Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመሬት ሊዝ መጫረቻ ዋጋ እየጨመረ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፈው ሳምንት በተከፈተው 14ኛ የዙር ሊዝ ጨረታ ከዚህ ቀደም ከተለመደው ውጪ አብዛኞቹ ተወዳዳሪዎች በካሬ ሜትር ያቀረቡት የመጫረቻ ዋጋ፣ ከፍተኛና ተመሳሳይነት ያለው ሆኖ ቀርቧል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለቡ አካባቢ ለቀረበ 664 ካሬ ሜትር ቦታ አቶ ኃይለ ጊዮርጊስ ታምራት የተባሉ ባለሀብት፣ በካሬ ሜትር 36,555 ብር በማቅረብ የዙሩን ሪከርድ ሰብረዋል፡፡

በዚህ ክፍለ ከተማ ለቀረቡት ዘጠኝ ቦታዎች አብዛኛዎቹ ተወዳዳሪዎች በካሬ ሜትር ከ20 ሺሕ ብር በላይ በማቅረብ የተወዳደሩ ሲሆን፣ የቀረበው መጫረቻ ዋጋ ቀደም ሲል በአካባቢው ከተሰጠው አራት ሺሕ ብር አንፃር እጅግ ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 መሪ ሎቄ አካባቢ ለቀረቡ 37 ቦታዎች በካሬ ሜትር ከ20 ሺሕ ብር በላይ የቀረበ ሲሆን፣ የዙሩ አነስተኛ ዋጋ ወ/ሮ ደጊቱ አበጋዝ በተባሉ ባለሀብት የቀረበው ነው፡፡ ወ/ሮ ደጊቱ በአካባቢው ለጨረታ የቀረበውን 475 ካሬ ሜትር ቦታ በካሬ ሜትር 6,669 ብር ያቀረቡ ሲሆን፣ ጨረታው በተከፈተበት ወቅት አግራሞት ፈጥረዋል፡፡ በዚህ አካባቢ በአብዛኛው ሲቀርብ የቆየው ከአሥር ሺሕ ብር በታች ነበር፡፡

በኮልፌ ቀራኒዮ 46 ቦታዎች ለጨረታ ቀርበው፣ አቶ ሳሙኤል መብራቱ የተባሉ ባለሀብት፣ በካሬ ሜትር 30,101 ብር በማቅረብ ለአካባቢው እንግዳ የሆነ የመጫረቻ ዋጋ በማቅረብ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ በዚህ አካባቢ በካሬ ሜትር ከአምስት ሺሕ ብር የበለጠ ዋጋ ቀርቦ እንደማያውቅ የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባለሙያዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  

በክፍለ ከተማው የቀረቡ አብዛኛዎቹ ቦታዎች በካሬ ሜትር ከ18 ሺሕ ብር በላይ ቀርቦላቸዋል፡፡ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቱሉ ዲምቱ አካባቢ ሁለት ተወዳዳሪዎች ብቻ አምስትና ስድስት ሺሕ ብር ያቀረቡ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ተወዳዳሪዎች ከ12 ሺሕ ብር በላይ በካሬ ሜትር አቅርበዋል፡፡ በዚህ ቦታ ከፍተኛው የሊዝ ዋጋ አራት ሺሕ ብር አካባቢ ነበር፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር በ14ኛው ሊዝ ጨረታ በቦሌ፣ በንፋስ ስልክ፣ በኮልፌ ቀራኒዮና በአቃቂ ክፍላተ ከተሞች 179 ቦታዎች ለጨረታ አቅርቧል፡፡ ጨረታው ግንቦት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ተከፍቶ ግንቦት 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ተዘግቷል፡፡ በዚህ ጨረታ ከሌላው ጊዜ አንፃር ሲታይ አብዛኛዎቹ ተጫራቾች ከፍተኛ የመወዳደርያ ገንዘብ አቅርበዋል፡፡ የቀረቡት ቦታዎች ለመኖርያ፣ ለፓርኪንግ፣ ለቅይጥና ለቢዝነስ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች