Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሲሚንቶን ዋጋ አንረዋል የተባሉ በሕግ ሊጠየቁ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የሲሚንቶ ዋጋ ከ400 ብር በላይ ሆኗል

– ምስርና ወተት ፍተሻ ከሚደረግባቸው ሸቀጦች ውስጥ ተመድበዋል

ሰሞኑን በመንግሥት መግለጫ ሲሰጥበት የቆየውና በሕዝቡ ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የምግብ ሸቀጥ ምስር እንደነበር ይታወሳል፡፡ የምስር ዋጋ እንደ መንግሥት አገላለጽ ‹‹ምክንያታዊ›› ባልሆነ መንገድ እየናረ ቆይቶ አሁን ላይ በኪሎ 55 ብር እያወጣ ይገኛል፡፡ እንደ ምስር ሁሉ የዋጋ ንረት ከታየባቸው ሸቀጦች መካከል ጤፍ፣ በርበሬ፣ ቅቤ እንዲሁም ከጥቂት ቀናት ወዲህ ደግሞ ወተት፣ በዓበይትነት ሲጠቀሱ፣ ምግብ ነክ ካልሆኑት ደግሞ ሲሚንቶን ጨምሮ የግንባታ ግብዓቶች ለዋጋ መጨመርና መባባስ ምክንያት መሆናቸው ታይቷል፡፡

የማዕከላዊ ስታቲስቲክሰ ኤጀንሲ ይፋ ያደረገው የሚያዝያ ወር የአገሪቱ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ወደ አሥር ከመቶ የሚጠጋ ጭማሪ ማሳየታቸውን አስፍሯል፡፡ የኤጀንሲው ወርኃዊ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ተቋሚ አኃዝ እንደሚያሳየው በሚያዝያ ወር ሁሉም የምግብ ክፍሎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡ በተለይ ሥጋ፣ ወተትና አይብ፣ እንቁላል፣ ዘይትና ቅባቶች፣ ስኳር፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ቅመማ ቅመም (ከእነዚህ መካከል ያልተፈጨ ወይም ዛላ በርበሬ) ላይ የዋጋ ጭምሪ ታይቷል፡፡ በዳቦና በእህል ላይ ታይቶ የነበረው የዋጋ ቅናሽ በሚያዝያ ጨምሮ መታየቱንም የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል፡፡ ምግብ ነክ ባልሆኑት ሸቀጦች ላይም የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን ይጠቁማል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ በተለይ በምስርና በሲሚንቶ ዋጋዎች ላይ የታየው ጭማሪ መንግሥትን መግለጫ እንዲያወጣ አስገድዶታል፡፡ በኪሎ ከሃያ ብር በታች ሲሸጥ የነበረው ምስር፣ አሁን ላይ ከ55 ብር በላይ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮም ሆነ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የምስር ዋጋ በኪሎ 50 ብር በነበረበት በሚያዝያ ወር መግለጫ ማውጣታቸው አይዘነጋም፡፡ የዋጋው ጭማሪ ‹‹ኢኮኖሚያዊ ምክንያት›› የለውም በማለት ምርቱን ደብቀዋል፣ ዋጋ ለማስወደድ ሆነ ብለው ከገበያ ሰውረዋል ባለቸው ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ሲያስታውቅ እንደበርም ይታወሳል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የምስር ዋጋ ከመጨመር አልቦዘነም፡፡

ይባስ ብሎም በዋጋ ንረት ማባባስ ላይ ሚና ካስመዘገቡና የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጅንሲ ምግብ ነክ ላልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ግሽበት አስተዋጽኦ አድርገዋል ካላቸው ምርቶች መካል ሲሚንቶ ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ ሲሚንቶ ዋጋ እንደዘበት መጨመር ብቻ ሳይሆን በእጥፍ ወደ ላይ መወንጨፍ የጀመረው የትራንስፖርት ችግር ተከስቷል በተባለበት ሰሞን ሲሆን፣ በወቅቱ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ230 ብር ጀምሮ በመሸጥ ላይ ነበር፡፡ የትራንስፖርት ችግር የተመረተውን ሲሚንቶ ማጓጓዝ አልተቻለም የሚሉ ምክንያቶች ሲደመጡ በቆዩበት አፍታ፣ የሲሚንቶ ዋጋ እየተወነጨፈ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ከ400 ብር በላይ በኩንታል እየተሸጠ ይገኛል፡፡

