ፣ ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ምግባር መያዝ፣ ይህን የሚደግፍና የሚያንሰራፉ ሕጎችና ተቋማት መልማት አለባቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችም ትናንሽ ቡድን እየፈጠሩ ካብ ለካብ መተያየት የሚያስከትለውን ክስረት ሊረዱ ይገባል፡፡ የመያያዝን፣ ኅብረት የመፍጠርን አስፈላጊነት አሁንም አላጤኑትም፡፡ በተናጠል መቆም የሚያስከፍለውን ዋጋ ገና አልተረዱትም፡፡

መጪው ዘመን ሻል ያለ ይሆን ዘንድ ከዚህ መንደርደርና መጀመር ያለብን ይመስለኛል፡፡

 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...