Tuesday, December 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የገዥው ፓርቲና የተቃዋሚዎች መሠረታዊ ችግሮች

የምርጫ 2007 ሒደትና ይፋ የተደረገው ጊዜያዊ ውጤት የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር አብዛኞቹን ችግሮች ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አጋሮቹ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የውጤት ሪፖርት መሠረት፣ ሪፖርት ከተደረገባቸው 442 የፓርላማ ወንበሮች ሁሉንም ጠቅልለው ወስደዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ባዶአቸውን አጨብጭበው ቀርተዋል፡፡ በአፍሪካ አኅጉር በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ በምትባለውና ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባትና በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ ፍላጎቶች በሚንፀባረቁባት አገር ውስጥ፣ ገዥው ፓርቲ ከነአጋሮቹ ምርጫውን ሙሉ በሙሉ አሸነፈ በሚባልበት ደረጃ በጊዜያዊ ውጤቱ ድሉ ሲገለጽ ችግሩ ምንድነው ብሎ መነጋገር ጠቃሚ ነው፡፡ ምንም እንኳ ይፋዊ ውጤቱ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚነገር ቢሆንም፣ በጊዜያዊው ውጤት ላይ በመመሥረት ዙሪያ ገብ ችግሮችን ማንሳት አስፈላጊ ነው፡፡

  1. የገዥው ፓርቲ ከመጠን በላይ መግዘፍ 

ኢሕአዴግ ላለፉት 24 ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየ ፓርቲ ነው፡፡ ባለፉት አራት ምርጫዎችም አማካይነት በየአምስት ዓመቱ የመንግሥት የሥልጣን ኮንትራቶች ሲያድስ ኖሯል፡፡ አሁንም ለመጪዎቹ አምስት ዓመታት ኮንትራቱን ለማደስ ተዘጋጅቷል፡፡ ኢሕአዴግ የመንግሥትን ሥልጣን ለረጂም ጊዜ በመቆጣጠሩ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ተንሰራፍቶበታል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ መንግሥትን የሚመራ በመሆኑ ልዩ የተጠቃሚነት ዕድል አለው ቢባልም፣ እንደ ኢሕአዴግ ግን ከመጠን በላይ የተገለገለበት አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ኢሕአዴግ ከበፊት ጀምሮ በተደጋጋሚ የሚተችበት አንዱ ችግር የፓርቲና የመንግሥት ተግባራትን መቀላቀል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግሥት የሰው ኃይል፣ መዋቅሮች፣ ቁሳቁሶችና የመሳሰሉትን ከወረዳ እስከ ፌዴራል ድረስ እንደሚገለገልባቸው በስፋት ይተቻል፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ የመገናኛ ብዙኃንን እንደ ልሳኑ እንደሚጠቀምባቸው በርካታ እሮሮዎች ይቀርባሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በምርጫ ወቅት ከተመደበለት የአየር ሰዓት በላይ በተለያዩ የዜና ሽፋኖችና ፕሮግራሞች ይጠቀማል፡፡ በአሁኑ ምርጫም በስፋት ታይቷል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ሕጉ መሠረት ለምርጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችንና የሚዲያ የአየር ሽፋን በተገቢው መንገድ ለማግኘት አልታደሉም፡፡

ኢሕአዴግ በመንግሥት ተቋማት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በየደረጃው በተደራጁ የወጣቶችና የሴቶች ማኅበራት፣ በአርሶ አደሩ ማሳዎችና በተለያዩ ሥፍራዎች ያደራጃቸው ሰባት ሚሊዮን ያህል አባላት አሉት፡፡ ከእነዚህ አባላት ከሚያገኘው የገንዘብ፣ የዕውቀትና የጉልበት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በርካታ ደጋፊዎቹ የሚያጎርፉለት ገንዘብ አለው፡፡ በዚህም ምክንያት ምርጫ ሲደርስ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ወቅቶችም ከመጠን በላይ ገዝፎ ይታያል፡፡ በዚህ ደግሞ አጋሮቹ ታክለውበት የተራራ ያህል እንዲገዝፍ ያደርገዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩን ይውጠዋል፡፡

ኢሕአዴግ በሚመራው መንግሥት አማካይነት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ ያዘጋጁትን ሰላማዊ ሠልፍ ከመከልከል ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ይደፍቃቸዋል፡፡ በውስጣቸው ያለውን ደካማ ጐን በመጠቀም ይፈረካክሳቸዋል፡፡ ሕዝብ ዘንድ ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረትም ያደነቃቅፈዋል፡፡ ይህ ብዙ የተባለበት በመሆኑ ሁልጊዜም ምላሽ ሳያገኝ የቀጠለ ነው፡፡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን የተቀላቀሉ አብዛኞቹ ፓርቲዎች የሚያሰሙት ምሬት ይኼንኑ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ጠበበ የሚለው የዘወትር ወቀሳ አሁንም ድረስ በማስተጋባት ላይ ነው፡፡ አባላቶቻቸው የተሰሩባቸው፣ የተደበደቡባቸውና የተንገላቱባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ አቤቱታ የሚያሰሙበት ዋነኛ ችግር ነው፡፡

ኢሕአዴግ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ ያሰኘው የኢኮኖሚ ዕድገቱ ጉዳይ፣ በዚህ ምርጫ ሰሞንም ከመጠን በላይ ተስተጋብቷል፡፡ ምርጫውን የዘገቡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሙሉ በኢሕአዴግ ዘመን የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ዕድገት ሲያወሱ፣ በአፍሪካ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ደግመው ደጋገመው አውስተዋል፡፡ ኢሕአዴግ በዚህ ስኬቱ ብቻ እንደሚመረጥም ተንብየዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ረገድ ያለውን ጉዳይ ‹‹ተከድኖ ይብሰል›› ነው ያሉት፡፡ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያዊያን ኢሕአዴግ በልማቱ ሲሳካለት ለምን በፖለቲካው መስክ ወደኋላ ቀረ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለምን ይታሰራሉ የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ ተቃውሞ መስማት የማይፈልገው ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነቶቹን ዕርምጃዎች ወስዶ ቢገዝፍ ምን ይገርማል እየተባለ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከላይ የተጠቀሱትን ቢያስተባብልም፣ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ግን እጅግ የፈረጠመውን ኢሕአዴግንና የጫጩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ነው እያሳየ ያለው፡፡ ኢሕአዴግ በሕዝብ ድምፅ ነው የተመረጥኩት ቢልም፣ ተቃዋሚዎችን የሚመርጥ ሌላ ፍላጎት ያለው ሕዝብ የለም ወይ የሚል ጥያቄ ይቀርባል፡፡ ይኼ በቅጡ ካልተመለሰ አስቸጋሪ ነው፡፡     

  1. ምስቅልቅላቸው የወጣው ተቃዋሚ ፓርቲዎች

ኢሕአዴግ ሥልጣን ይዞ የሽግግር መንግሥቱ ሥራ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ቁጥራቸው በጣም የበዛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተመሥርተዋል፡፡ ኅብረ ብሔራዊና ብሔር ተኮር የሆኑት እነዚህ ፓርቲዎች ተመሥርተው ሥራ መጀመራቸው በበጎ ጎኑ የሚወሳ ቢሆንም፣ ለረጂም ጊዜያት የተስተዋሉባቸው ችግሮች ግን ሳይቀረፉ ቀጥለዋል፡፡ በምርጫ ጊዜ እንደ መስቀል ወፍ ብቅ የሚሉትን ትተን፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ጎላ ብለው የታዩትን በተመለከተ ስንነጋገር በርካታ ችግሮቻቸው እንዳሉ ናቸው፡፡ ኅብረት ሲመሠርቱ፣ ግንባር ሲፈጥሩ፣ ትብብር ሲሉ፣ ሲቀናጁ፣ ሲዋሀዱና ሲፈራርሱ ኖረዋል፡፡ በአስቸጋሪው ምኅዳር ውስጥ በርካታ ጫናዎችን ተቋቁመው ከማይጋፉት ባላጋራ ጋር ሲወድቁና ሲነሱ እዚህ የደረሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የመጡበትን መንገድ ሲገመግሙና መዋቅራዊ ለውጥ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡ ስህተቶችን በተደጋጋሚ በመሥራት አንዱ ከሌላው መማር አልቻሉም፡፡ በአባላቶቻቸውና በደጋፊዎቻቸው ከመመካት ይልቅ ውጭ ውጩን ሲያዩ የትም የቀሩ አሉ፡፡

ፖለቲካ ሰጥቶ የመቀበል መርህ መሆኑን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እያወቁ በተግባር ላይ ማዋል ያቃታቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ በተደጋጋሚ ከፈጸሙዋቸው ስህተቶች መማር አቅቷቸዋል፡፡ የፖለቲካው ዓውድ የሚፈልገውን ፖለቲካዊ ግንኙነት (Political Engagement) ከማደፍረስ በተጨማሪ፣ በጠራ ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተ ፕሮግራም መቅረፅ አልቻሉም፡፡ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ፖሊሲዎች ሲነድፉ አልታዩም፡፡ አባላትን በብዛትና በጥራት መመልመል አልቻሉም፡፡ ለመደራደር የሚያስፈልጉ ብልኃቶችንና ክህሎቶችን ያልተላበሱ በመሆናቸው፣ ከማይችሉት ባላጋራ ጋር እየተላተሙ የትም ወድቀው ቀርተዋል፡፡ የፈለገውን ያህል የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩ ይጥበብ ለዓላማቸው ስኬት ማንኛውንም መስዋዕትነት የሚከፍሉ የሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን አላፈሩም፡፡ ይልቁንም የገዥውን ፓርቲ ስህተቶችና ግድፈቶችን በማነፍነፍ ብቻ በመጠመዳቸው የሠለጠነ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ማከናወን አቅቷቸዋል፡፡ የኢሕአዴግን ተቃዋሚዎች ከማንጠራራት የዘለለ የሰፊውን ሕዝብ ልብ ማግኘት አልቻሉም፡፡

እንዲህ ዓይነት ትችቶች መቅረብ ያለባቸው በሠለጠነና በተመቻቸ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ ለሚሠሩ ፓርቲዎች ነው የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ መነሳቱም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ የሚታወቁት ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቁ ችግራቸው ባላጋራቸውን ጠንቅቀው አለማወቃቸው ነው፡፡ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኢሕአዴግ ጋር በሚደረግ ሙግት አንድ አዳራሽ ውስጥ ቢገኙ፣ በአገሪቱ ሁለገብ ጉዳዮች ላይ ያላቸው አመለካከት አንድ ነው፡፡ ሁሉም በአንድነት ለክርክር ተዘጋጅተው የመጡ እስኪመስሉ ድረስ ገዥው ፓርቲ ላይ ይረባረባሉ፡፡ ለምሳሌ መድረክ፣ ሰማያዊ፣ ኢዴፓ፣ መኢአድ፣ ወዘተ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ኢሕአዴግን አንድ ላይ ሲዘምቱበት አንድ ለመሆን ምን ያቅታቸዋል? በመካከላቸው ፈጥጦ የማይታየውን አብዛኛውን ልዩነት በማቻቻል ለምን አማካይ የሆነ ፕሮግራም ነድፈው አይዋሀዱም? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቁ ችግር የመርህ ነው፡፡ የሚተዳደሩት እንደ መሪዎቻቸው ፍላጎት ነው፡፡ ብዙዎቹ ቀለብ የሚሰፈርላቸው ከውጭ በመሆኑና በአባላትና በደጋፊዎች ላይ ስለማይተማመኑ ምርጫ ውስጥ የሚሳተፉት በተከፈለ ልብ ነው፡፡ ግንባር ለመፍጠርም ሆነ ለመዋሀድ እንቅስቃሴዎች ሲጀመሩ ደጅ ያሉት ‹‹አዛዦች›› ይሁንታ ከሌለበት ይከሽፋሉ፡፡ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን እውነታ መሠረት ያላደረገ ምስቅልቅል እንቅስቃሴ ይጀምሩና ሕዝቡን ግራ ያጋቡታል፡፡ ይኼ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ የትኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ምን ዓይነት ርዕዮተ ዓለም እንደሚያራምድ በግልጽ በማይታወቅበት አገር ውስጥ ሊበራል፣ ግራ ዘመም፣ ቀኝ ዘመም፣ ሶሻል ዴሞክራት፣ ወዘተ. ሲባል ቀልድ ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታና የአገሪቱን ሕዝብ ፍላጎት ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ እያቀረቡ፣ በርዕዮተ ዓለም አለመጣጣም አንድ መሆን አይቻልም ሲሉ ከቀልድም በላይ ነው፡፡ አሁን ያለው የተመሰቃቀለ አካሄድ ቆሞ በሰከነ መንገድ የሚመራ፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ቁርጠኛ የሆነ፣ አባላትንና ደጋፊዎችን አደራጅቶና አንቅቶ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራሱን ያላዘጋጀ ፓርቲ ባይኖር ይሻለዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዥውን ፓርቲ ጫና ይቋቋሙ ሲባል አጉል ምክር መሆን የለበትም፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ገዥውን ፓርቲ በመርህ ላይ ተመሥርቶ የሚወዳደር ጠንካራ ፓርቲ የግድ ይላል፡፡ ሁልጊዜም ለሕግ የበላይነት መቆም፣ ከሕገወጥ ተግባራት ራስን ማራቅ፣ ፖለቲካን የትርፍ ጊዜ ሥራ አለማድረግ፣ ወጣቶችን ለአመራር ማብቃትና በወሳኝ ቦታዎች መሰየም፣ ጊዜው የሚፈልገውን ሥልጡን ፖለቲካ ማራመድ፣ ከጥላቻና ከጽንፈኝነት ውስጥ መውጣት፣ ከሸፍጥና ካልተገባ ተግባር ራስን በማፅዳት በመርህ መመራት፣ ለዓላማቸው ፅኑ የሆኑ ጠንካራ አባላትን መመልመል፣ ከጠባብነትና ከቡድንተኝነት ፀድቶ ለብዙኃን እምነት መገዛት፣ ከፓርቲው ዓላማና መርህ ጋር ግጭት የሚፈጥር የውጭ ጣልቃ ገብነትን መከላከል፣ የሕዝብን ፍላጎት የሚወክሉ ፕሮግራሞችና የፖሊሲ አማራጮች መንደፍ፣ በሚያግባቡ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ጋር መመካከር፣ በፖሊሲ ጉዳዮች ተሳታፊ መሆን፣ ለብሔራዊ ደኅንነት አደጋ ከሆኑ ተግባራት ራስን ማራቅና በአገር ጉዳይ ዋነኛ ተሳታፊ የሚሆን ጠንካራ ፓርቲ መምሥረት የወቅቱ ጥያቄ መሆን አለበት፡፡ ከአሁን በኋላ በደመነፍስ የሚመሩና በጥላቻ የታወሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለፖለቲካ ምኅዳሩ አይጠቅሙም፡፡ በምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የሚያኮራ ውጤት የሚያስመዘግብ እንጂ፣ ልፍስፍስ ተቃዋሚ ፓርቲ ለማንም አይጠቅምም፡፡ አዲሱ ትውልድም ገፍቶ መጠየቅ ያለበት ለመርህ የቆመ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ እንጂ፣ በገጠመኝ የሚኖር ምስኪን አይደለም፡፡

በአጠቃላይ ምርጫ 2007 ያሳየው ከላይ የተመለከትናቸውን ያልተመጣጠኑ ኃይሎች ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም ለአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ካልሆነ የአንድ ፓርቲ አውራነት ምንም አይፈይድላትም፡፡ ባልተመጣጠነ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚገኝ ውጤትም የአሁኗን ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አያመላክትም፡፡ በሕግ የበላይነት የሚያምን ጠንካራ ባለመርህ ተቃዋሚ ፓርቲ መፈጠር አለበት፡፡ በዚህ ዓይነቱ ድባብ ውስጥ ተሁኖ ስለነገ ካልታሰበ የዛሬው አሸናፊነትና ተሸናፊነት ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ለዚህም ነው ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎቹ ችግሮቻቸውን ይመልከቱ የሚባለው፡፡

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...