የዋጋው ንረትም ግሽበትም በዚህ የተገታ አይመስልም፡፡ ከቀናት ወዲህ ደግሞ በወተት ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ብቻም ሳይሆን በኮታ ለሱፐርማርኬቶችና ለኪዮስኮች ሲታደል እንደነበር ታየ፡፡ ባለ 500 ሚሊ ሊትር ወይም ግማሽ ሊትር ወተት በመደበኛው ወቅት ይሸጥበት ከነበረው አሥር ብር ጨምሮ ከ12 እስከ 13 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ይህንን በሚመለከት ሪፖርተር ወተት አቀናባሪ ፋብሪካዎች በተደጋጋሚ ለማነጋገር ሞክሮ ነበር፡፡ ስልክ የተደወለላቸው ኃላፊዎች፣ በጽሑፍ መልዕክት ጭምር ማብራሪያ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም፡፡ ይህም ሆኖ የወተት ምርት ዋጋ ላይ ለታየው ንረት፣ የመኖ ዋጋ ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይ የፍሩሽካ ዋጋ መናር ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ይህም ሆኖ የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶች ከሆኑት መካከል፣ የስኳር ተረፈ ምርት የሆነው ሞላሰስ በፊት ይሸጥበት ከነበረው አራት ብር በኪሎ ወይም 400 ብር በኩንታል ይልቅ፣ በአሁኑ ወቅት በአንድ ብር ከአርባ ሳንቲም በኪሎ ወይም በ140 ብር በኩንታል እንዲሸጥላቸው ማድረግ መጀመሩን ይፋ ካደረገ ሳምንታት ቢቆጠሩም፣ የመጣ ለውጥ ያለ አይስልም፡፡

የወተት ዋጋ መናርን በሚመለከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ወተትና ሥጋ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ጉታ እንዳብራሩት፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ የሚያቀናብሩ ፋብሪካዎችን በመደገፍ ላይ የሚገኘው ኢንስቲትዩቱ፣ የወተት አቅርቦት እጥረት እንዳለ ይገነዘባል፡፡ ምንም እንኳ በምርት ሥርጭትና አቅርቦት ሥራ ላይ የማይሳተፍ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የወተት ምርት ምንጭ ከሆነው ሰላሌ አካባቢ ይመጣ የነበረው የአቅርቦት መጠን ቀንሶ ታይቷል፡፡ ከኦሮሚያ እንስሳት ሀብት ኤጀንሲ ጋር በመሆን ጥናት መካሔዱን የጠቀሱት አቶ ታደሰ፣ በሰሜን ሸዋና በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው የወተት ሀብት ላይ የተደረገው ጥናት ለውይይት ቀርቦ መፍትሔ እንዲበጅለት ለማድረግ ነገሮች በእንጥልጥል ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ መንግሥት የኢንዱስትሪው ተረፈ ምርቶች እየቀረቡ ቢሆንም፣ የመኖ እጥረት መኖሩን አቶ ታደሰ ገልጸው፣ በጥናት ባይደገፍም እንኳ የበልግ ዝናብ መዘግየት ከብቶች የሚመገቡትን የግጦሽ መጠን በመቀነስ በተለይ በሰላሌ አካባቢ የሚገኙ ከብቶች የሚሰጡት ወተት ምርት እንዲቀንስ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡ ከብቶቹ የውጭ ዝርያዎች በመሆናቸው ከፍተኛ የመኖ ፍጆታ ያላቸው በመሆኑ፣ የመኖ አቅርቦት ሲቀንስ የሚሰጡት ወተት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አብራርተዋል፡፡ ‹‹መኖ ላይ ሊሠራ አለመቻሉ ነው ትልቁ ችግር፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ ገበሬዎች የፋብሪካ ተረፈ ምርቶችን እንደልብ ማግኘት አለመቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከቢራ ገብስ የሚወጣ ጭማቂ ተረፈ ምርትም ለገበሬው በሚገባ መጠን እየደረሰ አለመሆኑን አቶ ታደሰ ጠቁመው፣ የወተት ማቀናበሪያ ፋብሪካዎችን ወቅሰዋል፡፡

‹‹የወተት ፋብሪካዎች ሽሚያ ላይ ናቸው፡፡ አቅርቦቱ ዝቅተኛ በመሆኑ አንዱ ከሌላው የበለጠ መጠን ለማግኘት ሽሚያ ውስጥ ነው፡፡ ወተቱን ራቅ ካሉና በመቶ ኪሎ ሜትር ዙሪያ በሚገኝ ርቀት ውስጥ ወተት ማሰባሰቢያ ማዕከል ማቋቋም ይገባቸው ነበር፤›› በማለት የወተት ከሰላሌ በተጨማሪ ቢሾፍቱ፣ አሰላ፣ አምቦ፣ ወለንጪቲ፣ አዋሽ መልካሳ አካባቢዎች አገሪቱ የወተት ተፋሰስ ከሆኑ አካባቢዎች ውስጥ የሚጠቀሱ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ ፋብሪካዎች ወጪ በመሸሽ እንዲህ ካሉ አካባቢዎች ወተት እንደማይሰበስቡ ሲገለጽ፣ ገበሬዎች በበኩላቸው ከመኖ እጥረት የተነሳ ላሞቻቸውን እየሸጡ እንደሚገኙ አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከተማ አካባቢ የሚኖሩ ገበሬዎችን በሚመለከት ያልተቀናጀ አሠራር በመኖሩ ከሚያመርቱበት አካባቢ አምራቾች እየተገፉ፣ ከብቶቻቸውን እየሸጡ በሌሎች ሥራዎች ላይ ለመሠማራት መገደዳቸውን አብራርተው፣ በከተማ ያለው የወተት ሀብት እንደ ህንድ አገር ተቀናጅቶ ውጤታማ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች የወተት ዋጋ እየናረ አቅርቦቱ እየጠፋ መምጣቱ ሲታይ፣ ምንም እንኳ በቀጥታ የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ የሥራ ድርሻው ባይሆንም እየታዩ ያሉትን የዋጋ ለውጦች እያጠና እንደሚገኝ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ገልጿል፡፡ በባለሥልጣኑ የገበያ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢቲሳ ደሜ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ዋጋቸው ጨምሯል በተባሉት ምርቶች ላይ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር በመሆን ጥናት እየተካሔደ ይገኛል፡፡ የምስር ዋጋ ጭማሪ አግባብነትና ገበያ ነክ ምክንያታዊነት ያለው ስለመሆኑ እያየን ነው ያሉት አቶ ኢቲሳ፣ ከዚህ ባሻገር በግንባታ ግብዓቶች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ላይ በተካሔደ ጥናት ለሕግ የሚቀርቡ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሲሚንቶ ከ230 ብር ጀምሮ ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ከ400 ብር በላይ የደረሰበት አኳኋን በቂ ምክንያት በሌለበት፣ ትራንስፖርት የለም በማለት ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል የተባሉት ላይ ጥናት ተደርጎ፣ በዚህ ሳምንት በችሎት ጉዳያቸው የሚታዩ ፋይሎች እንዳሉ ይፋ አድርገዋል፡፡

ወተት ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ የቅርብ ጊዜ በመሆኑ፣ አሳማኝነቱ ገና እየታየ ያሉት አቶ ኢቲሳ፣ የዋጋው ጭማሪ ምክንያታዊነትና ፍትኃዊነት ታይቶ የሚያስጠይቅ ከሆነ በሕግ እንደሚታይ፣ የባለሥልጣኑ ባለሙያዎችም የዋጋውን መጨመር ከምንጩ ለመርመር የመስክ ጉብኝት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የዋጋ ጭማሪ ከሚደረግባቸው ዘዴዎች መካከል ስምምነት በማድረግ፣ በምርት ቅብብሎሽ ሒደት ወቅት ዋጋ ያለአግባብና ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ማለትም የፍላጎትና የአቅርቦት ወይም የገበያ ኃይሎች የሚፈጥሩት የዋጋ ለውጥ ሳይሆን ሆን ተብሎ የሚደረግ ጭማሪ ከተገኘ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ የንግድ ውድድርና የሸማቾች መብት ጥበቃ ባለሥልጣን ይገልጻል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች