Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤት ሕንፃ ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለሁለተኛ ጊዜ መመርያ ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ20 ዓመታት በላይ የይመለስልኝ ጥያቄ ሲቀርብበት በነበረው የድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ጫት ላኪዎች ማኅበር ሕንፃ ጉዳይ ላይ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለሁለተኛ ጊዜ መመርያ ሰጠ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ሕንፃውን ለመረከብ እንዲከፍል የተጠየቀውን ገንዘብ ከባንክ በመበደር እከፍላለሁ አለ፡፡

በድሬዳዋ ከተማ የሚገኘውና ባለ አራት ወለል ሕንፃ በቀድሞ የደርግ መንግሥት በቀላጤ የተወረሰ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የድሬዳዋ አስተዳደር እየተገለገለበት ይገኛል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሕንፃው ጉዳይ ለሁለተኛ ጊዜ ውሳኔን ሊያስተላልፍ የቻለው ለሕንፃው የጋራ ባለቤቶች ለድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤትና ለኢትዮጵያ ጫት ላኪዎች ማኅበር እንዲመለስ የተሰጠው ውሳኔ ሳይፈጸም በመዘግየቱ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ሕንፃው ለቀድሞ ባለቤቶቹ እንዲመለስ ለመጀመርያ ጊዜ ውሳኔ አሳልፎ የነበረው ሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ ይህንንም ውሳኔ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ እንዲያስፈጽም በደብዳቤ አሳውቆት ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ይህንን ውሳኔ የሰጠው ሕንፃውን በመርህ ደረጃ እንዲመለስ በኤጀንሲው ተላልፎ የነበረውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ ይህ ሕንፃ ለባለንብረቶቹ በመርህ ደረጃ እንዲመለስ ኤጀንሲው ወስኖ የነበረው ግን በ1994 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ሕንፃውን እየተገለገለበት ካለው የድሬዳዋ አስተዳደር የቀድሞውን የኤጀንሲውን ውሳኔና አሁን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የተላለፈውን መመርያ ባለመቀበሉ ርክክቡ እየተንከባለለ ቆይቷል፡፡ የድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ወንድወሰን ዘለቀ ለሪፖርተር እንደገለጹትም እንዲመለስላቸው ውሳኔ የተሰጠበትን ሕንፃ መረከብ ያልተቻለው የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የሰጠውን ውሳኔ የድሬዳዋ አስተዳደር በመቃወሙ ነው፡፡ ኤጀንሲው ከ14 ዓመታት በፊት ሕንፃው እንዲመለስ የሰጠውን ውሳኔ ለማስፈጸም ግን በወቅቱ በጫት ማኅበሩና በንግድ ምክር ቤቱ መካከል የነበረው አለመግባባት ርክክቡን እንዳዘገየው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ግን ሕንፃውን እየተጠቀመበት ያለው የድሬዳዋ አስተዳደር ሕንፃውን ለንግድ ምክር ቤቱ እንዳይተላለፍ ያቀረበው ተቃውሞ ሕንፃው ላይ ከፍተኛ ወጪ በማውጣቱና የተለያዩ የአስተዳደሩ ቢሮዎች በሕንፃው ላይ ስለሚገኙ ነው፡፡ በተለይ ሕንፃው ለቀድሞ ባለቤቶቹ መመለሱን በመቃወም ባለፈው ወር እንደገና በደብዳቤ ባቀረበው አቤቱታ፣ ሕንፃውን ለባለንብረቶቹ ከመመለስ አስፈላጊው ካሳ ተከፍሎ መንግሥት (አስተዳደሩ) እንዲያስቀረው የሚጠይቅ ጭምር ነበር፡፡ ይህም ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከደረሰ በኋላ ግን ለጉዳዩ የመጨረሻ እልባት ይሰጣል የተባለውን ደብዳቤ መጻፉን  አቶ ወንድወሰን ይገልጻሉ፡፡ ኤጀንሲውም ይህንኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ተከትሎ የመጨረሻ ነው የተባለውን የመንግሥት አቋም ለድሬዳዋ አስተዳደር ገልጿል ተብሏል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ለኤጀንሲው በላከው ሁለተኛው ደብዳቤው የድሬዳዋ አስተዳደር ለሕንፃው አወጣሁ ያለውን ወጪ ባለመብቶቹ ከፍለው ሕንፃውን እንዲረከቡ የሚያዝና የአስተዳደሩን ሐሳብ ያልተቀበለው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በእዚሁ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ላይ ግን ንግድ ምክር ቤቱና ጫት ማኅበሩ ለመንግሥት እንዲከፍሉ የተጠየቁትን ገንዘብ የማይከፍሉ ከሆነ አስተዳደሩ፤ ተገቢውን ካሳ በመክፈል ለባለመብቶቹ ከሊዝ ነፃ ቦታ እንዲሰጥ የሚል ይገኝበታል፡፡

