Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሚድሮክ አጥሮ በያዛቸው 13 ቦታዎች ላይ ግንባታ ለማካሄድ 18 ቢሊዮን ብር መመደቡ ተሰማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ ተጨማሪ የግንባታ ጊዜ የተሰጠው ሚድሮክ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለዓመታት አጥሮ ባስቀመጣቸው 13 ቦታዎች ከመስከረም 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ግንባታ ለማካሄድ 18 ቢሊዮን ብር መመደቡ ታወቀ፡፡

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እነዚህን ቦታዎች በሕጉ መሠረት መንጠቅ ቢኖርበትም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ  ጣልቃ በመግባት በልዩ ሁኔታ ተጨማሪ የግንባታ ጊዜ እንዲሰጥ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህ መሠረት የግንባታ ጊዜ የተጨመረለት ሚድሮክ በቦታዎቹ ላይ ግንባታ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ነው ተብሏል፡፡

የሚድሮክ ባለቤትና ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ የ13 ቦታዎች ግንባታ በመስከረም 2008 ዓ.ም. እንዲጀመር፣ ለሚድሮክ ኮንስትራክሽን መመርያ መስጠታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በ13ቱም ቦታዎች ላይ የሚሠሩት ሕንፃዎች ዲዛይንን ናሽናል ኮንሰልት ኩባንያ ከጣሊያንና ከስፔን ኩባንያዎች ጋር በጋራ የሠራ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ እያቀረበ መሆኑ ታውቋል፡፡

የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በመስከረም ወር ለማስጀመር ሙሉ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ሚድሮክ ለዓመታት አጥሮ የያዛቸው ቦታዎች ካዛንቺስ፣ ሜክሲኮ፣ ሳር ቤት፣ ፒያሳና ጉርድ ሾላን ጨምሮ በተለያዩ የከተማው ክፍሎች ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ቦታዎች ቀደም ሲል የተሰጣቸው የግንባታ ጊዜ በማለፉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲነጠቁ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ አስተዳደሩ እነዚህን የሚድሮክ 13 ቦታዎች ጨምሮ ታጥረው የተቀመጡ 109 ቦታዎች ላይ ስለሚወስደው ዕርምጃ ጥናት ማስጠናቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ በሚድሮክ የተያዙትን ቦታዎች በተመለከተ መውሰድ ያለበትን ዕርምጃ እንዲያጠና ልዩ የባለሙያዎች ኮሚቴ አዋቅሮ አስጠንቷል፡፡

ኮሚቴው ባጠናው ጥናት ሚድሮክ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ መሠረት ያወጣ ቢሆንም፣ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ምንም ዓይነት ግንባታ አለማካሄዱን በመግለጽ ቦታዎቹ  ለሌሎች አልሚዎች እንዲሰጡ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡

በዚህ መሠረት በተለይ በልደታ ክፍለ ከተማ ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ አጠገብ የሚገኘውን ቦታ፣ በየካ ክፍለ ከተማ ደግሞ ጉርድ ሾላ በሻሌ ሆቴል አካባቢ የሚገኘውን ቦታ ካርታ አምክኗል፡፡

ነገር ግን ሼክ አል አሙዲ በቦታዎቹ ላይ ግንባታ ያልተካሄደው በሚድሮክ ብቻ ሳይሆን በከተማ አስተዳደሩ ጥፋት ጭምር ነው በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የሚያካሂዷቸው ግንባታዎች ግዙፍና ውብ በመሆናቸው ለከተማው ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚኖራቸው የግንባታ ጊዜ እንዲራዘም ጠይቀዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከመከረ በኋላ የሼክ አል አሙዲ አላሙዲ ጥያቄ በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገድ ወስኗል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ በሰጠው መመርያ መሠረት ሚድሮክ የውል ማሻሻያ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች