Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከአንድ ሺሕ በላይ መራጮችን ያስተናገዱ የምርጫ ጣቢያዎች ከሕጉ ተጣርሰዋል ተባለ

ከአንድ ሺሕ በላይ መራጮችን ያስተናገዱ የምርጫ ጣቢያዎች ከሕጉ ተጣርሰዋል ተባለ

ቀን:

–  ምርጫ ቦርድ ማጣራት አደርጋለሁ ብሏል

የተሻሻለው የምርጫ ሕግ በአንድ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብና መምረጥ ያለበት መራጭ ከአንድ ሺሕ በላይ መሆን የለበትም ቢልም፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በርከት ያሉ የምርጫ ጣቢያዎች ከአንድ ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን በማስመረጥ ሕጉን መጣረሳቸው ታይቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ ‹‹እኛ የምናውቀው በሁሉም ምርጫ ጣቢያ አንድ ሺሕና ከዚያ በታች መራጭ መመዝገቡንና መምረጡን ነው፡፡ የተባለውን ስህተት አጣራለሁ፤›› ብሏል፡፡

ይኼንኑ ችግር የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ጊዜያዊ ሪፖርቱ ጠቁሞታል፡፡ የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ያሰማራቸው ጋዜጠኞችም በአንድ የምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺሕ በላይ መራጮች መሳተፋቸውን በማስረጃ ማረጋገጥ ችለዋል፡፡

የሪፖርተር ጋዜጠኞች ከጎበኟቸው የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ የተወዳደሩበት በኦሮሚያ አርሲ ዞን ምርጫ ጣቢያ ኢተያ 01-2ሀ-1 ማሳያ ነው፡፡

አቶ አባዱላ ከላይ በተገለጸው የምርጫ ጣቢያ 1,214 ድምፅ በማግኘት አንደኛ ደረጃ ሲይዙ፣ የኦብኮ ተፎካካሪያቸው ደግሞ 10 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ምርጫ ጣቢያ ብቻ 224 መራጮች ከሕጉ በተቃራኒ ተሳትፈዋል፡፡

በፓርላማው የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በተወዳደሩበት በስልጤ ዞን ዱና ምርጫ ጣቢያ በብቸኝነት ተወዳድረው 1,459 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ምርጫ ጣቢያ ከሕጉ በተቃራኒ 459 መራጮች ተስተናግደዋል ማለት ነው፡፡ ወ/ሮ ሙፈሪያት በተወዳደሩበት ሌላ ምርጫ ጣቢያ በቅበት ምርጫ ክልል ሸ/ገሬም ቁጥር 0-1 ምርጫ ጣቢያ ብቻቸውን ተወዳድረው 1,370 ድምፅ አግኝተዋል፡፡ ይኼ ማለት በምርጫ ጣቢያ ከሕጉ በተጣረሰ መልኩ 370 መራጮች ተሳትፈዋል፡፡

 በተጨማሪም በወላይታ ሁለገብ ምርጫ ክልል በቦዲቱ ቆርኬ ምርጫ ጣቢያ ከመድረክ ዕጩ ጋር የተወዳዳሩት የኢሕአዴግ ተወካይ አቶ አማኑኤል አብረሃም 1,182 ድምፅ ሲያገኙ፣ የመድረክ ተፎካካሪያቸው አንደ ድምፅ አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ የምርጫ ጣቢያ 183 መራጮች ያላግባብ ተስተናግደዋል፡፡

ሌላው በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ስቄ 02 ምርጫ ክልል የኢሕአዴጉ አቶ ዮሴፍ ዳኤሞ 1,051 ድምፅ ያሸነፉ ሲሆን የመድረክ፣ የሰማያዊና የቅንጅት ተፎካካሪዎቻቸው ደግሞ አንደ ቅደም ተከተላቸው 171፣ 19፣13 ድምፆች አግኝተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ የምርጫ ጣቢያ 254 መራጮች ያላግባብ ተሳትፈዋል፡፡

በደሴ ከተማ ሮቢት ክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው በሚወዳደሩበት ምርጫ ጣቢያ 22 ላይም 1,049 መራጮች ተመዝግበው የነበረ መሆኑን ሪፖርተሮቻችን አረጋግጠዋል፡፡

ጊዜያዊ የምርጫ ውጤቱን ቦርዱ ይፋ ባደረገበት ወቅት ስለጉዳዩ የተጠየቁት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር፣ ‹‹አንድ ምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው አንድ ሺሕ መራጮችን ብቻ ነው፡፡ እኛ የምናውቀው በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺሕ በላይ መራጭ አለመመዝገቡን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የምርጫ ሕጉ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ከአንድ ሺሕ በላይ መራጭ መመዝገብ የለበትም እንደሚል የገለጹት ዶ/ር አዲሱ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ 45,795 ምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ የተደረገውም በዚሁ ሥሌት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከአንድ ሺሕ በላይ ያስተናገዱ ምርጫ ጣቢያዎችን ማጣራትና መመርመር ይኖርብናል፡፡ በመሆኑም ይኼንን ጥያቄ በተመለከተ ይኼ ነው ብለን የምንሰጠው መልስ የለም፤›› ብለዋል፡፡

የተሻሻለው የኢትዮጵያ ምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. በአንቀጽ 22(6) ላይ ‹‹እያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው የመራጮች ብዛት ከ1,000 መብለጥ የለበትም፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...