ኤጀንሲውም ለድሬዳዋ አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ አስተዳደሩ ሕንፃውን ለማስቀረት ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውቋል፡፡

ርክክቡን ለማስፈጸምም አስተዳደሩ ለሕንፃው አወጣሁ ያለውን ወጪ በመረጃ በመቀበል ባለመብቶቹ እንዲከፍሉ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበት ዋጋ 3,783,469 ብር መሆኑን በማሳወቅ ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን ገንዘብ በኤጀንሲው አካውንት፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገባ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በዚሁ ውሳኔ መሠረት ሕንፃው ላይ ወጣ የተባለውን ገንዘብ ለመክፈል እየተዘጋጁ መሆኑን የገለጹት አቶ ወንድወሰን፣ ‹‹የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትና ኤጀንሲው እየወሰዱ ያሉት ወቅታዊ ዕርምጃ ከ20 ዓመታት በኋላ ሕንፃችንን በእጃችን የምናስገባ መሆኑን አረጋግጦልናል፤›› ይላሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ሕንፃውን ለመረከብ የገጠማቸውን ዓይነት ችግር ይገጥመናል ብለው እንደማያስቡም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ንግድ ምክር ቤቱ ለመንግሥት ገቢ እንዲያደርግ የተጠየቀውን ያህል ገንዘብ ንግድ ምክር ቤቱ ስለሌለው ከባንክ ብድር በመውሰድና ክፍያው እንዲፈጸም የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ስለመወሰኑም አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡

ለዓመታት ሲንከባለል የቆየው የድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤት ሕንፃ አመላለስን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድአፍራሽ አሰፋ፣ ‹‹አሁን የሚጠበቀው መንግሥት ሕንፃው ላይ የወጣውን ወጪ ንግድ ምክር ቤቱ እንዲከፍል ነው፡፡›› ክፍያው ከተፈፀመ ባለመብቶቹ መረከብ የሚችሉ መሆኑን የአቶ ወንድአፍራሽ ገለጻ ያስረዳል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት የተጠቀሰውን ገንዘብ ንግድ ምክር ቤቱ የማይከፍል ከሆነ ግን፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ለመንግሥት መክፈል ያለበትን ገንዘብ ከፍሎ ሕንፃውን ሊያስቀረው የሚችል ስለመሆኑም አቶ ወንድአፍራሽ ገልጸዋል፡፡ የድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ግን፣ ‹‹ገንዘቡን ከባንኮች በብድር ለማግኘት የምንችል መሆኑን ቃል ስለተገባልን ለብድር ማስያዥያ የኢትዮጵያ ጫት ላኪዎች ማኅበር ሕንፃን በመጠቀም ብድሩን እንዳገኘን ክፍያውን እንፈጽማለን፤›› ብለዋል፡፡

እንደተባለው ሕንፃው ለቀድሞ ባለንብረቶቹ የሚመለስ ከሆነ በሕንፃው ላይ የአስተዳደሩ ምክር ቤት፣ ድሬ ኤፍኤም ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚገለገሉ በመሆኑ የራሳቸው ቢሮ እስኪያገኙ እዚያው በኪራይ እንዲጠቀሙ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው አቶ ወንድወሰን ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ንግድ ምክር ቤት ሕንፃ በቀላጤ ከመወረሱ በፊት ጫት ማኅበሩና ንግድ ምክር ቤቱ ይገለገሉበት ነበር፡፡ ሕንፃውንም በጋራ የገነቡት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች