Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ተከሰሱ

የመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ተከሰሱ

ቀን:

–  የኮበለሉ መኮንንና አክራሪነትን ሰበኩ የተባሉ ሼክም ክስ ተመሥርቶባቸዋል

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዚዳንት መሆናቸው የተገለጸውና አድራሻቸው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ማክሰኝት ከተማ መሆኑ የተጠቀሰው አቶ ዘመነ ምሕረቱ ታከለ፣ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

ተከሳሹ በሰው ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ፣ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ ዓላማ ካለውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ግንቦት ሰባት ድርጅት ጋር አብረው ለመሥራት መስማማታቸውን፣ ክስ የመሠረተባቸው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ መስከረም 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ በሚገኘው የመኢአድ ጽሕፈት ቤት ውስጥ አባላቱን በመሰብሰብ ‹‹የወያኔ መንግሥት መውደቂያው ደርሷል፡፡ አንድ የጦር አውሮፕላን፣ 12 የጦር ጄኔራሎች መንግሥትን ከድተው ወደ ኤርትራ ገብተዋል፡፡ ኢሕአዴግን በጦር ካልሆነ በሰላማዊ መንገድ ከሥልጣን አይለቅም፡፡ የሕዝብ እምቢተኝነትን በመፍጠር የወያኔን መንግሥት መጣል አለብን፡፡ በ2007 ዓ.ም. የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ አይካሄድም፡፡ ወደ ምርጫው አንገባም፡፡ ሌላ አማራጭ መጠቀም አለብን…›› በማለት ሕጋዊ አማራጮችን ትተው የኃይል አማራጮች ለመጠቀም ሲቀሰቅሱ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቱ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቦምብ አወራወርና መሣሪያ መፍታት የሚችል በማነጋገርና በጥምቀት በዓል ላይ ተልዕኮ መፈጸም የሚችል ሰው ሲያፈላልጉ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ በአጠቃላይ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የሽብር ዓላማን ለማራመድ በማሰብና የሽብርተኝነትን ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴርና ማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውን የክስ ሰነዱ ያብራራል፡፡

ከመኢአድ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር በአንድ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው፣ አድራሻቸው አዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ውስጥ መሆናቸው የተጠቆመው አቶ ጌትነት ደርሶ አዱኛ ናቸው፡፡ እሳቸውም የግንቦት ሰባት ድርጅት አባል በመሆን እንደ አቶ ዘመነ ምሕረቱ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም መንቀሳቀሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ተከሳሹ ከድርጅቱ ጋር አብሮ ለመሥራት በመፈለግ ወደ ኤርትራ በመሸጋገር የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር ከሆኑት ዶ/ር ክፈተው አሰፋ ጋር በመገናኘት፣ ስለድርጅቱ ዓላማ ፖለቲካዊ ሥልጠና መውሰዳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በወታደራዊ ሥልጠና የመሣሪያ ተኩስ፣ የዒላማ ተኩስ፣ መከላከልና ማጥቃት በድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችና በኤርትራ መንግሥት ወታደሮች መሠልጠናቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ ተከሳሹ ለድርጅቱ አባላትን እንዲመለምሉና ወደ ኤርትራ ወታደራዊ ሥልጠና መስጫ ካምፕ እንዲልኩ የፌስቡክ አካውንት [email protected] የሚል አድራሻ እንደተሰጣቸውም ክሱ ያብራራል፡፡ በአጠቃላይ የሽብር ድርጅቱ አባል በመሆናቸው፣ በማንኛውም መልኩ በሽብርተኝነት ድርጅት ውስጥ መሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸው የክስ ቻርጁ ያስረዳል፡፡

በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸው ሌላው  ተጠርጣሪ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነዋሪ መሆናቸው የተገለጸው አቶ መለሰ መንገሻ የተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ፣ ራሱን የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ብሎ በሚጠራው ቡድን ውስጥ አባል ሆነው የተገኙ መሆናቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ጠቁሟል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳይ ለማድረስ መንቀሳቀሳቸውን፣ በትጥቅ ትግል ሥልጣን ለመያዝ ከሚንቀሳቀስ ቡድን ጋር ማበራቸውን፣ በኤርትራ አውሃጅራ አካባቢ ለሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድን ከፍተኛ አመራር ከሆኑት ግለሰብ ጋር በተለያዩ ጊዜያት በስልክ በመገናኘት አባላትን ይመለምሉ እንደነበር በክሱ ተካቷል፡፡ ተከሳሹ የኢትዮጵያ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚበዙበት አካባቢ እንዴት ጥቃት መፈጸም እንዳለበት ለሽብር ድርጅቱ አመራሮች ገለጻ በማድረጋቸው፣ በሽብር ተግባር ላይ በመሳተፍ ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ሌላው ክስ የመሠረተው የአየር ኃይል ባልደረባ በሆኑት ምክትል መቶ አለቃ አንተነህ ታደሰ ዘውዴ በተባሉት ተጠርጣሪ መኮንን ላይ ነው፡፡

ምክትል መቶ አለቃው ወደ ኤርትራ እንዲኮበልሉ ምክንያት የሆናቸው ቀደም ብሎ የአየር ኃይል ባልደረባ የነበረውና ባልታወቀ ምክንያት በጥቅምት ወር በ2007 ዓ.ም. ወደ ኤርትራ መሄዱ በተጠቀሰው ምክትል መቶ አለቃ ዳንኤል የሸዋስ ጋር በፌስቡክ በመገናኘት መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ “Doni Yeshu Sweet” በሚል አድራሻና በተለያዩ ስልኮች ይገናኙ እንደነበርና ታኅሳስ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ከደብረ ዘይት አየር ኃይል በመነሳት ወደ ኤርትራ ጉዞ እያደረጉ መንገድ ከሚያሳያቸው ሌላ ሰው ጋር ታኅሳስ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ወሮታ ከተማ ላይ መያዛቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ወንጀልም መከሰሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በተለያዩ የክስ መዝገቦች ክስ ከመሠረተባቸው ውስጥ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ቶንጎ ወረዳ ሻንቦላ ከተማ ሻንቦላ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ ነዋሪ መሆናቸው የተጠቀሰው ሼክ መሐመድ አብዱል ቃድር የሚባሉ ተጠርጣሪ ናቸው፡፡

ተከሳሹ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደርና ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት የእስልምና ሃይማኖትን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ በኃይል እስላማዊ መንግሥት ለማቋቋም ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

ሼክ ሐመድ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቶጎ ወረዳ ጎሬ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ውስጥ በሚገኙ መስጊዶች በመዘዋወርና ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በማሰባሰብ፣ ‹‹እኛ የካዋርጃ እምነት ተከታይ መሆን አለብን፡፡ ለመንግሥት አትታዘዙ፡፡ ግብር አትክፈሉ፡፡ ጤና ጣቢያ ሄዳችሁ እንዳትወልዱ፡፡ ወላጆች ልጆቻችሁን ትምህርት ቤት አትላኩ፡፡ የእኛን አስተምህሮ የማይከተል ካፊር ነው፤›› ብለው በግልጽ በመናገር፣ ኅብረተሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡

‹‹የሻንቦላና የአካባቢው ነዋሪዎች በአጠቃላይ መመራት ያለብን በሸሪዓ ሕግ ወይም እስላማዊ መንግሥት መሆን አለበት፤›› በማለት በመቀስቀስና የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ በማሴር፣ በማዘጋጀትና በማነሳሳት ወንጀል ሼኩ መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...