Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአፍሪካ ልማት ባንክ የተወዳደሩት አቶ ሱፍያን አህመድ ሳይመረጡ ቀሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፍሪካን ልማት ባንክን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ዕጩ ሆነው የቀረቡት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፍያን አህመድ ሳይመረጡ ቀሩ፡፡ ናይጄሪያዊ የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስትር የ55 ዓመቱ ኦኪንውሚ ኦዴሲና የባንኩ ፕሬዚዳንት አድርጎ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ግንቦት 20 ቀን 2007 ዓ.ም. መርጧቸዋል፡፡

ባንኩን ላለፉት አሥር ዓመታት ሲያስተዳድሩት የቆዩትን ሩዋንዳዊውን ዶናልድ ካቤሩካን ለመተካት አቶ ሱፍያንን ጨምሮ ስምንት ዕጩዎች ቀርበው የነበረ ቢሆንም፣ በምርጫ ሥነ ሥርዓቱ አቶ ሱፍያን በሁለተኛ ዙር ከውድድር ውጪ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

አቶ ሱፍያን ቀደም ብሎ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ሆነው ባስመዘገቡት ስኬት የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ተጠብቆ ነበር፡፡ አቶ ሱፍያን ከ20 ዓመታት በላይ በመሩት ሚኒስቴር ካከናወኗቸው ዓበይት ተግባራት መካከል፣ በአገሪቱ ሲከሰት የነበረውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አኃዝ በማውረድ ረገድ የተጫወቱት ሚና ይነገርላቸዋል፡፡ በአገሪቱ አዲስና የቅርብ ክስተት ከሆኑት ውስጥ፣ አገሪቷ በዓለም ቦንድ ገበያ ውስጥ ተሳታፊ መሆኗም ከሚጠቀሱላቸው ተግባራት መካከል ይካተታል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ሱፍያን የባንኩ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ የሆነውን ፈረንሳይኛ ቋንቋ መናገር የማይችሉ በመሆናቸው ከፍተኛ ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል የገመቱም ነበሩ፡፡ በተለይ አንዳንድ የመስኩ ባለሙያዎች የፕሬዚዳንትነቱን ውድድር ለምዕራብ አፍሪካ አገሮች ተወካዮች የተሻለ ቅድመ ግምትን ሰጥተውም ነበር፡፡

በስምንተኛው የባንኩ ጉባዔ ላይ ይፋ በሆነው የምርጫ ሥነ ሥርዓት ላይ አሸናፊ በመሆን የተመረጡት ናይጄሪያዊው ኦዴሲና ‹‹ዛሬ ታላቅ ኃላፊነትን ተቀብያለሁ፤›› በማለት ደስታቸውን ከሚጠብቃቸው ኃላፊነት ጋር በማያያዝ ገልጸዋል፡፡

በቅድመ ምርጫ ወቅት ስምንቱ ዕጩዎች ለውድድሩ የየራሳቸውን ስኬትና አሸናፊ ከሆኑ ለባንኩ ይበጃል ያሉዋቸው ዕቅዶች አቅርበው ነበር፡፡ በተለይ አቶ ሱፍያን ኢትዮጵያ ላለፉት አሥር ዓመታት አስመዝግባዋለች ያሉትን የኢኮኖሚ ዕድገትና የገንዘብ ግሽበትን በመቆጣጠር ልማትን እንዴት ማፋጠን ያስችላል ያሉትን ዕቅድ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ካቤሩካ በበኩላቸው በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ለተተኪያቸው የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት በማስተላለፍ መልካም ምኞታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡ ‹‹ለተተኪዬ መልካሙን ሁሉ እመኝለታሁ፡፡ አሥር ዓመት በፍጥነት መሄዱን አይቻለሁ፡፡ እጅግ ውስብስብና ውጥረት የተሞላበት ሥራ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን አስደሳች የሥራ ወቅት ነበር፡፡ በእርግጥ ይኼን ሥራ ብዬ ከምጠራው ተልዕኮ ብለው ይሻለኛል፤›› ሲሉ ባንኩን ለአሥር ዓመት ያስተዳደሩት ዶናልድ ካቤሩካ በባንኩ ስላሳለፉት የሥራ ዘመን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች