የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመላ አገሪቱ ተካሂዷል፡፡ የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ 532/99 አንቀጽ 76 (5) አጠቃላይ የምርጫ ውጤት ከየምርጫ ክልሉ ተጠናቆ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እስኪደርስ ድረስ፣ እንዳስፈላጊነቱ ከየምርጫ ክልሉ ለቦርዱ የተላኩ ውጤቶችን የቦርዱ ጽሕፈት ቤት በጊዜያዊነት ይፋ ይደርጋል ይላል፡፡ ይኼንንም መሠረት በማድረግ ቦርዱ ከተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቀደም ሲል በመመካከር በወጣው የጊዜ ሰሌዳው መሠረት እስከ ግንቦት 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ጊዜያዊ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ በጊዜ ሰሌዳ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይኼንንም መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስከ ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ከየምርጫ ክልሉ የደረሱትን ውጤቶች በጊዜያዊነት ይፋ አድርጓል፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፣ ምክትል ሰብሳቢው ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔርና የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳ በጋራ በመሆን ከ442 ምርጫ ክልሎች የተላኩ ውጤቶችን ለጋዜጠኞች ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ አድርገዋል፡፡ በዘጠኙም ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳሮች ውስጥ በሚገኙ 442 የምርጫ ክልሎች በተደረገው ምርጫ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አጋሮቹ ሁሉንም የምርጫ ክልሎች ማሸነፋቸው ተገልጿል፡፡ በዘጠኙ ክልሎች በተደረጉ የክልል ምክር ቤት ምርጫዎችም ኢሕአዴግና አጋር ፓርቲዎች ሙሉ በሙሉ የምክር ቤቱን መቀመጫዎች ማሸነፋቸውን ፕሮፌሰር መርጋ ይፋ አድርገዋል፡፡ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች፣ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች በጋራ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መግለጫውን የተከታተለው ዮሐንስ አንበርብር የጥያቄና መልሱ አንኳር ነጥቦችና የተሰጡ ምላሾችን እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡
ጥያቄ፡- በተለያዩ አካባቢዎች የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና ታጣቂዎች ኮሮጆ ሰርቀው ተሰውረዋል የሚሉ ወሬዎች ይናፈሳሉ፡፡ የቦርዱ አስተያየት ምንድነው? ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሰማሯቸው ታዛቢዎች በፀጥታ ኃይሎች መዋከባቸውንና አንዳንዶቹም መታሰራቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይስ የቦርዱ ምላሽ ምንድነው አምቦ አካካቢ አንድ ግለሰብ ከምርጫ ጋር በተገናኘ ተገድሏል ይባላል፡፡
ፕ/ር መርጋ፡- ምርጫ ቦርድ ለአምስተኛው ዙር ምርጫ ዝግጅት ማድረግ የጀመረው ከ2002 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት አንስቶ መሆኑንና ዝግጅቱም ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መደረጉን ደግመን ደጋግመን ገልጸናል፡፡ የተደላደለ የውድድር መድረክ ለሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል አመቻችተናል፡፡ የእኛ ሥራ ይኼ ነው፡፡ ብይኑ የሥልጣን ምንጭ ባለቤቱ የሕዝብ ነው፡፡ ብቃት ያላቸው የምርጫ አስፈጻሚዎችን አሠልጥነን አሰማርተናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በበቂ ሁኔታ በምርጫ ጉዳይ ላይ አሠልጥነናል፡፡ ምክክር አድርገናል፡፡ የሥነ ዜጋ ትምህርት በሚገባ ለመራጩ ሕዝብ ሰጥተናል፡፡ ይኼ ነው የውድድር መድረኩን ያደላደለው፣ ምርጫውንም ስኬታማ ያደረገው፡፡ ኮሮጆ ተሰረቀ፣ ታዛቢዎቻችን እንዳይታዘቡ ተደረጉ የመሳሰሉት የሚባሉት መሬቱ አንሸራተተኝ ወደድኩኝ እንደ ማለት አድርገን ነው የምንወስደው፡፡ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡ አግባብ ካላቸው የደኅንነት አካላት ጋር ተቀራርበን በመሥራታችን ሰላማዊነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ አምቦ አካባቢ ተገደለ የተባለውን ግለሰብ በተመለከተ ሁለት ተመሳሳይ ቅሬታዎች ለቦርዱ ደርሰዋል፡፡ አንዱ በመድረክ በኩል የቀረበ ሲሆን፣ እከሌ እከሌ የሚባል ተገደለ የሚል ቅሬታ አቅርቧል፡፡ በዚሁ ተመሳሳይ ቦታ ላይ ኦሕዴድም እከሌ የሚባል አባሌ ተገደለ ብሎ ቅሬታ አቅርቧል፡፡ ይኼንን የምናጣራውና ለሕዝብ ይፋ የሚደረግ ነው የሚሆነው፡፡
ጥያቄ፡- የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ይፋ ባደረገው ጊዜያዊ ሪፖርት ከ20 እስከ 30 በመቶ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ኮሮጆዎች ባዶ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ድምፅ መስጠት መጀመሩን፣ እንዲሁም ድምፅ መስጠት መጀመር በነበረበት ሰዓት አለመጀመራቸውን ገልጿል፡፡ ቦርዱ ለዚህ ምን ምላሽ አለው?
ፕ/ር መርጋ፡- የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን ሪፖርት ቦርዱ በቀጥታ አልደረሰውም፡፡ ህፀፆች አሉ የሚባል ከሆነም ይህ አገር አቀፍ ምርጫ ነው የሚል ነው መልሳችን፡፡ እንኳንስ ኢትዮጵያ ገና በ25 ዓመት የዴሞክራሲ ጎዳና ውስጥ ያለች ይቅርና ከሁለት መቶ ዓመት በላይ የዴሞክራሲ ባህል ባላቸው አገሮችም አንዳንድ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እኛም የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚደረጉ ምርጫዎችንና በርካታ የሠለጠኑ በሚባሉ አገሮች የተካሄደ ምርጫዎችን ሄደን ዓይተናል፡፡ ስለዚህ ይህ አያስገርመንም፡፡ ከ45,795 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በጥቂቶቹ ህፀፆች ቢታዩ እንኳን እንደ ችግር መቆጠር የለበትም፡፡
ጥያቄ፡- የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች ሆነ ተብሎ እጥረት እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች የነበራቸው የመምረጥ መነሳሳትን ገድሏል የሚሉ ስሞታዎች እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡
ፕ/ር መርጋ፡- ይህ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ተቀባይነት የሌለው ስሞታ ነው፡፡ የድምፅ መስጫ ወረቀት እጥረት የተፈጠረው በኦሮሚያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ነው፡፡ ይህ እጥረት ምንድነው ምንጩ ከተባለ በአገራችን 140 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በመላ አገሪቱ መኖራቸው፣ በእነዚህ በእያንዳንዱ ለ547ቱም የፓርላማ መቀመጫዎች ድምፅ መሰጠቱ ነው፡፡ እያንዳንዳቸው 140 የምትህርት ተቋማት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ናቸው፡፡ የምትህርት ተቋማቱ ትንሿ ኢትዮጵያ ናቸው ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ አንድ ተማሪ የሚመርጠው እናት አባቱ የሚመርጡበት አካባቢ ወይም በተወለደበት አካባቢ ለሚፎካከሩ ፓርቲዎች ወይም ዕጩዎች ነው፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረገው ምርጫ ውስብስብ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ነው እጥረቱ የተፈጠረው፡፡ ችግሩ እንደታወቀም ቦርዱ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ የሚደረግ ምርጫ በአንድ ቀን እንዲራዘም በሰጠው መመርያ መሠረት በስኬት ተጠናቋል፤ ችግሩም ተቀርፏል፡፡
ጥያቄ፡- መድረክ የተባለው ፓርቲ 60 በመቶ የሚሆኑት ታዛቢዎቹ፣ ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ 80 በመቶ የሚሆኑት ታዛቢዎቹ በተፈረጠባቸው ጫና በሐዋሳ ምርጫውን መታዘብ አለመቻላቸውን በመጥቀስ ወቀሳ እየሰነዘሩ ነው፡፡ በትግራይ ክልልም አረና ፓርቲ ተመሳሳይ ችግር እንደገጠመው ቅሬታ አቅርቧል፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ አብዛኞቹ የምርጫ ክልሎች የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎች ላይ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ጫና በመፍጠራቸው መታዘብ አለመቻላቸውን የሚገልጽ ቅሬታ እየተደመጠ ነው፡፡ በዚህ ላይ የቦርዱ አስተያየት ምንድነው?
ፕ/ር መርጋ፡- እያንዳንዱ ፖለቲካ ፓርቲ ሕጉ የሰጠውን መብት እንዲጠቀም፣ ማለትም ታዛቢ በምርጫው ወቅት እንዲያስቀምጥ ቀደም ብለን ተመካክረናል፡፡ እኛም መታወቂያ ሰጥተናቸዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ምርጫውን በመታዘብ ተሰማርተዋል፡፡ ግማሹ ቋሚ ታዛቢ ግማሹ ተንቀሳቃሽ ታዛቢ አሰማርተዋል፡፡ ሕጉ የሚለው ምንድነው? አንድ ታዛቢ ብቻ ነው አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የሚያስቀምጠው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ሦስት ታዛቢ ነው ለማስቀመጥ የሞከሩት፡፡ አንዳንዶቹ ስድስት፣ ዘጠኝ ለማስቀመጥ ነው የሞከሩት፡፡ ሆነ ብለው የምርጫውን ሰላማዊና ጤናማ ሒደት ለማወክ የፈለጉ ነበሩ፡፡ ስለዚህ መሬት ያለው ሀቅ ይህ ነው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ምርጫ ጣቢያ ውስጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር ታዛቢዎች ከድርጊቸው እንዲታቀቡ እስኪጠየቁ ድረስ፡፡ ስለዚህ ታዛቢ ተከለከልን የሚለው ወቀሳ ከእውነት የራቀ ነው፡፡
ጥያቄ፡- አገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን እንደምትከተል ቢነገርም፣ የምርጫው ውጤት የሚያሳየው ግን የአንድ ፓርቲን የበላይነት ነው፡፡ ምንም እንኳን ከ50 በላይ ፓርቲዎች በምርጫው ቢሳተፉም ውጤቱ እያሳየ ያለው የአንድ ፓርቲ የበላይነትን ነው፡፡ መንግሥት የሚሰብከው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በኢትዮጵያ አለ ወይ የሚለውን ጥያቄ፣ ምርጫ ቦርድ ከምርጫው ውጤት በመነሳት እንዴት ይገልጸዋል? የአንድ ፓርቲ የበላይነት እየገነነ የመጣበት ምክንያትም ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሜዳውን በገለልተኝነት ለሁሉም ፓርቲዎች ምቹ አድርጎ ስላላደላደለ ነው የሚሉ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ ለዚህ ምን ምላሽ አላችሁ?
ፕ/ር መርጋ፡- የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን አስመልክቶ የሚሰነዘረውን ቅሬታ በተመለከተ ባልደረቦቼ የበለጠ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይችላሉ፡፡ በእኔ በኩል የምለው ምርጫው ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ነው፡፡ የምረጡኝ ቅስቀሳውና የዕጩዎች ብዛት ሁሉም የቻለውን ታግሏል፡፡ ውሳኔው የሕዝብ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ አሳታፊ የሆነ የውድድር ሜዳ አዘጋጅቷል፡፡ መራጩንም ተመራጩንም ከቀድሞ በተሻለ ያስተናገደ ምቹ ሜዳ ምርጫ ቦርድ አዘጋጅቷል፡፡ ይኼም በግልጽ ታይቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ ያለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ልፋቱን ነው እያሳየና እያየ ያለው፡፡ ከዚያ ውጪ ሕዝቡ ይጠቅመኛል ብሎ ድምፁን የሰጠውን ውጤት ተቀብሎ ማወጅ ነው የምርጫ ቦርድ ሥራ፡፡
ዶ/ር አዲሱ፡- በምርጫው የነበረው ፉክክርን ስንመለከት የአገራችን ሕዝቦች በሚገባ የፉክክሩን ዓይነት እንዲረዱ ፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳቦቻቸውን ለሕዝብ በመግለጽ ያደረጉት ፉክክር አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በሁሉም የመገናኛ ብዙኃን ማለት ይችላል ነፃ የአየር ሰዓት ተመድቦላቸው፣ የጋዜጣ ዓምድም ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የተመደበውን ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበው የበጀት እገዛ ለፉክክሩ በትክክል እንዲረዳቸው ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን ዕጩዎች በየምርጫ ክልሉ እንዲያስመዘግቡ፣ እንዲቀሰቅሱ፣ ለአባላቶቻቸው እንዲያስተምሩና ለሕዝቡም ያላቸውን አማራጭ ሐሳብ እንዲያቀርቡ የተደረገው እገዛ ፉክክሩን ጤናማ ለማድረግ ነው፡፡
ውጤቱንም ስናየው ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ የምርጫ ውጤትን ብንመለከት፣ በተወሰኑ የአዲስ አበባ የምርጫ ክልሎች ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ 39,848 ድምፅ ያገኘበት ውጤት፣ ሰማያዊ ፓርቲ 15,192 ያገኘው ውጤት የፉክክሩ መገለጫ ነው፡፡ ፉክክር መኖሩን የሚያሳይ አኃዝ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል የምሥራቅ ሸዋ የምርጫ ውጤትን ብንመለከት ኢሕአዴግ/ኦሕዴድ 40,357 ድምፅ ሲያገኝ መድረክ 12,834 ያገኘው ውጤት የፉክክሩ ማሳያ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ፉክክር ያረጉበት አንድና ሁለት ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ መሆኑ የፉክክሩ ሜዳ ምቹ መሆኑን ነው፡፡ የየትኛውም አገር የምርጫ አካል ትልቁ ኃላፊነት ለሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እኩል ሜዳ መፍጠር ነው፡፡ በእኛም ሕግ ያለው ኃላፊነት ተመሳሳይ ነው፡፡ ሜዳ በማመቻቸት ረገድ፣ እገዛ በማድረግ ረገድ፣ ሜዳው አባጣ ጎርባጣ ነበር ወይ መሆን ያለበት ጥያቄው፡፡ ያኔ ነው ቦርዱም የሚተቸው፡፡
ጥያቄ፡- በአገሪቱ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫውን ውጤት በበነጋታው ለሕዝብ በሚታይ ሰሌዳ ላይ እንደሚለጥፉ በሕግ በተቀመጠው መሠረት ይኼንኑ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ይኼንን ለሕዝብ ይፋ የሆነ ውጤት የመገናኛ በዙኃን እንዳይዘግቡ ምርጫ ቦርዱ ራሱ ካወጣው የመገናኛ ብዙኃን የምርጫ ዘገባ ሥነ ምግባር በተጣረሰ ሁኔታ ማስጠንቀቂያ ያወጣው ለምንድነው? ድርጊቱ የሕግ አግባብ አለው ወይ?
አቶ ነጋ፡- ሥራችን ግልጽ ነው፡፡ በየምርጫ ጣቢያው ያለው ውጤት ግንቦት 17 ቀን በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ለሕዝብ ይፋ ሆኗል፡፡ አይደለም የመገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ዜጋ እግረ መንገዱን ሲያልፍ ዓይቶ ተረድቶ ማን በምን ያህል ድምፅ አሸነፈ? የሚለውን እንዲለይ ነው በምርጫው ማግሥት ውጤቱ በምርጫ ጣቢያዎች የሚለጠፈው፡፡ የሚዲያ ተቋማት እንዳይዘግቡ ስለመከልከላቸው አሁን ነው የምንሰማው፡፡ ማንኛውም ሰው ውጤቱን እንዲመለከት ነው የሚለጠፈው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ ሕዝቡና የሚዲያ ተቋማትም መረጃ እንዲያገኙ ነው የሚለጠፈው፡፡ (የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ከላይ የተገለጸውን እየተናገሩ ባለበት ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በጆሯቸው መልዕክት አቀብለዋቸው መልስ መስጠታቸውን ቀጠሉ) ግን ምንድን ነው? ውጤቱ በምርጫው ቦርዱ እስኪገለጽ ድረስ ውጤቱ እንደዚህ ነው ብሎ ሪፖርት ማድረግ አይቻልም፡፡ እንደ ዜጋ ግን የተሸፋፈነበት ሁኔታ የለም፡፡ ማየት ይቻላል ማለት ነው፡፡ ውጤቱን ይፋ ማድረግ ግን አይቻልም፡፡
ጥያቄ፡- ቦርዱ እየገለጸው ያለው ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት እንደሚያሳየው 442 የፓርላማ መቀመጫዎችን ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አጋር ፓርቲዎቹ ናቸው ያሸነፉት፡፡ ካልተገለጹት የምርጫ ውጤቶች ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፓርላማ ወንበር ያገኙ ይሆን?
ፕ/ር መርጋ፡- ቦርዱ ይፋ እያደረገ ያለው የደረሱትን ውጤቶች ብቻ ነው፡፡ የተቀሩትን ውጤቶች በተመለከተ ከየምርጫ ጣቢያዎቹ መሰብሰብ ይኖርብናል ባስቀመጥነው የጊዜ ሰሌዳ [ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም.] መሠረትም ይፋ ይደረጋል፡፡ አሁን ከተቀሩት የምርጫ ጣቢያዎች የሚመጡ ውጤቶች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወይም ኢሕአዴግን የፓርላማ ወንበር ያስገኛሉ ብዬ መናገር አልችልም፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ሰፊ አገር ናት፡፡ በመላ አገሪቱ ከ45,000 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች አሉን፡፡ የእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ውጤት በመጀመርያ ወደ ምርጫ ክልሎች ነው የሚላከው፡፡ ይኼም ማለት ከ45,000 በላይ የሆኑት የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ውጤቱን 547 ለሚሆኑት የምርጫ ክልሎች መላክ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የምርጫ ክልሎቹ ወደ ምርጫ ቦርድ የሚልኩት፡፡ ስለዚህ ጊዜው እስኪደርስ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ አሁን ይፋ ባደረግነው 442 የምርጫ ክልሎች ወይም የፓርላማ ወንበሮች ላይ ግን ተቃዋሚ ፓርቲ አላሸነፈም፡፡
ጥያቄ፡- በአዲስ አበባ በተዘዋወርንባቸው አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሕጉ እንደ ድምፅ ከሚቆጥራቸው የኤክስና የአሻራ ምልክቶች ውጪ ያሉ ምልከቶችን የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች በቃለ ጉባዔ ተፈራርመው እንደ ድምፅ ተቆጥረዋል፡፡ ይህ በእናንተ ቆጠራ ላይ ችግር አይፈጥርም ወይ? በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በሚስጥራዊ ድምፅ መስጫ ክልል ውስጥ ከአንድ ሰው በላይ ተመልክተናል፡፡ ይህ አግባብ ነው ወይ?
ፕ/ር መርጋ፡- ሚስጥራዊ የድምፅ መስጫ ቦታ ውስጥ ለቅልጥፍና ሲባል ከአንድ ሰው በላይ ቢገኝ ችግር የለውም፡፡ ሕጉ ይፈቅዳል፡፡ ሁለት ማድረግ ይቻላል፡፡ ሌላ አገር ከአምስ እስከ ሰባት ያደርጋሉ፡፡ ይኼን በዓይናችን ያየነው ነው፡፡ ኢትዮጵያ እኮ ታዳጊ አገር ነች፣ ደሃ አገር ነች፡፡ ስለዚህ ለቅልጥፍና ሲባል ሁለት ሰው ቢገባ ችግር የለውም፡፡ ሕጉ የሚደግፈው ነው፡፡ አቅመ ደካሞችን ለመርዳት፣ ማየት የማይችሉትን ለመርዳት ሌላ ሰው መግባት ይችላል፡፡ ሕጉ ይፈቀድለታል፡፡ ከኤክስና ከአሻራ ምልክት ውጪ ያሉ ምልክቶች በቃለ ጉባዔ ተይዘው እንደ ድምፅ ተቆጥረዋል የተባለውን ማመን ያቅተኛል፡፡ ይኼ ተቀባይነት የለውም፡፡ ነገር ግን ተከስቶም ከሆነ ከ45,000 በላይ ምርጫ ጣቢያዎች ባሉበት አገር የተፈጠረ ስህተት በመሆኑ ይኼንን ስህተት በሁሉም ጣቢያ እንደተፈጠረ አድርጎ አብዝቶ መገመት ተገቢ አይደለም፡፡
እኔ እኮ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ምርጫን ተገኝቼ ተመልከቻለሁ፡፡ ጋና ነበርኩ፡፡ እዚያ ያየሁት ስህተት እዚህ አይታይም፡፡ የጋና ምርጫ በጣም ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡ እኔ ግን በዓይኔ ያየሁት ሌላ ነገር ነው፡፡ ዋናው ሰላም ተረጋግጧል አልተረጋገጠም? ነፃ ምርጫ ተካሂዷል? አልተካሄደም? ሕዝቡ ወጥቶ ችግር አጋጥሞታል ወይ? የምርጫ ሒደቱ ችግር አለበት? የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ አንድ ምርጫ ጣቢያ ላይ የታየ ህፀፅ ነው ብለን ነው መውሰድ ያለብን፡፡ አንዳንድ ህፀፆች በየትኛውም የዓለማችን ክፍል መከሰታቸው አይቀርም፡፡
ጥያቄ፡- የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን ሪፖርት ካነሳቸው ችግሮች መካከል በአንድ የምርጫ ጣቢያ በሕጉ ከሚፈቀደው 1,000 መራጭ በላይ ተመዝግበው ሲመርጡ ታይተዋል የሚለው አለ፡፡ ይህ ይቻላል ወይ? ያላችሁ መረጃ ምንድነው?
ዶ/ር አዲሱ፡- አንድ ምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው 1,000 መራጮችን ብቻ ነው፡፡ የተመዘገበውም 1,000 መራጭ ነው፡፡ ከ1,000 በላይ መራጭ ነበረ የሚለውን ማጣራት ይኖርብናል፡፡ እኛ የምናውቀው በአንድ ምርጫ ጣቢያ የተመዘገበው ከ1,000 በላይ አለመሆኑን ነው፡፡ ሕጉም የሚለው በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከ1,000 በላይ መራጭ መኖር የለበትም ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ45,000 በላይ ምርጫ ጣቢያዎችን ያቋቋምንበት ምክንያትም 1,000 መራጭ ለአንድ ምርጫ ጣቢያ በሚል አስልተን ነው ከ45,000 በላይ ምርጫ ጣቢያዎችን ያቋቋምነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን ያቀረበው ሪፖርት በቀጥታ አልደረሰንም፡፡ በተጨማሪም ያቀረቡትንም ነጥብ መመርመር አለብን፡፡ ከዚያ አኳያ ይኼንን ጥያቄ በተመለከተ ይኼ ነው ብለን የምንሰጠው መልስ የለም፡፡